Saturday, 09 March 2024 20:30

በ44ኛው የለንደን ማራቶን

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

44ኛው የለንደን ማራቶን ከ42 ቀናት በኋላ የሚካሄድ ሲሆን፤ በሁለቱም ፆታዎች  የዓለማችንን ፈጣን ሯጮችን ማሳተፉ ልዮ ትኩረት ስቧል። ከዋናው የአትሌቶች ውድድር ባሻገር ከ578 ሺ በላይ ተሳታፊዎች ማመልከታቸው በውድድሩ ታሪክ አዲስ ሪከርድ ሆኖ ተመዝግቧል። ለተሳትፎ ካመለከቱት መካከል 50,000 ያህሉ በልዮ እጣ ተመርጠው የመሮጥ እድል እንደሚያገኙ ታውቋል። የለንደን ማራቶን በኒውካስል ከሚደረገው “ግሬት ኖርዝራን” ቀጥሎ በተሳታፊዎች ብዛትና በአጠቃላይ ግዝፈቱ ይጠቀሳል። የማራቶን ውድድሩ በዓለማችን ትልልቅ ከተሞች  ከሚከናወኑ 6 ግዙፍ ማራቶኖች አንዱ ሲሆን በለንደን ጎዳናዎች ከ750ሺ በላይ ተመልካቾች የሚያገኝ ነው። ማራቶኑ በ2020፤ በ2021 እና በ2022 እኤአ ላይ በኮቪድ ወወረርሽኝ ሳቢያ በጥምቀት/ኦክቶበር ላይ ተዘጋጅቶ ነበር። ከ2023 እኤአ ወዲህ ግን ወደ መደበኛው የማካሄጃ ቀን ሚያዚያ/አፕሪል ላይ የተመለሰ  ሲሆን በዚህ ወቅት የለንደን ከተማ የአየር ንብረት ተስማሚ መሆኑ ፈጣን ሰዓቶች የመመዝገባቸውን እድል ያጠናክረዋል።
በ44ኛው የለንደን ማራቶን ላይ የኢትዮጵያ ፈጣን ማራቶኒስቶች በብዛት መሳተፋቸው ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል። በተለይ በሴቶች  የዓለም ማራቶን ሪከርድን በ2:11:53 በሆነ ጊዜ ያስመዘገበችው ትግስት አሰፋ፤ እንዲሁም በወንዶች ደግሞ በማራቶን 3ኛውን የምንግዜም ፈጣን ሰዓት በ2:01:41 ያስመዘገበው ቀነኒሳ በቀለ ዋናዎቹ የመነጋገሪያ አአጀንዳዎች ናቸው።
የለንደን ማራቶን ዋና ዲያሬክተር ሁግ ብራሸር  ሲናገሩ “ በሴቶች ማራቶን ወርቃማው ዘመን ላይ እንገኛለን። በ2003 እኤአ ፓውላ ራድክሊፍ በ2:15:23 የዓለምን ሪከርድ በወንድ አሯሯጮች በመታገዝ በለንደን ማራቶን ማስመዝገቧ ይታወሳል። ከ16 ዓመታት በኋላ ደግሞ ኬንያዊቷ ማሪ ኪታኒ በሴት አቋቋጮች በመታገዝ ሌላ የዓለም ክብረወሰን ተመዝግለታል። ባለፉት 3 ዓመታት ደግሞ  በሴቶች ማራቶን 4 ፈጣን ሰዓቶች ተመዝግብዋል።  አሯሯጮች በመታገዝ የተገኙ ናቸው። ዘንድሮ በተለይ በሴት አሯሯጮች በመታገዝ ብቻ አዲስ የዓለም ሪከርድ መመዝገቡን እንጠብቃለን” ብለዋል። በሴት አሯሯጮች  በ2017 እኤአ ላይ በኬንያዊቷ ማሪ ኪታኒ የተመዘገበው የዓለም ክብረወሰን 2:17:01 ነው። የለንደን ማራቶን አዘጋጆች ዘንድሮ ይህን ሪከርድ እንደሚሻሻል ተስፋ አድርገዋል።
