Saturday, 06 April 2024 20:08

አንቺ ልጅ! አንቺ አገር!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(3 votes)

 “ወድቆ የተገኘ ሐገር” አግኝቼ ረፋዱ ላይ አልጀምረው መሰላችሁ? ወዲያውኑ ይዞኝ ጭልጥ አላለም? ምሳ አለመብላቴን አልረሳሁትም?  
ይሄ ደግሞ ምን ዐይነት አጻጻፍ ነው? ጉዳዩስ ምንድነው? ያስብላል። ቢሆንም… ነገሩና አነጋገሩ እንዳልተምታታ ይገባችኋል - መጽሐፉን ካነበባችሁ ማለቴ ነው።
ልብወለድ መጽሐፍ ነው።
ደራሲዋ ይፍቱሥራ ምትኩ ናት።ርዕሱ ደግሞ “ወድቆ የተገኘ ሐገር” ይላል።
ድርሰቱ ውስጥ፣ ጥያቄ በሚመስል አነጋገር የሚያወራ ወጣት አለ። የ15 ዓመት ልጅ ምንድነው የሚባለው? ታዳጊ ለጋ ወጣት? ምንም በሉት ምን፣ አነጋገሩ እንደዚያ አልነበረም። በለጋ ዕድሜ ወደ ጦርነት ከሄደ በኋላ ነው አነጋገሩ ተቀይሮ የተመለሰው።
እንዲህ ሲባል ግን፣ ድርሰቱ ስለ ጦርነት ነው ማለት አይደለም። በእርግጥ ስለ ጦርነትም ነው። ነገር ግን፣ ድርሰቱ የ”አንቺነሽ” እና የወንድሟ የማስረሻ ነው። እና የእናታቸው።
ርዕሱን በማየት ብቻ፣ ድርሰቱ ስለ አገር ነው ብለን ካሰብንም ልንሳሳት እንችላለን። በእርግጥ ስለ አገር ነው። ነገር ግን የነ “አንቺነሽ” ሕይወት ነው - ድርሰቱ።
መቼም…የእናታቸው ሕይወት አያድርስ ነው። ሕይወታቸው አንዴ በአናቱ ሲፈጠፈጥ፣ አንዴ ኑሯቸው ለማንሰራራት ሲሞክር፣ አንዴ “እንደ ብረት የጠነከረ” መንፈስ ይዘው ደፋ ቀና ሲሉ፣ በአንብርክክ ስለት ሲገቡ… ለልጆቻቸው ሲሉ ተራራውን ለመውጣት፣ እንጦሮጦስ ለመግባት አያመነቱም።
ቢጨንቃቸው ውቃቢና ጠንቋይ እስከመሞከር ቢደርሱ ማን ይፍረድባቸዋል? ለነገሩ ፈራጅ እስኪመጣ ድረስ የሚጠብቁ አይደሉም። አዎ አምላክን አማላጅን ያማርራሉ። ግን በራሳቸው ላይም ይፈርዳሉ። የጥፋተኝነት ስሜት? የኑሮ መከራ ያነሰ ይመስል የጸጸት ሸክም ይጨመርባቸዋል። ስህተት ቢሠሩ እንኳእንዴት ያስወነጅላል? ለልጆቻቸው ሲሉ ላይ ታች መሰቃየታቸውም እንደ ጥፋት ተቆጥሮ!
አንዳንዴ፣ ከሕይወታችሁ ውስጥ እስከዘላለም እንዲኖር የምትጠብቁት ሰው ሲጎድል፣ ሐዘኑ ሳያበቃ ሌላ መከራ ጎትቶ ሲያመጣ፣ ሌላ ሰው ሲያሳጣችሁ፣ የወንድም የእህት መንፈስ ሲሰበር… ሕይወት ምስቅልቅሉ ሲወጣ፣ የሁሉም ሸክም አንዱ ላይ እየተደራረበ ይከመርበታል። ሕይወቱ ሁሉ ሸክም ይሆናል። መጀመሪያ እናትዬው ላይ፣ ከዚያም ልጃቸው አንቺነሽ ላይ።
የአባት፣ የወንድም፣ የእናት ሀዘንና መከራ ሁሉ ተሰብስቦ  ሲመጣባት “አንቺነሽ” ምን ታድርግ? አንድ እርምጃ መነቃነቅ የሞት ያህል ሲከብድ ምን ይባላል? በዝምታ በትዕግሥት በጽናት መታገል? ያልደረሰበትማ ማውራት ይችላል።
ያ ሁሉ የልጅነት ሕልም እንደ ጉም ሲጠፋ፣… “እንዲህ ተምሬ”፣ እንዲያ ሰርቼ”፣ “ያሰብኩት ተሳክቶ”፣ ፍቅር፣ ደስታ… እንዲህ ብሎ ማሰብ እየከበደ ሲመጣ ለማን አቤት ይባላል? ከሚወዳት ከአበራ ጋር ለፍቅር ጊዜ የሚሰጥ ዕድል መች አገኘች? “አንቺ ልጅ አንቺ ልጅ” እያለ እያዜመ በፉጨት ሲጠራት የነበረ ጊዜ ከማስታወስ ውጭ ምን ቀራት?
