Monday, 11 March 2024 10:32

ያ ዕለት ይናፍቀኛል !

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“የዘመናት መድረክ ላይ ረዥሙን የታሪክ ጉዞ ተጉዘው ለሰው ልጆች ተስፋንና ጥበብን ይዘው ለትውልድ በመተላለፍ እንደ ውርስ የተሰጡ ቅርሶች መጻሕፍት ናቸው”  ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ።
ስለ መጻሕፍት፣ ስለ ንባብ አዲሱ ባህላችን  ላወጋችሁ ነው። መጻሕፍትን በመላው አገራችን አዳርሰው የንባብ ባህልን የህዝብ ቋሚ ባህል  ለማድረግ፣ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ  በአያሌው እየተንቀሳቀሰ ነው። በዚህም እንቅስቃሴው 337916  መጻሕፍትን፣ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለ590 ተቋማት ሰጥቷል። ተቋማቱ  ዩኒቨርሲቲዎች ፣ የህዝብ ቤተ መጻሕፍት፣ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ማረምያ ቤቶች ናቸው። መጻሕፍትም እንዴት መነበብ እንዳለባቸው ደራሲያንን ፣ ገጣሚያንን፣ የዩኒቨርስቲ መምህራንን በመጋበዝ፣ ለታዳሚዎች ልምዳቸውን እንዲያጋሩ ያደርጋል። በየክልሉ ለሚገኙ የህዝብ ቤተ መጻሕፍት ሰራተኞች ሙያዊ ስልጠና ይሰጣል። በመዲናችን ለሚገኙ መጻሕፍት ነጋዴዎች ትራንስፖርት በማመቻቸት፣ በተጋባዝዋ ከተማ የመጻሕፍት አውደ ርእይ ያዘጋጃል። በዚህም ከየከተሞቹ ባህል፣ ስፖርት ቢሮ ጋር በመቀናጀት ህዝብ አውደ ርእዩ ላይ እንዲሳተፍ ያደርጋል።
ኤጀንሲው ወሳኝ የሆኑ ዶክሜንቶችን ኦርጂናሌውን ፣ አልያም ፎቶ ኮፒዎች በማቅረብ የራሱን የዘመናት እንቅስቃሴዎች በአውደ ርእዩ ላይ ያቀርባል። በቅርቡ በአርባምንጭ ከታዩ ዶክሜንቶች መካከል አቶ ታደሰ ታቼ የተባሉ አርቆ አሳቢ ከ70 አመታት በፊት፣ በ1946 ዓ.ም በወቅቱ አገሪቱን ሲመራ ለነበረው መንግስት የጻፉት ደብዳቤ ለትእይንት ቀርቦ ነበር ፡፡ አቶ ታደሰ፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አምስት ፣ አምስት ብር ቢያዋጣ እንዴት የአባይን ወንዝ መገደብ እንደሚቻል ይገልጹና፣ እርሳቸው ይህንኑ መዋጮ በወር 5 ብር በአመት 200 ብር ለመለገስ ቃል ይገባሉ። ይህ ሃሳብ ይሆን ለእነ አቶ መለስ ዜናዊ፣ ከሰባ አመታት በኋላ የህዳሴውን ግድብ መሰረት ለመጣል ያስቻላቸው ? ስል አውጠንጥኛለሁ።
 እዚያው በጉባኤው ላይ የከተሞቹ ከፍተኛ ሀላፊዎች፣ ታዳሚዎች በተገኙበት ትዕይንቱ ይጎበኛል። የከተማዋ ነዋሪዎች ይታደማሉ። በዚህም የማንበብ ፍቅር ያላቸው በደስታ የፈለጉትንና ገበያው ያቀረበላቸውን መጻሕፍት ሲሸምቱ ይስተዋላሉ።  
