Monday, 08 April 2024 20:00

በልኩ ያልተዘመረለት ገጣሚ!

Written by  ብርሃነ ዓለሙ ገሣ
Rate this item
(1 Vote)

 ”ይልማ በገጣሚነቱ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሳያሰልስ ከአርባ ዓመታት በላይ አገልግሏል፡፡ የማይረሱ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚተላለፉ ሕያው የሆኑ ሥራዎችን አበርክቶልናል፡፡ ይልማ በልኩ አልተሾመም፣ አልተሸለመም፡፡ በአገራችን በኢትዮጵያ ምድር በይልማ ደረጃ የገጠመ፣ ግጥምን ከዜማ ያሰናኘ፣ ያዋሃደ .. የጥበብ ጀግና ማን ነው?--”
           ብርሃነ ዓለሙ ገሣ



      ትዝ ይለኛል - ከአስር ዓመት በፊት፡፡ ዕለቱ ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን 2005 ዓ.ም፡፡ የአየሩ ሁኔታ ዝናባማ፣ ሰዓት ከቀኑ 11፡45፣ ቦታው ቀበና ሲሆን የተቀጣጠርኩት ደግሞ ከዝነኛው ገጣሚ ይልማ ገብረአብ ነበር፡፡ ስለ ይልማ የዘፈን ግጥም ተሰጥኦ፣ ስለ ኤፍሬም የአዘፋፈን ጥበብ ሁሌም ትንግርት ይሆንብኛል፡፡ ከላይ ከሆነ አዎ ለሰው ልጅ እንዲህም ይሰጠዋል፡፡ በየተግባሩና በየፊናው የሚሰጠው የራሱ የሆነ ጥበብና ተሰጥኦ እንዳለው ባይካድም፤ ሰው በየመስኩ ከበረታ፣ ጥረት ካደረገ አሻራ መተዉ የማይቀር ነው፡፡ በየክፍሉ ባሉ በሁሉም የሙያ ዘርፎች አንቱ የተባሉ ሰዎች መውጣታቸው ያለ፣ የነበረ፣ ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ተፈጥሮ ለየት ይልብናል፡፡ አንዳንዶችን የራሳችን አድርገን ስለምንወስዳቸው የልፋታቸው ውጤት፣ የአእምሯቸው ምጥቀትና ምሉዕነት ለመመስከር እንቸገራለን፡፡ በርካታ ሊዘመርላቸው የሚገቡ ወገኖች፣ የአገር ባለውለታዎችና ባለሙያዎች በአግባቡ አይነገርላቸውም፤ አይጻፍላቸውም፡፡ ተሸፍነው ኖረው ተሸፍነው ያልፋሉ፡፡
አንዳንዴ ቲፎዞ የሌላቸው ጥበበኞች በአግባቡ እንኳ ሥማቸው አይነሳም፡፡ ለዛሬ በጥበቡ ዓለም ብዙ ልንጽፍላቸውና ብዙ ልንዘምርላቸው ከሚገቡ መካከል አንዱ የሆነው ገጣሚ ይልማ ገብረአብን ለማስታወስ ወደድኩ፡፡ ይልማ፣ ሥሙን ለማንሳት ያህል እንጂ ስለ ግጥሞቹ ለመተንተን አይደለም፡፡ ይልማ ከመጽሐፍም በላይ ስለሆነ በጥናታዊ ጽሑፍ ደረጃ እንዲወጡት በዚህ አጋጣሚ ከአደራ ጋር ለመስኩ ባለሙያዎች የቤት ሥራውን እናስተላልፋለን፡፡
ይልማ፣ ከቀኝ አዝማች ገብረአብ ይነሱና ከወይዘሮ ጽጌ እንዳለ ፒያሣ አርሾ ክሊኒክ አካባቢ ተወለደ፡፡ አሁን ላይ ዕድሜው ሰባዎቹን ይዟል፡፡ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንደስትሪ ውስጥ ወርቃማ ጊዜ ተብሎ ሊጠቀስ በሚችለው ሁነት የይልማ ግጥሞች ሁነኛ ቦታ ነበራቸው፤ አሁንም አላቸው፡፡
ይልማ፣ በ2005 ዓ.ም
የይልማ እትብት የተቀበረበት ፒያሣ በመልሶ ማልማት ሰበብ ከዚህ ዓለም ተለይቷል፡፡ ከእንግዲህ የይልማ እትብት የተቀበረበት ቦታ እዚህ ጋ ነው፤ እዚያ ጋ ነው ብሎ ቦታውን ነክቶ ማሳየት የሚቻል አይሆንም፡፡ ለቅርስና ጥበብ ያለን ብያኔ ከተንጋደደ ብዙ ነገራችን ተረት፣ ተረት ይሆናል፡፡
ከይልማ ገብረአብ በላይ የዘፈን ግጥም ገጣሚ ከየት ሊመጣ ይችላል? ማንስ ይሆን ከይልማ በላይ ባለታሪክ? ይልማ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ታሪክ አልሠራም ማለት ነው? እውቅና ማግኘት ወይም መስጠት እንዴት ነው?
