Saturday, 06 April 2024 20:29

የሀገር ሽማግሌዎች

Written by  ቶማሰ በቀለ
Rate this item
(0 votes)

     ከሀገራችን ባህላዊ እሴቶች አንዱና ዋነኛው የሐገር ሽማግሌዎች በህብረተሰቡ ውስጥ የሚጫወቱት ከፍተኛ ሚና ነው። ይህ ባህላዊ እሴት በተለይም በከተሞች አካባቢ ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ መምጣቱ የሚታወቅ ሲሆን፤ ለሀገራዊ አንድነትና ሰላማዊ ኑሮ ከማስፈን አኳያ ካለው ጠቀሜታ አንፃር የሚመለከተው ሁሉ ትኩረት ሰጥቶት ልንንከባከበው የሚገባው ጉዳይ ነው። በሀገራችን ታሪክ በተለያዩ አካባቢዎች የሀገር ሽማግሌዎች ለህብረተሰቡ ያበረከቱት ይፃፍ ቢባል ብዙ መድብል ያለው ያለው መፅሐፍ እንደሚወጣው አልጠራጠርም። እኔ በዚህች አጭር ፅሁፌ ከማውቃቸው ታሪኮች ውስጥ በአምስቱ ላይ ብቻ አተኩሬ ሀሳቤን ለመግለፅ እሞክራለሁ። ከአምስቱ ታሪኮች ውስጥ ሁለቱ በአርሲ፤ ሁለቱ በወላይታ እና አንዱ በሲዳማ ሽማግሌዎች የተፈፀሙ ድርጊቶች ናቸው።


የአርሲ የሐገር ሽማግሌዎች፡ በሀገራችን በሁሉም አካባቢ እንደሚታወቀው የሐገር ሽማግሌዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ አላቸው። በአርሲ ኦሮሞ ብሄረሰብ ውስጥም በተመሳሳይ የሐገር ሽማግሌዎች ህብረተሰቡ በአንድነትና በሰላም እንዲኖር የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው። በህብረተሰቡ ዘንድ አንድ ችግር ሲያጋጥም ጉዳዩ ወደሀገር ሽማግሌዎች ዘንድ ይቀርባል፤ ከዚያም የሐገር ሽማግሌዎቹ ጉዳዩን በጥልቀት ያዩታል፤ ይመረምሩታል። በተሟላ መረጃ ላይ ተደግፈው በቂ የሆነ ትንተና ከመደረጉ በፊት ውሳኔ ለመስጠት አይቸኩሉም። በመሆኑም ሂደቱ ብዙ ቀናቶች ሊፈጅ ይችላል። ከዚህ አኳያ አርሲዎች አንድ አባባል አላቸው። ጉዳዩን በአንድ ቀን መፍታት ካልቻሉ በቁቤ “Haabultu dubbiin”; በግዕዝ ፊደል “ሀኣቡልቱ ዱቢኢን”፤ በአማርኛ ሲተረጎም ደግሞ “ጉዳዩን በይደር እንዝጋው” ብለው በመዝጋት በሚቀጥለው ቀን ካቆሙበት ይቀጥላሉ። ይህ አባባል “ስለጉዳዩ በቂ መረጃ ሰብስበን በጥልቀት ሳንመረምረው ውሳኔ ለመስጠት ብንሞክር የተሳሳተ ውሳኔ ስለምንሰጥ ጊዜ ወስደን ብናየው ይሻላል” የሚል አንደምታ አለው።ከዚያም ለህብረተሰብና ለሐገር የሚበጅ ውሳኔ ይሰጡበታል። እስቲ ከዚህ በታች በነዚህ ሽማግሌዎች የተሰጡ ውሳኔዎችን እንይ።