በቅርቡ በአገራችን “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል!” የሚሉት ብሂል በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙሃን ይደመጣል። አባባሉ ሊያከራክር ቢችልም ከማንበብ የተሻለ ሰውን ሙሉ ሊያድርገው የሚችል ሙያ የለም ማለት እንችላለን። አዎን ልጆቻችንን ዩኒቨርስቲ ልከን የአንድ ሙያ ባለቤት ማድረግ እንችላለን። የህክምና ዶክተሮች ፣ ኢንጂነሮች ፣ ኢኮኖሚስቶች ወዘተ ማድረግ ይቻላል። ዓለምን በምልአት እንዲያዩዋት ግን መጻሕፍት ማንበብን ልንጨምርበት ይገባል። በዚህ ጉዳይ ላይ በእንድ ወቅት ከዶክተር ተወልደ ብርሃን ጋር ስንጨዋወት፤ “ማንኛውም ሰው የራሱ የእኔ የሚለው  ሙያ ሊኖረው ይገባል። በሙያው ላይ ዓለምን በምልአት ለማየት ታሪክንና ሥነ ጹሑፍን ሙያው ላይ ማከል አለበት። ይህንን ካደረገ ሥነ ጹሑፍ የወደፊቱን ሲያመላክቱት ፣ ታሪክ ደግሞ በሙያው ላይ ባለፈው ዘመን ምን እንደተሰራ ያሳውቁታል” ብሎኛል።
የኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍት እና ቤተ መዛግብት እንድታደም ጠርቶኝ በድሬዳዋ ፣ አርባምንጭ ፣ ወላይታ ሶዶ፣ዱራሜ እና ዲላ ከተሞች  ላይ ተገኝቼ፣ የመጻሕፍት ንባብ ልምዴን ለታዳሚው አጋርቻለሁ። በዚህም የሚገርመኝ አይነት ገጠመኞችም በህይወቴ ውስጥ ተከስተዋል። ከማስታውሰው አንዱ  ድሬዳዋ ማረሚያ ቤቶች ተገኝቼ ልምዴን ያጋራሁበት እለት ነው። በእለቱ አንድ ታራሚ በእርማቱ ወቅት ምን ማድረግ እንዳለበት፣ ጊዜውን እንዴት መጠቀም እንደሚገባው ካነበብኩት እንዳጋራ ጥናቴ  እዚህ ላይ እንዳተኩር አቶ ያሬድ ተፈራ ነገረኝ። አቶ ያሬድ፣ ከቤተ መዛግብቱ ከፍተኛ ሀላፊዎች መካከል አንዱ ነው። እኔም ህይወቱ በእስር ቤት 100% የተቀየረ አንባቢ የማስታውሰው ማልኮም ኤክስን ነው።(1925 - 1965)  ኤክስ ጥቁር አሜሪካዊ ነው፣ ትምህርቱን ከዝቅተኛ ክፍል ነው ያቋረጠው። ዘመኑ በፈጠረበት ተጽእኖ አስፈሪ ወመኔ ሆነ። አንድ በታደለበት ቀን እስር ቤት ገባ። ያቺ ቀን ዳግም ልደቱ ሆነች ፣ ያቺን እለት ቢያልፋት ኖሮ በቀጣዩ ቀን ሟች ነበር። ምክንያቱም አንድ ነጭ ሰውዬ ሚስቴን አባልጎብኛል ብሎ ሊገድለው እርሱ በታሰረ የእለቱ እለት ጠመንጃ ገዝቶ ነበር። ኤክስ በእለቱ በመታሰሩ ሟችና ገዳይ ሳይገናኙ ቀረ። ከዚያ በኋላ የማልኮም ኤክስ ህይወት በእስር ቤት በመጻሕፍት ንባብ ታንጻ መቶ በመቶ ተቀየረች። ይህንን ላወጋቸው እራሴን አዘጋጀሁ ፤ አንድ ቅር ያለኝ ነገር ይህ ታሪክ የአንድ ሩቅ አገር የሚገኝ ጥቁር ልጅ ታሪክ ቢሆንም፣ ለአበሻ ምናብ ይርቅ ይሆን?  