Friday, 23 February 2024 17:05

‹‹ፍለጋው አያልቅም…›› የአዲስ ዋልታ የውህደት ፖለቲካ

Written by  ስሜነህ ባይፈርስ
Rate this item
(2 votes)
የኢትዮጵያ ሚዲያ በዘውድ እና በጎፈር የተለያየ መልክ አለው፡፡ ‹‹ማሞ ሌላ፣ መታወቂያው ሌላ›› ማለት ይቻላል፡፡ ገና በማለዳው፣ የጋዜጠኝነት መምህሬ አብዲ ዓሊ የነገረኝ ነገር ሌላ፤ በሜዳው ያየሁት ሌላ ሆኖ ተቸግሬ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ሚዲያ ጎዳና ስጓዝ፣ መጀመሪያ ያንኳኳሁት የህትመት ሚዲያውን በር ነበር፡፡ የአንድ ሰሞን ባልደረቦቼ ‹‹ወንጭፍ›› ብለው የሰየሙት ጋዜጣ ሲዘጋባቸው፣ ‹‹ዳግም ወንጭፍ›› ብለው መጥተዋል፡፡ አብዲ ዓሊ ከመረጃ አሰባሰብ እስከ ማጠናቀር፤ ከአርትኦት እስከ ሌይ አውት፤ ከኪከር እስከ ቲከር ብዙ አስተምሮናል፡፡ በተማርነው ትምህርት፤ በጨበጥነው ዕውቀት ሚዛን፤ የተቀላቀልኳቸውን ተቋማት ስመለከታቸው፤ ሁሉም በፈተናው የሚወድቁ ናቸው፡፡
‹‹ስምን መልዓክ ያወጣዋል›› እንዲሉ የ‹‹ዳግም ወንጭፍ›› ዋና መርህ የሚወናጨፉ ዜናዎችን ማምረት ነበር፡፡ ሰሜን ሆቴል አካባቢ በአንድ ግቢ ውስጥ በምትፈበረከው ‹‹ዳግም ወንጭፍ›› በሚሰሩት ጋዜጠኞች ዘንድ አንዳችም የጋዜጠኝነት ስብዕና አስተውዬባቸው አላውቅም፡፡ የተንጨበረረ ጸጉራቸው ከጋዜጠኛ ይልቅ ነፃ አውጪ ያስመስላቸዋል፡፡ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዜናዎችን እየበለቱ የሚወናጨፉ ዜናዎችን ያመርታሉ፡፡ ከዚህ እና ከዚያ እያጋጩ፤ አውዱን እያዛቡ፤ ‹‹ከውስጥ ምንጫችን›› እያሉ ይለቀልቃሉ፡፡
ጊዜው፣ ህወሓት ለሁለት ተከፍሎ፤ ‹‹አንጃ›› እና ‹‹ተንበርካኪ›› እየተባባለ የሚጠዛጠዝበት ጊዜ ነበር፡፡ እናም በ‹‹ዳግም ወንጭፍ›› ይወጡ የነበሩ ዜናዎችን በጋዜጠኝነት ዓይን ለሚመለከታቸው አስደንጋጭ መሆናቸው ባይቀርም፣ በተቃውሞ ስሜት ለሚንገበገበው ህዝብ እና ለአንጃው ደጋፊዎች አንጀት አርስ ዜናዎች ነበሩ፡፡
ሆኖም እንደኔ ቀረብ ብሎ ለተመለከተ ሰው የ‹‹ዳግም ወንጭ›› ነገር አስደንጋጭ ነበር፡፡ ማንነታቸው ሳይታወቅ በስውር ለመንቀሳቀስ የሚሞክሩት የ‹‹ወንጭፍ›› ጋዜጠኞች ሁኔታ መጥፎ አደጋ እንዳሸት አደረገኝ፡፡ ስለዚህ በፍጥነት ከሰሜን ሆቴል ተንደርድሬ ወደ ሃያ ሁለት ተሰደድኩ፡፡ በሃያ ሁለት ከ‹‹ማትሚኖ›› ጋር ተገናኘሁ፡፡