ታዋቂ የአትሌቲክስ ሚዲያዎች እነ ሐጂ አዴሎ፣ ሁሴን ሸቦ፣ ገመዶ ደደፎ አይነት አሰልጣኞችን Super coach እያሉ ያደንቋቸዋል። በኦሎምፒክ በዓለም ሻምፒዮና በትልልቅ ማራቶኖች ያስመዘግቧቸውን የላቁ ውጤቶች በመንተራስ ነው። በዴሞዴና አትሌቲክስ  ፕሮሞሽን በአትሌቶች አሰልጣኝነትና በማናጀርነት የሚሰራው ገመዶ በማራቶን የዓለም ሻምፒዮን፤ የዓለም ሪከርድ ባለቤትና የዓለም ኮከብ አትሌት፤ በታላላቅ ማራቶኖች ያሸነፉ አትሌቶች የያዘ ቢሆንም “ሱፕር ኮች” ለመባል ገና ብዙ ይቀረኛል ይላል።
አሰልጣኝ ገመዶ በለንደን ማራቶን ላይ የዓለም ሪከርድ ባለቤትና ኮከብ አትሌት ትግስት አሰፋ፤ የዱባይ ማራቶን አሸናፊዋን ትግስት ከተማ እና የኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊውን ታምራት ቶላ ያሰልፋል።
አሰልጣኝ ገመዶ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው በሴቶች ማራቶን ላይ ሁለት አይነት የዓለም ሪከርዶች ይመዘገባሉ። ሁለቱም እኩል እውቅናና ክብር ይሰጣቸዋል። የዓለም ኮከብ የማራቶን አትሌት ትግስት አሰፋ በ2023 እኤአ በበርሊን ማራቶን ያስመዘገበችው 2:11:53 የዓለም ሪከርድ ውድድሩ ሲጀመር ሴቶችም ወንዶችም እኩል የሚነሱበት ነው። ወንድ አሯሯጭም ተመድበውበታል። በሌላ በኩል ደግሞ Women Only በሴቶች ብቻ የሚካሄድም የማራቶን ሪከርድ አመዘጋገብ ያለ ሲሆን፤ ውድድር ሲጀመር ሴቶች ለብቻ የሚነሱበትና አሯሯጮችም ሴቶች የሆኑበት ነው።
የማራቶን አሰልጣኝ ገመዶ ለስፖርት አድማስ በለንደን ዙሪያ አስተያየት ሲሰጥ
“በሴቶች ብቻ Women only የተመዘገበው ሰዓት ከትግስት አሰፋ ሪከርድ ጋር ሲነፃፀር እጅግ የተራራቀ ነው። ዘንድሮ ለንደን ላይ ብቁ ሴት አሯሯጮች ከተሳተፉና አየሩ ጥሩ ከሆነ 2 ሰዓት ከ17 ደቂቃዎች የተባለው ሰዓት ሊሻሻል ይችላል። በእኛ በኩል በወንድ አሯሯጮች  ከሚመዘገበው ሪከርድ ይሄኛው እንደሚቀል ነው የምናምነው። ለንደን ላይ ተወዳዳሪዎቹ በጣም ጠንካሮች ናቸው። ምንም የትግስትን ያህል 2:11 ባይኖራቸውም ጥሩ ስምና ሰዓት ያላቸው አትሌቶች ተሳታፊ ናቸው። ስለዚህ በቀላሉ አሸንፋለሁ እንዲህ አደርጋለሁ የምትልበት አይደለም።” በማለት ያስረዳል።
