Saturday, 02 March 2024 21:07

የዐድዋ ጉራማይሌ ቀለሞች

Written by  -ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

አንዳንድ ብርቅዬ ሁነቶች፣በየዐረፍተ ዘመን አንጓ የተደረደሩ፣ እንደየመልካቸው አድማሳት ተሻግረው፣ከነቃናቸው  ዕድሜ ይቆጥራሉ፤እንደየቆሙበት ምሰሶና እንደረገጡት እውነት ጥንካሬና ልልነት ደግሞ ዘለቄታቸው ይወሰናል።
ጠለቅ ብለን ስናየው፣ሀገር የታሪክ መሠረት፣ሰዎች ደግሞ የታሪክ ብዕር ናቸው። አንዳንዴ ላብ፣ሌላ ጊዜ ደግሞ ደም አጥቅሰው በዘመን ገጾች ላይ ይጽፋሉ። ሕይወትም በራሷ እንደ ሰንሰለት የተቀጣጠለች ብትሆንም፤ በየአጽቁ ላይ በየምዕራፋቸው  የየትውልዱን ሥዕል ቀለም ነክራ፤ ምስል ፈጥራ ለመጪው ታቀብላለች። መልካሙን በመልካም፤ክፉውን በክፉ አስቀምጣ ሕያው ትሆናለች፤ታደርጋለችም።
ሕይወት ዜማም አላት፤ወይ የሚጥም፤አሊያም የሚቆረጥም።...አንዳንዴ በእንባ የተለወሰ፣ሌላ ጊዜ ሳቅ የለበሰ ገጽታ ስለሚኖራት መልኳ ዝንጉርጉር ነው። ይሁንና በሰው ልጅ የታሪክ ጉዞና መልክ ውስጥ ጣፋጭ ነገር ያለ መራራ ጽዋ አይመጣም። እንዲያውም አንዳንዴ አንዱ ትውልድ ስለሌላው የተጎነጨው መራራ ጽዋ፣ለቀጣዩ ጣፋጭ ሆኖ ይመነዘራል። ጨለማ ብርሃንን እንደሚወልድ፣ሞት ማኅጸን ውስጥ ሕይወት ተረግዞ ሕያው ይሆናል።
ሕይወት ከሞት፤ብርሃን ከጨለማ እንደሚወለድ፣ጥቁር ሰማይ ውስጥ ብርሃን ያፈካች ፀሐይ እንደምትበቅል ካሳዩ የታሪክ ገጾች ውስጥ፣ የኛ የኢትዮጵያውያን ታሪክ እጅግ ደማቅ ማሳያ አድርጎ መውሰድ የዛሬው መጣጥፌ ትኩረት ነው። በተለይ በጥቁር ሕዝቦች ሰማይ ሳይመት የፈካው የዐደዋው የጀግንነት ቀንዲል ፣ዐለምን ለሁለት የከፈለ፣አንዱን ወገን ያስደነገጠና ሌላውን ወገን የነሸጠ፤እንደ ተዐምር የታየም ነበር።
የዚህ ታሪክ ፊት መሪ የሆኑት፣ብልሁ ምኒልክ  ነጭ ይሁን ጥቁር፣የዐፈታሪክን ያህል ግራ አጋቢ ክስተት ተብለው መነጋገሪያ ሆነው ነበር። ቴአትር የሚመስለው የዐደዋ ጦርነትና ድል የተሟሸው፣እሰጥ አገባው የከረመና ጉዳዩም ውስጥ ውስጡን የተብላላ ቢሆንም፤በአምባላጌ ጦርነት ግን ነገሩ እንደ ጎመራ ፈንድቷል።