እነ ታንጎ፣ ማሕሙድ፣ አያሌው መስፍን … ሙዚቃ ቤቶች፣ ደሐብ፣ ጥቁር አንበሣ፣ ገሊላ .. ሆቴሎች … መኮንን ባቅላባ፣ ወልደ ተንሳይና ታዋቂ ኬክ ቤቶች በነበር ቀርተዋል፡፡ ብዙ ገጠመኝ፣ ብዙ የሕይወት ፍልስፍና፣ ብዙ ትዝታ፡፡ ደሐብ ሆቴል እንዲያው ትዝታው ቀርቶ ታሪክ የለውም ልበል? ኃያላን ሉካንዳ ቤቶች፣ ዝነኛ መዝናኛ ቤቶች፣ ሆቴሎች ወዘተ. እንደ ይልማ የእትብት ቦታ ሁሉ በነበር ይቀራሉ፡፡ ዶሮ ማነቂያ፣ ሠራተኛ ሰፈር …? በአንድ በኩል እየገነባን ታሪክ እየሠራን ነው እያልን በሌላ በኩል ታሪክ እያጠፋን እንዳይሆን የተጠነቀቅንም ለመጠንቀቅ የፈለግንም አይመስለኝም፡፡ ኧረ ኢትዮጵያውያን ኳስ በመሬት፣ እስኪ እየተነጋገርንና እያስተዋልን!  የይልማ ገብረአብን የገጣሚነት ብቃትና ችሎታ ለማመሳጠር እትብቱ የተቀበረበትን ቦታ ስናነሳ ነው የፒያሣን ወቅታዊ ሁኔታ የገለጽነው፡፡ ገና ወደ ፊት ብዙ ይባላል፡፡ እነ ተክሉ ደስታ ወርቅ ቤት … ምንም አይነት የቅርስነት ባህርይ የሌላቸው ናቸው? ስለ ታሪክና ቅርስ ለመነጋገር በቀጠሮ እናቆየውና ወደዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን እንሸጋገር፡፡
ይልማ የሠራቸው የዘፈን ግጥሞች ብዛት፣ ይዘትና ቅርጽ ለመተንተን ሥራዬ ብሎ በደንብ ተዘጋጅቶ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ ይልማ፣ እጅግ በርካታ ግጥሞችን ሠርቶ ለተለያዩ ድምጻውያን አበርክቷል፡፡
ብዙዎቹ ከይልማ ግጥም ተቀብለው የዘፈኑ ድምጻውያን ተዋጥቶላቸዋል፤ ሕዝብ ሥራቸውን አጣጥሞላቸዋል፤ ወዶላቸዋል፡፡ በደርግ ዘመን በቀበሌ ኪነት የጀመረው የይልማ ብዕር የሙሉቀን መለሰ “ይረገም”ን ወለደ፡፡ ይልማ በይረገም ሰው ዓይንና ጆሮ ውስጥ ገባ፡፡ ቀስ በቀስ ፈላጊው በጣም በዛ፡፡ የወደፊት መክሊቱ የዘፈን ግጥም መሆኑ እያደር እውነት ሆነ፡፡ ከዚያ የለጠቀው “ዝነኛውና ከዘፋኞች ኩሩ ኤፍሬም ታምሩ“ የተባለለት ድምጻዊ ነው፡፡ ኤፍሬም፣ ለሙሉቀን መግጠሙን ሰምቶ ይልማን በእግር በፈረስ አፈላልጎ አገኘው፡፡
ከዚያማ የጥበብን ጎርፍ ማን ሊገድበው? ጥበብ በኤፍሬም አካባቢ ብቻ ሳይሆን በድፍን ኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ናኘ፡፡ ዘመናት የሚሻገሩ ዘፈኖች ተንቆረቆሩ፡፡ ምን መንቆርቆር ብቻ ፈሰሱ ቢባል ይቀላል፡፡ ለዚህ ጥበብ እውን መሆን ደግሞ የሁለቱ መጣመር ነው አብነቱ፡፡ ይልማ ገብረአብ በግጥም፣ አበበ መለሰ በዜማ ድርሰት፡፡ ለካስ እንዲህም ተሰናስሎና ተጣጥሞ መሥራት ይቻላል?
