Saturday, 13 April 2024 20:13

የፖለቲካ “ሚቴረሎጂያችን” ምን ይላል?

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(2 votes)

ትዝብት1።
የ60 ቤቶች ግንባታ ለማስጀመር የመሠረት ድንጋይ እንደተጣለ በዜና ሲነገር ሰምተናል፤ አይተናል። “የአዲስ አበባ የኮንዶምኒዬም ፕሮጀክት” ነው። ትልቅ ፕሮጀክት ነው። ከ40 እስከ መቶ ቢሊዮን ብር ሊፈጅ ይችላል።
ትዝብት 2።
“መጋቢት 24 ቀንን በማሰብ”… በኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልሎች፣ በአዲስ አበባ፣ እንዲሁም በአማራ ክልል አንዳንድ ከተሞች ለገዢውን ፓርቲና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በርካታ የድጋፍ ሰልፎች ተካሂደዋል። ታጣቂ ቡድኖችን በማውገዝ የየአካባቢው ባለሥልጣናት ጠንከር ያለ ንግግር አድርገዋል።
ትዝብት 3።
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተሰራጨ ዜና ደግሞ አለ። በኦሮሚያ ክልል ተከታታይ ዘመቻ እየተካሄደ እንደሆነ በዜናው ተዘግቧል። በርካታ ታጣቂዎች እንደተገደሉ፣ በርካቶችም እንደተማረኩ በቁጥር እየዘረዘረ በምስል አሳይቷል። ነዋሪዎች በታጣቂው ቡድን እንደተማረሩና አስወግዱልን የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ እያቀረቡ እንደሆነም በዜናው ተነግሯል።
መከላከያ ኃይል በጀመራቸው ዘመቻዎች “ታጣቂው ቡድን እየተዳከመ ነው፤ ብዙ ታጣቂዎችም ቡድኑን እየለቀቁ እጃቸውን እየሰጡ ነው” ብሏል - ዜናው።
ትዝብት 4።
ቀደም ባሉት ሳምንታት ጠ/ሚ ዐቢይ ከተለያዩ ክልሎችና ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር በርካታ ስብሰባዎችን አካሂደዋል። ከተሰብሳቢዎች ለተነሡ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል። ከሴቶች፣ ከወጣቶች፣ ከሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋርም ተነጋግረዋል።
ትዝብት 5።
የዐድዋ ድል መታሰቢያ ግዙፍ ሕንጻ ተገንብቶ ከተመረቀ በኋላ በአካባቢው የሚገኙ የፒያሳ መንደሮች በመፍረሳቸው ጠንካራ ተቃውሞዎችና ውዝግቦች ተፈጥረዋል። ብዙም ሳይቆይ፣ የፒያሳ አካባቢን ጨምሮ በርካታ የልማት ሥራዎች  እየተከናወኑ መሆናቸውን በሰፊው የሚያብራራ ስብሰባ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተላልፏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ እንዲሁም የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አበቤና ሌሎች ዋና ዋና ባለሥልጣናት የተገኙበት ስብሰባ ነው።
የዐድዋ ድል መታሰቢያ ምርቃትን ጨምሮ በአንድ ወር ውስጥ የተካሄዱ የገዢው ፓርቲና የመንግሥት ባለሥልጣናት እንቅስቃሴዎችን ሰብሰብ አድርገን ስናያቸው፣… አንዳች የፖለቲካ ቅርጽ፣ አንዳች የፖለቲካ ትልም አይፈጠሩልንም?
ገዢው ፓርቲ በመጪዎቹ ወራት ለቀጣዩ የምርጫ ጊዜ ከወዲሁ ተፍተፍ ማለት እንደጀመረ ለመገመት ብዙም አያስቸግርም ባይ ነኝ። ይልቅስ፣ ወደ ምርጫ ያነጣጠረው “የፖለቲካ ትልም” ምን ዐይነት ባሕርይ አለው የሚለው ጥያቄ ጥሩ የመነጋገሪያ ርዕስ ሊሆን ይችላል። ለገዢው ፓርቲም ሳይጠቅመው አይቀርም።