አንዳንድ የታሪክ ጸሐፍት እንደሚሉት፣የጦርነቱ ቀስቃሽ የሚባሉት ፊታውራሪ ገበየሁ  መነሻቸውም የባንዳው የስብሀት ሠራዊት ከፊት ለፊታቸው ሲመጣ ማየታቸው ያጫረው ቁጣ ነበር። ሰው የገዛ ወገኑን ሊወጋ ከጠላት ጋር ተሰልፎ ቁጣቸውን መደበቅ አልቻሉምና ባረቀና ወጣ። የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ ሥልጡን የሚባሉት የንጉሡ አጎት ራስ መኮንን፣ ያ ጦርነት እንዲደረግ ትዕዛዝ አልሰጡም። ይልቅስ ስሜት ሥርዐትን ጥሶ፣የሥልጣን ተዋረድን አልፎ የወጣበት ድንገተኛ ማዕበል ነበር። ደግነቱ  ውጤቱ እንደ ድንገተኝነቱ አልነበረም፤ይልቅስ ለዐደዋ ድል የሚጠቅሙ ብዙ አዎንታዊ ዐምዶች የቆሙበት ነበረ። ለዐደዋው ሠፊ የታሪክ እንጀራ እንደ እንጎቻ የሚቆጠረው እርሾ የተቀመመበት ነበር። ምክንያቱም የአምባላጌው ድል ለኢጣልያ ጦር ከፍተኛ ግምት የሰጡና ንጉሡን በባላንጣነት የሚያዩ ሀገረ ገዢዎች ሳይቀር፣ከድሉ በኋላ ሰልፋቸውን እንዲቀይሩ አስገድዶ ነበር።
ጦርነቱ መጀመሩ ሲታወቅ፣እንደዋዛ ከሠሙት ውስጥ በብዙ ግንባር በጠላቶቻቸው ላይ ድል መቀዳጀት የለመዱት ብርቅዬው ራስ አሉላ አባነጋ፣”የንጉሠ ነገሥቱ ጀኔራል ጦርነት ውስጥ ሆኖ እኛ ዝም እንላለን እንዴ?”ብለው ወደ ፍልሚያው ከጓዶቻቸው ጋር ዘው ብለዋል። ራስ ወሌ፣ራስ መንገሻ፣ራስ መኮንንና ሌሎችም ጦርነቱን ተቀላቅለው፣መድፍ አለቅጥ ይጠቀም የነበረውን የፔየተሮ ቶዜሌን ሠራዊት በጀግንነት ምሽጉ ድረስ በመሄድ ልክ አስገብተውታል።
በጠላት በኩል፣ጦርነቱ እንደታሰበው ቀላል ያልሆነለት የኢጣሊያ ጦር፣ በደቂቃዎች ውስጥ ስመጥር የነበሩ የጦር አዛዦች ሲወድቁበት ተርበትብቶ፣የሞተው ሞቶ፣የተማረከው ተማርኮበት የተረፈው፣ እንደምንም በመድፍ ሽፋን ወደ መቀሌ ምሽግ ፈርጥጧል። ጦርነቱን ለሹመት መንጠላጠያ መሠላል፣ለክብር ዘውድ መድፊያ መንገድ ሊያደርግ  ሲጎመዥ የቆየው ሜጀር ቶዚሊም አጋጣሚውን ተጠቅሞ ድሉን ሊያጣጥም፣ሠረገላውን የኮረኮረውን ያህል ምድር ቁና ሆናበት እሳቱ መሀል ከስሎ ቀርቷል።
በወዲህ ወገን ደግሞ እጃቸውን ታምመው፣ከነሕመማቸው ወደ ውጊያ የገቡት ፊታውራሪ ገበየሁ በፈረሳቸው ላይ ተቀምጠው በእጃቸው የያዙትን በትር እያወዛወዙ “ግፋ፤በርታ” እያሉ ሠራዊቱን በማነቃቃት ትልቅ ሚና ተጫውተው እንደነበር ይነገራል። ከድሉ በኋላ በዕለቱ የተሞገሱት ገበየሁ የተለያዩ የሙገሳ ግጥሞች ተገጥሞላቸዋል፤
ከነፍጥ ጎበዛየሁ
ከጀግና ገበየሁ።
የንጉሥ ፊታውራሪ የጎራው ገበየሁ
አላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው
ለምሳም አልበቁ ጉድ አደረጋቸው።
ተብሎ ተዘፍኖላቸዋል።