የሥነ ግጥም ባህሪያትን መሠረት አድርገን የዘፈን ግጥሞችን እንገምግም አንልም፡፡ ከመገምገማችን በፊት እስኪ እውቅናውን እናስቀድም፡፡ ይልማን እንደ ዘበት ገጣሚ ብቻ ብለን ማለፍ አይቻለንም፡፡ አንዳንድ ግጥሞቹ ከግጥምም በላይ ብዙ የሚያነጋግሩ ይመስለኛል፡፡ ከተማ ተወልዶ የገጠሪቷን ኢትዮጵያ ለዛና ውበት በግጥም ማምጣት፣ ሥነ ቃሉን መተግበር፣ ቃላቱን አስፈላጊ በሆነ ቦታ ላይ መሰካካት ትልቅ ችሎታና ተሰጥኦን ይጠይቃል፡፡ በዚህ መጠን የገጠሪቷን ኢትዮጵያን ሕይወት ገመናና ገጽታ ሊገልጹ የሚችሉ ግጥሞች መሥራት እንደሚቻል ይልማ ስላሳየን ከማመስገን ውጪ ምን ማለት እንችላለን? እስኪ ለሙሉቀን መለሰ የሰጠውን “ይረገም”ን ግጥም አለፍ አለፍ ብለን እንየው፡፡
ይረገም ይህ ልቤ - አልፎ የሄደበት፣
ይረገም ይህ ሆዴ - ሄዶ የተኛበት
ይረገም ይህ ልቤ ሌላ ያሰበበት
የዓይኔ ነገርማ፣ የዓይኔ ነገርማ
ገና ብዙ አለበት፡፡  …
ከይረገም በኋላ ዝነኛው ድምጻዊ ኤፍሬም ታምሩ - ይልማን አፈላልጎ አገኘው፡፡ ይልማና አበበ እንደ አንድ ሰው ተሰናስለው በሠሩት የኤፍሬም ዘፈን እንደ ድምጻዊው ሁሉ ዝና፣ ፍቅር፣ ክብርና እውቅና ለማግኘት ችለዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንደስትሪ እንዲያብብ፣ አድማጭ እንዲያገኝና እንዲደመጥ አድርገዋል፡፡ የኤፍሬም የ1976ቱ ካሴት ከያዛቸው ዘፈኖች መካከል “ነይልኝ”፣ “አካሌ” … ብዙ ሊባልላቸውና ሊጻፍላቸው የሚችሉ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ዘፈኖች እስከ አሁንም ድረስ አልደበዘዙም፡፡ የበርካታ አድማጮችና ተመልካቾች ምርጫ ሆነው ቀጥለዋል ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡   
ነይልኝ፣ ነይልኝ - አንቺዬ ነይልኝ፣
ሆድዬ ነይልኝ
አትቅሪብኝ
አፍ በኖረውማ አንጀቴ ቢናገር፣
ዘርዝሮ ባወጋሽ የመውደድን ነገር፡፡

ለአካላት ውበቷ ልቤ መች ተገዛ፣
አስቀረችኝ እንጂ መስተዋድድ ይዛ፡፡
ነይ መውደዴ
አይጠላሽም ሆዴ፡፡
