Wednesday, 28 February 2024 21:01

አዳም ረታ እንደ ኤግዚስቴንሻሊስት ልብ ወለድ ደራሲ

Written by  መኮንን ደፍሮ-
Rate this item
(1 Vote)

”--የአዳም የከረሜላ ፍልስፍና አንኳር ዐሳብ (central thesis) እንዲህ የሚል ነዉ፡ የቱንም ያህል የሰዉ ልጅ ህልዉና
በተለያየ ጎዳና ቢጓዝ፣ እንደ ዉሃ ቅዳ ዉሃ መልስ ጨዋታ በአሰልቺ የድግግሞሽ ዑደት የሚነጉድ ነዉ፡፡ ባለፈዉ፣
በዛሬዉና በመጪዉ ጊዜ መካከል መሠረታዊ ልዩነት የለም፡፡ ሰዉ ይኸን ፈፅሞ ሊሸሽ የማይቻል ገሀድ ሲገነዘብ ነፍሱ
የስልቹነትን ብሉኮ ትከናነባለች፡፡--”


(የመጨረሻ ክፍል)
               ፫. ሐቀኝነት
ከግብዝነት ጋር ተቃራኒ የሆነዉ ሴማ ሐቀኝነት ነዉ፡፡ ይህ ሴማ ከጭንቀት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነዉ፡፡ ጭንቀት እና ሐቀኝነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸዉ፡፡ ከላይ እንደ ዳሰስኩት፣ ጭንቀት ሰዉ በመሆን ለተጎናፀፍነዉ ፍፁማዊ አርነት እዉቅና መስጠታችን የሚፈጥረዉ ስሜት ነዉ፡፡ ሐቀኝነት ሳርተር እንደሚነግረን፣ ግለሰቦች ከግብዝነት የሚወጡበት መንገድ ነዉ (ሳርተር፣ 2018)፡፡ ሐቀኝነት ከግብዝነት በተቃራኒ ልንሸሸዉ የማንችለዉን ፍፁማዊ አርነት እና የሞራል ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ መቀበል ነዉ፡፡ በመሆኑም፣ ሐቀኛ ግለሰብ ምንጊዜም በሕይወቱ ለሚከናወን ማንኛዉም አይነት ኹነት ብቸኛዉ ተጠያቂ ራሱ መሆኑን በፀጋ ይቀበላል፡፡ በተጨማሪም፣ ሐቀኛ ግለሰብ ገሀድ (objectivity) እና ሽግግር (subjectivity) ብለን የምንጠራቸዉን ሁለቱን የሰዉ ልጅ ደረቅ ሐቆች በይሁንታ የሚቀበል ነዉ፡፡
ከላይ ፍፁማዊ አርነት ዉስጥ በጠቀስኩት አለንጋና ምስር በተሰኘዉ የአዳም የአጫጭር ልብ ወለዶች መድበል ዉስጥ የቀረበዉ ያ ሐመልማል የተሰኘዉ አጭር ትረካ፣ ሐቀኝነት ብለን የምንጠራዉ የግብረ ገብ ሴማ የተዳሰሰበት ሥራ ነዉ፡፡ በእዚህ አጭር ትረካ ዉስጥ የተሳለችዉ ዋና ገጸባሕርይ በየትኛዉም መንገድ ልትሸሸዉ የማትችለዉን ፍፁማዊ አርነት እና የሞራል ኃላፊነት (guilt) ሙሉ በሙሉ በመቀበሏ ሳቢያ በፀፀት ስትሰቃይ እናገኛታለን፡፡ ይቺ ሴት በወንጀለኝነት ስሜት ለመማቀቅ የተገደደችዉ ምንተስኖት የተባለዉን የሕግ ባሏን ዐይኑን በዐይኑ ሳታሳየዉ ድንገት በመኪና አደጋ በመሞቱ ምክንያት ነበር፡፡ ይህ ሟች ባሏ እሷ እንደምትነግረን