እያልኩኝ በቅጡ አውጠነጠንኩ። እንደ መታደል የዚህ እለት የኢትዮጵያ ህዝባዊ ደሞክራሲያዊ ሪፕብሊክ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጓድ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ተጋባዥ ስለነበሩ ጎን ለጎን ስንቀመጥ፣ ከቁም እንቅልፌ ባነንኩ። ማውራት ያለብኝ ስለ ማልኮም ኤክስ ሳይሆን ስለ ጓድ  ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ነው አልኩኝ። ልብ አድርጉልኝ፤ እኒህ ሰው በኢህዲሪ ዘመን ከፍተኛ ባለሥልጣን ነበሩ። ስርአቱ ሲፈርስ በእነ መንግስቱ ኃይለማሪያም ፋይል በተመሰረተባቸው ክስ የመጀመሪያ ተከሳሽ ናቸው። የክስ ሂደቱን እንደማስታውሰው  ሞት ተፈረደባቸው ፣ በሂደት ወደ ዕድሜ ይፍታህ ተቃለለላቸው፡፡ ከሁለት አስርት አመታት በኋላ በምህረት ተለቀቁ። ይህንን የመሰለ ጮማ ወሬ እንደዋዛ ካለፍኩት ድንቅ የመድረክ ሰው አይደለም አልኩት ለራሴ። አቶ ያሬድንም ሆነ ጓድ ፍቅረ ሥላሴን ሳላስፈቅድ ለታራሚው እጥር ምጥን ያለች አይን ገላጭ ንግግር አደረኩ። ንግግሬን ስቋጭ ሞቅ ያለ ጭብጨባ ተከተልኝ።
አልዋሽም፤ የጓድ ፍቅረ ሥላሴ ጽናታቸውን ከልብ አደንቃለሁ። ፌዎዶር  ዶስቶዬቭስኪ የተባለ አንጋፋ ሩሲያዊ ደራሲ፣ ደራሲ ለመሆን ለሚሹ ወገኖች ተጠይቆ ሲናገር፤ “ሞት ይፈረድብህ፤ በዚህ ስትጨነቅ በእድሜ ይፍታህ ይቃለልልህ ፣ ይህም ሲያስጨንቅህ በነፃ  ትለቀቃለህ፤ የዚያን ጊዜ ደራሲ ትሆናለህ” ይላል። ይህንን መራር  መንገድ ጓድ ፍቅረ ሥላሴ በጽናት ሲያልፉበት ባይ ነው ማድነቄ። ከዚያ በኋላ በእኔ እና በፍቅረ ሥላሴ መካከል ወዳጅነታችን ስር ሰዶ አዲስ አበባ ተገናኝተን መጻሕፍት ተቻችረናል። አገር ውስጥ እስካሁን ያልተነበበው መጽሐፋቸው ፤”እኔና አብዮቱ” እጄ ላይ አለ። ሌሎች የተጠናቀቁ ሥራዎች እንዳላቸው አውግተውኛል።  አንድ ቀን ያነበብኩላቸውን እዳስሰዋለሁ።
እንዲህ እይነቱ ጉዞ በተጋባዥ እንግዶች የሚወደድ ነው። እኔ ከተጋበዝኩ ስለምጓጓ እነማን አብረውን እንደሚጓዙ አስቀድሜ እጠይቃለሁ። አንዳንዴ የተነፋፈቅን ወዳጆች የምንገናኝበት ጊዜ አለ። አዲስ አበባ እንደሁ የምታገናኘን ቀብር ላይ ነው። “ተዋናይ እገሌ አረፈ!” ከተባለ ቀብር ላይ እንገናኛለን።
 ስለዚህ በህይወት ተገናኝቶ  እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ላይ መገናኘት  በጣም ተወዳጅ ነው።
የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ጽሁፍ መምህር የነበረው መሰረት አበጀ፣ ዲላ እንግዳ ሆነን ሄደን የሆድ የሆዳችንን ስንጨዋወት፣ የካቲት ወር የተወለደበት ቀን እንደሆን ነገረን። የሚገርመው ወጣቶቹ ይህንን መረጃ ወደ ተግባር ቀይረው ምሽቱን 60ኛ ዓመት የልደት በዓሉን አከበርንለት። እርሱም በወጣቶቹ ድርጊት ልቡ ተነክቶ  ይህንን የመከባበርና የመዋደድ ባህልን  መጪው ትውልድ ላይ ማስታዋሉ እንዳስደሰትው አወጋን።