ዘፈኑን በዜማ ሳይሆን በግጥም ትውልድ እየተቀባበለው እስካለንበት ዘመን ደርሶ፣ዛሬም ፊታውራሪ ገበየሁን በየመገናኛ ብዙኃኑና አደባባዩ በክብር እንዘክራቸዋለን። ጀግናችን ብለን አንገታችንን ቀና በማድረግ እንጓደድባቸዋለን። ምሥጋናችንም አድማሳትን ይሞላ ዘንድ ያለ ስስት ስማቸውን እያገነንን እናስባቸዋለን። መቸም ታሪክ በአንድ ምሽት ምጣድ ላይ የሚያሠፉት እንጎቻ አይለምና ሥር ለሰደደ ጽናታቸውና አልበገር ባይነታቸው፣በእሳት ነድደው ነፃነታችንን ያበሩትን ጀግና በታሪካችንን ማማ ላይ ሰቅለን እንደ ችቦ እንደምቅባቸዋለን።
ይሁንና በእኛ በኩል የአምባላጌ ጦርነት እልልታ ሲያጅበው፣በኢጣልያ ወገን ቀናቸው እንባና ደም ታጥቧል። ይህንን የምናየው ገና የጦርነቱ ምድጃ ሳይቀዘቅዝ፣ጢሱ በርዶ ትዝታ ሳይባል፣ከኢጣሊያ ጦር ጋር ተሰልፎ የነበረው አንድ ወታደር የተሰማውን ስሜትና የነበረውን ሁኔታ የገለጸበትን አጋጣሚ ትልቁ ጋዜጠኛና ታሪክ ጸሐፊ ጳውሎስ ኞኞ እንደዚህ አስፍሮት ስናይ ነው፦
“ሰላም የመቶ አለቃ።አበሾች ደርሰዋል፥እዚህ ናቸው።የአራተኛው ወታደር ሁሉ አለቀ።ሁሉም ሞቱ።ማጆር ቶዚሊ ሞተ።አንጊራ ሞተ።ማንፍሬዲኒ ሞተ። ሁሉም ፥ሁሉም ሞቱ አለኝ።
“ንገረኝ እንዴት ሞቱ?”አልኩት።
“ዛሬ ጧት።አበሾቹ ብዙ ነበሩ። ግማሹ ያህል ሞተ።ሌሎቹ ግን መጡብን።መድፍ ይተኮሳል።ጥይት ይተኮሳል።አበሾቹ ግን መጡብን።ኦህ ስንትና ስንት መሰሉህ።”
“በማን ውስጥ ነበርክ?” አልኩት።
“ማንፍሬዲኒ ውስጥ።”
“አይተሃል እሱን?”
“አዎ አይቸዋለሁ፤ሞቷል።”
“አስካላንስ አይተኸዋል?”
“አዎ አይቸዋለሁ፤ሞቷል (አስካላ ግን ቆስሎ ተማርኳል)ሁሉንም አይቻለሁ። ሁሉም ሞተዋል፤ታመልጡ እንደሆነ አምልጡ። አበሾቹ ከኋላዬ ናቸው። ጥፉ አለን የሶማሌው ወታደር።”
ስለዚህ  ጦርነት የጻፉትን አለቃ ተክለሥላሴን ጠቅሶ፣ጳውሎስ ከከተበው  ጥቂት ማሳያ እንውሰድ፤
”--የመድፉ አረር በሰማይ ሲሄድ የተወረወረ ኮከብ ይመስል ነበረ።የመድፉ ጥይት ዋንጫ ያህል ነበረ። ኋላም ቀለሃውን ገረድ ለውሃ መቅጃ አደረገችው.....እግረኛው እሮጣለሁ ሲል ጫማው እየከበደው፤አውልቆ እንዳይሮጥ አቀበትና ቁልቁለት ጠጠር እየወጋው፥የኋሊት እየተኮሰ እሮጣለሁ ሲል ከእንዝርት የቀለለ የጁየ፥ከነብር ነፈጠነ ቤገምድሬ፣ከቋንጣ የደረቀ ትግሬ፣ከአሞራ የረበበ ሸዌ፣ከንብ የባሰ ጎጃሜ እያባረረ በየጎዳናው ዘለሰው። አውሬ የነጨው ነጭ መጋዣ እየመሰለ በየዱሩ ሆዱን ገልብጦ ወደቀና የአውሬ ቀለብ ሆነ።--”
