Saturday, 16 March 2024 19:52

ዘውድ ሳይደፉ መንገስ

Written by  እዝራ እጅጉ -
Rate this item
(1 Vote)

ዘውድ ሳይደፉ መንገስ አዳጋች ይመስለኛል፡፡ በአገራችን ግን በአንድ ወቅት  ያለ በአለ ሲመት የነገሱ ነበሩ፡፡ መንገስ ሲባል አድራጊ ፈጣሪነትና ተፈሪነትን የሚያመለክት ሲሆን፤ በቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ታሪካችንም ውስጥ ድምጻቸውን አጥፍተው ከኋላ በመሆን የንጉስ ወይም የርእሰ ብሄር ያህል የሚፈሩ ነበሩ ይኖራሉም፡፡ በዚህ ጽሁፍ ስለ እነርሱ በዝርዝር ማውራቱን ለጊዜው ትቼ፣ ከ80 አመት በፊት የተሰጣቸውን የመንግስት የሥራ ኃላፊነት ይዘው፣ እጅግ ወሳኝ የአገሪቱ ቁልፍ ሰው በመሆን አሻራ ማኖር ስለቻሉ አንድ ሰው ላጫውታችሁ ፈልጌ ነው፡፡

ሰውየው ጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ ይባላሉ፡፡ ከ1933 እስከ 1947 ዓ.ም ለ14 ዓመታት  የንጉስ ኃይለስላሴን ማህተም በመያዝ በወሳኝ፣ ጉዳዮች ላይ አደራቸውን ሲወጡ የቆዩ  ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡ ንጉስ ኃይለስላሴ  ስልጣናቸውን ከማጋራት ባልተናነሰ እንዴት ለእኒህ ሰው  እድል ሰጡ? እያልኩ ጥያቄ የምጠይቅበት ጊዜ አለ፡፡ ጃንሆይ ወልደጊዮርጊስን ፈርተው ይሆን? የሚል ጥያቄ ሳነሳ ደግሞ  አንዷ ባህር ማዶ ያለች ወዳጄ፤ ‹‹ንጉሱ እንኳን ማንንም አይፈሩም” ብላ እንደመለሰችልኝ አስታውሳለሁ፡፡
የንጉሱ ዘመን ሰዎች ይመስጡኛል፡፡ የድሮ ዘመን ናፋቂ ሆኜ ሳይሆን፤ አብሮ ከመዋልና ከመሥራት አንዳንድ ጠቃሚ ነገሮችን በመቅሰሜ  ነው፡፡ ሁሉን ነገር ያሟሉ ብቁ ናቸው ብዬ ከፍ ከፍ ላደርጋቸው ሳይሆን፤ ከጊዜና ከቋንቋ አጠቃቀም አንጻር ያላቸውን ልዩ አቅምና ክህሎት ለማድነቅ ፈልጌ ነው፡፡  
በነገራችን ላይ በንጉስ ኃይስላሴ ዘመን ለነበረው የትምህርትና የሀገር አስተዳደር ዘይቤ ልዩ ቦታ አለኝ፡፡ ንጉሱ ፊውዳሊዝምን አንግሰዋል ተብለው ቢታሙም፣ ትምህርት ላይ የነበራቸው ልዩ ትኩረት ዛሬም ድረስ ያስመሰግናቸዋል፡፡
ባለፉት 7 አመታት ‹‹የንጉሱ ዘመን ባለውለታዎች›› በሚል መነሻ ሀሳብ  የብዙዎቹን ታሪክ ስመረምርና ሰነድ ሳገላብጥ  ስለቆየሁ፣ የእነዚህን ታላላቅ ሰዎች ድንቅ አቅም መመስከር ችላለሁ፡፡ አሁንም በዚህ መጣጥፌ ስለ ጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ ሳጫውታችሁ፣ የሰውየውን አበርክቶ ለማውሳትና  እናንተም ተጨማሪ ንባብ አድርጋችሁ የበለጠ እንድታውቋቸው ለማነቃቃት ነው፡፡
ጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ ከንጉሱ በመቀጠል አድራጊ ፈጣሪ የሆኑበት ሚስጥር ምንድነው? ንጉሱ በስደት ወደ እንግሊዝ በሄዱበት ጊዜ አብረዋቸው የነበሩት ወልደጊዮርጊስ፣ ራሳቸውን በማስተማር ለንጉሱ ታማኝነታቸውን ያሳዩበት ሂደት ምን ይመስላል? በስተፍጻሜ ደግሞ ወልደጊዮርጊስ ከንጉሱ ጋር ተቀያይመው ግዞት የመላካቸው አሳዛኝ ሁነት እንዴት ተከሰተ? እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡ አንዱ ሌላውን የሚጥልበት  በሴራ የታገዘ የፖለቲካ ጥሎ  ማለፍ፣ በወልደጊዮርጊስም  ዘመን የታየ በመሆኑ  ያኔም ”ኮንስፓይረሲ ቲዮሪ” ወይም የሴራ ፖለቲካ ነበር እንዴ? ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርገን ነው፡፡ ልጃቸውን ቃለ-ምልልስ በማድረግ፣ በእርሳቸው ዙሪያ መጽሐፍ የደረሰ ሰውን በማነጋገር፣ ራሳቸው  ወልደጊዮርጊስ የጻፏቸውን ደብዳቤዎች በማጤን፣ ዘውድ ሳይደፉ የነገሱትን ወልደጊዮርጊስን ላሳያችሁ እሞክራለሁ፡፡
 እኒህ ሰው ትውልዳቸው አዲስ አበባ አራት ኪሎ፣ በተለምዶ ስሙ ‹‹አባታችን ሰፈር ›› ሲሆን፤ የልጅነት ዘመናቸውንም  በዚሁ አካባቢ ነበር ያሳለፉት፡፡ በእለተ ጊዮርጊስ ጥቅምት 23 ቀን 1893 ዓ.ም ወልደጊዮርጊስ ተወለዱ፡፡  በልጅነታቸው በጣም ቁጡ የነበሩ ሲሆን፤ ይህም ባህሪያቸው ከእናታቸው ጋር ይመሳሰላል የሚሉ አልጠፉም፡፡  
አባት አቶ ወልደዮሀንስ ናዳቸው በአንጻሩ ትእግስትን የተላበሱ ነበሩ፡፡  እናት ወይዘሮ ወደር የለሽ ልጃቸው ከቤተ ክርስቲያን ተጠግቶ በመንፈሳዊ ህይወት እንዲበረታ የዘወትር ምኞታቸው ነበር፡፡ በወቅቱ የሀገሪቱ የትምህርት ስርአት በአብነት ትምህርት ቤቶች ቅኝት የተሰራ ስለነበር፣ እናትም ልጃቸው ከዘመናዊ ትምህርት ይልቅ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቱ ውስጥ በቶሎ እንዲገባ ሰርክ ይጎተጉቱ ነበር፡፡
ገና በልጅነት የፈረንሳይኛ ቋንቋን ያዳበሩት ወልደጊዮርጊስ፤ በቋንቋ የልዩ ክህሎት ባለቤት ለመሆን የግል ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ በኋለኛው የሥራ ዘመናቸው ከንጉስ ቀጥሎ ወሳኝ ሰው ለመሆን የቻሉት ወልደጊዮርጊስ፤ ገና በልጅነት ለማደግ ያደርጉት የነበረው ታላቅ ጥረት ትልቅ ሰው እንደሚሆኑ ተስፋን ያመላከተ ነበር፡፡
የመሳፍንት ወገን፣ የመኳንንት ዘር፣ የጨዋና የደሀ ልጅ የሚል ክፍፍል በገነነበት ዘመን፣ ወልደጊዮርጊስ ግን ድምጻቸውን አጥፍተው፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለሟል ለመሆን ሌት ተቀን ይተጉ ነበር፡፡
ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ውስጥ ጎበዝ ከነበሩት መካከል ወልደጊዮርጊስ ይጠቀሳሉ፡፡ በ1912 ዓ.ም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ወልደጊዮርጊስ፤ በንግስት ዘውዲቱና በአልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ፈቃድ ሰኔ 4 ቀን 1912 ዓ.ም በጉምሩክ መስሪያ ቤት  ተቆጣጣሪ  ሆነው እንዲሰሩ ተመደቡ፡፡ ወጣቱ ወልደጊዮርጊስ ግን የጉምሩኩን ሥራ ፈጽሞ አልወደዱትም፡፡ በእርግጥ በንግስት ዘውዲቱ ዘመን  የጉምሩክ ባልደረባ መሆን እንደ ቀልድ የሚገኝ እድል አልነበረም፡፡