ቢሆንም፣… የመጣውን መከራ ብትሸከምም፣ እጣፈንታዬ ነው ብላ እዚያው ተደፍጥጣ ለመቅረት ፍቃደኛ አይደለችም።” የኔ ቦታ እዚህ አልነበረም” ብላ የመነሣት ብርታት አላት። ግን ስንቱን ታግላ ማሸነፍ ትችላለች? ለነገሩ ሕይወቷን በሙሉ ስትታገል አይደል የመጣችው?
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ርዕሱ “ወድቆ የተገኘ ሐገር” ስለሚል፣ ድርሰቱ ስለ ሀገር ነው ማለት አይደለም። የአንቺነሽ ታሪክ ነው። የእናትዋ፣ የወንድሟ፣ የአፍቃሪዋ ታሪክ ነው። ቢሆንም ግን ስለ ሀገርም ነው።
ምርጥ ድርሰት እንዲህ ለገለጻ ያስቸግራል።
የድርሰት መጻሕፍት ላይ አስተያየትና ዳኝነት የሚሰጡ የኪነጥበብ ተቋማት፣ ያለ ሐተታና ያለ ትንታኔ “የአምስት ኮኮብ ወይም የአራት ኮኮብ” ምልክት በማሳየት ብቻ አድናቆታቸውን የሚገልጹት ወደው አይደለም። ድርሰቱን ወድደው፣ መውደዳቸውን ማስረዳት ግን ቢጨንቃቸው ነው።
የድርሰቱን ይዘት ለመግለጽ ቢቸግረኝ አይግረማችሁ ለማለት ነው። ቢሆንም መሞከሬ አልቀረም።
ድርሰቱ የጦርነት ሳይሆን የአንቺነሽ ታሪክ ነው ብዬ የለ? እንዲህ ስላልኩ ግን፣ ድርሰቱ ስለ ጦርነት አይደለም አልልም። ነው። የድርሰቱ አሪፍነትም እዚህ ላይ ነው። ስለ ሀገር ወይም ስለ ጦርነት ለማውራት እንዲያገለግል የተፈጠረ ታሪክ አይደለም። የአንቺነሽና የወንድሟ ታሪክ ነው ዋናው ቁምነገር። ሕይወታቸው ነው ዋናው ነገር።
እዚያው ውስጥም ነው ሀገርንና ጦርነትን የምናገኘው።
እንዴት ልበላችሁ? ስለ ጦርነት ወይም ስለ ሀገር ለብቻው የተነጠለ ወሬ ወይም አየር ላይ የተንሳፈፈ ትንታኔ በድርሰቱ ውስጥ የለም። የሚማርከንና የሚመስጠን፣ የሚያስጨንቀንና የሚያብሰለስለን… የአንቺነሽ ሕይወትና ኑሮ፣ ሐሳቧና ውሳኔዋ፣ ተግባሯና ፈተናዋ ነው። ከተስፋዋ ጋር ልባችን ፈካ ይላል፤ ከመከራዋ ጋር ልባችን ይከፋዋል። እንደ ራሳችን ሕይወት ያሳስበናል።
እናም… የጦርነት ወይም የሀገር ጉዳይ የሚተርክ ድርሰት አይደለም ብለን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። ግን ደግሞ፣ ከትንታኔና ከሐተታ እጅግ በጠለቀ መንገድ የጦርነትና የሀገር ጉዳይ ውስጣችን ድረስ የሚዘልቅ “ስሜት” እንዲፈጠርብን ያደርጋል። በቀጥታ አይነግረንም፤ ያሳየናል እንጂ።
ትንታኔና ሐተታ አያስፈልግም ለማለት አይደለም። ለማናናቅም አይደለም። ያስፈልጋል። ያለ ዕውቀትማ ድርሰትስ ከየት ይመጣል? ነገር ግን፣ ሐተታውና ትንታኔው የፓለቲካ ምሁራን ሥራ ነው። ሙያውና ዕውቀቱ ያላቸው እንደየዐቅማቸው ያብራሩ። ካስፈለገ በቁጥርና በመቶኛ እየዘረዘሩ ይንገሩን።
የኪነጥበብ ድርሻ ከዚህ የተለየ ነው። ኪነጥበብ፣ “የመንገር ሳይሆን የማሳየት ጥበብ ነው” ይባል የለ!