የ‹‹ማትሚኖ›› ድባብ ቀለል ያለ መሰለኝ፡፡ ጋዜጠኞቹ በኃላፊነት ስሜት የሚሰሩ ይመስላሉ፡፡ ትክክለኛው የሥራ አካባቢ ውስጥ የገባሁ መሰለኝ፡፡ ሆኖም ይህ ሀሳቤ ትክክል አለመሆኑን ለመገንዘብ ከ3 ሣምንታት በላይ አልወሰደብኝም፡፡ እሁድ ለንባብ የምትበቃውን ‹‹ማትሚኖ›› ለማዘጋጀት ቅዳሜ ጠዋት ቢሮ እንገባለን፡፡ ከገቡ መውጣት የለም፡፡ አሳታሚዋ ፀሀይ፣ ፀሀይ የመሰለ አገልግሏን ከምሳ እስከ እራት እንዲሆን አድርጋ ይዛ ትመጣለች፡፡ ከዚያ ያን እየበሉ ልክ እንደ ‹‹ዳግም ወንጭፍ›› የአዲስ ዘመን ዜናን ‹‹ከውስጥ ምንጫችን›› በሚል ሀረግ እየደገፉ፣ አውድ እያዛቡ፣ ዜና የመፈብረክ ሥራው ይቀጥላል፡፡
‹‹ማትሚኖ›› ምናባዊ ቃለ ምልልሶች የምታስተናግድበት አንድ ዓምድ አላት፡፡ አሳታሚዋ ከርዕሰ አንቀጽ በላይ ብዙ የምትጨነቀው፤ ለዚህ አምድ መሆኑን አስታውሳለሁ፡፡ ከዚህ ከዚያም ከየጋዜጦቹ ተቦጫጭቀው የተወሰዱና ከጋዜጣው ጀርባ ያሉ አካላትን ታሳቢ ያደረጉ ዜናዎች ተፈብርከው፤ ‹‹ከውስጥ ምንጫችን›› በሚል ሽፋን ወሬ የሚፈተፈትባቸውን መድረኮች እንጂ አብዲ አሊ ፈትፍቶ ያጎረሰንን የጋዜጠኝነት መርሆችንና አሰራሮችን የተላበሱ ሪፖርቶችን አላየሁም፡፡ ‹‹ማትሚኖ›› ቤቴ እና ቦታዬ እንዳልሆነችና መሆንም እንደማትችል በመገንዘብ፤ ትክክለኛ ቦታ የመፈለግ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ ራስን ፍለጋ ነው፡፡ ራስን ፍለጋ አድካሚ ነው፡፡ በዲቁና ዘመን፣ በቅዳሴ በተሟሸ አንደበቴ የዲፒ ሽንዴን ‹‹ፍለጋው አያልቅም…››ን እየዘፈንኩ፤ በፍለጋዬ ጸናሁ፡፡
ኢህአዴግም የተሀድሶ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ እኔም የሙያ ጉዞዬን ጀምሪያለሁ፡፡ የቋጠርኳት ጥቂት ሳንቲም ዓይኔ እያየ እየሟሸሸች ነው፡፡ ሥራ ፍለጋውን ለመቀጠል፣ አራት ኪሎ ደርሶ ለመመለስ የሚበቃ የአውቶቢስ ሣንቲም ጠፋ፡፡ የአንድ ሰው ኮሌጅ መበጠስ ወድያው የገንዘብ ምንጭ እንደሚሆን በሚቆጥር ማህበረሰው ውስጥ መወለዴ እና ማደጌ ቤተሰቦቼን ተስፋ እያስቆረጠ ነው፡፡
ክፍት የስራ ቦታ ፍለጋ ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣን፣ ዘወትር ጠዋት ቃሊቲ ማዞሪያ 08 ቤተ-መጽሐፍት እየገቡ መሳለም መደበኛ ሥራዬ ሆኗል፡፡ ግን በአጋጣሚው የተለያዩ የታሪክ እና የልብ-ወለድ መጻሕፍትን የማንበብ ባህሌ ዳብሯል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ከፓርቲ እና መንግስት ጋር የመተዋወቅ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ጉዞው ቀጥሏል፡፡