የብሔር ፖለቲካ መዘዝ፡ በ1980ዎቹ አመታት በወቅቱ በነበረው የብሔር ፖለቲካ የተለያዩ አሳዛኝ ሁኔታዎች በተለያዩ ቦታዎች መፈፀማቸው ይታወሳል። ከነኚህ መሀከል በአርሲ ክፍለ ሀገር አርባጉጉ አውራጃና በሐረርጌ ክፍለሀገር በደኖ አካባቢ የተፈፀሙ ድርጊቶች የሚረሱ አይደሉም። በአርባ ጉጉ አውራጃ አቦምሳ ከተማ በኦሮሞና በአማራ ብሔረሰቦች መሀከል ቅራኔ እንዲፈጠር ተደርጎ ብዙ የአማራ ብሔረሰብ ተወላጆች መገደላቸው ይታወሳል። የአቦምሳ ከተማ አመሰራረት ታሪክ ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ለየት ያለ ነው። በጣሊያን ወረራ ጊዜ ብዙ ኢትዮጵያውያን ደማቸውን አፍሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው የሀገሪቷን ነፃነት በመጠበቅ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስረከባቸው ይታወቃል። ጣሊያን ከሀገር ከተባረረ በኋላ ጃንሆይ ለሀገራቸው ደማቸውን ላፈሰሱ ወታደሮች ውለታ ለመመለስ አሰቡ። በዚሁ መሰረት ከመላው ኢትዮጵያ ለተውጣጡና በወቅቱ ከጣሊያን ጋር ለተዋጉ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወታደሮች በአርሲ ክፍለሀገር አርባጉጉ አውራጃ(የወቅቱን አጠራር የተጠቀምኩት ከመቼቱ ጋር እንዲገጥም በማሰብ ነው።) ቦታ ተሰጥቷቸው እንዲሰፍሩና ኑሮአቸውን እንዲመሰርቱ ተደረገ። በሂደትም የሰፈሩበት ቦታ እየተስፋፋ መጥቶ አቦምሳ የምትባለዋን ከተማ ፈጠረ። የአቦምሳ ከተማ ነዋሪ ከመላው ኢትዮጵያ በተውጣጡ ወታደሮች የተመሰረተች በመሆኗ አማርኛ ቋንቋ በስፋት የሚነገርባት ከተማ ነች። በመሆኑም ኦሮሞና አማራ እንዲጣሉ ተደርጎ አማሮች በተገደሉበት ጊዜ አማርኛ ቋንቋ በመናገራቸው ብቻ የሌላ ብሔረሰብ ተወላጆችም እንደተገደሉ የከተማው ተወላጅ የሆነ ወዳጄ አጫውቶኛል። በሌላ በኩል ደግሞ በሐረርጌ ክፍለ ሀገር በበደኖ ከተማ አማራና ኦሮሞ እንዲጣሉ ተደርጎ ብዙ አማሮች መገደላቸው የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው።  በተመሳሳይ ሁኔታ በአቦምሳና በበደኖ የተፈፀመው ድርጊት በአሰላ ከተማ ለመድገም ሴራ ተጠነሰሰ። ሴራው ወደድርጊት ከመቀየሩ በፊት ወሬው የሐገር ሸማግሌዎች ጆሮ ገባ። ከዚያም በአካባቢው ተደማጭነት ያላቸው የሐገር ሽማግሌዎች(ማለትም የአርሲ ኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ) ጊዜ ሳያጠፉ እራሳቸውን በማደራጀት የከተማውን ህዝብ ሰበሰቡ።(በነገራችን ላይ ከሐገር ሽማግሌዎቹ መሀከል አንዱ የኔ አጎትና ታሪኩን ያጫወተኝ ሰው ሲሆን፤ አንደኛው ደግሞ በኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የፓርላማ አባል የነበሩ ይገኙበታል።) ከዚያም ለሕዝቡ “በከተማችን ውስጥ የአርሲ ኦሮሞንና አማራውን ለማጣላት ሴራ እየተጠነሰሰ ነው፤ እኛ የአርሲ ኦሮሞዎች ከአማራውም ሆነ ከሌላው ብሔረሰብ ጋር ተዋልደናል፤ ለረዢም ጊዜም አብረን ኖረናል፤ በመሆኑም የአርሲ ኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆነ ማንኛውም ሰው በአማራውም ሆነ በሌላው ብሔረሰብ ተወላጅ ላይ ምንም አይነት ጉዳት ቢያደርስ ከማህበረሰባችን ይገለላል፤ መገለል ብቻ ሳይሆን በኦሮሞ ባህልና ወግ መሰረት ተገቢው ቅጣት ይሰጠዋል፤ በመሆኑም ከዚህ በፊት እንደነበረው በሰላምና በፍቅር እንድንኖር ሁሉም ሰው ተገቢውን ጥንቃቄ ያድርግ።” ብለው የመገዘት ያህል ተናገሩ። በመሆኑም በአቦምሳና በበደኖ የተፈፀመው አሳዛኝ ድርጊት በአሰላ ከተማ ሳይደገም ወቅቱ በሰላም ታለፈ።