ዲላ ዩኒቨርስቲ ለወጣቶች የንባብ ልምዱን ሲያጋራ፣ የመግለጽ አቅሙ፣ የመመሰጥ ባህሪው ፣ ልክ እንደ ተዋጣላት ተዋናይ መድረክ ጠቦት ያደረገው ገላጻ ግሩም ነበር፡፡ ከእኔ ጋር በግል ስንጨዋወት፤ “ይህ የኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍት እና ቤተ መዛግብት የሚሰራው ሥራ እጅግ የሚያስመሰግነው ነው። ቢያድለን ይህንን ተግባር መከወን ያለባቸው ትምህርት ሚኒስቴር እና ዩኒቨርስቲዎቹ ነበሩ፡፡ አልሆነም። አሁን ልብ ብዬ ሳስተውል ማንበብ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሞቷል። ኤጀንሲው ለመጻሕፍት ንባብ ዳግማዊ ትንሳኤ እያደረገለት  ነው። ደሞ እየተዋጣላቸው ነው። ታያለህ፤ ህዝቡ ተማሪው በታላቅ ፍቅር ሲቀበላቸው?! ሥራውም ግዴታቸውም ነው።እነርሱም ደስ ብሏቸው እየተወጡት ነው” ያለኝን አልዘነጋውም። መምህር መሰረት አበጀ ዘንድሮ የ62 ዓመት ጎልማሳ ነው ።
ለዲላ ከተማ ነዋሪዎች ንግግር እንዳደርግ የተመረጥኩት እኔ ነበርኩ። የጌዲዮ ህዝብ ከምግብ ሥጋ እንደሚወድ አውቃለሁ። በርካታ አዝናኝ ቀልዶች ተነግረውበታል፡፡ የተወሰኑትን አውቃቸዋለሁ። በነገራችን ላይ ሥጋ መብላት በመላው ህዝባችን እንደሚወደድ አውቃለሁ። የጌዲዮ ከሁላችንም ይልቃል ለማለት ነው። የቆየ ቢሆንም አንድ ጥናት ሲገልጽ፤ አመታዊ ፍጆታችን 6% ነው።አምሮታችን 94% መሆኑ ነው። በአለማችን ከፍተኛ ሥጋ ተመጋቢ ህዝብ፣ የቻይና ህዝብ ነው። የአመት ፍጆታቸው 60% ነው።
ወደ ጌዲዮ እንመለስ፡፡ አንዷን ቀልድ እነሆ። ዲላ ከተማ ውስጥ  ከሰአት በኋላ ሙቀት ያይላል። አንዱ  ብልሁ አስተማሪ ጥቁር ሰሌዳው ላይ በቅጡ የተቀለበ ሰንጋ ሳለ እና አንዴ በደንብ አጨብጭቦ ተማሪዎቹ ትኩረት እንደሰጡት፤ “ልጆች ከሻኛ ላይ ልቁረጥ? ወይንስ ከሽንጥ ላይ ?!” አሉዋቸው።
ልጆቹን በታላቅ ጉጉት፣ የአምሮት ምራቅ አፋቸውን እየሞላው፤ “ ከሻኛ ቁረጥ ፣ ከሽንጥ ቁረጥ ! “ እያሉ እንደ ምርጫቸው ተንጫጩ ። መምህሩም ተማሪዎች እስኪነቁ እንጫጩዋቸው። ከልብ መንቃታቸውን ካስተዋሉ በኋላ ወደ እለታዊ ትምህርት ገቡ። እኔም ወጌን በስጋ ወግ አሟሟቅሁት። ወዳጆቼም ሆኑ የቤተ መዛግብቱ ሀላፊዎች፣ ታዳሚው ህዝብ  “ምን ሊያወራ ነው ?” በሚል ስሜት ተደንቀው ሲከታተሉኝ አስታውሳለሁ። እኔም ሥጋ በበላ አንጀት ትንሽ መጻሕፍት ማንበቡ፣ አስተዋይና አርቆ አሳቢ እንደሚያደርግ፣ ጭብጤን ሳስይዝ፣ ሞቅ ያለ የጭብጨባ ሽልማት ተቸረኝ፡፡
ድሬዳዋ ፣እርባምንጭ፣ ጬንቻና ዲላ ማረሚያ ቤቶች የተለያዩ ገጠመኞች አሉን። የዲላው ልብ የሚነካ ነበር። የማረሚያ ቤቱ ከፍተኛ ሀላፊ ኮማንደር እንስት ናቸው። በሁለት ነገር አስታውሳቸዋለሁ። አንደኛ ከልክ በላይ ግዙፍ ቁመናቸው ሲሆን ፣ ሁለተኛው ልብ የሚነካው ንግግራቸው ትውስ ይለኛል፡፡ “ማረሚያ ቤታችንን የእውነት ማረሚያ እንዲሆን መጥታችሁ አስተዋፅኦ ስላደረጋችሁልን ከልብ አመሰግናለሁ። ሌሎች አካላት ህግን ከማስከበር ውጪ እንዴት ሊያስቡን አልቻሉም ? እናንተ በራሳችሁ ፍቃድ  ስላሰባችሁን ከልብ! ከልብ! እናመሰግናችኋለን !” አሉ ፤ትክዝ ብለው።