Saturday, 30 March 2024 19:23

በወሊድ ወቅት የሚፈጠር የማህፀን ጫፍ መሰንጠቅ

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

 በዚህ እትም ልናስነብባችሁ ያሰናዳነውን የማህጸን ጫፍ መሰንጠቅ [መቀደድ] አስመልክቶ የህክምና ባለሙያ የሰጡንን ማብራሪያ ከማስነበበቻን አስቀድሞ የ3 እናቶችን ልምድ እናካፍላችሁ።
“ሀውለት እባላለው ተወልጄ ያደኩት አሁንም የምኖረው በገጠር ከተማ ውስጥ ነው። ልጄን የወለድኳትም በአነስተኛ የህክምና ተቋም ውስጥ ነው። ልጄን ከወለድኩ በኋላ ግን ከዚህ በፊት ያልነበረብኝ ችግር አጋጠመኝ። በተለይ ከበድ ያለ እቃ ሳነሳ ነፋስ እና አንዳንድ ጊዜ ሰገራ መቆጣጠር አልችልም። በሰዎች ፊት ሲሆን እሳቀቃለው። ወደ ህክምና ተቋም ሄጄ ችግሬን ለማስረዳት ስላሳፈረኝ ዛሬ ነገ እያልኩ ከነ ችግሬ ቤቴ ተቀምጫለው።” ሀውለት ከለገዳዲ
“ባለትዳር እና የልጆች እናት ነኝ። ከባለቤቴ ጋር ጥሩ የሚባል ትዳር ነው ያለን። 3ኛ ልጄን ከወለድኩ በኋላ ግን ማህፀኔ ላይ ባጋጠመኝ ችግር ምክንያት ከባለቤቴ ጋር ከባድ ሁኔታ ውስጥ ገብተናል። 3ኛ ልጄን የወለድኩት ቤት ውስጥ ነው። ከዛ ጊዜ በኋላ ግንኙነት በምንፈፅምበት ወቅት ማህፀኔ ድምፅ አለው። እናም ይህ ሁኔታ ትዳሬን እያፈራረሰው ነው።” ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ እናት
“የመጀመሪያ ልጄን ስወልድ ባጋጠመኝ የማህፀን ጫፍ መሰንጠቅ ምክንያት በፊስቱላ ችግር ተጠቅቼ ነበር። ነገር ግን ህክምናውን ተከታትዬ ከበሽታው ማገገም ችያለው። የፈጣሪ፣ የህክምና ባለሙያዎች እና የባለቤቴ ድጋፍ ችግሩን ተቋቁሜ አንዳልፍ አድርጎኛል። በአሁኑ ወቅት በቀዶጥገና ህክምና አማካኝነት 2ኛ ልጄን መውለድ ችያለው። እናቶች እንደ እኔ አይነት ችግር ሲያጋጥማቸው ህክምና እንዲያደርጉ እመክራለው።”
 ወ/ሮ ካሰች ተስፋዬ ከአዲስ አበባ         
በ32ኛው የኢትዮጵያ የፅንስ እና ማህፀን ሀኪሞች ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ከቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎች መካከል እናቶች በማህፀን(በምጥ) በሚወልዱበት ወቅት በማህፀን ጫፍ እና በፊንጢጣ መካከል በሚፈጠር ቀዳዳ (perineal tear) ላይ የተደረገ ጥናት አንዱ ነው። በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሙሴ ነጋሲ ናቸው። ዶ/ር ሙሴ ነጋሲ እንደተናገሩት ይህ የጤና እክል ብዛት ባላቸው እናቶች ላይ እያጋጠመ የሚገኝ ቢሆንም የሚፈልገውን ያህል ትኩረት አልተሰጠውም። ዶ/ር ሙሴ ነጋሲ በመቐለ ከተማ ካደረኩት ጥናት በተጨማሪ በኢትዮጵያ ውስጥ በጉዳዩ ላይ ተደረገ ጥናት 1 ብቻ ነው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም አቀፍ ደረጃ በማህፀን (በምጥ) ከወለዱ እናቶች ውስጥ ከ53 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት የማህፀን ጫፍ የመሰንጠቅ ችግር [perineal tear] አጋጥሟቸዋል። እንዲህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ ልጃቸውን በማህፀን(በምጥ) ከሚወልዱ ከ10 እናቶች መካከል 9 የሚሆኑት ከቀላል እስከ ከባድ የማህፀን ጫፍ ላይ የመሰንጠቅ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ይገመታል።
“በማህፀን ልጅ ሲወጣ የህክምና ባለሙያ ድጋፍ ሊያደርግለት ይገባል፤ ድጋፍ ካልተደረገ በማህፀን እና በሰገራ መውጫ መካከል መቀደድ ይፈጠራል፤ መሰንጠቅ ሲያጋጥም ደግሞ የህክምና ባለሙያ በመስፋት ህክምና ይሰጣል” ብለዋል ዶ/ር ሙሴ ነጋሲ።
አጋላጭ ሁኔታዎች
በማህፀን መውለድ
ከፍተኛ ክብደት ያለው ልጅ መውለድ; በጥናቱ መሰረት ከ3.5 ኪሎ በላይ
የመጀመሪያ ልጅ መውለድ
እንደ ዶ/ር ሙሴ ነጋሲ ንግግር ከተጠቀሱት አጋላጭ ሁኔታዎች በተጨማሪ በጥናቱ ውጤት መሰረት በይበልጥ ገጠራማ አከባቢ የሚኖሩ (የወለዱ) እናቶች ለችግሩ ተጋላጭ መሆናቸው ተረጋግጧል። እንዲሁም በሌሎች ጥናቶች ላይ በስቲች መውለድ እንደ አጋላጭ ምክንያት ቢጠቀስም በዶ/ር ሙሴ ነጋሲ ጥናት ግን እንደ አጋላጭ ሳይሆን እንደ መከላከያ መንገድ ተቀምጧል።  