ጋብቻ፡ ሁለተኛው ደግሞ የአባቴና የእናቴን ጋብቻ ይመለከታል። ጋብቻው ከሌሎች ጋብቻዎች የተለየ ሆኖ ሳይሆን፤ በጋብቻው ሂደት ላይ የሐገር ሽማግሌዎቹን በሳልነት ለማሳየት ፈልጌ ነው እዚህ ታሪክ ላይ ትኩረት ለማድረግ የፈለግሁት። አባቴና እናቴ የተጋቡት በ1930ዎቹ የመጨረሻ አመታት አካባቢ ነው። ለጋብቻው መነሻ የሆነው ታሪክ አባቴ በመጀመሪያ የእናቴን እህት ለማግባት ያስባሉ፤ ከዚያም በሆነ አጋጣሚ የእናቴ ወላጆች ቤት የመሄድ እድል ያጋጥማቸዋል፤ በሄዱበት ወቅት ግን የእናቴን እህት ሳይሆን እናቴ ወተት ስትንጥ ያገኟታል። አባቴ የአርሲ ኦሮሞ ተወላጅ ናቸው። ከዚያም የእህል ውሀ ነገር ሆኖ ሲያይዋት ስለወደዷት እህቷን የማግባቱን ሀሳብ ትተው እሷን ለማግባት ይፈልጋሉ። የልጅቷ ፍቅር ቢበረታባቸው ለወላጆቻቸው ነገሯቸው። ከዚያም በሀገሩ ባህል መሰረት ለሽማግሌዎች ተነገረ። ሽማግሌዎቹም ለሽምግልና ወደልጅቷ ቤት ለመሄድ ከመስማማታቸው በፊት የልጅቷን ማንነት ማወቅ እንዳለባቸው ስላመኑ ምርመራቸውን ቀጠሉ። በምርመራቸው ሂደት ልጅቷ የሸዋ ደብረብርሀን አካባቢ አማራ ተወላጅ መሆኗን ደረሱበት። ይህ እውነታ ለነሱ ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አላገኙትም፤ ማለትም የልጅቷ ብሔር ስለልጅቷ ማንነት እንደማይገልፅ ተረዱ። በሌላ አነጋገር የልጅቷ አማራነት ልጅቷን የመውደድም ሆነ የመጥላት ስሜት አላሳደረባቸውም። ስለዚህ ምርመራቸውን ቀጠሉ። አባቷ የመሬት ባለንብረት መሆናቸውን ደረሱበት። የመሬት ባለንብረት መሆናቸውን ባይጠሉም ይህም መረጃ ልባቸውን ባለማሸነፉ ምርመራቸውን ገፉበት።በመጨረሻም ልባቸውን ሊገዛ የቻለ አንድ መረጃ እጃቸው ገባ።     

         የእናቴ አባት ባሻ ገድሌ ክብረት ይባላሉ። የደብረብርሀን አካባቢ አማራ ተወላጅ ናቸው። አፄ ምኒልክ አርሲን ባስገበሩበት ወቅት የራስዳርጌ ስልከኛ ሆነው ወደአርሲ ይዘምታሉ። ራስዳርጌ አርሲን ለማስገበር የተላከው የአፄ ምኒሊክ ጦር አዝማችና የንጉሱ አጎት ናቸው። አርሲን ካስገበሩ በኋላ ራስዳርጌ ከወታደሮቻቸው ጋር ወደሸዋ ሲመለሱ የተወሰኑ የራስዳርጌ ሰዎች እዚያው አርሲ ቀርተው ኑሮአቸውን ይመሰርታሉ፤ ከነኚህ ሰዎች አንዱ ባሻ ገድሌ ክብረት ናቸው። አርሲ ለመቅረታቸው ዋናው ምክንያት ኑሮ በጣም ርካሽ ከመሆኑ የተነሳ አንድ ጋሻ መሬት በአንድ አሞሌ ጨው የሚገዛበት ዘመን ስለነበረ ነው። በመሆኑም ባሻ ገድሌ በተወሰነ አሞሌ ጨው ጋሻ መሬት ገዝተው በእርሻ ስራ ኑሯቸውን እዚያው አርሲ ጠቅላይ ግዛት መሰረቱ። አሞሌ ጨው የመሬት ከበርቴ አደረጋቸው። (ጠቅላይ ግዛት የሚለውን ስም የተጠቀምኩት ከታሪኩ መቼት ጋር እንዲገጥም ብዬ ነው።) በመቀጠል በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን ወረረ። ጣሊያን ኢትዮጵያን እንደያዘ በየጠቅላይ ግዛቱ በመሄድ የየአካባቢዎቹን አስተዳዳሪዎችና ሽማግሌዎች ለጣሊያን እንዲያድሩ(ባንዳ እንዲሆኑ) ይሰብካቸዋል፤ ባንዳ ከሆኑ ይጠቀምባቸዋል፤ ለጣሊያን አናድርም ወይም አንገዛም የሚሉትን ወዲያው ለመቀጣጫ በህዝብ ፊት ይረሽናቸዋል። ይህን ሲፈፅም በዋነኛነት ትኩረት ያደርግ የነበረው የአካባቢው ተወላጅ ሆነው በህብረተሰቡ ዘንድ ከበሬታና ተሰሚነት ባላቸው ሰዎች ላይ ነበረ።

 