እጅግ በጎ ሰዉ ነበር፡፡ ገጸባሕርይዋ በአንደኛ መደብ የትረካ አኳያ እንደምትተርክልን ባሏ ምንተስኖት በሕይወት ሳለ ከእሷ ልጅ ወልዶ መሳም ዘወትር ይፈልግ ነበር፡፡ በተቃራኒዉ፣ እሷ ደግሞ ከባሏ ጋር ዓለሟን መቅጨት እንጂ ልጅ ማርገዝና ማጥባት አትፈልግም ነበር (አዳም፣ 2001)፡፡ እነዚህ ሁለት ጥንዶች፣ ተራኪዋ ትቀጥላለች፣ ልጅ ሊያፈሩ ጫፍ ላይ ደርሰዉ በነበረበት አንድ ቀን ምሽት እሷ መልካም አጋጣሚዉን አጨናግፋ ልጅ መዉለድ እንደማትፈልግ ለባሏ ምንተስኖት ትነግረዋለች፡፡ በሚስቱ እንቢታ እጅግ የተበሳጨው ምንተስኖት፤ አኩርፎ በቀጣዩ ቀን ማለዳ ሚስቱን በተኛችበት ትቶ ከቤቱ ወጥቶ ይሄዳል፡፡ ምንተስኖት ግን ዳግመኛ ወደ ቤቱ አልተመለሰም – በመኪና አደጋ እስከ ወዲያኛዉ አሸለበ፡፡ በአጭሩ፣ የገጸባሕርይዋ ፀፀት ምንጭ ይህ አሳዛኝ ኹነት ነው፡፡ አዳም የሚከተለውን ጽፏል፡-   
… አልመጣም፡፡ ለዘላለም አልመጣም፡፡ የተቀመጠበት ታክሲ ከአንድ አምቡላንስ ጋር ተጋጭቶ ነዉ አሉ፡፡ ከአምቡላንስ ጋር፡፡ ከሁለት ሰዐት በኋላ ሆስፒታል ተጠርቼ ሔድኩና ሲሞት አየሁት፡፡ ጭንቅላቱን እየነቀነቀ … ለምን እንደነቀነቀ ይገባኛል፡፡ እተጋደመበት ሕይወቱ ሲያልፍ … አንጀቴን አጥፌ ሆስፒታል ወለል ላይ እንደ አበደ ሰዉ ስፈራገጥ … ‘ዓለም ከአሁን በኋላ ትጥፋ’ ስል ለምወደው ባሌ ብቻ ያለቀስኩ የመሰላቸው ብዙ ነበሩ፡፡ ለእኔ እሱ ብቻ አልነበረም … መወደዴ ብቻ አልነበረም … አንድ የተመኘውን ነገር ላደርግለት ባለመፈለጌ ቆጭቶኝ ነው (አዳም፣ 2001፡ገጽ 288)፡፡
   ፬. ወለፈንድ
     ወለፈንድ (absurdity) በታዋቂው ፈረንሳዊ ፈላስፋ እና ደራሲ አልበርት ካሙ ፍልስፍና ውስጥ ልዩ ሥፍራ ያለዉ ፅንሰ ዐሳብ ነው፡፡ ለካሙ፣ ሕይወት ወለፈንድ ወይም ከንቱ ነው (ካሙ፣ 1955፤ ቶዲ፣ 1959)፡፡ ይህ ሐቅ የሰዉ ልጅ ፈፅሞ ሊሸሸው የማይችለው ደረቅ ሐቅ ነዉ፡፡ ካሙ እንደሚነግረን፣ የሕይወት ወለፈንድነት ምንጩ በፍፁማዊ ትርጉም ፈላጊዉ የሰዉ ልጅና በፍፁማዊ ትርጉም አልባዉ ሁለንታ (universe) መካከል ያለ ግጭት፣ ታላላቅ ስኬቶቻችንን ሁሉ በአይቀሬው ሞት በቅፅበት መና አንደሚሆኑ ማወቃችን፣ ሁለንታ ለእኛ ትልምና ፍላጎት መልስ አልባ መሆኑን መታዘባችን፣ የሰው ልጅ ኅሊና የሁለንታን ምስጢር ለመግለፅ ብቁ አለመሆኑ እና የውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ጨዋታ የሆነውን አታካቹን የሰርክ ሕይወታችንን ግብ አልባነት መታዘብ ነው (ካሙ፣ 1955፤ ቶዲ 1959፤ ኮፕልስተን፣ 1994፤ ደ ሉፕ 1968፤ ዌበር 2018፤ ቤኔት 2001፤ ኮፕልስተን፣ 1956፤ ፎለይ 2008)፡፡