“የዓለም ሪከርድ ስትሞክር አዕምሮህ ንፁህ ሆኖ፤ ብዙም ተፎካካሪ ሳይኖርበት ነው። ለንደን ላይ የመጀመሪያው ዋናው ትኩረት ማሸነፍና በትልቅ ማራቶን ክብር ማግኘት ነው። የዓለም ሪከርድን ማሻሻል ከዚያ በኋላ የሚመጣ ነው። አሁን ለምሳሌ በርሊን ላይ ከመነሻው የእኛ ዓላማ የነበረው የዓለም ሪከርድን ለማስመዝገብ ነበር። ስለዚህም በተቻለ መጠን በሴቶች አሯሯጮች ብቻ የተመዘገበውን ክብረወሰን እንሞክረዋለን በሚል ነው ከለንደን ማራቶን አዘጋጆች ጋር የተነጋገርነው። የመጀመሪያው ሙከራችን ማሸነፍ ነው። እንደ ለንደን አይነት ማራቶኖችን ማሸነፍ በራሱ ትልቅ ክብር ነው። በትልልቅ ከተሞች የሚካሄዱ ማራቶኖችን ማሸነፍ ብዙ ተመልካችና በሚዲያዎች ትልቅ ትኩረት ያስገኛል።” ይላል አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎ።
በሴቶች ምድብ ከሚሰለፉት መካከል 10 አትሌቶች ከ2 ሰዓት 18 ደቂቃዎች በታች ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡ መሆናቸው በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። የዓለም ማራቶንን ሪከርድ የያዘችው ትግስት አሰፋ ከፍተኛ ግምት ቢሰጣትም ሌሎቹ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶችም ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ተጠብቋል። ከኢትዮጵያ በ2022 ለንደን ማራቶን ያሸነፈችውና በዓለም ሻምፒዮና 5ኛ የነበረችው ያለምዘርፍ የኋላው፤ በቫሌንሽያ ማራቶን ሁለተኛ የነበረችው አልማዝ አያና፤ ባለፈው ዓመት በለንደን ማራቶን ሁለተኛ የነበረችውና ቺካጎ ላይ ሶስተኛ የወጣችው መገርቱ አለሙ፤ የዱባይ ማራቶን አሸናፊዋ ትግስት ከተማ እና ፅጌ ሐይለስላሴ ናቸው። ከኬንያ ደግሞ በ2021 የለንደን ማራቶን አሸናፊ የኒውዮርክ ማራቶን ላይ አራተኛ እንዲሁም የአቡዳቢ ማራቶንን ያሸነፈችው ብርጊድ ኮሴጊ፤ በቺካጎ ማራቶን በ2021 እና በ2022  ያሸነፈችው ሩት ቼፕጌቲች፤ በ2022 የቦስተን ማራቶንን ያሸነፈው ፔረስ ጄፕቸሪርና ጆይስሊን ጆፕኬሲጊ  ይጠቀሳሉ።
በወንዶች ምድብ ከ2 ሰዓት 4 ደቂቃዎች በታች የሚገቡ 6 እንዲሁም ከ2 ሰዓት 5 ደቂቃዎች በታች  የገቡ 10 አትሌቶች ይወዳደራሉ።  አትሌት ቀነኒሳ በ2:01:41 የግሉ ፈጣን ሰዓት የሚጠቀስ ሲሆን በቫሌንሽያ ማራቶን ሲያሸንፍ ያስመዘገበው 2:04:19 ለንደን ላይ በማሻሻል ለፓሪስ ኦሎምፒክ ትኬቱን ለመቁረጥ አነጣጥሯል። ሌሎች የኢትዮጵያ ጠንካራ የማራቶን ሯጮች የኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊው ታምራት ቶላ፤ ዳዊት ወልዴ፤ ክንዴ አጥናው፤ በዓለም ሻምፒዮና የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ልዑል ገብረስላሴ ፤ ሰይፉ ቱራ፤ አዲሱ ጎበናና ሚልኬሳ መንገሻ  ናቸው። የኬንያዎቹ አሌክሳንደር ሙቴሶና ጂዮፍሪ ኪምዎሩር የብራዚሉ ዳንኤል ዶናሺሜንቶ የኤርትራ አትሌቶችም ተጠቅሰዋል።