በመሆኑም ጣሊያን አርሲ ጠቅላይ ግዛት መጥቶ ከዚህ በላይ የተጠቀሰውን ድርጊት ሲፈፅም ትኩረት ያደረገው የአርሲ ኦሮሞ ተወላጅ ሆነው በህብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ተሰሚነት ባላቸው ሰዎች ላይ ነበረ። ስለዚህ ባሻ ገድሌ ክብረት ከዚህ አሰሳ ነፃ ነበሩ፤ ምክንያቱም ባሻ ገድሌ የአርሲ ኦሮሞ ተወላጅ ሳይሆኑ የሸዋ ደብረብርሀን አማራ ተወላጅ ስለሆኑ ነው። ባሻ ገድሌ በዚያ ጭንቅ ወቅት አንድ ትልቅ ሊባል የሚችል ታሪክ ሰሩ። እሳቸው የሸዋ አማራ በመሆናቸው ጣሊያን በሳቸው ላይ ትኩረት የማያደርግ መሆኑን በመገንዘብና ይህን ሁኔታ በመጠቀም በጣሊያን በጣም ይፈለጉ የነበሩትንና የአርሲ ኦሮሞ ተወላጅ ሆነው በህብረተሰቡ ዘንድ በጣም የሚከበሩና ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎች በቤታቸው ውስጥ በመደበቅ ከዚያ የጣሊያን ምህረት የለሽ አሰሳ እንዲያመልጡ አደረጉ፤ በዚህም ብዙ የአካባቢው ታዋቂ ሰዎች እንዲድኑ ምክንያት ሆኑ።(በዚህ ታሪክ መነሻነትም የባሻ ገድሌ ክብረት ቤተሰብ በአካባቢው ባሉ የአርሲ ኦሮሞ ብሔረሰብ ዘንድ በጣም የሚከበሩና የሚወደዱ ነበሩ።) ይህ መረጃ በነኚያ የአርሲ ኦሮሞ ሽማግሌዎች ጆሮ ገባ። እስካሁን ካሰባሰቡት መረጃ ይልቅ ይሄኛው ልባቸውን ገዛው። የልጅቷን ወላጆች ማንነት(psychological makeup) እንደ መስታወት ፍንትው አድርጎ አሳያቸው። የልጅቷን ማንነት ደግሞ በወላጆቿ ማንነት ውስጥ ተረዱት። በመሆኑም ልጅቷን ወደዷት። ከዚያ ሽማግሌዎቹ ለአባቴ ወላጆች የደረሱበትን ሁኔታ በዝርዝር አስረዱ። ማብራሪያቸውን “የልጅቷ ወላጆች በጣሊያን ዘመን የኛን ታዋቂና የተከበሩ ሰዎች በቤታቸው ውስጥ በመደበቅ ከሞት አትርፈዋቸዋል፤ በመሆኑም ይህን የመሰለ ድርጊት ከፈፀመ ወላጅ አብራክ የወጣች ሴት ልጅ ምንም ቢሆን ለልጃችን ክፉ አትሆንም፤ እንደውም ጥሩ የትዳር አጋር ትሆነዋለች ብለን ስላመንን በሰጣችሁን ሀላፊነት መሰረት ወደልጅቷ ወላጆች ቤት ለሽምግልና ለመሄድ ተስማምተናል።” ብለው በማጠቃለል ወደልጅቷ ወላጆች ቤት ለሽምግልና ሄዱ፤ የልጅቷ ወላጆችም ስርዐቱን ጠብቀው ፍቃደኝነታቸውን በመግለፃቸው ጋብቻው ተፈፀመ፤ ጋብቻውም በስነምግባር የታነፁ፤ እንደዚያ ዘመን ልጆች ከብሔርተኝነት የፀዱና በሀበሻነታቸው ማለትም በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ ልጆችን ሊያፈራ በቃ።
የወላይታ የሐገር ሽማግሌዎች፡ እስቲ አሁን ደግሞ የወላይታ የሐገር ሽማግሌዎች ያሉትን ወይም ያደረጉትን እንይ።


የብሔር ፖለቲካ ዲስኩር፡ ይህንን ታሪክ የሰማሁት ከማስ ሚዲያ ነው። ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ አንድ ባለስልጣን ወላይታ ሄደው ምኒልክን በመጥፎ ገፅታ በመሳል የወላይታን ህዝብ በግድ እንደገዙና እንደበደሉ የሚያትት ሰፋ ያለ ዲስኩር አደረጉ። ባለስልጣኑ ምኒልክ የፈፀሙትን “በደል” በሰፊው ከተናገሩ በኋላ ህዝቡ አስተያየትና ጥያቄ እንዲያቀርብ ጋበዙ። አንድ ጥግ ላይ የተቀመጡ የወላይታ ሽማግሌ ባለስልጣኑ የተናገሩትን በጥሞና ካዳመጡ በኋላ ለህዝቡ ዕድል ሲሰጥ እጃቸውን አወጡ። ዕድሉ ሲሰጣቸውም “አሁን ያሉትን በደምብ ሰማን፤ እኔ በበኩሌ ባሉት አልስማማም፤ ምኒልክ ምንም አልበደሉንም፤ ይልቁንም ጠቀሙን፤ ትንሿን ወላይታ ወስደው ትልቋን ኢትዮጵያን ሰጡን እንጂ ምን በደሉን?” ብለው ተናገሩ። እግዚአብሔር ይስጣቸው። ምኒልክም ሆነ ማንኛውም ሰው የራሱ የሆነ ጠንካራና ደካማ ጎን አለው፤ የአንድን ሰው ደካማ ጎን ችላ ብለን ጠንካራ ጎኑን አግዝፈን ማየት በጣም የሚበረታታ አመለካከት ነው፤ ለሀገር አንድነትም ይበጃል።