     የአዳም ረታ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ የተሰኘው የአጫጭር ልብ ወለዶች መድበል ከላይ የተዳሰሰው ወለፈንድ የተሰኘዉ ሴማ የቀረበበት ሥራ ነው፡፡ ይህ ሴማ የቀረበዉ አሕዛብ ማ’ድ ቤት በር ላይ በተሰኘዉ አጭር ልብ ወለድ ውስጥ ነው፡፡ በእዚህ ትረካ ውስጥ የተሳለው ዋና ገጸባሕርይ ቆስጠንጢኖስ የሕይወት ሂደት በአጠቃላይ ወለፈንድ ወይም ከንቱ ነው ብሎ የሚያስብ ሰው ነው፡፡ ይህ ገጸባሕርይ ይህን የግሉን ርዕዮተ ዓለም እንዲገነባ ሰበብ የሆነው በእዚህ በጊዜ እና በቦታ በታሰረ ዓለም የሰው ልጅን ጨምሮ ሁሉም ነገር ኃላፊ መሆኑን መታዘቡ ነው፡፡ አዳም የሚከተለውን ጽፏል፡-    
… ከልጅነቴም ‘መልክህ ያስከፋል’ የሚለኝ ሰዉ አላጋጠመኝም፡፡ መልኬ ሴት እንዳልቀርብ ግድግዳ ሆኖብኝ አያውቅም፡፡ ይልቁን የሚያቆመኝና ሁልጊዜ ብቸኝነቴን እንድወደዉ የሚያደርገኝ የሆነ ድብርት ነዉ፡፡ የዚህ ድብርት መሰረታዊ መልዕክት ሁልጊዜ በነገሮች ሃላፊነት ላይ ያተኮረ ነዉ፡፡ ነገሮች ባያልፉ ኖሮ፣ ምሉዕ ገጠመኞች በመረሳት ባይገደፉ ኖሮ፣ ከእናትና ከአባቴ ጋር አብሬ እሆን አልነበር? ካየኋቸዉ አመታት አለፉ፡፡ በጨካኝ ቤት አከራይ ነጋ ጠባ እየተገረፍኩ ብኖርም፣ ቤት ለመስራት ሰዎች በማሕበር ሲደራጁ ያልገባሁበት አንዱ ምክንያት ቤቱን በሰራሁት በበነጋታዉ የሚፈርስ ወይ የምሞት፣ ወይ ቤቱ የሚቃጠል ወይ የሚወረስ ስለሚመስለኝ ነው (አዳም፣ 2003፡ገጽ 365)፡፡
     ከሰማይ የወረደ ፍርፍር እና ሌሎች አጫጭር ልብወለዶች የተሰኘው የአዳም የአጫጭር ልብ ወለዶች መድብል ወለፈንድ የተሰኘዉ ሴማ የቀረበበት ሌላኛዉ ሥራ ነው፡፡ ይህ ሴማ የቀረበዉ ከረሜሎች በተሰኘዉ አጭር ልብ ወለድ ውስጥ ነዉ፡፡ በእዚህ ትረካ ውስጥ አዳም እንደሚነግረን፣ ከረሜሎች የተሰኘው ልብ ወለድ ዐቢይ ጭብጥ በእየለቱ የምንገፋው ተመሳሳዩ ህልውናችን የወለደው ስልቹነት (boredom) ነዉ፡፡ ይኸ ልብ ወለድ ታሪክ ጥቂት ብቻ ለውጦች በማድረግ ተደጋግሞ የተጻፈ ነው፡፡ ደራሲው ይኸን በማድረጉ ኋላ ላይ በሥራው መደምደሚያ ላይ ያቀረበው ፍልስፍና የሰመረ እንዲሆን ረድቶታል፡፡  