የሰብለወንጌልና የበዛብህ ታሪክ እንል የለ!
“የፊውዳል ዘመንና የለውጥ ጅምር በሰዎች ሕይወት ላይ ያስከተሉትን ምስቅልቅል” የሚያብራራ ወይም የሚተነትን ሐተታ አይደለም - “ፍቅር እስከ መቃብር”።
የኪነጥበብ ፈጠራ ነው። ድርሰት ነው። አዎ ያንን “ምስቅልቅል” ያሳያል። የአገር ምስቅልቅልን ለማስረዳት እንደ ማብራሪያ የሚያገለግል መሣሪያ ግን አይደለም። የነ ሰብለወንጌል ሕይወት ነው ድርሰቱ። በታሪካቸው ውስጥ ከምናያቸው ጉልህ ነገሮች መካከል አንዱ ነውና ያንን “ምስቅልቅል” እንመለከታለን።
ያየነውን ታሪክ ወደ ሐተታ ቀይረን ስለዘረዘርን፣ ድርሰቱን ገልጸናል ማለት አይደለም። በጭራሽ! እንዲያውም ክብሩን እንቀንሰዋለን።
መቼም ስለ ጦርነት አጫጭር አስተያየቶችን መናገር አያቅተንም። በትንሹ እንሞክር?
ከሁሉም ከሁሉም አሳዛኙ ነገር፣ ጦርነት የመጣባቸው ሰዎች በሕይወት አምልጠው የመውጣት ዕድል ሲያጡ ነው። ወደ ጦርነት የሄዱ ብዙዎች ሰዎችም በሕይወት የመመለስ ዕድል አያገኙም።
በሕይወት የተመለሱትም፣ ሙሉ አካላቸውን ይዘው አይመጡም።
አካል ባይጎድልም፣ በዐይን የሚታይ ቁስል ባይኖርም ግን፣ ወደ ጦርነት የሄደ ሰው እንዲሁ አይመለስም። ከውስጥ ተቀይሯል። ወደ ጦርነት የዘመተው ሌላ፣ ከጦርነት የሚመለሰው ሌላ! እንዲሉ ነው።
የተሰናበተው ቤተሰብም፣ እንደድሮው ሆኖ አይጠብቀውም።
ምናለፋችሁ!
የሀገርና የጦርነት ነገር፣… በየት በየት በኩል የስንቶችን ሕይወት እንደሚበላና እንደሚያመሳቅል ብዙ መዘርዘር ቢቻልም፣ “ዝርዝሩ ነፍስ ዘርቶ በገሀድ እንጨብጠዋለን” ማለት አይደለም። ያስቸግራል (በድርሰት ካልሆነ በቀር)።
አንዳንዴማ ስለ ሀገር ስናወራ፣ የሰዎች ሀገር መሆኑን እንዘነጋዋለን።
በሰዎች ሕይወት ላይ የሚያስከትለውን ውጤትና መዘዝ አናስበውም።
ሕይወታችንን ስናስብና ለኑሮ ስንሯሯጥ ደግሞ፣ ስለ ሀገር የምናስብበት ምክንያት አይታየንም። ሀገር ማለት ድሮም ነበረ፤ ዛሬም አለ፤ ነገም ይኖራል ብለን የደመደምን፣ አስበን የጨረስን ይመስላል። እንዲያውም፣ ከነጭራሹም በሐሳባችን አይመጣ ይሆናል። “ወድቆ የተገኘ ሐገር” ይመስለናል።
ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ “ሁሉም ነገር ለሀገር” እንላለን። ጦርነት፣ ዘመቻ፣ ውጊያ፣ ድል… እያልን እናወራለን። አንዳንዶቹማ የኳስ ግጥሚያ፣ የፊልም ቤት ፍልሚያ ያስመሱልታል። በእርግጥ ብዙዎቻችን ጦርነትን እንደ ቀልድ እናየዋለን ማለት አይደለም። በጦርነት ወሬ ለመዝናናት አንጠብቅም። እንዲያም ሆኖ፣ ጦርነትን ከነምንነቱ፣ ከነነፍሱ፣ ከነቅርንጫፎቹ፣ በሄዱበት ሁሉ ያገኙትን የሚያጭዱ የእሳት አለንጋ የመሰሉ የጦርነት ቅርንጫፎችን፣ አገር ምድሩን የሚናደፉ መርዛማ የእሾህ ሐረጎቹን ሁሉ በእውን እንረዳለን ማለት አይደለም።  