የጬንቻው ማረሚያ ቤት የሚደንቅ ነው። እንግዳ አቀባበሉን ብሔራዊ በአል ነበር ያደረጉት።ታራሚዎቹ የክት ልብሳቸውን ለብሰው  ደማቅና ውብ በሆነ ስሜት፤ “እንኳን ደህና መጣችሁ!”ብለው ተቀበሉን። በቆይታ አስተዳደሩም በአገር አቀፍ ደረጃ የተሸለመ የማረሚያ ቤቶቻችን አምባሳደር እንደሆነ ተገንዝበናል፡፡ ረዳት ኮሚሽነር አጥናፉ አሰፋ ቦቃ ለማንም የማይከብዱ ድንቅ መኮንን ናቸው። ከባልደረቦቻቸው ጋር ባደረጉት ድንቅ አመራር፣ ጬንቻ ማረሚያ ተቋም የድንቅ ዜጎች መፈጠሪያ ማእከል አድረገውታል። አብረውኝ ከተጓዙ ጓደኞቼ ጋር ስንጨዋወት፤ “ይህ ማረሚያ ቤት ጬንቻ እንደ እንዱ የቱሪስት መስህብ ልትጠቀምበት ይገባል“ ማለታቸውን አስታውሳለሁ። በርግጥም የሚጎበኝ ተቋም ነው።ጬንቻ የታዋቂው ፖለቲከኛና ደራሲ አሰፋ ጫቦ የትውልድ ስፍራ ነች። አሰፋ በአንደበቱ ም በብእሩም አንስቶ አይጠግባትም። ይህንን የሚያውቁት የፖለቲካ ተጻራሪዎቹ፣ ጬንቻን በዘመኑ ከጣሩት ልማት ተቋዳሽ ሳያደርጓት አለፉ። የማጣጣል ብእር ተስፋዬ ገብረአብም፣ በጬንቻ ላይ መዞባታል። የሚገርመው አሰፋም አርፎ የፖለቲካ ድርጅትም ታሪክ ከሆነ በኋላ፣ ዘንድሮ ተነቃቅታ በዘመንዋ የአስፓልት መንገድ ለመስራት ተፍተፍ ስትል አስተዋልኳት። የመንግስትም ሆነ የግል ባንኮች ተከትፈውባት፣ ሞቅ ደመቅ እያለች ነው። “አንድን የስድስት አመት ህጻን ያሰብከውን ጉዳይ ለማብራራት ካልቻልክ  ጉዳዩን አንተም አላወቅኸውም “ ይላል አልበርታይን አነስታይን። ንባብን ለመጀመሪ ደረጃ ተማሪዎች በጣም አቅልለን ማቅረብ። ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ትንሽ ከፍ አድርጎ መግለጽ ፣ ጥልቀቱን ጨምሮ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማውሳት በሂደት እየበሰልንበት መጣን ።
መሥሪያ ቤቱ የሁሉንም ደራሲዎች ሥራ ሸምቶ፣ ተረታ ተረቱን ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ፣ የጠቅላላ እውቀቱን ለመምህራኑ ሸምቶ ሰጥቷል። ለሁለተኛ ደረጃና ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከልብ ወለዱም፣ ከግጥሙም  ከፍልስፍናውም  እያደረገ ሲለግስ የአይን ምስክሮች ነን።
ሌላው አስተዋጽኦ ለገጠር ቤተ መጻሕፍት የሚያደርገው ልግስና የሚደነቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ጋሞ ውስጥ ኤዞ በተባለ ገጠር ውስጥ በዶክተር ታደሰ ወልዴ ስም በተሰየመው ቤተ መጻሕፍት ምረቃ ላይ ተገኝቼ በጉዳዩ ላይ ከእንድ ወዳጄ ጋር ስናወጋ፤ “በህይወት ዘመናቸው መጽሐፍ ምን እንደሆን አይተው የማያውቁ ወገኖቻችን እንዳሉ ታውቃለህ ?!” ሲል ያነሳልኝ ጥያቄ የማልዘነጋው ነው። ከአመታት በፊት ገጠር ውስጥ አንድ ማለዳ እለት መደብ ላይ ጋደም ብዬ አንድ መጽሐፍ አነባለሁ ። ይህንን ልብ ብላ ታስተውል የነበረች አዛውንቷ አክስቴ፣ ወ/ሮ ወዘንቴ ወጋ፤ “ ምንድነው የያዝከው ?” አለቺኝ። መጽሐፍ እንደሆነ ነገርኳት። መጽሐፍ ምን እንደሆነ ጠየቀችኝ ፤ዝግ ባለ ሁኔታ መጽሐፍ ምን እንደሆነ አስረዳኋትና ከልብ ተደነቀች ። በወቅቱ 100 አመት ይሞላት ነበር ። በዚህ አንድ ምእተ ዓመት ባስቆጠረ እድሜዋ፣ መጽሐፍ ስትመለከት ይህ  የመጀመሪያዋ ነበር።
በዚህ ነው የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት ጥበቡን አይቶ የማያውቅ እንዲያውቀው ፣ ያወቀው ከህጻናት እስከ አዋቂው  እንዲፈትሽና ውስጡን እንዲያይ የሚያደርገውን ጥረት ይበል ልለው የወደደድኩት፡፡
ይህ ከላይ በቁጥር ያሰፈርኩት መረጃ ኤጀንሲው ከ2011 ዓ.ም እስከ 2015 ዓ.ም ያከናወነው ሲሆን፤ 2016 ዓ.ም የመጀመሪያ መንፈቅ አመት ተካቶበታል፡፡ ኤጀንሲው 82 ዓመታት ባስቆጠረ የስራ ልምዱ፣ አገልግሎቱ በአዲስ አበባና አካባቢው ነበር። ባለፉት አምስት አመታት በኢትዮጵያ ቆዳ ስፋት ልክ ባደረገው ጥረት፤ “ የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንዲሉት እየሆነ ነው።
ተቋሙ፤የኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍት እና ቤተ መዛግብት ወመዘክር በሚል ስያሜ በ1934 ዓም የተመሰረተ ነው። ወደ ኋላ ሄዶ በማንበብ ባህሪዬ እንደመረመርኩት፤ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለወመዘክር የተለያዩ መንግስታትም ሆነ ትቋማት መጻሕፍት በልግስና ሲቸሩ፣ ንጉሰ ነገስቱ በአካል ተገኝተው መቀበላቸውን ማንበቤን አስታውሳለሁ። በዚህም በበርካታ የዓለም ቋንቋዎች አያሌ የመጻሕፍት ክምችት እንደሚኖረው እገምታለሁ። እራሳቸው አፄ ኃይለ ሥላሴ በቤተ መጻሕፍቱ በመገኘት እንደሚያነቡና በወቅቱ ከነበሩ ምሁራን ጋር በነጻነት ሲወያዩ ማየቱን ወዳጄ ኃይለ መለኮት መዋዕል አጫውቶኛል። ይህ ታላቅ የጥበብ ቤት ሲጠራኝ  በታላቅ ደስታ ነው  ከጎናቸው  የምቆመው። ይህን የተቀደሰ እንቅስቃሴያቸውን አብዝቼ ስለምወደውም  የሚጠሩኝን  ቀን እናፍቃለሁ፡፡
***
ከአዘጋጁ፡-
 ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ከ6 በላይ መጻሕፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡ ከጥበባዊና ወጋዊ ጸሃፊነቱ ባሻገርም የህይወት ታሪኮችን (ባዮግራፊስ) በመጻፍም ይታወቃል፡፡ ዘነበ ወላ አርታኢም ነው፡፡ ደራሲውን በኢሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 755 times