እንዴት? የየካቲትና የመጋቢት ወር እንቅስቃሴዎቹን በመታዘብ መገመት እንችላለን።  ገዢው ፓርቲ ጥንካሬውን ለማሳየት ብቻ ሳይሆን፣ የዜጎችን አዝማሚያ ለማየት፣ የአገሬውን ግለትና ቅዝቃዜ ለመለካት የፈለገ ይመስላል።
ታዲያ፣ ዜጎችስ የገዢውን ፖርቲ አዝማሚያ ለማየት፣ “የፖለቲካ ትልሙ” ምን እንደሆነ እንቅጩን ለማወቅ ባይችሉ እንኳ ወዴት ወዴት እንደሚያዘነብል ለማወቅ ቢሞክሩ ምን ክፋት አለው? ተገቢ ነው እንጂ።
መንግሥትና ገዢው ፓርቲ ምን ምን እንዳቀዱና በየት በየት በኩል ለመጓዝ እንዳሰቡ አቅጣጫቸውንና መንገዳቸውን በግልጽ ቢነግሩን፣ ከድካም እንድን ነበር። ባይነግሩን እንኳ፣ አዝማሚያቸውን ለማወቅ ቀላል ቢሆን እንዴት ጥሩ ነበር? “ንገሩን” እያልን ፖለቲከኞችን አናስቸግራቸውም ነበር።


የአገራችን የፖለቲካ ሚትሮሎጂ ምን ይላል? ምን ይነግረናል? ብለን በመጠየቅ ብቻ መልስ ብናገኝ አስቡት። የሚትሮሎጂ ቃል አቀባይ የሚነግረንን ሰምተን፣ አዋዋላችንን አለባበሳችንን ማሰብ እንችላለን።
ዝናቡ፣ በረዶው፣ ፀሓዩ፣ ነፋሱ… እርሻና አዝመራው፣ ግድቡና መስኖው፣ ወይም ጎርፉና የመሬት ናዳው፣ ውጭንፍሩና ሐሩሩ፣…
የሚትሮሎጂ ቃል አቀባይ፣ የፖለቲካ አየር ትንበያውን በቀላሉ ይነግረናል። እኛ ደግሞ መስማት አይከብደንም። እንደ ትንበያው ሁኔታ፣ በተስፋም ይሁን በስጋት ስሜት የቻልነውን ያህል ከወዲሁ ለመዘጋጀት ይጠቅመን ነበር።
ግን ምን ዋጋ አለው? የአገራችን ፖለቲካ ለሚትሮሎጂ አይመችም። በእርግጥ አንዳንዴ ፖለቲካችን ለትንበያ ከብድ።
የገዢው ፓርቲ ፖለቲከኞች እርስ በርስ ወይም ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጋር በብርቱ መወዛገብ ካዘወተሩ፣ በብሽሽቅና በውንጀላ ከተጠማመዱ፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ግጭትና ጦርነት መነሣቱ እንደማይቀር መገመትና መናገር ይቻላል።


የፖለቲካ ንትርክ ሲበረክት፣ ውግዘት የሚወራወሩ ፖለቲከኞችም ድምጻቸው እየገነነ ሲመጣ ካያችሁ፣ ያለጥርጥር የመጠፋፋት አደጋ እየመጣ እንደሆነ መገመት አያቅታችሁም።
ዕድለኞች ሆነን ጦርነት ባይፈነዳ እንኳ፣ ግጭት ይለኮሳል።
ከግጭት ብናመልጥ እንኳ፣ ረብሻና ወከባ ይኖራል።
ወይ የተቃውሞ ዐመጽ ይነሣል፣ አገር ይረበሻል።
ወይ ደግሞ መንግሥት ተቀናቃኞችን ያሳድዳል፣ አገር ይርዳል።
እንዲህ እንዲህ ዐይነት የአገራችን አሳዛኝ የፖለቲካ ባሕርይ፣ ለትንበያ ባያስቸግርም እንኳ፣ ለግምት የማያመቹ ውስብስብ ገጽታዎቹ ይበዛሉ።
“በትግራይ የተካሄደው ጦርነት በድርድር ለማስቆም ተስማምተው ተፈራረሙ” የሚለውን ዜና እንዴት እንደሰማን አስታውሱ። ሲጠበቅ የነበረ ዜና አይደለም። ያልተገመ ዜና ነው።