ደሞዙም ጠቀም ያለ ነበር፡፡ የ19 ዓመቱ ወልደጊርጊስ ግን እርካታን አስቀደመ፡፡ ከጉምሩክ  ሥራው ይበልጥ ከፈረንሳይኛ ቋንቋ ጋር በተያያዘ ቢሰሩ ደስታውን አይችሉትም ነበር፡፡ ትምህርታቸውንም ባህር ማዶ የመቀጠል ልዩ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ በዚያው አመት በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል  ውስጥ በአስተርጓሚነት ሥራቸውን ጀመሩ፡፡ በዚህ ሆስፒታል  ውስጥ ለመታከም ይመጡ የነበሩ  ባለሙያዎች ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ስለነበሩ ለወጣቱ ወልደጊዮርጊስ አመቺ እድል ተፈጠረላቸው፡፡ በወር 80 ብር እየተከፈላቸው  የአስተርጓሚነት ስራን ሲሰሩ፣ ከከፍያው ይልቅ ውስጣዊ ፍላጎታቸውን አረካው፡፡  በፈረንሳይኛ ችሎታቸው ብዙዎች ጥሩ ምስከርነት ይሰጧቸውም ነበር፡፡
የንጉሰ ነገስቱ አማካሪ በመሆን ከአሜሪካ የመጣው ጆን ስፔንሰር፣ ከወልደጊዮርጊስ ጋር በመጀመሪያ የተገናኘው ደሴ ላይ ነበር፡፡ እናም ‹‹ኢትዮጵያ አት ቤይ›› መጽሐፍ ላይ እንዲህ ሲል ገልጧቸዋል፡-
‹‹….. ለ12 አመታት ያህል በተለያዩ ኮሚቴዎች ውስጥ አብረን  በመሳተፍ ጠንካራ ውይይቶች አካሂደናል፡፡ ወልደጊዮርጊስን በተለይ የማስታውሰው በፈረንሳይኛ የንግግር ልዩ  ችሎታው ነው ›› ይህ እንግዲህ ከሆስፒታል የተነሳው ወጣቱ አስተርጓሚ፤ በአለም አቀፍ መድረኮችና ውይይቶች ላይ በፈረንሳይኛ ቋንቋ የነበረውን ችሎታ የሚነግረን ነው፡፡
ወልደጊዮርጊስ፣ በሆስፒታል ውስጥ ያሳዩት ቅልጥፍና  ወደ ቤተ መንግስት አስጠጋቸው፡፡  አንድ ቀን የወቅቱ የጉምሩክና የገቢዎች ባለስልጣን የበላይ ኃላፊ ክቡር አቶ መኮንን ሀብተወልድ፣ ህክምና ለመከታተል  ወደ ምኒሊክ ሆስፒታል ያቀናሉ፡፡ እዚያም ለማስተርጎም ላይ ታች ሲል በነበረው ወልደጊዮርጊስ ክህሎት ተደነቁ፡፡
 ”…ይህ አፍላ ወጣት በመንግሥት ሥራ ውስጥ ገብቶ ቢሰራ  የተሻለ ይሆናል” ሲሉ ክቡር አቶ መኮንን ሀብተወልድ፣ ወልደጊዮርጊስን ወደ ቤተ መንግስት ሥራ እንዲገባ አደረጉት፡፡ በዚህም አጋጣሚ የአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንንና የወልደጊዮርጊስ  ትውውቅ አንድ ብሎ ጀመረ፡፡ ወልደጊዮርጊስም በ20ዎቹ የመጀመሪያ እድሜ ላይ  የአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንንን  የትርጉም ሥራ ለማከናወን ከቤተ መንግስት ተሰየሙ፡፡
‹‹ዘውድ ያልደፋው ንጉስ የለውጥ ሀዋርያ›› የተሰኘውን በጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ ህይወት ላይ ያተኮረውን መጽሐፍ የጻፈው ደራሲ ደረጀ ተክሌ፤ ወልደጊዮርጊስ ከልጅነት ጀምሮ ለማደግ ሲያደርጉት የነበረው ልፋት ያስገርመዋል፡፡ ይህንን መጣጥፍ ለመጻፍ ስል ያነጋገርኩት ደረጀ እንዳጫወተኝ፤ ወልደጊዮርጊስ ያገኙትን እውቀት ወደ ሥራ ተርጉመው የመገኘት ብቃታቸው በፍጥነት  ከስኬት ማማ ላይ እንዲወጡ አድርጓቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ወልደጊዮርጊስ ገና በታዳጊነታቸው ከራስ ብሩ ጋር ፈረንሳይ ባቀኑበት ወቅት  ያነበቧት ባለ 100 ገጽ መጽሐፍ፣ ትልቅ ተጽእኖ እንዳሳደረችባቸው ደራሲ ደረጀ ያስረዳል፡፡ በፈረንሳይ ሳሉ  ያገኙት ዣን አዊኒ የሚባል ፈረንሳዊ  ስለ ወልደጊዮርጊስ ሲናገር፡-