የጣሊያን አገዛዝ መገለጫ፡ ይህንን ደግሞ የወላይታ ተወላጅ ከሆነው ጎረቤቴ የሰማሁት ታሪክ ነው። ከዚህ በላይ እንደገለፅኩት አንዱ የጣሊያን ዘመን ገፅታ     በየአካባቢው ያሉትንና ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎች ባንዳ ማድረግ፤ ባንዳ አንሆንም ያሉትን መግደልና በአካባቢው የሚገኘው ህዝብ በድለውናል ያሏቸውን ባለስልጣናትንም መግደል ነበር። በዚሁ መሰረት የወላይታ ተራ ደርሶ ጣሊያን ለዚሁ ስራ ወደወላይታ ተንቀሳቀሰ። ጣሊያን ወደወላይታ በመምጣት ላይ እንዳለ ወሬው በወላይታ ሽማግሌዎች ጆሮ ገባ። ሽማግሌዎቹም ወዲያው ተጠራርተው ስብሰባ ተቀመጡ። በስብሰባው ላይ በተለይ ከማዕከላዊ መንግስት የተሾሙ ባለስልጣናትን ምን እናድርግ? ብለው ተማከሩ። በዚህም መነሻነት የተለያዩ ሀሳቦች ቀረቡ። በመጨረሻ አካባቢ አንድ ኮስመን ያሉ ሽማግሌ እጃቸውን አወጡ። እድሉን እንዳገኙ “ወንድሞቼ” ብለው ንግግራቸውን ጀመሩ፤ “ወንድሞቼ አንደኛ የኛ ሰው ችግር ይችላል፤ ችግር ከመቻሉ  ተነሳ አፈር ልሶ የሚነሳ ነው፤ ስለዚህ የኛም መንግስት አሁን በጣሊያን ቢሸነፍም ውሎ አድሮ ማሸነፉ አይቀርም፤ ሁለተኛ ደግሞ በዝርያም ቢሆን የመንግስት ሰዎች(በዋነኛነት የአማራን ህዝብ ለማለት ነው) ከጣሊያን የበለጠ ለኛ ይቀርባሉ፤ በመሆኑም እነኚህን የመንግስት ባለስልጣናት አሳልፈን መስጠት የለብንም፤ ማድረግ ያለብን የኛ የወላይታ ተወላጆች ሆነው ህብረተሰቡን የሚያስቸግሩ ዘራፊዎችና ሌቦችን ለይተን አቅርበን እነኚህ ናቸው ይገዙን፤ ይበዘብዙን የነበሩት ብለን አሳልፈን እንስጣቸው።” የሚል አስተያየት አቀረቡ። ከተሰጡት አስተያየቶች በሙሉ የኚህ ሽማግሌ አስተያየት ሚዛን ደፍቶ በሙሉ ድምፅ ፀደቀ። ከዚያም ጣሊያኖች መጥተው ዲስኩራቸውን ከደሰኮሩ በኋላ “ከማዕከላዊ መንግስት ተሾመው እናንተን ያሰቃዩና የበዘበዙ ባለስልጣናት ስጡን” ብለው ህዝቡን ጠየቁ። የሀገር ሽማግሌዎቹም ቆፍጠን ብለው ያዘጋጇቸውን አስቸጋሪ ሰዎች አሳልፈው ሰጧቸው። ጣሊያንም አገኘሁ ብሎ ዘራፊዎቹንና ሌቦቹን በህዝብ ፊት ረሸናቸው። በመሆኑም ከመንግስት የተሾሙ ባለስልጣናትም ተረፉ፤ ህዝቡም እፎይ ብሎ መኖር ጀመረ። በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መምታት ማለት እንዲህ ነው። 

         ጣሊያን ከሀገር ከተባረረ በኋላ ጃንሆይ በአንድ ወቅት ሀገር ለመጎብኘት ብለው በየጠቅላይ ግዛቱ ይዞሩ ነበር። በሄዱበት ቦታ ሁሉ የሾሟቸው ባለስልጣኖቻቸው በጣሊያን ተረሸነው ስለነበረ ሊያገኟቸው አልቻሉም። ወላይታ በሄዱበት ወቅት ግን የሾሟቸው ባለስልጣናት አንዳቸውም ሳይነኩ አገኟቸው። ይህ ሁኔታ በጣም አስገርሟቸው እንዴት እንዲህ ሊሆን እንደቻለ የሀገር ሽማግሌዎቹን ጠየቋቸው። ሽማግሌዎቹም ታሪኩን በዝርዝር ነገሯቸው። ጃንሆይም ታሪኩን ሲሰሙ በጣም ገረማቸው። ከዚያም ጃንሆይ የሚከተለውን አዋጅ አስነገሩ። “ማንኛውም ከሌላ አካባቢ የሚመጣ ኢትዮጵያዊ በወላይታ ንብረት ማፍራት የሚችለው የወላይታ ተወላጅ ከሆነ ሰው ጋር በጋብቻ ከተሳሰረ ወይም በሽርክና ከተጣመረ ብቻ ነው”። ጃንሆይ ይህንን አዋጅ ያስነገሩት የወላይታን ህዝብ ውለታ ለመክፈል አስበው እንደሆነ ግልፅ ነው። የሽማግሌዎቹም ተግባር ዘራቸው ይባረክ የሚያስብል ነው። ለራሳቸው ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለሀገር አንድነት ታስቦ የተፈፀመ ትልቅ ተምሳሌትነት ያለው ድርጊት አድርጌ ነው የምወስደው።


የሲዳማ የሀገር ሸማግሌዎች፡ ሀዋሳ ከተማ ለብዙ ዘመን ከኖረና በቅርብ ከማወቀው ሰው የሰማሁት ታሪክ የሚከተለውን ይመስላል።             በአንድ ወቅት የውጪ ዜጋ የሆነ አንድ ቱሪስት ሀገር ለመጎብኘት ከአዲስ አበባ ወደ ሀዋሳ ከአስጎብኚ ጓደኛው ጋር ይሄዳል። ሻሸመኔ ከተማ ሲደርሱ ትንሽ እረፍት ካደረጉ በኋላ ወደሀዋሳ መንገድ ይጀምራሉ። ትንሽ እንደተጓዙ መኪናው በከፍተኛ ፍጥነት በመብረር ላይ እንዳለ ከየት መጣ ሳይባል አንድ ታዳጊ ወጣት መኪና መንገድ ውስጥ ጥልቅ ይላል። ልጁን ለማዳን ሾፌሩ ቢታገልም መኪናው ፍጥነት ስለነበረው ልጁን ገጭቶ ወዲያው ይገድለዋል። ከዚያም የአካባቢው ህዝብ ይገድለናል ብለው በመፍራት የመኪናቸውን ፍጥነት ጨምረው በማምለጥ ሀዋሳ ደረሱ። ሀዋሳ እንደደረሱ ያጋጠማቸውን አደጋ ለፖሊስ በማስረዳት ለደህንነታቸው ሲባል ፖሊስ ተሰጥቷቸው አደጋው ወደደረሰበት ቦታ ለመሄድ መፈለጋቸውን ገለፁ። ከዚያም ፖሊስ ጣቢያው በሀሳባቸው ተስማምቶ ፖሊስ ተሰጥቷቸው ከፖሊሱ ጋር አደጋ ወደደረሰበት ቦታ ሄዱ። በቦታው ሲደርሱ የሲዳማ ሽምግሌዎች ተሰብስበው ሲመካከሩ ደረሱባቸው።

ሽማግሌዎቹ ፈረንጁንና አስጎብኚውን እንዳዩ “አደጋው እንደደረሰ ለምን አምልጣችሁ ሄዳችሁ?” አሉዋቸው። ፈረንጁም “ብንቆም አደጋ ታደርሱብናላችሁ ብለን ስለሰጋን ፖሊስ ይዘን ለመምጣት ፈልገን ነው እንጂ ለማምለጥ አስበን አይደለም” በማለት በአሰተርጓሚ መልስ ሰጠ። ከዚያም ሽማግሌዎቹ “ብትቆሙም ኖሮ ጉዳዩን በሽምግልና አይተን ከመፍረድ ውጪ አደጋ አናደርስባችሁም ነበር፤” ብለው ሀሳባቸውን ገለፁ። በሽምግልናው ወቅት በሰፊው ከተወያዩ በኋላ በሚከተለው መንገድ ሸምግልናውን ቋጩት። “ይህ እንግዳ ፈረንጅ ከቤቱ ሲወጣ አገር ጎብኝቼ በሰላም ወደቤቴ እመለሳለሁ ብሎ ነው የወጣው፤ ከሞተው ልጅ ጋር በምንም መንገድ አይተዋወቁም፤ ልጁም በጨዋታ ላይ እያለ፤ የቀን ጉዳይ ሆኖበት፤ በራሱ ጥፋት መንገድ ላይ ሮጦ በመግባት ህይወቱ ተቀጠፈ። ይህ በእግዜር ፍቃድ የተፈጠረ አደጋ ነው። በመሆኑም በፈረንጁ በኩል ምንም ጥፋት ስላላገኘንበት በነፃ አሰናብተነዋል።” ሽማግሌዎቹም ጉዳዩን በሽምግልና አይተውት የደረሱበትን ውሳኔ ገልፀውላቸው ፈረንጁን እንደማይፈልጉት ነገሩት። 