ጦርነቱ በጣም ዘግናኝና ከፈራነው በላይ እጅግ አሳዛኝ የመሆኑ ያህል፣ ጦርነቱን ለመግታት የተደረገው ስምምነት ደግሞ በብዙዎች ዘንድ ከነበረው ተስፋና ግምት እጅግ የተሻለ እንደነበረ ማስታወስ እንችላለን።
የጦርነቱ ዘግናኝነትም ሆነ የሰላም ስምምነቱ፣ ለግምት ቀላል አልነበሩም ማለት ነው።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? የፖለቲካውን አየር በመታዘብ ወደፊት ምን እንደሚመጣብን ወይም ምን እንደሚመጣልን በቀላሉ መገመት የማንችላቸው ጉዳዮች አሉ። ለግምት የማያስቸግሩ ነገሮችም አሉ።
የኢኮኖሚ ትንበያ ሐሳቦችን በምሳሌነት ብናይ፣ የፖለቲካ ትንበያዎችን ለመረዳት ሳይጠቅመን አይቀርም።
ኤክስፖርት ካላደገ በስተቀር የዶላር እጥረት እንደሚፈጠር መገመት ይከብዳል? አይከብድም።


ጦርነቶች ሲቀጣጠሉ ወይም የመንግሥት ፕሮጀክቶች ሲበረክቱስ፣ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የብር ሕትመት እንደሚጧጧፍ መጠበቅ የለብንም? መጠበቅ አለብን።
የብር ሕትመት ሲጦፍ፣ በዚያው መጠን ብር እየረከሰ የዋጋ ንረት እንደሚጦዝ መገመትስ ይከብዳል? አይከብድም።
የዋጋ ንረትን ለመግታት የገንዘብ ሕትመትን ከማርገብ ይልቅ፣ መንግሥት የዋጋ ቁጥጥር ዘመቻዎችን እንደሚያውጅም እናውቃለን። ወይም እናውቅ ነበር። የዋጋ ቁጥጥር ዘመቻዎች ደግሞ፣ የገበያ ግርግርን ያባብሳሉ፡፡ በዋጋ ንረት ላይ የሸቀጦች እጥረትን ደርበው እንደሚያስከትሉ መገመት አያስቸግርም።
ነገር ግን፣ መንግሥት እንደተለመደው የዋጋ ቁጥጥር ዘመቻ በሰፊው አላካሄደም። ይሄ… ለአገራችን “እንግዳ ክስተት” ነው። ከምንጠብቀው ውጭ ነው። ግን መጥፎ አይደለም።
እንዲያውም “ከግምታችን የተሻለ ነው” ማለት እንችላለን። የዋጋ ቁጥጥሮችን ከማግተልተል ታቅቦ፣ የገበያ ግርግር ከመፍጠር ተቆጥቧል። ጥሩ ጅምር ነው።
የዋጋ ንረት ላይም፣ “ከግምታችን ውጭ” የብር ሕትመትን ገታ ቢያደርግ… እጅግ በጣም የሚያስመሰግን ተግባር ይሆን ነበር (እንደ አፋችን ያድርግልን እንበላ)። በእርግጥ አስቸጋሪ ፈተና እንደሆነ መገመት አይከብድም። የጦርነት መዘዝ ከባድ ነው። ውድመቱና ወጪው ብዙ ስለሆነ፣ መንግሥት ወጪዎቹን ለመሸፈን ሌላ አማራጭ ያጣል። ከልክ ያለፈ የገንዘብ ሕትመት ውስጥ ይገባል።
ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዐቅም በላይ የሆነ የብር ሕትመት ደግሞ፣ ያው… ውጤቱ ሁሌም ተመሳሳይ ነው። የዋጋ ንረት እንደሚፈጠር አስቀድሞ ማወቅ ይቻላል። ይጠበቃል፤ ይገመታል። ይታወቃል።