     አዳም፣ በእዚህ ሥራው የሚያሳየን የሰው ልጅ መኖር ኩነኔ ሆኖበት ሰርክ በልማድ የሚጓዘው ጉዞ አዲስ መዳረሻ የሌለው ከንቱ ጉዞ የመሆኑን ሐቅ ነው፡፡ የከረሜሎቹ ውክልና የሰዉ ልጅ ህልዉና ነዉ፡፡ እነዚህ ከረሜሎች፣ የተለያየ ቀለም ባለዉ ማራኪ ወረቀት የተጠቀለሉ፣ ተመሳሳይ ቅርፅ ያላቸዉና በተለያዬ ቄንጥ የተሸመለሉ ናቸዉ፡፡ የከረሜሎቹ በመልክና በሽፋን መለያየትና በተለያየ ቄንጥ መሸምለል በእያንዳንዱ ዕለት የምንኖረዉ ፈርጀ ብዙው ሕይወታችን ተምሳሌት ነዉ (አዳም፣ 2002)፡፡ ይኸ የዕለት ተዕለት ህልውናችን በደምሳሳዉ ስናስበዉ አንዱ ከአንዱ የተለያየ ይመስላል፡፡ ነገር ግን፣ ይኸ ሕይወት ልክ በመልክና በሽፋን የተለያዩ ከረሜሎች አፍ ውስጥ ገብተዉ ሲመጠጡ ቢጎረብጡም፣ ጣዕማቸዉ የማይወደድ ዕንግዳ ቢሆንም፣ ተራ በተራ ተገልጠዉ ሲቀመሱ ያላቸዉ ጣዕም ተመሳሳይ እንደሆነ ሁሉ አዲስነት የሌለዉና ለመኖር የሚያስፈራ ነዉ (አዳም፣ 2002)፡፡
በድግግሞሽ ዑደት እንዲጓዝ የተደነገገዉ ህልዉናችን የወለደዉ ስልቹነት የወለፈንድነት ስሜት መንስኤ ነዉ፡፡
     ካሙ እንደሚነግረን፣ ሰዉ ከሕይወት ፋይዳ ቢስነት ሐቅ ጋር ሲላተም ራስን ማጥፋትን መፍትሄ አድርጎ ይወስዳል፡፡ ራስን መግደል ታዲያ የሕይወት ፋይዳ ቢስነት ትክክለኛ መፍትሄ ይሆናል? በፍፁም ይለናል ካሙ፡፡ እንደ እሱ እሳቤ፣ ራስን መግደል የሕይወት ፋይዳ ቢስነት ስሜት ትክክለኛ መድኀኒት ባለመሆኑ በፅኑ የሚወገዝ ተግባር ነዉ (ካሙ፣ 1955)፡፡ ካሙ እንደሚነግረን፣ የወለፈንድ ስሜት እዉነተኛ መፍትሄ (authentic solution) ራሱ ፋይዳ ቢስነት ላይ ማደም (revolt) ነዉ (ቶዲ፣ 1959፤ ዊክ፣ 2003፤ ደ ሉፕ፣ 1968)፡፡ አድማ የወለፈንድ ስሜትን በፀጋ ተቀብሎ ሕይወትን በመቀጠል ይገለፃል፡፡ ይህን አይነቱን ዉሳኔ ካሙ እዉነተኝነት (authenticity) ብሎ ይጠራዋል (ዊክ፣ 2003)፡፡ ካሙ ራስን መግደልን የሚያወግዘዉ ለፋይዳ ቢስነት እጅ መስጠት ነዉ የሚል አተያይ ስላለዉ ነዉ፡፡ ራሳችንን እንዳንገድል የሚያደርጉን ፍፁማዊና ዘላለማዊ መሆን የማያሻቸዉ አያሌ የትርጉም ምንጮች አሉ ይለናል ካሙ (ዊክ፣ 2003)፡፡
     ለካሙ ትክክለኛ ሕይወት የሲስፈስ አይነት ነዉ፡፡ ሲሲፈስ በግሪክ አፈታሪክ ዉስጥ የሚገኝ የኮርኒት ንጉሥ ነው፡፡ የአማልክቱን አለቃ ዚውስ ምስጢር አስፐስ ለተባለው የባሕር አምላክ አሳልፎ በመስጠቱ ከዚውስ ጋር ተቃቃረ፡፡ ዚውስም ሀዴስ የተባለ ቦታ ውስጥ ግዙፍ ቋጥኝ ወደ አንድ ተራራ እየገፋ ወደ ጫፍ እንዲያደርስ ፈረደበት፡፡ ቋጥኙ ከግዝፈቱ የተነሳ ተራራ ጫፍ ሲደርስ መልሶ ቁልቁል ወደ ግርጌ የሚንከባለል ነበር፡፡ ይህ የሲሲፈስ ተግባር እረፍት የለሽ ነው፡፡ ሲሲፈስ የሚወክለዉ የእያንዳንዳችንን ሕይወትና ዕጣ ነዉ፡፡ ቋጥኙ የሕይወታችን ሸክም ምሳሌ ነዉ፡፡ ሁላችንም ይህን ሸክም ተሸክመን ዘወትር ተመሳሳይ ጉዞ እንጓዛለን፡፡ ህላዌ ታላቅ መከራ ነዉና ዕጣችንን ከመቀጠል ዉጪ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ ካሙ እንደሚነግረን፣ ምንም እንኳን የሲስፈስ የኑሮ ዕጣ ፋታ በሌለዉ ድግግሞሽ የተሞላ ቢሆንም፣ ይህን በድግግሞሽ የተሞላ ፋይዳ ቢስ ዕጣዉን በፀጋ ተቀብሎ በጀግንነት በመጋደል ሕይወቱ ትርጉም ያለዉ እንዲሆን አድርጓል፡፡     እንደ ካሙ እሳቤ፣ በኑሮ ሂደት ዉስጥ ወለፈንድነትን መጋፈጥ በራሱ ታላቅ ትርጉም ነዉ፡፡ ለአዉዳሚነት (nihilism) ፍልስፍና አቀንቃኙ ኤሚሊ ሚሃይ ቾራን ግን በሕይወት ዉስጥ ጨርሶ ፋይዳ ያለዉ ነገር የለም (ዊክ፣ 2003)፡፡ ቾራን ከካሙ የሚለየዉ በእዚህ አተያዩ ነዉ፡፡
     የአዳም የከረሜላ ፍልስፍና አንኳር ዐሳብ (central thesis) እንዲህ የሚል ነዉ፡ የቱንም ያህል የሰዉ ልጅ ህልዉና በተለያየ ጎዳና ቢጓዝ፣ እንደ ዉሃ ቅዳ ዉሃ መልስ ጨዋታ በአሰልቺ የድግግሞሽ ዑደት የሚነጉድ ነዉ፡፡ ባለፈዉ፣ በዛሬዉና በመጪዉ ጊዜ መካከል መሠረታዊ ልዩነት የለም፡፡ ሰዉ ይኸን ፈፅሞ ሊሸሽ የማይቻል ገሀድ ሲገነዘብ ነፍሱ የስልቹነትን ብሉኮ ትከናነባለች፡፡ ነገር ግን፣ አዳም ካሙ እንደተናገረዉ፣ ስልቹነት ራስን የመግደል ዐሳብን ልቡና ዉስጥ ይጠነስሳል የሚል እምነት የለዉም፡፡
     ማጠቃለያ
     በእዚህ ኂሳዊ መጣጥፍ የእዚህ ትዉልድ ደራሲያን “የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ንጉሠ ነገሥት” ብለዉ የሚጠሩት አዳም ረታ ደንበኛ ኤግዚስቴንሻሊስት ልብ ወለድ ደራሲ መሆኑን ሥራዎቹን ከኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና አንጻር በመፈከር አሳይቻለሁ፡፡ አርነት፣ ኃላፊነት፣ ጭንቀት፣ ግብዝነት፣ ሐቀኝነት፣ ባይተዋርነት እና ወለፈንድ በአለንጋና ምስር እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች፣ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ፣ እቴሜቴ ሎሚ ሽታ እና ከሰማይ የወረደ ፍርፍር እና ሌሎች አጫጭር ልብወለዶች ዉስጥ ዐቢይ ጉዳይ ሆነዉ በጥልቀት የተዳሰሱ የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ሴማዎች ናቸዉ፡፡
     በኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ውስጥ ልዩ ሥፍራ የሚሰጠዉ ሴማ ፍፁማዊ አርነት ነዉ፡፡ ሳርተር እነነዳተተው፣ አርነት የሰዉ ልጅ ፈፅሞ ሊሸሸዉ የማይችለዉ የሰዉ ልጅ መገለጫ ባሕርይ ነዉ፡፡ እኛ እያንዳንዳችን የራሳችን ዕጣ ፈንታ ቀያሾች የሆነውም በእዚህ ምክንያት ነው፡፡ ይህ ፍልስፍናዊ ሴማ የተፈከረባቸዉ የአዳም የድርሰት ሥራዎች ኦቾሎኒ እና እቴሜቴ ሎሚ ሽታ ናቸው፡፡
     ግብዝነት ሌላው በኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ዉስጥ አፅንኦት የሚሰጠው ፅንሰ ዐሳብ ነዉ፡፡ ሳርተር እንደነገረን፣ ሰው በግብዝነት ውስጥ ሲወድቅ ሁለቱን የሰው ልጅ ደረቅ ሐቆች ገሀድ እና ሽግግር ይሸሻል፡፡ የእዚህ ሽሽት ዐቢይ ግብ ለአርነት እውቅና በመስጠት ሳቢያ ከሚፈጠር የጭንቀት ህመም እፎይ ለማለት ነው፡፡ ይህ አይነቱ የግብዝነት አይነት ሽግግር ሽሽት ተብሎ ይጠራል፡፡ የሌሎች ሰዎችን ፍረጃ በፀጋ መቀበል ሌላኛው ሽግግር ሽሽት ተብሎ በሚጠራው የግብዝነት አይነት የመውደቅ መገለጫ ጠባይ ነው፡፡ ይህ የግብዝነት አይነት የተፈከረባቸዉ የአዳም የድርሰት ሥራዎች ኦቾሎኒ፣ ቀዳዳ እና እቴሜቴ ሎሚ ሽታ  ናቸው፡፡
     ሐቀኝነት ከፍፁማዊ አርነት እና ግብዝነት በተጨማሪ በእዚህ ኂሳዊ መጣጥፍ ውስጥ የዳሰስኩት በኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ውስጥ የሚገኝ ሌላኛዉ ሴማ ነዉ፡፡ ሐቀኝነት የግብዝነት ተቃራኒው ፅንፍ ሲሆን ፈፅሞ ልንሸሸው ለማንችለዉ ፍፁማዊ ነፃነታችን እውቅና በመስጠት የሚገለፅ ጠባይ ነው፡፡ በተጨማሪም፣ ሐቀኝነት ገሀድ እና ሽግግር ብለን የምንጠራቸዉን ሁለቱን የሰዉ ልጅ ደረቅ ሐቆች በይሁንታ በመቀበል ይገለጣል፡፡ ይህ ፍልስፍናዊ ሴማ የተፈከረበት የአዳም የድርሰት ሥራ ያ ሐመልማል ነው፡፡
ወለፈንድ በእዚህ ኂሳዊ መጣጥፍ የዳሰስኩት የመጨረሻው የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ሴማ ነው፡፡ ለካሙ የሰው ልጅ ሕይወት ከንቱ ነው፡፡ ከሕይወት ከንቱነት መንስኤዎች መካከል ሁለቱ ሞት እና የሕይወት የድግግሞሽ ዑደት ናቸው፡፡ ሞት ታላላቅ ስኬቶቻችንን ሁሉ በቅፅበት እንዳልነበሩ እንደሚያደርጋቸዉ መታዘባችን ሕይወት ከንቱ የመሆኑን ሐቅ ይገልጥብናል፡፡ እንዲሁም፣ አዲስነት የሌለው ሕይወትን መግፋታችን ስልቹነትን ይወልዳል፡፡ ስልቹነት ደግሞ ሕይወት ውስጥ ትርጉም የማጣት ስሜት መንስኤ ነው፡፡ ይህ ፍልስፍናዊ ሴማ የተፈከረባቸዉ የአዳም የድርሰት ሥራዎች አሕዛብ ማ’ድ ቤት በር ላይ እና ከረሜሎች ናቸው፡፡                

Read 224 times