የይልማ ብዕር ተግ ብሎ አያውቅም፡፡ ሴት ወንድ፣ ትልቅ ትንሽ ብሎ አያብልም፡፡ እንደ ድምጻዊው ፍላጎትና ችሎታ ይፈስሳል፡፡ ያኔ ከይልማ ጋር ባደረግኩት ቃለ ምልልስ፣ “አባቴ የሰጠኝ ፍቅርና ነጻነት ለሙዚቃው መውደድ ምክንያት ሆነኝ፡፡ እነ ዓለማየሁ እሸቴ፣ ሙሉቀን መለሰ፣ በተለይ የጥላሁን ‘ኩሉን ማንኳለሽ’ን አልረሳቸውም” ነበር ያለኝ፡፡ ሰምና ፈትል እንዲሁም የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታ ሆነው በአገራችን ኢትዮጵያ ሙዚቃ ከፍተኛ አሻራ ያሳረፉት ይልማና አበበን ያስተዋወቃቸው ኤፍሬም ታምሩ መሆኑን ከዓመታት በፊት ይልማ አጫውቶኛል፡፡ ኤፊ ግሩም የሆኑ ዘፈኖች ለኢትዮጵያውያን ከማበርከቱ በተጨማሪ ሁለት መጋጠም ያለባቸው የጥበብ አርበኞችን ያገጣጠመ ድምጻዊ ነው፡፡
“ከአበበ ጋር ኤፍሬም ነው ያስተዋወቀን፡፡ በ1974 ዓ.ም ያንን ሠርተን በ1975 ዓ.ም ለሌላ ካሴት ሲዘጋጅ ሴንትራል ሙዚቃ ቤት ከአበበ ጋር ያገናኘዋል፡፡
ለወንድሙ ዘመን መለሰ ዜማ ሠርቶ ነበር፡፡ በዚህ አማካይነት ከአቤ ጋር ተዋወቁ፡፡ የተዋወቁ ዕለት ይመስለኛል እኔ ጋ ይዞት የመጣው፡፡ ከኤፍሬም ጋር እኔ ቤት ነበር የምንገናኘው፡፡ ፒያሣ የእኔ ቤት ለሥራ ይመች ነበር፡፡” ይልማና አበበ በጥበብ ሥራ ያሳለፉት ጊዜ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ለሙዚቃ ጥበብ ውሎ ማደር፣ ለጥበብ ራስን አሳልፎ መስጠት፡፡ የይልማን ግጥሞች ስመለከት በጣም የሚገርመኝ የሚጠቀማቸው ቃላትና የሚከስታቸው ምናባዊ ምስሎች ናቸው፡፡ “እንደ ገብሱ ዛላ”፣ “አካሌን”፣ “ስፊልኝ ገሣ”ን ለአብነት ያህል ማንሳት እንችላለን፡፡
እንደ ገብሱ ዛላ የእኔ ዓለም - ፀጉሯ ተጎንጉኖ፣
መላ ሰውነቷ የእኔ ዓለም - በመውደድ ተክኖ፡፡

የዘንድሮ ክረምት አጉረመረመና
ሐምሌና ነሐሴ አጥግቦታልና
አሳየኝ ይኼ ዓመት አሄሄ
ያቺን መልከ ቀና፡፡

ሸጋ የለም ብዬ - እውነት ነው ተብሎ፣
ቆንጆ የለም ብዬ - እውነት ነው ተብሎ
ጉድ አረገኝ ዓባይ አሄሄ - ጠምበለል አብቅሎ፡፡
አይግጠም ነው እንጂ መቼም ከገጠመ
ልብን በሁዳዴ እየቆረጠመ
የዞረ ያስፈታል አሄሄ - የተጠመጠመ፡፡  …
እንዴት ቢሰጥ፣ እንዴት ቢታደል ነው ይህን ያህል ረቀቅ ያለና የበዛ ግጥም መግጠም የሚቻለው? ይህ በሰፊውና በጥልቀት መጠናት አለበት፡፡ ይልማ ገብረአብና አበበ መለሰ መጠናት ያለባቸው የዘመናችን ክስተቶች ናቸው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ በኢትዮጵያ ምድር እንዲህ ተቀናጅተው ዘመን የሚሻገር ሥራ የሚሠሩ የጥበብ ሰዎች እናይ ይሆን?