ከ7 ዓመት በታች ልምድ የማይጠይቁ የአዲስ ዘመን ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያዎች እየሰለቹኝ ቢሆንም ፍለጋዬን ለአንዲትም ቀን ሳላቋርጥ ቀጥያለሁ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ‹‹አዲስ ዘመን›› አዲስ ነገር ይዞ መጣ፡፡ 0 ዓመት የሥራ ልምድ የሚጠይቅ ክፍት የሥራ ቦታ አገኘሁ፡፡ የጉራጌ ዞን ም/ቤት ጽ/ቤት፣ የማስታወቂያው ባለቤት ነው፡፡ ወደ ባለቤቱ ተጓዝኩ፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ የ30 ኪሎ ሜትር ያህል እንኳ የጉዞ ልምድ ለሌለው ለእንደ እኔ ዓይነቱ ሰው ሆድ የሚያስብስ ጉዞ ነበር፡፡ ወልቂጤ ሄድኩ፡፡ ወልቂጤ ኖርኩ፡፡ ‹‹ፍለጋው አያልቅም……›› ወልቂጤ የወሰደኝ መንገድ ኮኪር ገደባኖ ጉታዘር ወረዳ ዶለኝ፡፡ በሁሴን ሃጂአልዬ በኩል ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ እና ከአርሶ አደሩ ጋራ አሰናሰለኝ፡፡ በመጨረሻ ወልቂጤ የወሰደኝ መንገድ ወደ አዲስ አበባ መለሰኝ፡፡ ከፋና ጋር አገናኘኝ፡፡
ፍለጋው አያልቅምና በ‹‹ዳግም ወንጭፍ›› እና በ‹‹ማትሚኖ›› የተራብኩትን ጋዜጠኝነት በፋናው ብሩክ ከበደ በኩል አጠገበኝ። እንደገናም በመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ከነበረከት ስምኦን እና ከጌታቸው ረዳ ዘንድ አደረሰኝ፡፡ ይህ ፍለጋዬ የዛሬው ማንነቴን ቀርጾ፣ በዋልታው ተተካ በቀለ በኩል ከ‹‹አዲስ ዋልታው›› ማሜ አደረሰኝ። አሁን በአዲስ ዋልታ የውህደት ፖለቲካ ዜማ ተከብቤ ‹‹በነጻ ሀሳብ›› መድረክ፤ ከመሐመድ ሀሰን ጋር ነኝ፡፡
መሐመድ ጥሩ አለቃ ነው፡፡ ወጣት ነው፡፡ ብዙ ነገሮችን ሰርቷል፡፡ ግን ከሰራው ይልቅ ሊሰራ የሚችለው ያጓጓኛል፡፡ አብዛኛው ሰራተኛ በአመራሩ ደስተኛ ይመስለኛል፡፡ በእኔ እይታ መሀመድ በሚከተሉት ሁለት ምሳሌዎች ሊገለጽ ይችላል፡፡
ምሳሌ አንድ
- በቅርቡ አንድ ፊልም አይቼ ነበር፡፡
- መስሪያ ቤቱ፣ በርካታ ሰራተኞች አሉት፤
- ወንድ፣ ሴት፣ ነጭ፣ ጥቁር፤
- ታች ያሉ፣ መሀል ያሉ፣ ላይ ያሉ ሰራተኞች፤
- አዳራሹ ትልቅ ስለሆነ፣ ሰራተኞቹ፣ እርስ በእርስ ይተያያሉ፡፡ ዋናው ኃላፊም፣ ዞር ዞር እያለ ያያቸዋል፣ ያናግራቸዋል፡፡
- አንድ ቀን እንዲህ እየተዘዋወረ እያያቸው ሳለ፣ ተላላኪዋን ሰራተኛ፣ አርፍዳ ስትገባ ያያትና፣ በስጨት ብሎ ያናግራታል፡፡
- ሁል ጊዜ አርፍደሽ ስትመጪ አይሻለሁ፣ ችግር አለ? - - - -
- ደንገርገር ይላታል፣ ተላላኪዋ፡፡ ግራ ቀኝዋን ትገላመጣለች፡፡
- ቆጣ ብሎ፣ ‹‹የት እየሄድሽ ነው እንዲህ በየቀኑ የምታረፍጂው?›› ይላታል አለቃዋ፡፡
- ‹‹ንጽህና ቤት እየሄድኩ ነው›› ትለዋለች፡፡
- ‹‹እዚህች ንጽህና ቤት ደርሶ ለመምጣት ነው፣ ይህን ያህል ጊዜ አርፍደሽ የምትመጭው?›› ይጠይቃል፡፡
- አዎ ጌታዬ!
- ምን ማለትሽ ነው? (ይገርመዋል)
- እዚህ ያለው ንጽህና ቤት እኮ፣ ለነጮች ብቻ የተሰራ ነው!
- አልገባኝም! (ከመገረምም፣ ይደነቃል)
- ጽሁፍ እኮ ተጽፎበታል፣ ጌታዬ!
- ምን የሚል ጽሁፍ?