‹‹…. ወልደጊዮርጊስ  የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ  ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አደረጃጀትና የዲፕሎማሲ አመራር  እንዴት እንደሆነ ለማወቅ  አጥብቆ ጠየቀኝ፡፡ በነበረኝ ኃላፊነት መሰረትየፈረንሳይን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በየዲፓርትመንቱ  እየተዘዋወረ ጥናት እንዲያደርግ ፈቀድኩለት፡፡ የዲፕሎማሲ ሀሁ የምትሰኝ 100 ገጽ የማትሞላ መጽሐፍም በማስታወሻነት አበረከትኩለት ፡፡ ያ ሰው ከብዙ አመት በኋላ ከፍተኛ ስልጣን ላይ ደርሶ ሳገኘው ተገረምኩ›› ብሏል፡፡
ራሳቸውን ለማስተማር  ሳይታክቱ የደከሙት ወልደጊዮርጊስ፤ ከጣሊያን ወረራ አስቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የክፍል ሹም፣ ቀጥሎም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ዋና ጸሀፊ ፤ በመጨረሻም የንጉሰ ነገስቱ ልዩ ጸሀፊና የጽህፈት ሚኒስቴር ዋና ዲሬክተር በመሆን አገልግለዋል፡፡ በንጉስ ኃይለስላሴ ዘመን አንድ ሰው አቅሙን ሳይቆጥብ ለንጉሱ ታማኝ ሆኖ  ካገለገለ፣ ለስኬታማነት እንደሚበቃ የእኚህ ታላቅ ሰው የሥራ ተሞክሮ ይነግረናል፡፡
ገና በ33 ዓመታቸው የንጉስ ኃይለስላሴ የጽህፈት ሚኒስቴር ዋና ዲሬክተር የሆኑት ወልደጊዮርጊስ፣ ስልጣን ያገኙት በደጅ ጥናትና በልመና ሳይሆን፣  ንጉሱ መርጠዋቸውና ችሎታቸውን ፈልገውት ነው፡፡ ጣሊያን በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን በግፍ በወረረ ጊዜ፣  ረዳኢ ንጉስ የሚል ስም የተሰጣቸው ወልደጊዮርጊስ፤ በውጊያ ሜዳ  ወደ  አዲስ አበባ በተደረገው ስልታዊ ማፈግፈግ በእውቀታቸው አማክረዋል፡፡
 እንደ ልጅ በመላላክ የንጉሱን ትእዛዝ ተፈጻሚ በማድረግ  አደራቸውን በሚገባ ተወጥተዋል፡፡ የንጉሱ የቅርብ ዘመድ ሳይሆኑ የአገሪቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ሁለተኛ ሰው ሆኑ፡፡ በስደት ዘመን ንጉስ ኃይለስላሴ ወደ ጄኔቫ ባቀኑ ጊዜ ወልደጊዮርጊስ የልኡካን ቡድኑ አባል ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ ጣሊያንን አሸንፋ የነጻነት አየር ሲገባ፣ ወልደጊዮርጊስ ከጠላት በኋላ ከተሾሙ ሰባት የካቢኔ ሚኒስትሮች አንዱ ነበሩ፡፡ በዚህ ወቅት የ40 አመት ጎልማሳ የነበሩት ባለሟሉ፤ ኢትዮጵያን በአዲስ የእድገት ጎዳና ላይ ለማራመድ መንገድ ቀያሽ ሆኑ፡፡ የጽህፈት ሚኒስትር ሆነው የንጉሱን ማህተም በመያዝ ፤ የቤተ መንግስቱን የክብር መዝገብ በክብር በማስቀመጥ ፣ የመንግስትን ውሎችና ስምምነቶች መልክ  በማስያዝ  የጸሀፌ ትእዛዝ ሚና ትልቅ ነበር፡፡ ጣሊያን የኢትዮጵያን ግዛት ለቆ ከወጣ በኋላ ወዳጅ መስሎ  እንግሊዝ ለዳግም ቅኝ ግዛት በቀረበን ጊዜ፣ ወልደጊዮርጊስ ለእንግሊዞች ፊት ባለመስጠት ለእናት አገራቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር አሳይተዋል፡፡ በዚህም እንግሊዞች ”ጸረ እንግሊዝ ነው“ እስከማለት ደርሰው ነበር፡፡