“ከአቤ ጋር ስጀምር ዜማ እየተሠራ ከድምጻዊው ጋር መስማማቱ ይረጋገጣል፡፡ ልክ ነው ከተባለ በኋላ ተቀብዬ ግጥም እጽፋለሁ፡፡ ግጥሙ ከሙዚቃው ባህርይ ጋር ይያያዛል፤ ይተሳሰራል፡፡ ይህን ያህል ጊዜ ዜማ ውስጥ ነው ግጥም ስጽፍ የቆየሁት፡፡ ዜማ ይወለዳል፡፡ ኪቦርዴን እከፍትና በሥነ ሥርአት ዜማ እሠራለሁ፡፡ እንዲህ የማደርገው የግጥም ሃሳብ ለማምጣት ነው፡፡
 አዲስ ዜማ ስትፈጥር፣ አዲስ ያልተዘጋጀህበት ግጥም ይመጣልሃል፡፡ ያንን ለቅሜ አዘጋጃለሁ፡፡ እዚያ ውስጥ ጥሩ የመሰሉኝን ለዘፋኝ አስጠንቼ ሲስማማ ነው እንጂ ለዘፋኝ ግጥም ልሥራ ብዬ አልቀመጥም፡፡” ይልማ በገጣሚነቱ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሳያሰልስ ከአርባ ዓመታት በላይ አገልግሏል፡፡ የማይረሱ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚተላለፉ ሕያው የሆኑ ሥራዎችን አበርክቶልናል፡፡ ይልማ በልኩ አልተሾመም፣ አልተሸለመም፡፡
 በአገራችን በኢትዮጵያ ምድር በይልማ ደረጃ የገጠመ፣ ግጥምን ከዜማ ያሰናኘ፣ ያዋሃደ .. የጥበብ ጀግና ማን ነው? ይልማ ገና በወጉ ያልተጠና፣ ያልታወቀ፣ ልተዘመረለት ውለታው ያልተመለሰ የጥበብ አድባር ነው፡፡
ከአራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች፦ ከአንቺ ሆዬ፣ አምባሰል፣ ትዝታና ባቲ አንጻር ግጥሞችህን እንዴት ነው የምትፈርጀው ብዬም ጠይቄው ነበር፡፡ “ልኬት አላቸው፡፡ ሜጀር ትዝታን በርከት እናደርጋለን፡፡
 ትዝታ የጀርባ አጥንት ነው የምንለው፡፡ እርሱም ቢሆን የሚዘፍነው ይፈልጋል፡፡ በዚያ ሰዓት ከእኛ ጋር የሚሠሩ ዘፋኞች ጥሩ የተፈጥሮ ድምጽ የነበራቸው ናቸው፡፡ እነ አንቺ ሆዬ፣ ባቲና አምባሰል ጣል ጣል ነው፡፡ ሜጀር ትዝታ አምስት ስድስት የማይቀር ነው፡፡”
ይልማ ግጥም ያልሠራለት ታዋቂ ድምጻዊ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡ በበርካታ ድምጻውያን እውቅና ውስጥ ይልማና አቤ አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የነኩት ሁሉ ትንግርት ነው እስከሚባል ድረስ በሥራቸው ሲያስደንቁን ኖረዋል፡፡
እዚህ ላይ በወርቃማው የይልማና የአቤ የጥበብ ዘመን የነበሩ አሁን በሕይወት የሌሉ ሙዚቃ ቤቶችን ማስታወስ የግድ ይለናል፡፡
 ለሙዚቃው ጥበብ አበርክቶ ከነበራቸው መካከል፦ አምባሰል፣ ኤሌክትራ፣ ሴንትራል፣ ኢትዮ፣ ታንጎ፣ አያሌው መስፍን፣ ማሕሙድ፣ ሱፐር ሶኒክ፣ ገነት፣ የምሥራች፣ ሶልኩኩ፣ ማራቶን፣ ዜድ፣ ዓለም፣ ዋልያ፣ ማሬ፣ ቮይስ፣ ሉላ፣ ለገሃር፣ መጋላ (ሐረር) … ይጠቀሳሉ፡፡
የዛሬው ጽሑፌ በተወሰኑ ድምጻውያን ሥራዎች ላይ ብቻ የተገደበ ስለሆነ ወደፊት በሰፊው እንደምመለስበት ከይቅርታ ጋር ማስታወስ እወዳለሁ፡፡
ስለ አገራችን ድምጻውያን፣ ስለሙዚቃ ሥራ … መረጃና ማስረጃ በምፈልግበት ሰዓት ሁልጊዜ ከጎኔ የማይለየኝ ድምጻዊ ጸጋዬ እሽቱን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ በሌላ በኩል፤ በዚህ አጋጣሚ ማንሳት ያለብኝ፤ ለቃለምልልስ ፈልጌው እስከ ዛሬም ድረስ ያልተገጣጠምነው ድምጻዊ ኤፍሬም ታምሩ፣ “ለበይኩ!” እንዲለኝ በአንባብያን ሥም እየጠየቅኩ፤ ለዛሬ እዚህ ላይ እሰናበታለሁ፡፡ ሰላም!

Read 192 times