      ፈረንጁ ህጋዊ ፍ/ቤት ቢቀርብ ኖሮ ልጁን የገደለው በአጋጣሚ እንጂ በቂም በቀል ባይሆንም ቅጣቱ ይቀልለት እንደሆነ እንጂ ከተጠያቂነት አያመልጥም። በመሆኑም የፍርድ ቤት ሂደትን ተከትሎ ተገቢውን ፍርድ እስኪያገኝ ድረስ ለተወሰነ ጊዜ በእስር መንገላታቱም የማይቀር ነበር። ከተፈረደበት በኋላም የተፈረደውን ቅጣትና እስር መፈፀምና መጨረስ ግዴታው ነበር። ፈረንጁ የሽማግሌዎቹን ውሳኔ ሲሰማ እጅግ በጣም ተገረመ፤ መገረም ብቻ ሳይሆን ማመን አቃተው። 

        ይህን ታሪክ ከዚህ በፊት ያጫወተኝ አቶ ደረጀ በቀለ የሚባል ሰው ነው። የታላቅ ወንድሜ ጌታቸው በቀለ የህይወት ዘመን ጓደኛ ነበር። ሰሞኑን አቶ ደረጀ እዚሁ አዲስ አበባ የሚኖርበት ቤት ሄጄ ስለሀገር ሸማግሌዎች አንድ ፅሁፍ  በጋዜጣ ለማውጣት እንዳሰብኩና ከማወጣቸው ታሪኮች አንዱ እሱ ከዚህ በፊት የሲዳማ የሀገር ሽማግሌዎች ስለፈፀሙት ታሪክ ያጫወተኝን መሆኑን ስነግረው “የምሰራበት ቦታ በዚህ ቀን እንገናኝ፤ ከዚያ አንድ የሲዳማ ተወላጅ ጓደኛ ስላለኝ በስልክ አገናኛችኋለሁ አለኝ፤ ባለኝ መሰረት የስራ ቦታው ስሄድ ለጓደኛው ስልክ ደወለና ምን እንደምፈልግ ነግሮት ስለባህሉ እንዲነግረኝ ጠየቀው፤ በዚሁ መሰረት የሲዳማ ተወላጅ ጓደኛው የሚከተለውን አጫወተኝ። “በሲዳማ ባህል አንድ ሰው በሌላ ሰው ላይ አደጋ ሲያደርስ የሀገር ሽማግሌዎች ተሰብስበው ጉዳዩን ይመረምራሉ፤ በምርመራው ሂደት ላይ አደጋ ያደረሰው ሰው በምን ምክንያት ነው ያደረሰው? ሆነ ብሎ ወይም በቂም በቀል ነው ወይስ በአጋጣሚ የተከሰተ አደጋ ነው ብለው በጥልቀት ጉዳዩን ያዩታል። አደጋው የደረሰው ሆነ ተብሎ ታስቦበት ወይም በቂም በቀል ከሆነ በሌላ መንገድ ፍርዳቸውን ይሰጣሉ። አደጋው የደረሰው በአጋጣሚ ከሆነ ግን ከአደጋ አድራሹ የሚጠበቀው ሁለት ነገር ብቻ ነው።

አንደኛው አደጋውን እንዳደረሰ ለማምለጥ ሳይሞክር እጁን ለአካባቢው ሰው መስጠት፤ ሁለተኛው ደግሞ በሀዘኑ ሂደት ላይ ከሟች ቤተሰብም ሆነ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ሀዘኑን መግለፅና ማድረግ ያለበትን አስተዋፅዖ ማበርከት ነው። ይህን ካደረገ ጉዳዩ በሀገር ሽማግሌዎች በሚታይበት ጊዜ በነፃ መለቀቅ ብቻ ሳይሆን ካሳ እንዲከፍል አይደረግም፤ ልክፈል ቢልም አይቀበሉትም።””                             ከዚህ በላይ የቀረበው የሽምግልና ታሪክ የሲዳማ የሀገር ሸማግሌዎች ውሳኔ የሚዛናዊነትና የምክንያታዊነት ጥግ የታየበት ውሳኔ ነበር አያስብልም? ለራሳቸው ወገንና ለልጃቸው ከማድላት የፀዳ  ብቻ ሳይሆን ተከሳሹ ምንም ሳይንገላታ የተሰጠ እውነተኛ ፍርድ መሆኑ ሽማግሌዎቻችን ምን ያህል ብስለት እንዳላቸው የሚያሳይ በመሆኑ ያኮራል። በሌላ በኩል ደግሞ ባህላዊ ሽምግልናን በአግባቡ ከተጠቀምን የህጋዊ ፍ/ቤትን ስራ ምን ያህል እንደሚያቀል መገመት አዳጋች አይሆንም።