በእርግጥ፣ እንደ ዘበት የምንሰማው የጦርነት ወሬና የድል ዜና ውስጥ ብዙ መከራና መዘዝ እንደሚኖር በደፈናው ይሰማን ይሆናል። መሞት አለ፤ መቁሰልና አካል ማጣት አለ። ከአእምሮ የማይጠፋ የመንፈስ ጠባሳ አለ። የሟቾችና የቁስለኞች ብዛት በቁጥር ሲነገር የምንሰማበት አጋጣሚም ይኖራል።
ማዘናችን አይቀርም። ኅሊናችን ይረበሻል። እንዲያም ሆኖ፣ እንደ ጉም ነው። ጥርት ብሎ የማይታይ ብዥታ ነው። ከውስጥ የማይዘልቅ የሩቅ ጉምጉምታ ነው። ጦርነት፣ አጠገባችን ወድቆ የቤታችንን ጣሪያ በርቅሶ የሚገባ ምድር ሰማዩን የሚደባልቅ መብረቅ አይሆንብንም።
የጦርነትና የዘመቻ፣ የውጊያና የድል ወሬ የቱንም ያህል ብንሰማና በቁጥር ብናወራ፣ ብናዝንና ብንጨነቅ እንኳ ለጊዜው ነው። በስሱ ነው። በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ላይ የሚያስከትለው “ለውጥ” አይታየንም።
የተጎዱ ሰዎች በቀጥታ ቢነግሩንም እንኳ፣ ልቅሶ ብንደርስ ወይም ቁስለኛ ለመጠየቅ ብንሄድ እንኳ፣… ክፉኛ ማዘናችን ባይቀርም፣ እንደሚያሳስበን ባይካድም፣… ጦርነትና መዘዙ፣ ነፍስ ዘርቶ በገሀድ አይታየንም። እስከ አጥንት ድረስ ዘልቆ ሕመሙ አይታወቀንም።
ልበ ደንዳና ስለሆንን ወይም ኅሊናችን እንደ ዐለት ስለጠጠረ፣ ማሰብ ስለጠላን ወይም የመረዳት ዐቅም ስላጠረን፣ ሕይወትን ስለናቅን ወይም ደንታ ቢስነት ስለተጠናወተን ላይሆን ይችላል።
ከማብራሪያ፣ ከትንታኔና ከሐተታ አስፈላጊ ናቸው። ነገር ግን፣ የሕይወትን ጉዳዮች በጥልቅ መንፈስ መጨበጥ የምንችለው በኪነጥበብ አማካኝነት ነው። እናም አዎ፣ ምርጥ ድርሰት “ትልልቅ ጉዳዮችን” ያዘለ ነው። ነገር ግን፣ “የትልልቅ ጉዳዮች” ድርሰት አይደለም።  በጥንቃቄ የተለቀመና የነጠረ፣ በጥበብ የተቀመመና የተዋሐደ የሰዎች ታሪክ ነው - ድረሰት። የፍቅር እስከ መቃብር የተሰኘው ድርሰት “የሰብለ ወንጌልና የበዛብህ ታሪክ ነው” ስንል እንደነበርነው፣ አሁን ደግሞ “ወድቆ የተገኘ ሐገር” የሚለው ድርሰት  “የአንቺነሽና የአበራ ታሪክ” እንላለን።
የድርሰት ባህርይ፣ በታሪኩ ይዘት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የአተራረክና የቋንቋ አጠቃቀም ጥበብ ላይም ይታያል። አተራረኩ “የሚያጠግብ ድል ያለ ድግስ፣ የተንዠረገገ የፍራፍሬ ዛፍ” እንደማለት ነው። ይህ ቀረው አይባልም።
 ግን ደግሞ ለትርፍ ነገሮች ቦታ መስጠት የለበትም። ትርፍ ዓረፍተ ነገሮችን… ትርፍ ቃላትን አይፈልግም።
በዚህ ዐይን ስናይም፣ የደራሲዋ ጥበብ ድንቅ ነው። ለነገሩ ካሁን በፊት “በተለይ ዐሥራ አንደኛው!” በሚል ድርሰቷም አስገራሚ ችሎታዋን አሳይታለች። ከብዙዎችም አድናቆትን አትርፋለች።



Read 713 times