የአምባላጌው ጦርነት፣ለኢትዮጵያውያኑ የቀጣዩ ድልና ክብር መድረሻ እርከን መሆኑን ያሳየና በብዙዎች ዘንድ ያልተገመተ ውጤት ያመጣ ቢሆንም፤የኢጣልያ ጦር አዛዦች ሌላ ተስፋ ስለነበራቸው የመቀሌውን ምሽግ ማጠናከር ምርጫቸው አድርገውት ነበር። ጀኔራል ባራቲየርም አምባላጌን፣እንደማስፈራሪያና ሀገሩን ተቆጣጥረናል ለሚያሰኝ የሥነ ልቡና የበላይነት ያደረገው ቢሆንም፣ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ሲገጥም ወደ መቀሌው ምሽግ ማፈግፈግን አማራጭ አድርጎ መውሰድን አመራር ሰጥቶ ነበር።
ጦርነቱ የተጀመረበት አጋጣሚ ከመፈጠሩ በፊት፣ የኢትዮጵያ ጦር አዛዦች ነገሮችን ሁሉ በሰከነ መንፈስ ማየትና ችግሮችን ያለደም መፋሰስ መፍታት ይመርጡ ስለነበር ጦር ለመስበቅ አልቸኮሉም። ይሁን እንጂ በጠላት ወገን ሜጀር ጁሴፔ ጋሊያኖ  በተቀበላቸው የተሳሳቱ መረጃዎች ተደግፎ፣ልቡ በመደንደኑ አሁንም ሌላ ጦርነት  እንዳይጀመር ለሚጠነቀቁት ለኢትዮጵያ ጦር አዛዥ ራስ መኮንን የልግጫ ዐይነት ደብዳቤ ጽፎ ነበር። ቀደም ሲል ለጻፉለት ደብዳቤ መልስ ሲሰጥ፣ ሥፍራውን እንዳይለቅቅ አለቃው እንዳዘዙትና ትዕዛዙን ለመፈጸም የሚያስችለው በቂ የጦር መሳሪያና ዝግጅት እንዳለው በመኩራራት አስረግጦ ነበር።
በጊዜው ይህን ሲል የተለያዩ ምክንያቶች ነበሩት። ከነዚህ ምክንያቶች አንዱ ምኒልክ ለትግራይ መሬት ብለው ዘውዳቸውን ለአደጋ አያጋልጡም” የሚል ወሬም ተነዝቶ ስለነበረ ነው የሚለው፣ ትልቅ ግምት የሰጡት ነው። በዚህ ጊዜ ሁሉ ከጦርነት ይልቅ በሰላማዊ ውይይት ችግሮችን መፍታት የሚፈልጉት ራስ መኮንን፣ በተቻለ መጠን ጦርነት እንዳይቀሰቀስ መታገሳቸው፣በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ አልተወደደላቸውም  ነበር። እንዲያውም፣ ከኢጣሊያ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ጥብቅ በመሆኑ በማባበያ ወደ ኢጣልያ የማዘንበል አዝሚያ ያላቸው ተደርጎም ነበር። ይህ ደግሞ ከእቴጌ ጣይቱ አልፎ በዐፄ ምኒልክ ዘንድ ሳይቀር ጥርጣሬ አሳድሮ ነበር።
ይሁን እንጂ ለትዕግስት ልክ ማበጀት እንደሚገባ ጠንቅቀው የሚያውቁት ራስ መኮንን፣የታገሱትን ያህል ለጋሊያኖ ቁርጡን የሚነግር ወሳኝ ደብዳቤ እንዲህ ሲሉ ጻፉለት፤
“አምባላጌንና የቶዚሊን መጨረሻ አስታውስ። ተጨማሪ ደም እንዲፈስ አታድርግ። ምፅዋ ድረስ እሸኝሃለሁ፤ጓዝህንም እልክልሀለሁ።” አሉት። ይህ ማለት ጦርነቱ እዚህ ጀምሮ አያበቃም፤እስከ ምፅዋ እነዳሀለሁ የሚል ትርጉም ነበረው። የመቀሌ ውጥረት በዚህ ሁኔታ ሲቀጥል፣ የዐደዋው ጦርነት ጀግና ለመውለድ እያማጠ ነበር።