ከዓለማችን ታላላቅ ማራቶኖች የለንደን ማራቶንን ልዩ የሚያደርገው  በፈጣን ሰዓት፤ በቦታው ሪከርድና በዓለም ሪከርድ ዙርያ ለሚመዘገቡ ምርጥ ሰዓቶች ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ በማቅረቡ ነው፡፡ በሁለቱም ፆታዎች ቀዳሚ ሆነው ለሚገቡት አትሌቶች 44ሺ ፓውንድ በነፍስ ወከፍ እንደሚሸለም ሲታወቅ ፤ ለሁለተኛ 24 ሺ፤ ለሶስተኛ 18ሺ እንዲሁም ለ4ኛ 12ሺ ፓውንድ የሚታሰብ ይሆናል። ለቦታው ሪከርድ 19500 ፓውንድ እንዲሁም ለዓለም የማራቶን ሪከርድ እስከ 98ሺ ፓውንድ  መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡ የውድድሩ አዘጋጆች እንዳስታወቁት በተለይ በሁለቱም ፆታዎች ለምርጥና ፈጣን ሰዓቶች ከፍተኛ የቦነስ ክፍያዎች መዘጋጀቱ ነው። ይህም የዓለም ማራቶን ሪከርድ የሚሻሻልበትን እድል ሊያሰፋው ይችላል፡፡
በወንዶች ምድብ  ከ2 ሰዓት 2 ደቂቃዎች በታች 120ሺ፤ ከ 2 ሰዓት 3 ደቂቃዎች በታች 80ሺ ፓውንድ፤ ከ 2 ሰዓት 4 ደቂቃዎች በታች ለሚገቡ 60ሺ ፓውንድ እንዲሁም ከ2 ሰዓት 5 ደቂቃዎች በታች ለሚገቡ 50ሺ ፓውንድ የሚከፋፈል ይሆናል። በሴቶች ምድብ ደግሞ  ከ2 ሰዓት 17:30 ደቂቃዎች በታች 120ሺ፤ ከ 2 ሰዓት 18 ደቂቃዎች በታች 80ሺ ፓውንድ፤ ከ 2 ሰዓት 19 ደቂቃዎች በታች ለሚገቡ 60 ሺ እንዲሁም ከ2ሰዓት 20 ደቂቃዎች በታች ለሚገቡ 50ሺ ፓውንድ የሚከፋፈል ይሆናል።
ባለፉት 43 የለንደን ማራቶኖች ላይ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበችው ኬንያ በሁለቱም ፆታዎች 31 አሸናፊዎች 17 ጊዜ በወንዶች እንዲሁም 14 ጊዜ በሴቶች ምድብ በማስመዝገብ ነው። ዮናይትድ ኪንግደም 13 አሸናፊዎች 6 ጊዜ በወንዶች እንዲሁም 7 ጊዜ በሴቶች በማግኘት ትከተላለች።
የኢትዮጵያ አትሌቶች ደግሞ በሁለቱም ፆታዎች 9 ጊዜ 5 ጊዜ በወንዶች እንዲሁም 4 ጊዜ በሴቶች በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ናቸው። በወንዶች በ2003 እኤአ ገዛሐኝ አበራ፤ በ2010 እና በ2013 ፀጋዬ ከበደ ፤ በ2020  እኤአ ሹራ ኪታታ እንዲሁም በ2021 እኤአ ላይ ሲሳይ ለማ ናቸው። በሴቶች ደግሞ በ2001 ደራርቱ ቱሉ፤ በ2010 አሰለፈች መርጊያ እና በ2015 እኤአ  ትግስት ቱፋ አንዲሁም በ2022 እኤአ ያለምዘርፍ የኋላው አሸናፊዎች ሆነዋል።

Read 384 times