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሙሴ ነጋሲ ባደረጉት ጥናት ላይ 60ሺ 4 መቶ እናቶች ተሳታፊ ሆነዋል። እናቶቹ በአይደር እና በመቐለ ሆስፒታል በ7 ዓመታት ውስጥ በማህፀን (ምጥ) የወለዱ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ 95 እናቶች ናቸው የማህፀን ጫፍ ላይ መሰንጠቅ ያጋጠማቸው። “ቁጥሩ አነስተኛ ነው፤ ይህም የሆነው ችግሩ ሲያጋጥም ስለማይመዘገብ እና በፋይል ስለማይቀመጥ ነው” ብለዋል ዶ/ር ሙሴ ነጋሲ።
በወሊድ ወቅት የሚያጋጥም የማህፀን ጫፍ መሰንጠቅ የሚያስከትለው ጉዳት
ሰገራ እና ነፋስ መቆጣጠር አለመቻል
ፊስቱላ
በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ድምፅ መኖር
ዶ/ር ሙሴ ነጋሲ እንደተናገሩት ይህ የጤና እክል በጤና፣ በትዳር እና በማህበራዊ ግንኙነት ላይ ችግር የሚፈጥር ነው። እንደ የህክምና ባለሙያው ንግግር ሴቶች (እናቶች) በብዛት ወደ ህክምና የሚሄዱት በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ችግር ሲፈጠር ነው። ይህም ከትዳር አጋራቸው ጋር እስከ መለያየት(ፍቺ) የሚደርስ ሁኔታ መሆኑን ዶ/ር ሙሴ ተናግረዋል።
“ጥናቶች እንደሚያሳዩት በወሊድ ወቅት የተፈጠረ የማህፀን ጫፍ መቀደድ ህክምና ከተደረገለት (ከተሰፋ) በኋላ ከ15 እስከ 60 በመቶ በሚሆኑ እናቶች ላይ በድጋሚ ችግሩ ይመጣል” ብለዋል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሙሴ ነጋሲ። የማህፀን ጫፍ መሰንጠቅን ተከትሎ ያሉ ችግሮች ተመልሰው የሚመጡት (የሚያገረሹት) እናቶች አስፈላጊውን ህክምና ስለማይከታተሉ መሆኑን የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል።
መከላከያ መንገዶች
ከ8 ወር የእርግዝና ወቅት ጀምሮ እራሷ ነፍሰ ጡሯ ሴት ወይም የትዳር አጋሯ ማህፀን አከባቢ እንዲፍታታ (ማሳጅ) ማድረግ እና ጨርቅ በሙቅ ውሃ ነክሮ ማህጸን ጫፍ ላይ ማስቀመጥ
በህክምና ባለሙያ አማካኝነት በወሊድ ወቅት ማህጸን እንዲፍታታ (ማሳጅ) ማድረግ
በወሊድ ወቅት ልጅ በተስተካከለ መንገድ እንዲወጣ የህክምና ባለሙያ ድጋፍ ማድረግ
በወሊድ ወቅት የማህፀን ጫፍ ማስፋት (ስቲች); ዶ/ር ሙሴ ነጋሲ በሰሩት ጥናት ላይ እንደ መከላከያ መንገድ የተጠቀሰ ሲሆን በዓለምአቀፍ ደረጃ ግን አጋላጭ ወይም መከላከያ መንገድ መሆኑ ያልተረጋገጠ እና ስምምነት ላይ ያልተደረሰ መሆኑን የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል።
የማህፀን ጫፍ ላይ መሰንጠቅ ካጋጠመ እና ህክምና ከተደረገ(ከተሰፋ) በኋላ ቤት ውስጥ ሞቅ ያለ ውሃ ላይ ከ5 እስከ 20 ደቂቃ መቀመጥ ይመከራል። ይህም የሚደረገው በቀን ለ2 ወይም 3 ጊዜ ነው። እንዲሁም ውሃው ላይ ጨው መጨመር ይቻላል።
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሙሴ ነጋሲ እንደተናገሩት የማህፀን ጫፍ ላይ መሰንጠቅ (perineal tear) ያጋጠማት ሴት በቀጣይ እንድትውልድ የሚደረገው በቆዶ ጥገና ነው። ነገር ግን ይህ አሰራር በኢትዮጵያ እንጂ በሌሎች (ባደጉ) ሀገራት ተግባራዊ የሚደረገው ምርመራዎች ተደርገው በድጋሚ በማህፀን (በምጥ) መውለድ እንደማትችል ከተረጋገጠ በኋላ ነው። በኢትዮጵያ ካለው የህክምና ቁሳቁስ እጥረት አንፃር 1 ጊዜ የጤና ችግሩ ያጋጠማት ሴት በቀጣይ በቀዶ ጥገና እንድትወልድ መደረጉን ባለሙያው ተናግረዋል።
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሙሴ ነጋሲ በወሊድ ወቅት በማህፀን ጫፍ ላይ የሚፈጠር የመሰንጠቅ ችግር ከሚያደርሰው ጉዳት አንፃር ትኩረት እንዳልተሰጠው እና እንደተረሳ ጠቅሰው የህክምና ባለሙያ፣ ህብረተሰቡ እና የሚመለከተው አካል እንዲሰራበት መልእክት አስተላልፈዋል።  

Read 299 times