ጋሊያኖ፣አለቃው የነበረው ሜጀር ቶዜሊ፣ በኢትዮጵያውን ፈጣንና ቆራጥ ተዋጊነት መፈናፈኛ አጥቶና ከጥድፊያው የተነሳ መራመድ እንኳን አቅቶት፣ጭንቅላቱን ከጥይት ያድነው ይመስል፣በእጁ እየከለለ ቆይቶ በኋላ “በቃ አበሻ ሰዎች መጥተው ይግደሉኝ” ብሎ አቅም አጥቶ እንደሞተ ጋሊያኖ የረሳው ይመስላል።
የቶዚሊ አሟሟት በተለያዩ ጸሐፍት የተለያዩ ሰበበ ሞቶች የተጠቀሱበት በመሆኑ ሁለቱን እንደ ሁለት አተያይ ከመውሰድ ውጭ አንዱን ጥሎ አንዱን ማንሳት የሚቻል አይመስልም። ከላይ ከተጠቀሰውና በከፍተኛ ድካም ሆኖ መራመድ ሲያቅተው ሞትን ናፍቆ በጥይት አረር መንደዱን ብናይም፣ሌላው ኢትዮጵያዊ ጸሐፊ ሥርገወ ሐብለሥላሴ ሲጽፉት፣ ሌላ መልክ ይዞ በተለያዩ የጀግንነት ግጥሞች የታጀቡትን  የፊታውራሪ አባ ውርጂን ታሪክ ይዞ ይመጣል።
በዚህኛው ታሪክ ጸሐፊ ሲተረክ፣ቶዚሊ ከወዲያ ወዲህ እየተዘዋወረ ሲያዋጋ ድንገት ገደል ዳር ላይ የራስ መኮንን ጦር አባል ከሆኑት፣ከፊታውራሪ አባ ውርጂ ጋር ተገናኙ። እናም እኒህ ጀግና ቶዚሊ ሽጉጡን እስኪያወጣ ዕድል ሳይሰጡት፤ይዘውት አብረው ወደ ገደል ወረዱና የሁለቱም ህልፈት ሆነ።
ስለዚህ ጀግናው ፊታውራሪ እንዲህ ተብሎ ተገጠመላቸው፦
ጄነራል ባሕር ማጆ ቶዞሌ
ማን ይነካዋል ያለ ፈጣሪ
ገደል ሰደደው አንድ ፊታውራሪ።
አምባላጌ ላይ ከፊታውራሪ አባ ውርጂ ጋር በጦርነቲ የተሰዋ አንድ ሌላ ጀግና አለ፤ ይላሉ ሥርገወ።
ይህም ጊድን ገብሬ የሚባል የላስታና የዋግ የጦር መሪ ነበረ። እኅቱም በጦርነቱ መካከል፣በእሳቱ መሀል ጥይት በቀሚሷ ጫፍ እየቋጠረች ስታቀብል አብራ ሞታለች። ለእነዚህ ሁለት ጀግኖች ሕዝቡ ስንኝ ቋጥሮ፣ሙገሳውን ሰጥቷል። እኔም ገላጭ ነው ያልኩትን ጥቂቱን እዋሳለሁ።
የጊድን አገር አይተኛም በውን
ጦር መጣ ቢሉት ይነሳል አሁን
ጊድን ገብሬ የሜዳ ዝሆን
ፈረሱን ጫኑት ይነሳ እንደሆን።
አልሞተሞ ዛሬ ይጋልብ ከሜዳ
አኮላኮሎ የገደል ናዳ።

ለእህቱ ደግሞ፣
የጊድን እኅት ምጥን ወይዘሮ
ጥይት አቀባይ እንደአመልማሎ።

ራስ መኮንንም ጋሊያኖን ያስታወሱት ይህንን እንደተርብ የሚናደፍ፣እንደፌንጣ የሚወረወር ሕዝባዊ ሠራዊት ነው።