 ‹‹ዘውድ ያልደፋው ንጉስ›› የተሰኘው መጽሐፍ ላይ የጸሀፌ ትእዛዝ አገራዊ አበርክቶ በዝርዝር የቀረበ ሲሆን፤ በተለይ ዘመናዊ ትምህርት የተማሩ ሰዎች የስልጣን ቦታውን እንዲይዙ  ቆራጥ አመራር ሰጥተዋል፡፡  ለምሳሌ፡- እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ፤እንደ ከተማ ይፍሩ፣ እንደ አካለወርቅ ሀብተወልድ የመሳሰሉ  ሰዎች  ለዚህ በአብነትነት ይጠቀሳሉ፡፡
ተራማጅ የነበሩት ወልደጊዮርጊስ በጊዜ ሂደት በተለይ በ1947 ግድም ከወግ አጥባቂው የመሳፍንት ወገን ተቃውሞ በረታባቸው፡፡ ‹‹….ይህ ሰው በአገሪቱ በሁሉ ጉዳይ አድራጊ ፈጣሪ ሆነ ፡፡
 መፈንቅለ ጃንሆይ ማድረጉ አይቀርም›› የሚለው  ወሬ ንጉሱ ዘንድ እየተዋዛ መድረስ ጀመረ፡፡ በእርግጥም ወልደጊዮርጊስ ተሰሚነት ያላቸው፣ በየቦታው የራሳቸውን ሰው ያስቀመጡ፣ ንጉሱ ላይ ሂስ ለመሰንዘር ወደ ኋላ የማይሉ ሞገደኛ ሰው ሆነው ነበር፡፡
ይህን ሞገደኝነት እያዩ እንዳላዩ ማለፍ ለንጉሱም ሆነ ለወግ አጥባቂው የመሳፍንት ወገን የሚታገሱት አልነበረም፡፡ 30 አመት ከንጉስ ኃይለስላሴ  ጋር የደከሙት ወልደጊዮርጊስ፤  ከ1933 እስከ 1947 በጸሀፌ ትእዛዝነት የሰሩት ታላቅ ሰው፣ ከኃላፊነት ተነስተው ዝቅ ባለ ደረጃ የአሩሲ ጠቅላይ ግዛት ጠቅላይ ገዥ እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ ይህም ብዙዎችን አስደነገጠ፡፡ ግን ምንም ማድረግ አልተቻለም፡፡ የወልደጊዮርጊስ ደጋፊ የሆኑ አንዳንድ  ባለስልጣናት  በግዞት መልክ ከደረጃቸው ዝቅ እንዲሉ  ሽረት ሲደረግባቸው፣ በሌሎቹ ላይ ደግሞ አዳዲስ ሹመቶች ተሰጡ፡፡
አምባሳደር ዘውዴ ረታ የጻፉት “የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት” በሚለው መጽሐፍ ውስጥ እነማን ተሾሙ?   እነማን ተሻሩ? የሚለው በዝርዝር የቀረበ ሲሆን፤ አምባሳደር ዘውዴ ረታ ከጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ያደረጉት ቆይታም በመጽሐፉ  ውስጥ ተካትቶ ይገኛል፡፡አሩሲ በግዞት መልክ እንዲያስተዳድሩ እድል የተሰጣቸው ወልደጊዮርጊስ፤ ዋናው የግዞቱ ግብ ከንጉሱ ፊት ገለል እንዲሉ ለማድረግ ነበር፡፡  ከደረጃ ዝቅ ብሎ መሥራት ምን ያህል እንደሚያም የደረሰበት ብቻ  ነው ጠንቅቆ የሚያውቀው፡፡ ወልደጊዮርጊስ አሰላ ከሄዱም በኋላ  ሰላይ እየተላከባቸው ፈጽሞ አላሰራ ብለዋቸው ነበር፡፡ ለመሆኑ ወልደጊዮርጊስ አሰላ ሳሉ ምን አይነት ውሳኔዎችን ሲወስኑ ነበር ?  በሥራ መደባቸው ላይ ሆነው የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች ምን መልክ ነበራቸው?
