Saturday, 23 March 2024 20:21

ንግድ ባንክ የተወሰደው ገንዘብ እንዲመለስለት የሠጠው የጊዜ ገደብ ዛሬ ያበቃል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  የማይመልሱ ሰዎችን ፎቶና ማንነት በሚዲያ ይፋ አደርጋለሁ ብሏል
         - የራስ ያልሆነ ገንዘብ ህጋዊ ማድረግ እስከ 25 ዓመት እስራት ያስቀጣል
         - የአካውንቶች መታገድ ገንዘቡን ለመመለስ እንቅፋት ፈጥሯል ተብሏል


          የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጋጠመኝ ባለው  የሲስተም ችግር ምክንያት ያለአግባብ  ገንዘብ ከባንኩ  የወሰዱ ወይም ወደ አካውንቶች  ያስተላለፉ ግለሰቦች የወሠዱትን ገንዘብ ለባንኩ እንዲመልሱ የሠጠው የጊዜ ገደብ ዛሬ ያበቃል።  በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ገንዘቡን  ካልመለሱ ፎቷቸውንና ማንነታቸውን በመገናኛ ብዙኃን ይፋ እንደሚያደርግም ገልጿል ።
ባንኩ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም በተፈጠረው የሲስተም ችግር ምክንያት ከባንኩ  ገንዘብ የወሰዱ ወይም ወደተለያዩ ሂሳቦች ያስተላለፉ ግለሰቦች ገንዘቡን ተመላሽ እንዲያደርጉ ተደጋጋሚ ጥሪ ያቀረበ መሆኑን አመልክቶ፤  የመጨረሻ  ያለውን ጥሪ ከትላንት በስቲያ  ሐሙስ መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም.  አስተላልፏል። በዚህ ጥሪ መሠረትም ባንኩ ገንዘቡን ለማስመለስ የሠጠው የጊዜ ገደብ ዛሬ ይጠናቀቃል ።
ገንዘቡን ተመላሽ በማያደርጉ ሰዎች ላይ በሕጋዊ ሂደቱ ተገቢ ውሳኔ እስኪገኝ ድረስ ፎቶግራፋቸውንና ዝርዝር ማንነታቸውን የሚገልጹ መረጃዎች፤ ባንኩ በመረጠው የብዙኃን መገናኛ መንገድ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቋል። ከሕግ አካላት ጋር በመተባበር የግለሰቦችን ስም ዝርዝር በየቅርንጫፎችና እንደሁኔታው ግለሰቦቹ ሊታወቁ በሚችሉበት አካባቢ ይፋ በማድረግ ቀጣይ ሕጋዊ እርምጃዎችን እንደሚከተሉም  ገልጿል። በተጨማሪም “ከፍትህ አካላትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ተገቢውን የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔር እንዲሁም አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እንደሚያደርግም አሳስቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ከንግድ ባንክ የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ ያንቀሳቀሱ ግለሰቦች የማይመልሱ ከሆነ፣ በህግ እንደሚጠየቁ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በተፈጠረው ችግር ዙሪያ ከባንኩ ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ የገለፀው የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎቱ፤ የራስ ያልሆነን ገንዘብ ህጋዊ ማድረግ እንደ ወንጀሉ ክብደት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ እስራት እደሚያስቀጣ አሳስቧል፡፡
ባንኩ አርብ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ የሲስተም ችግር በገጠመው ወቅት የተወሰደበት ገንዘብ  መጠን ከባንኩ በይፋ ባይገለጽም ፣ በዕለቱ የተወሰደው የገንዘብ መጠን 2.4 ቢሊዮን ብር (40 ሚሊዮን ዶላር) መሆኑን አሶሺየትድ ፕሬስ  ዘግቧል።

Read 744 times