Thursday, 21 March 2024 20:38

በ1 ቢሊዮን ብር ይገነባል የተባለው "መቅደስ የልጆች አድማስ"

Written by 
Rate this item
(2 votes)
“ማዕከሉ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ 1ሺ ህፃናትን የመቀበል አቅም ይኖረዋል”
አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ ወላጆቻቸውን በሞት ላጡ ህጻናት፣ "መቅደስ የልጆች አድማስ" የተሰኘ ማዕከል በ1 ቢሊዮን ብር ወጪ ልትገነባ መሆኑ ተገለጸ፡፡
አርቲስቷ የምታቋቁመውን የበጎ አድራጎት ድርጅት አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በካፒታል ሆቴል ለጋዜጠኞች መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
ድርጅቱን ለማቋቋም ሃሳቡ የተፀነሰው ከ6 ዓመታት በፊት እንደነበር አርቲስት መቅደስ ጸጋዬ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግራለች፡፡
የድርጅቱ የቦርድ አባል ደራሲ ውድነህ ክፍሌ እንደገለጸው፤ ማዕከሉ በዋናነት ልዩ ትኩረትና ጥበቃ ለሚያስፈልጋቸው ወላጅ አልባ ህፃናት አስፈላጊውንና ሁሉን አቀፍ እንከብካቤ በመስጠት በቀጣይ የሕይወት ጉዟቸው ስኬታማ ይሆኑ ዘንድ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ነው፡፡
በማዕከሉ ውስጥ ለሚቆዩ ልጆች ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶችን ከመስጠትና፣ የአካል ብቃት ማጎልመሻ ከማደራጀት ባሻገር፣ የማኅበራዊ ሕይወትና የአእምሮ ማበልፀጊያ ስልጠናዎችን በመስጠት ሙሉ ጤንነታቸው የተረጋገጠ፣ በአካላዊ እድገታቸው የበቁ፣ በሥነ ልቦና፣ በግልና በማሕበራዊ ሕይወታቸው ጠንካራ የሆኑ እንዲሁም በአእምሮአዊ የጠራ ችሎታቸው የተደነቁና በዕውቀት የዳበሩ ሆነው የመጪው ጊዜ ብሩህና ስኬታማ ዜጎችን እንዲሆኑ በትኩረት ይሰራል ተብሏል።
“መቅደስ የልጆች አድማስ” በማእከሉ የሚያድጉ ልጆች በሁሉም ረገድ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን የተላበሱና አዎንታዊ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ማድረግ ዋና ትኩረቱ እንደሆነ ተገልጿል።
በሃያ አንድ ሺ ካሬ ሜትር ላይ እንደሚያርፍ የተነገረለት ማዕከሉ፤ ሙሉ ለሙሉ ለመገንባትና በሙሉ አቅሙ ስራውን እንዲጀምር ለማድረግ እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሏል፡፡
የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የመጀመሪያ ማዕከሉን የሚገነባው በአዲስ አበባ ሲሆን፤ ቀስ በቀስም ወደ ከልሎች ቅርንጫፎቹን የሚያሰፋ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡ ማዕከሉ በመጀመሪያው ዙር 200 ህፃናትን ከመላው ኢትዮጵያ የሚቀበል ሲሆን፤ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ደግሞ 1000 ህፃናትን የመቀበል አቅም እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡
ማእከሉን እውን ለማድረግ መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል በይፋ ገቢ በማሰባሰብ ወደ ስራ የሚገባበት ቀን ሲሆን፤ በዚህ መርሃ ግብር ላይ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ባለሃብቶች፣ የኤምባሲ ተወካዮች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ሃሳቡን የሚደግፉና ቀና ልብ ያላቸው ሰዎች ይታደሙበታል ተብሏል።
Read 884 times