ቢሆንም ግን፣ መንግሥት እንደምንም ወጪዎችን ለመቀነስና ጦርነቶችን ለማስቆም እየተጋ፣ የብር ሕትመቱን ማብረድ፣ የዋጋ ንረቱንም ማርገብ ይችላል።
ያኔ “ከግምታችን የተሻለ አንድ ተጨማሪ መልካም ውጤት አየን” ብለን የምንናገርበት አጋጣሚ ይሆንልናል።
እንግዲህ፣ ፖለቲካውም እንደዚሁ ነው። ለግምት የማያስቸግሩ መሠረታዊ ነገሮች አሉ። ለግምት የሚከብዱ የፖለቲካ ገጽታዎች ደግሞ ብዙ ናቸው።
ለግምት ቢያስቸግሩም፣ ከወዲሁ የፖለቲካችንን አዝማሚያዎች ለማወቅና አስቀድመን ለመዘጋጀት የዐቅማችንን ያህል መሞከር አለብን። ጥያቄዎችን እያነሣን ፖለቲካችንን መታዘብና መፈተሽ ይኖርብናል።
የአገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ አየር ምን ይመስላል? “ከፊል ደመናማ?”፣ “ዝናባማ” ወይስ “ፀሓያማ”? የቀንና የማታ የሙቀት መጠንስ? መካከለኛ ሙቀት ነው? ወይስ እንደ ትኩሳት የሚያቃጥል? ወይስ የሚያንቀጠቅጥ ውርጭ?
ለከርሞስ የበልግና የክረምት ፖለቲካው ምን ይዞ ይመጣል? መደበኛ ዝናብና አዝመራ? ከመደበኛው በላይ ወይስ በታች?
ከየአካባቢው የተመዘገቡ መረጃዎችና ከርቀት የሚያስቃኙ የሳተላይት ምስሎች ስለመጪዎቹ ወራት ምን ይነግሩናል?
የፖለቲካ ሚትሮሎጂ የዚህን ያህል እንደ ቀልድ የሚታይ አይደለም።


በእርግጥ፣ ዝናባማ፣ ፀሓያማ፣ ደመናማ… የሚል የተፈጥሮ ዑደት ትንበያም ዛሬ ዛሬ በጣም ተለመደ እንጂ፣ አጀማመሩ ቀላል ነበር ማለት አይደለም። ሳይንሱና ቴክኖሎጂው እየተራቀቀ ቢመጣም፣ ዛሬም ጭምር የአየር ሁኔታ ትንበያ አስቸጋሪ ነው። ቢሆንም ግን፣ በተለይ በምዕራብ አገሮች፣ ከሰዓት ሰዓት ከሰፈር ሰፈር የሚኖረውን የአየር ሁኔታ በትክክል መተንበይ እየተቻለ ነው። ረዘም ያለ ጊዜ ሲሆን ነው የአየር ሁኔታ ትንበያ አስቸጋሪ የሚሆነው። ቢሆንም ይቻላል። ተችሏል።
የፖለቲካ ትንበያ ግን፣ የግዑዝ ነገሮችን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን የሰዎችን ዝንባሌና ምርጫን አካትቶ የማሰብ ተጨማሪ ሸክም አለበት። በዚህም ምክንያት አስቸጋሪነቱ ተደራራቢ ይሆናል።
እንዲያም ሆኖ፣ የፖለቲካ ትንበያ፣ በጭራሽ የማይሞከር አይደለም። የአሜሪካ ወይም የአውሮፓ አገራት ውስጥ የሚካሄዱ የፖለቲካ ምርጫዎችን ማየት እንችላለን። የትኛው ተፎካካሪ በምን ያህል ብልጫ ተቀናቃኞቹን እየቀደመ እንደሆነ፣ ከዚያም ማን እንደሚያሸንፍ ከምርጫው በፊት ይታወቃል፡፡ ለዚህም ጥናታዊ ትንበያዎችን መስጠት እጅግ የተለመደ የሙያ ጥበብ ሆኗል። አንዳንዴ በጣም ሲሳሳቱ መታየታቸው ግን አልቀረም። ዶናልድ ትራምፕ የዛሬ 7 ዓመት ባልተገመተ ሁኔታ ነበር ያሸነፉት።  
የምዕራብ አገራት ፖለቲካ ለትንበያ ይከብዳል ካልን፣ የኛ አገርማ የማይሞከር ነው ብንል ይሻላላ?
ባለፉት ስድስት ዓመታት፣ የአገራችን ፖለቲካ እየደጋገመ ሲያተራምሰን አልነበር? አንዳንዴ በተስፋ ሲያጽናናን፣ እንደገና ተመልሶ ሲደፈርስ፣ ትንሽ ተረጋግቶ በማግስቱ ሲያገረሽበትና አገር ሲታመስ… እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ፣… “የዚህ አገር ፖለቲካ ሐዘን የሚያዘንብ ፖለቲካ ነው” ያሠኛል። ለትንበያ አያስቸግርም ማለት ነው።


