Saturday, 06 April 2024 00:00

የሥነጽሁፍ ሰዎች ስለ ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ የደራሲው 17ኛ መጽሐፍ ዛሬ ይመረቃል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“አንዱን ሥራ ከሌላው አላበላልጥም“

      አለማየሁ ገላጋይ የቃላት አመራረጡና አተራረኩ፣ ቦታዎችን የሚመርጥበትና አገላለፁ በእጅጉ ይገርመኛል፡፡ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎች የሚያነቧቸው መጻሕፍት  እያበረከተልን ነው፡፡ የብርሀን  ፈለጎች ወደ ፊልም ቢቀየሩ ምርጥ ድርሰት ነው፡፡ ውልብታ፤ የፖስት ካርድ አፃፃፍ ሙከራ ድንቅ ነው፡፡ በበኩሌ አንዱን መፅሐፍ ከሌላው ማበላለጥ አልችል፡፡ ምክኒያቱም ሁሉም የራሳቸው የሆነ ጣዕምና ለዛ አላቸው፡፡
(አስቴር - መምህርና አድናቂ)
***
አለማየሁ ገላጋይ - የአማርኛ ሥነጽሁፍ ጌጥ
አለማየሁ ገላጋይ ገና በማለዳው ጠለቅ ባለ ንባብ፣ በመጠቀ ምናብ፣ አድማስ-ዘለል ጭብጥና ጥልቅ ሥነ ልቡናዊ ፍተሻን በመፍተል ጀምሮ፣በየጊዜው መሰላሉን በወጉ እየረገጠ፣ ከፍ ያለ ማማ ላይ የተቀመጠ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ጌጥ ነው። መሥዋዕትነቱ እንደ ጆርጅ በርናንድ ሾ ፣ ተቆርቋሪነቱ እንደ ፑሽኪን፣የሰው ወገናዊነቱ እንደ ቶልስቶይ፣ፍልስፍናው እንደ ኤሚሊ ዲክንሰን ሆነው በጽሑፎቹ ውስጥ ብቅ ይላሉ።
አለማየሁ ወደ ፈጠራ ሥነ ጽሑፍ እልፍኝ ሲገባ፣ዘው ብሎ ሳይሆን ትንፋሹን ቆጥቦ፣የካበተ የንባብ ሀብቱን በካዝናው አጭቆ፣ በቶጀረ አቅም ስለሆነ ደመናውን ካሳየ በኋላ የጥበብ ዝናቡ ሳያባራ አስራ ሰባተኛ ጎሉን ሊያስቆጥር ነው። ቤቱን በአሸዋ ላይ አልጀመረምና የመጣው ንፋስ ሁሉ ሳይነቀንቀው፣የንፋሱን ፉጨት ሙዚቃው አድርጎ እየታጀበ፣ የሥነ ጽሑፍ ማጀታችንን እየሞላ፣ረሀባችንን እያስታገሰ፣ከአድማስ አንደምትናፈቅ የክረምት ጀንበር ብርቅ ሆኗል። ይህንንም ሲያደርግ፣ የአዲሱን ትውልድ ቀለም ሳይንቅ ፣ለቀደመው ሳይሰግድ፤የፈረንጁን ሳይገፋ፣ሀገራዊ እርሾውን ሳይደፋ አዋህዶና አዋድዶ፣በሮማዊ ሥልጣኔ ብልሃት፣የጥበብ ሥራውን ቀጥሏል። በቋንቋ ውበት፣በገለጻ ብቃት እያሳመረ፣በጣፋጭ ኪናዊ  ትረካ እነሆ የተጠማውን ምድረበዳ እያራሰ ዛሬን ደርሷል።
(ደራሲ ደረጀ በላይነሀ)
***