- ‹‹ለነጮች ብቻ!›› ተብሎ ተጽፎበታል እኮ፣ እኔ ደግሞ ጥቁር ነኝ፣ ስለዚህ ለጥቁሮች የተዘጋጀ ንጽህና ቤት ፍለጋ፣ ስንቱን ህንፃ አቆራርጬ፣ በየቀኑ እሄዳለሁ፣ እዚያ ደርሼ ስመልስ ይረፍድብኛል፡፡
- አለቃ፣ አላስጨረሳትም፣ እመር ብሎ ተፈናጥሮ ይሄዳል፣ ተላላኪዋም፣ ወደ ስራዋ ትመለሳለች፡፡
- ወድያው፣ ሰራተኛው ሁላ፣ ከወደ ጀርባ፣ በመዶሻ የሚቀጠቀጥ ነገር ይሰማል፡፡ ብድግ ብድግ እያሉ፣ ድምጹን ወደሰሙበት አቅጣጫ ያመራሉ፡፡ እቺም ትሄዳለች፡፡ እሱም ይከተላል፡፡
- አለቃቸው፣ ንጽህና ቤቱ አናት ላይ የተሰቀለውን፣ ለነጮች ብቻ የሚለውን የብረት ማስታወቂያ፣ ወዲያው ነቅሎ ለመጣል፣ እየደበደበ ነው፡፡
- ዷ!ዷ!ዷ!
- ተላላኪዋም ትደርሳለች፡፡ አለቃዋ፣ ያን ክፉ መልዕክት ነቅሎ ለመጣል እየታገለ ነው፡፡
- ገንድሶ ጣለው!
- ከዛሬ በኋላ፣ የሁላችንም ንጽህና ቤት ነው! ብሎ፣ መዶሻውንም አሽቀንጥሮ ይጥለዋል፡፡
- ተላላኪዋ፣ አንጀቷ ቅቤ ይጠጣል፡፡
- ማሜ ለኔ፣ እንዲህ ዓይነት አለቃ ነው!
- ግን … ግን በአዲስ ዋልታ ቴሌቭዥን የ2016 ዓ.ም የዘመን መለወጫ ዝግጅት አብረውኝ የቀረቡት የሣምራዊት እና የፋኖስ ታሪክ፤ የሲስተር አረፋይኒ አስተያየትና ለቅሶ እዚህ ከጠቀስኩት ፊልም አይበልጥም?
የሆነ ሆኖ፣ ማሜ ተላላኪም ሆነህ፣ ይሰማሀል፣ ፊት ያመጣሀል፣ ላይ ያወጣሀል፡፡ ንጽህና ቤቱ የሁሉም ሰራተኛ እንደሆነው ሁሉ፣ እስከማውቀው ድረስ፣ ማሜ ከመጣ ወዲህ፣ አዲስ ዋልታም፣ የሁሉ ሰራተኛ የጋራ ቤት ነው፡፡ አንድ ምሳሌ ይበቃኛል፡፡ ተላላኪዋ በአለቃዋ ስራ የተደነቀችውን ያህል፣ ይህም የዋልታ ሰራተኛ፣ በአዲሱ አለቃ ስራ፣ ደስታ ብቻ ሳይሆን፣ ሙሉነትም ተሰምቶታል፡፡ ስራችን፣ ሳይንቲስቶችን ወደ ጠፈር መላክ ነው! እንዳለው የናሳ ጥበቃ፣ በመስሪያ ቤቱ ላይ፣ ሙሉ ባለቤትነት ተሰምቶታል፡፡ ልጅ ወለደ፣ ልጁን፣ ዋልታ ብሎ ሰየመው፡፡ ለልጁ ስም እስከማውጣት ባይደርስም፣ እያንዳንዱ የአዲስ ዋልታ ሰራተኛ፣ አዲሱ አለቃ፣ መስሪያ ቤቱን አዲስ እንዳደረገው ያምናል፡፡ ደሞዝ ስለጨመረ አይደለም፣ ጊቢውን ስላሳመረ አይደለም፣ ስቱዲዮ ስለገነባ አይደለም፡፡ ቤቱ የሁላችንም ነው ብሎ ሁሉንም፣ ባለቤት እንዳደረጋቸው ስለሚሰማቸው ነው፡፡
ምሣሌ ሁለት
- ሁለተኛው ምሳሌዬ፣ ፈልም ሳይሆን፣ እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡
- ሰሊንበርገር (በቁልምጫ ስሙ፣ ሰሊ) አሜሪካዊ ፓይለት ነው፡፡ አደጋው ከደረሰ፣ ትንሽ ቆይቷል፡፡ ሰሊ፣ 155 መንገደኞችን አሳፍሮ፣ አገር አማን ነው ብሎ ሲጓዝ፣ አሞራዎች፣ ከሚያበርረው አውሮፕላን ጋር ተጋጭተው፣ ሁለቱንም ሞተሮች ያበላሹታል፡፡ አውሮፕላኑ አየር ላይ ሳለ፣ ሞተሮቹ ከጥቅም ውጭ ሆኑ፡፡ ሰሊንበርገር፣ ያን ሁሉ መንገደኛ እንደጫነ ያውቃል፣ ሞተሮቹ መስራት እንዳቆሙም ተረድቷል፡፡ ሰውየው፣ ይህ ሆነ ብሎ አልተርበተበተም፡፡ አቅሉን አልሳተም፡፡ ፓይለቱ፣ ምንም ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ፣ አደጋውን ለአየር ተቆጣጣሪዎች አስታውቆ፣ ሁኔታውን ለመንገደኞች በእርጋታ አስረድቶ፣ መሬት ላይ ቢፈጠፈጥ፣ አውሮፕላኑ ፈንድቶ፣ ሁሉም እንደሚያልቅ እንደሚያበቃለት ተረድቶ፣ ቀስ እያደረገ ወስዶ፣ አውሮፕላኑን፣ ባህር ላይ አሳረፈው፡፡ 155ቱም መንገደኞች ተረፉ፡፡
- የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ደርሰው ሁሉንም በሰላም አወጧቸው፡፡ አደጋው ከባድ ስለሆነ፣ ጉዳዩም እስኪጣራ ድረስ፣ ሰሊ፣ እረፍት ወሰደ፡፡ ምርመራው አልቆ፣ ፓይለቱም እረፍቱን ጨርሶ፣ ወደ አውሮፕላን ማብረሩ ተመለሰ፡፡ በመጀመሪያው ቀን በረራ፣ አስተናጋጇ፣ በዚህ ቁጥር፣ በዚህ አውሮፕላን፣ ዛሬ የምንጓዘው በካፕቴን ሰሊ አብራሪነት ነው! ስትል መላው መንገደኛ፣ በአድናቆት አጨበጨበ፡፡
- አሜሪካውያን ሰሊንበርገርን፣ በፍቅር እና በቁልምጫ፣ ‹‹ሰሊ›› እንደሚሉት ሁሉ፣ እኛም አለቃችንን፣ ‹‹ማሜ›› እያልን ነው የምንጠራው፡፡ ማሜም እንደ ሰሊ ሁሉ፣ በብዙዎች (ሁሉም አልልም፣ በሁሉ የሚወደድ አለቃ የለም) ከመወደድም ሌላ፣ ሞተር ቢጠፋ፣ ግርግር ቢነሳ፣ የሚርበተበት አለቃ አይደለም፡፡ አዲስ ዋልታ ከሌሎች ጋር ተዋህዶ፣ አዲስ ኩባንያ ይመሰረታል የሚል ጭምጭምታ መናፈስ ከጀመረ፣ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ አሞሮቹ፣ በየአቅጣጫው እየበረሩ ነው፡፡ የማሜ ሞተር ግን አይቆምም፣ ቢቆምም፣ አውሮፕላኑ እየበረረ ነው፡፡ በቀደም፣ እጃችንን ይዞ፣ ያልቆመውን አውሮፕላን አሳየን፡፡ (ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የጀመራቸውን ወደ 20 የሚጠጉ ፕሮግራሞች፣ ያስገነባውን ስቱዲዮ፣ ያሳደሰውን ህንጻ፣ ያስዋበውን ግቢ፣ የገነባውን ቲም እና የስራ ባህል ልርሳው) በዚህ የግርግር ሰዓት፣ ማሜ እና ልጆቹ (እሱ ልጆቼ ነው የሚላቸው) በአዲስ ዋልታ፣ አዲስ ፖድካስት ማውጣት ጀምረዋል፡፡ የአረንጓዴ ሽልማትን 2ኛ ዙር ለመጀመር፣ እያሟሟቁ ነው (እንደ ናሳው የጥበቃ ሰራተኛ፣ እያሟሟቅን ነው ብል አይሻልም!)፡ ‹‹ካሪቡ አፍሪካ›› የተባለ፣ አዲስ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አስመርቀናል፡፡ በመደመር ትውልድ ዙሪያ የተሰራ ዶኩሜንታሪ ፊልም ሰርተን ጨርሰን፣ ማስመረቅ ብቻ ነው የሚቀረን፡፡ በኢትዮጵያ የውሀ ስትራቴጂ ላይ የሚያጠነጥን፣ አዲስ መጽሀፍ አሳትመን፣ በቅርቡ እናስመርቃለን፡፡ የማሜ እና ልጆቹ አውሮፕላን አይቆምም፡፡ የዚህ ሰራተኛ ቡድን አንድ አባል በመሆኔ፣ እኮራለሁ፡፡ ቤቱን፣ ቤቴ ስላደረግከው፣ አመሰግናለሁ ማሜ! ፍለጋው ግን አያልቅም፡፡
Read 643 times