የዐለማችንን የደም ዝውውር ያናጋውና ድፍን ጥቁርን ከየቀፎው እንዲነቃና አንገቱን እንዲመዝዝ ያደረገውን የዐደዋውን ጦርነት ለመጀመር ምኒልክ በጣም ዘግይተዋል የሚሉ ወገኖች አሉ። በተለይ በጣሊያን ምኒልክ አቅማቸው ውስን፣ኀይላቸው ደካማ ተደርጎ ታስቦ ስለነበር፤ ከነበሩበት የሀገሪቱ ደቡብ ክፍል እስከ ትግራይ ድረስ ለውጊያ ይመጣሉ የሚል ግምት አልነበራቸውም። በርግጥም ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ከሆኑ ስድስት ዐመታት ቢያስቆጥሩም፣ከዚያ ቀደም ወደ ትግራይ ብቅ ብለው አያውቁም ነበር። ይልቁንም ሀገሩን የሚያስተዳድሩት በእጅ አዙር አማፂዎች በኩል በመሆኑ ይህም እንደ አቅም ማነስ ተቆጥሮባቸው ነበር። ይሁንና ይህን ጣሊያን እንደ ፍርሃት ቆጥሮ ዳር ዳር የሚልበትን ጦርነት ምኒልክ ገጥመው ልክ እንዲያስገቡ ከእኛ ወገን ብዙዎች ይፈልጉ ነበር። በተለይ ደግሞ ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱና ወንድማቸው ራስ ወሌ ጠላትን ለመበቀል ያቻኩሏቸው ነበር። ይሁን እንጂ ንጉሡ ጦርነት ለማካሄድ አሁንም አልቸኮሉም፤ነገሮችን በውል እያጤኑ፣ግራና ቀኙን እያስተዋሉ ያጠኑ ነበር።ሌላው ቀርቶ ለጦርነት የሚያመች ወቅትም ጭምር መምረጥ ስለሚያስፈልግ ጦርነቱ ክረምት ላይ እንዳይሆንና በዚያ የተነሳ የሚዘምተው ጦር ቁጥር እንዳይቀንስ ያሰሉ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ከሀገሪቱ ጋር ከሚጎራበቱ ሀገራት  ቁርሾ አላቸው ብለው የሚጠረጥሯቸው ወገኖች በጠላትነት እንዳይነሱባቸው በብልሀትና በማግባባት ነገሮችን ያሳልጡ ነበር። ለምሳሌ፣በሀገሪቱ ምዕራብ አቅጣጫ የነበሩትን ደርቡሾች ለማግባባት ፈረሶችና ቡና በመላክ ለማግባባት፣ በላቅ ሥነ ልቡናዊ ስልት “እኔም ጥቁር ነኝ፤እናንተም ጥቁሮች ናችሁ። የጋራ ጠላታችንን ለማደን አንድ እንሁን” በማለት ጠላት ቅነሳን እንደስትራቴጂ ተጠቅመው ነበር።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ በተለያየ አጋጣሚና ሁኔታ ቅሬታ የነበረባቸውን የጦር አለቆች ማግባባትና ሰላም መፍጠር ሌላ ስልታቸው ነበር። እንደ ራስ መንገሻና ራስ አሉላ፣ የጎጃሙ ተክለኀይማኖትም ሙሉ ለሙሉ ልባቸውን ለሀገር  እንዲሰጡ ሥራዎች ሠርተዋል።
ከዚህ በኋላ ጣይቱም በበኩላቸው ለዘመቻው የሚያስፈልገውን ሁሉ እየተዟዟሩ ያዘጋጁ ነበር። የእንጀራ ምጣድ ሳይቀር አሠርተው፣ስንቅ እንዲዘጋጅ አዝዘው፣ አዝማሪ አስከትለው ሲያበቁ በንጉሠ ነገሥቱ በኩል ነጋሪት አስጎስመው ጦርነት ተከተተ። ዐለምን የሚያስደንቅ አንድ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፈትበት ክስተት ዕጣ ሆኖ ኢትዮጵያ የምትባልና የሠለጠነ ዘመናዊ ሠራዊት የሌላት ሀገር ላይ ወደቀ።
በወዲያ በኩል፣ጦርነቱን በሚመለከት ጀኔራል አልቤርቶኒ አዛዦቹን ሰብስቦ ሲወያይ የተለያዩ አቋሞች ተንጸባርቀው ነበር። ይሁን እንጂ አልቤርቶኒን ጨምሮ ባብዛኛው ጦርነቱን መጀመር አስፈላጊ ነው የሚል እምነት አደረባቸው። በደረሳቸው መረጃ መሠረት የምኒልክ ጦር ተመናምኗል፤ ከፊሉም ስንቅ ፍለጋ ወደ ደቡብ ተበታትኗል የሚል ወሬ ናኝቷል። ጄነራል አርሞንዲ የበለጠ ጦርነቱን የናፈቀ ጠብ-አጫሪ ነበር። የተሻሉ ጦር መሳሪያዎች፣በርካታ ጥይቶች፣የተሻለ አልሞ ተኳሽነት፣የተሻለ አመራር፣የላቀ ጀግንነት፣ዒላማውን የሚያገኝ ተኩስ፣ይህ ሁሉ ደረት የሚያስነፋ ነው ብሎ አመነ።
ነገሩ እውነት ስለሚመስል በዚህ ያልተስማማ ጠላት አልነበረም። ስለዚህም ሁሉም ነገር ተጠናቅቆ ጉዳዩ ወደ ፍልሚያው ግንባር ወጣ፤ጦርነቱ በጧት ተጀመረ። እትጌ ጣይቱም ጦርነቱ መሐል ገብተው እያበረታቱ የዐደዋ ተራሮች ይጤሱ ጀመር፤ሰማይ ጥቁር ለበሰ፤ምድር ነደደች። ጀግና ተፈተነ።
ትልልቅ የጦር አዛዦች ሠራዊታቸውን ይዘው ገቡ። ብዙዎች ጥለው ወደቁ። መድፈኛው ሊቀ መኳስ አባተ ቧ ያለው፣ራስ አሉላ አባ ነጋ፣ራስ ሚካኤል፣ራስ ወሌ፣ፊታውራሪ ገበየሁ፣ደጃዝማች ጫጫ ሁሉም ንዳዱ ውስጥ አለፉ። በተለኮሰው እሳት ፣ዐለም በአዲስ የታሪክ ገጽታ ራሷን በመስታወት አይታ ተደመመች።
በጦርነቱ ማግሥት አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን፣ዐለም በድል ዜማ ሰከረች። ሮማም የራሷን መሪዎች ተቃውማ ለምኒልክና ጣይቱ ቪቫ እያለች ዘፈነች። የነጩ ዐለም ዐይኖች በእንባ ጤዛ ተጋረዱ፤የጥቁር ሕዝብ ድንኳኖች በእልልታ ተሞሉ። ዐድዋ ዝንጉርጉር ሥዕልዋን አስቀምጣ፣የቀደመውን የትዕቢት ጤዛ በደማቅ ፀሐይ አከሰመችው።
    ***
ከአዘጋጁ፡-
 ደራሲና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት በዚሁ ጋዜጣ ላይ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አያሌ መጣጥፎችን አስነብቧል፡፡ በርካታ የሥነጽሁፍ ሥራዎች ላይ ሂሳዊ ትንተና አቅርቧል፡፡ ደረጀ በላይነህ ገጣሚና አርታኢም ነው፡፡ 12 ያህል መጻሕፍትን አሳትሞ  ለአንባቢያን አድርሷል፡፡

Read 309 times