“የአገር ጉዳይ የሚገደው ደራሲ“
ለከት የተበጀለት ምናባዊነት የድርሰት ማባያ ነው፤ ምናብ ከዕውን የሰማይ ያክል መራቅ አይጠበቅበትም፤ ታዲያ ዓለማየሁ ገላጋይ ለምናባዊነት ገደብ ያበጅና፣ ማሕበረ-ባሕላዊ ዕሴቶቻችንን፣ ግርንቢጦሻዊ የአኗኗር ይትባሃላችንን፣ ላይሞላ ጎጆ ጉዟችን በመናጆ፣ የሚጣምን ግብታዊነታችንን…ሌላም ሌላም በድርሰቶቹ አስጎብኝቶናል፤ ከሚጽፍለትና ከሚጽፍበት ማሕበረሰብ የተናጠበ ድርሰት ጀባ ባለማለቱ ሁሌም ምስጉን ነው፤ የማይለፋደዱና የማይነታረኩ ስልታዊ ማንቂያና ማብቂያ ናቸው ድርሰቶቹ!... …ዓለማየሁ ገላጋይ አገር ይገደዋል፤ የአለማሰብ ጣመን ይመዘምዘዋል፤ ወለፈንዴነታችን እንደሻህላ ይቧጥጠዋል፤ በግብታዊነት የምንኖረው ሁሉ እንደ ለበቅ ይፈጀዋል፤ እንደ ዕጣን ፎናኔ ላንታይ ላናይ መንከላወስ መባተላችን ይመዘምዘዋል፤ ቁምነገር ላንጽፍ እንደ ጉንዳን ኮቴ መጥተን ማለፋችን የዕንቅልፍ ለምኔው ምክንያት ነው፤ ትውልድ እንዲገደው ዕሙን ነው፤ ገጸ-ባሕሪይ እና መቼት መቅረፅ ከረቀቀባቸው ጉዳዮች መካከል ዋንኞቹ ናቸው፤ የንባብ ልምዱ ግሩም ነው፤ ያንን ማካፈል ያውቅበታል፤ ሀሳቡን የሚሸከም ቋንቋ መቀመም ልማዱ ሆኖ በአሥራ ስድስቱም ድርሰቶቹ አስተውለናል፤ በአዲሱ ሥራ አዳዲስ የአተራረክ ቴክኒኮችን ይዞ እንደሚመጣ በልበ-ሙሉነት እጠባበቃለሁ!
(ዮናስ ታምሩ - ሃያሲ)




__________________




                     ”አሌክስ የሥነጽሁፍ አዝመራው ሰፊ ነው”


       አንድን ደራሲ ልናደንቀው የሚገባን በአንባቢነቱ መሆን የለበትም ብዬ አምናለሁ:: ወታደሩን ያለ ተኩስ፣ ገበሬውንም ያለ እርሻ ማሰብ ከባድ እንደሆነው ሁሉ፣ ለደራሲ ትጥቁና ስንቁ መጻሕፍት ናቸው:: ይልቁንስ ደራሲ ሊደነቅ የሚገባው ሳይታክት መናበብ ሲችል ነው::
ወዳጃችን አለማየሁ ገላጋይ ለዚህ ታድሏል:: ብዙውን ጊዜ ከራሱ፣ ከጊዜው መንፈስና ከዘመኑ የሥነፅሁፍ እንቅስቃሴ ጋር ለመናበብ ቤቱ ብቻ ሳይሆን ልቡም ክፍት ነው፡፡ ለዚህም ነው በሃሳብ የተለየህ ብትሆን እንኳን ሊያነብህና ሊያስነብብህ ዝግጁ ሆኖ የሚያስተናግድህ!
አሌክስ የሥነጽሁፍ አዝመራው ሰፊ ነው! ደግሞም በሰጠ ቁጥር የሚበዛለት አይነት ሰው:: ሲሰጥ የፊተኛውን ያልመሰለ እንዲሆንለት ይመኛል:: በተለይ ከቴክኒክ አንጻር! እንኳንስ ሌላውን ራሱንም ባይኮርጅ ጽኑ ምኞቱ ነው:: ጭብጦቹ የማህበረሰቡን ፎከሎር የሚገልፁ፣ ለተገፋው ለተከፋውና  ለተናቀው ‘ምስኪን’ ጥብቅና የሚቆሙ ናቸው:: የሚሞግቱ የሚያሟግቱ፣ ምን ሆነን ነው ከነበርንበት ዝቅ ያልነው? የሚሉ!
ዛሬ ዛሬ ‘እገሌ መጽሀፍ አወጣ!’ ሲባል፣ ‘ስለምን?’ ብለን ሳንጠይቅ፣ ተማምነን የምንገዛቸው ጥቂት ደራሲያን  መሃል አንዱ አለማየሁ ገላጋይ ሆኗል፤ መልሶ መላልሶ በመጣልን የምንለው ደራሲ ነው፤ እናም እንጓጓለን፤ በአዲሱ መፅሐፉ ምን ብሎ ያጫውተን፣ ይጎነትለን ይሆን እያልን!
(ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ)




_________________




                 ሌላው “የሥነጽሁፍ ወዛደር”