ማጠቃለያ፡ አሁን ያለንበት ዘመን ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ ማምጣት የምችለው እኔ ብቻ ነኝ ባይ የበዛበት ጊዜ ነው። የዚህ መገለጫ ደግሞ መደማመጥ አለመኖሩ፤ የሀሳብ ልዩነትን በንግግርና በውይይት ከመፍታት ይልቅ ጊዜው ባለፈበትና በሚያጠፋፋን ነፍጥና ጠመንጃ ለመፍታት የምንራኮትበት ዘመን መሆኑ ነው። የዘመነ መሳፍንት ግልባጭ ማለት ነው። ታዲያ ከኛ በላይ መካሪ ሽማግሌ የሚያስፈልገው ፖለቲከኛ፤ ተቃዋሚ ፖለቲከኛና አክቲቪስት ያለበት ሀገር ይኖር ይሆን? በመንግስት ተቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ ያለው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአሁኑ ጊዜ በተፈለገውና በታሰበው መንገድ ስራውን ዳር ማድረስ ከቻለ ሀገራችንን ወደሰላም መንገድ ማምጣት የሚችል ይመስለኛል። ሰላምን ለማምጣት ሌላ የተሻለ አማራጭ መንገድ ካለ ለመቀበል አይገደኝም። የተሻለ አማራጭ ከሌለ ግን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ዓላማ ተቀብለን እያንዳንዳችን ማድረግ የሚጠበቅብንን ብናደርግ ለሀገር ይበጃል እላለሁ።

በምን መንገድ የተቀናጀ ስራ መስራት እንደሚቻል ለጊዜው ሀሳብ ባይመጣልኝም የሀገራችን ሽማግሌዎችም ሰላምን ለማምጣት የሚቻላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ከልቤ እመኛለሁ። ከአራቱም አቅጣጫ የሀገር ሸዕማግሌዎቻችን ተሰባስበው በመመካከር ሀገራችን ያጣችውን ሰላም በመመለስ ቢታደጓት ብዬ ተመኘሁ። የተለያዩ የሲቪክ ማህበራትም ከየትኛውም አጀንዳቸው አስቀድመው በሀገራችን ሰላም ለማምጣት መስራት የውዴታ ግዴታቸው ይመስለኛል። መንግስትም ሰላም የማምጣት ስራው ከየትኛውም ስራ በላይ ክሬዲት ሊያሰጠው የሚችል ተግባር መሆኑን እንደሚገነዘብ አምናለሁ። ሁልጊዜ እንደምለው ከምንም ነገር በላይ ሀገራችን በአሁን ጊዜ የሚያስፈልጋት ሰላም ነው። ሰላም ካለንና ለረዢም ዘመናት ከባድ አቀበት የሆነብንን የሀሳብ ልዩነቶቻችንን በክብ ጠረዼዛ የመፍታት ባህል ካዳበርን፤ አሁን ከሚታዩ የተለያዩ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች አኳያ ሀገሪቷን በኢኮኖሚ ለማሳደግ ቀሪው የጊዜ ጉዳይ ብቻ ይሆናል። ዋናውና ትልቅ የጎደለን ነገር ነው ብዬ የማምነው የዘመነ የፖለቲካ ባህል ነው። ይህን አውን ለማድረግ ደግሞ አብይ ስራችን ሊሆን የሚገባው የብሔር ፖለቲካን እንደ አረጀ ልበስ ከላያችን ላይ ማውለቅ ነው።


 ካላወለቅነው እርስ በርስ በጥርጣሬ ከመተያየት አልፈን ከመባላትና ከመተላለቅ ውጪ አንዳችም የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ፋይዳ እንደማያመጣልን ለመገንዘብ ምሁር መሆን አይጠበቅብንም።                                                           በዚህ አጋጣሚ የዚህችን ሀገር የተለያዩ ብሔረሰቦች በአንድ አስተሳስረው አንድ ሀገር ላስረከቡን የሀገር ሽማግሌዎቻችን በሙሉ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ትልቅ ምስጋናና ክብር አቀርባለሁ። በመጨረሻም በዚህ ዘመን ላለነው ለሁላችንም፤ በተለይም ለመንግስት ባለስልጣናት፤ በሰላም ለሚታገሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ነፍጥ አንግበው ለሚታገሉ ወገኖች እና በተለያዩ ሚዲያዎች ለሚሰሩ አክቲቪስቶች የሀገር ሽማግሌዎቻችን ያላቸውን አስተዋይነትና ብስለት እንዲሰጣቸው ወይም እንዲኖራቸው በመመኘት ፅሁፌን አጠቃልላለሁ።


Read 348 times