ወልደጊዮርጊስ  ጠቅላይ ገዥ በሆኑ በሦስተኛ  ዓመቱ ነሐሴ 27 ቀን 1950 ዓ.ም  የጻፉት ደብዳቤ ብዙ እውነታዎችን የያዘ  ነበር፡፡  ያን ጊዜ ከቀድሞ ወዳጃቸው  ከክቡር አቶ መኮንን ሀብተወልድ  ጋር እንደ ሥራ መሪ የተለዋወጡት ደብዳቤ የሚከተለው ነው፡፡  ስካን የተደረገው ኦሪጅናል ደብዳቤ ከዚህ ጽሁፍ ጋር አብሮ የተያያዘ ስለሆነ ያነቡት ዘንድ እጋብዛለሁ፡፡
 ለክቡር አቶ መኮንን ሀብተወልድ
     ያገር ግዛት ሚኒስትር
ክቡር ሆይ፤  በአሩሲ  ጠቅላይ ግዛት ያለው ህዝብ  እህል አጥቶ ስለተራበ፤
1ኛ አሰላ ከተማ ካለው ህዝብ  የቀረበውን ማመልከቻ
2ኛ  ከዋናው መስሪያ ቤታችን ያሉት ሰራተኞች  ያቀረቡትን ማመልከቻ
3ኛ ከጠቅላይ ግዛቱ  በጅሮንድ ነሀሴ 1 ቀን 1950 በቁጥር 1124 ሀ/1/11  የተጻፈው ደብዳቤና ያባሪውንም ግልባጭ በድምሩ 6 ገጽ የሆነ ከዚሁ ጋር ልኬልዎታለሁ፡፡ በህዝቡና በሰራተኞች ላይ የደረሰውን ችግር ለማስታገስ እንዲቻልም መንግስት ለህዝብ ካስመጣው ዱቄትና እህል  አሰላ ከተማ ድረስ እንዲላክልን  በማክበር አሳስባለሁ፡፡
ከማክበር ሰላምታ ጋር
    ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሀንስ
   ፊርማ
ዘውድ ሳይደፉ የነገሱት ወልደጊዮርጊስ፤ የዛሬ 66 አመት ረሀብ በአሰላ ለመንገስ ባንዣበበበት ጊዜ ቀድሞ ለመድረስ የቀድሞ ወዳጃቸው ጋር ብእር ከወረቀት  አቆራኝተው ደብዳቤ ጻፉ፡፡ የዛሬውን መጣጥፍ በዚህ  ገታ ላድርግ፡፡ በመጪው ሳምንት ቀሪ ሀሳቦችን ከወልደጊዮርጊስ ደብዳቤዎችና ቀሪ ሰነዶች  ጋር አጠናክሬ እመለሳለሁ፡፡
***
ከአዘጋጁ
 ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የከዛሬ 20 ዓመት ገደማ፣ ”ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን”ን የመሰረተ ሲሆን፤ እስካሁንም በዚህ ድርጅቱ አማካኝነት የ44 ባለውለታዎችን ታሪክ በሲዲ፣ የ14 ሰዎችን ታሪክ በመጽሐፍ አዘጋጅቶ አቅርቧል፡፡
 በተጨማሪም የመጀመሪያውን የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ‹‹መዝገበ አእምሮ የሚድያ ሰዎች ታሪክን›› ያሳተመ ሲሆን፤ የመጽሐፍ፣ የሪል እስቴት፣ የሆቴልና ሌሎች ተቋማትን የምረቃና ክብረ በአል ስነስርአቶችን በማዘጋጀትም ይታወቃል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የ185 የኪነጥበብ ሰዎችን ታሪክ ለማሳተም በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1004 times