       ዓለማየሁ ገላጋይ፣ በወሪሳ አውድማ ላይ በምጸታዊ መንሽ ማኅበራዊ አዝዕርትን ንፋስ ላይ አበጥሯል። በታለ ማሰሮ ጦማራዊ ልቦለድን ንጧል። በኢህአዴግን እከስሳለሁ ሙቀጫ የጋዜጠኝነትን ዘነዘና ይዞ ምኩራብ ወጥቷል። በቅበላ ብራና የድህረ ዘመናዊ ልቦለድን ከትቧል። በመልክአ ስብሃት ሰፌድ ላይ ሰበዝም፣ አለላም፣ አክርማም ሆነ ስንደዶ ለመሆን የሚመች፥ የደቦ ከያኔ መሆኑን ተመልክተናል። በየፍልስፍና አጽናፍ ተርጓሚነቱን፣ በስብሃት ገ/እግዚአብሔር ሕይወትና ክሕሎት - ኀያሲነቱን አስመስክሯል። በየተጠላው እንዳልተጠላው አይነኬ ዕሳቤዎችን በመጠይቅ ወንፊት አንገዋሏል። በአጥቢያ የንስር ዓይናማነቱን፣ በመለያየት ሞት ነው ሊቀ-መጣጥፍነቱን፣ በፍቅር ስም ላይ ደግሞ experimental novelist-ነቱን ተመልክተናል። በኩርቢት መም ላይ የስሜት ጂምናስቲክ አሠርቶናል። በ17ኛው መጽሐፉ ደሞ 24 እንዳልሞላው ሊያስታውቀን ተከስቷል። እኔ በበኩሌ በጋሽ ወንድዬ ዓሊ ብሂል፤ “የሥነ-ጽሑፍ ወዛደር” ብዬዋለሁ።
(ደራሲ ቢንያም ቡራ)




__________________




                  “ቃላት አጠቃቀሙ ልክ እንደ ቼኾቭ ነው”


       ከጓደኞቻችን መሀል እንደሱ በንባብ የበልፀግ ሰው አላየሁም፤ የአስተሳሰብ አድማሱ ጥልቅ ነው ፤ ቃላት አጠቃቀሙ ልክ እንደ ቼኸቭ ነው፤ ገፀ ባሕርያቶቹን ደሞ የሚያብሰለስላቸው ልክ እንደ ደስታየቭስኪ ነው ፣ ያውቅበታል።
የጨፈገገ ፊት ያለው ደራሲ  አለማየው ገላጋይ፤ ተወልዶ ያደገው  የከተማ እንብርት በሆነችው አራት ኪሎ በፈካና በነቃ ማህበረሰብ ውስጥ ነው ።  በዚያ ሳቅና ፈገግታ፣ ጨዋታና ፌሽታ፣ ዝሙትና  ስካር ፣ማግኘትና ማጣት፤ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪ እስከ ዩንቨርስቲ ምሁራን፣ ከቄስ ቆጶሳት እስከ መነኮሳት ፣እስከ ጳጳሳት፣ ሲበሉ ሲጠጡ ሲሾሙ ሲሻሩ፣ ሲነግሱ፣ ሲረክሱ፤ የከተማ መናኝ ሆኖ ዘመኑንና  ዓይኑን በንባብና በትዝብት ያሳለፈ፤ የዓይን ምስክርነቱን በፃፋቸው መጻሕፍቱ  ፍትሃነቱን ያስመሰከረ፤ ከደመና መሳይ ጭጋግማ መልኩ ፈገግታን የሚፈነጥቅ ፣ሲያሻውም በምፀት የሚያስጨንቅ ሀቀኛ ብዕረኛ ነውና፡፡       ብዙ ህይወትና ገጠመኙን በመኖር ሳይሆን በትዝብትና በማብሰልሰል የሚፈጅ፤ አጭር ጊዜውን በማብሰልሰል የቋጠረውን የሀሳብ ሽል ደበቅ ብሎ እራሱን የሚያዋልድና ፈገግታ ፣ሀዘንና ፣ቁጭቱን ፣ህልምና ተስፋውን ፣ግን በመልካም ሥነ ፅሁፍ ላደገበትና ለኖረበት ማህበረሰብ የበኩሉን ዕሳቤ ጠብ የሚያደርግ. ኢትዮጵያ ዊ ዶስቶቭስኪ ነውና
     ዓለማየሁ ገላጋይ በአተራረኩ እየተረከ ሳይኾን እያጫወተ ያወያያል፣ ገጸ ባሕርያቱ አጠገብህ ያሉ እየመሰለኽ ከንባብ ተናጥበህ ዙሪያህ  ትፈልጋቸዋለህ። የሚጽፋቸው ልቦለዶች ውስጥ ጥልቅ ንባቡንና ብያኔዎቹን ታገኛቸዋለህ። ለመጻፍ ብሎ የጻፈ ይመስልሃል እንጂ እርሱ ግን ከንባቡ ሞልቶ ሲፈስ ነው የጻፈው። አንዳንዶች አለማየሁ ያነበበውን አስታውሶ ይጽፋል ቢሉትም፣ ነገሩ ግን ሙዚቃዊ ወይም ግጥማዊ ድንገቴነት የከሰተው ይመስለኛል።
(አለማየሁ አሊ)


Read 291 times