የፖለቲካው ቀለምና መልክ ስንቴ ከግምታችን ውጭ በፍጥነት እንደተለዋወጠ ስናስበው ደግሞ፣ “ፈጣሪ ይወቀው!” ያስብላል።
ቢሆንም ግን፣ ባለፉት ሁለት ወራት ያየነው የገዢው ፓርቲ መሪዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት እንቅስቃሴ፣ “የምርጫ ፖለቲካ ቅኝት” ውስጥ እየገቡ እንደሆነ እንሚያመለክት አያጠራጥርም። ማለቴ… “የምርጫ ፖለቲካ ቅኝት” ውስጥ እየገቡ እንደሆነ መገመት ይቻላል።
ከወዲሁ ለምርጫ ማሰብና መዘጋጀት ደግሞ ጥሩ ነው።


ቁም ነገር ሐሳቦች ላይ፣ ፋይዳ ያላቸው ተግባራት ላይ፣ እንዲሁም ሥርዓት ያለው ድባብ ላይ ለማተኮር በቂ ጊዜ ይኖራቸዋል።
የምርጫ ቀን ሲደርስ መሯሯጥ ለአደጋ ያጋልጣል። ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ ይሆናል ነገሩ። ገዢው ፓርቲ፣ ጠንከር ያለ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ውልብ ሲል ካየ፣ ተደናብሮ ይዋከባል፤ ከዚያም አገርን የማወክ አደጋ ይፈጥራል።
ቁም ነገር ለማውራት፣ የሠሩትን ነገር ለማሳየት ወይም እቅዳቸውን ለመናገር አስቀድመው ያልተሰናዱ ፓርቲዎች፣ በራስ የመተማመን ድባብ ለመፍጠር አስቀድመው ያልተዘጋጁ ፓለቲከኞች፣ ከስድብና ከብሽሽቅ ውጭ አማራጭ አይኖራቸውም። ውግዘትና ውንጀላ በገፍ በማግተልተል ነው የሚፎካከሩት።
ይሄ ደግሞ መጨረሻው እንደማያምር ለመገመት አያስቸግርም።
እናም፣ ባለፉት ሳምንታት የታዘብናቸው እንቅስቃሴዎች፣ እንደ ግምታችን “የምርጫ ፖለቲካ ቅኝቶች” ከሆኑ፣ አስቀድሞ የመዘጋጀት ጥረቶች ናቸውና እንደመልካም አዝማሚያ ሊቆጠሩ ይገባቸዋል ብዬ አስባለሁ።
ሌሎቹም ፓርቲዎችም ከወዲሁ ቢዘጋጁ ነው የሚሻላቸው። ለአገራችንም ይሻላታል። እስካሁን የምርጫ ዝግጅት ካልጀመሩ ማለቴ ነው።

Read 654 times