Sunday, 18 February 2024 00:00

የደራሲው የከሸፉ ሙከራዎች

Written by  -ምግባር ሲራጅ-
Rate this item
(4 votes)

ዘመናዊ ልብወለድ ትረካ ውስጥ ስሜትንና ድርጊትን Juxtapose በማድረግ በስንት ነገር አባብለን ያረጋነውን ልቡና በመረበሽ የለመድነውን የልብወለድ ተዋረድና ቅርፅ ማሳሳት አንዱ መታያው ነው፡፡ ዛሬ የምንዳስሰው ልቦለድ ደራሲ ይህን ስልት ይሁነኝ ብሎ በመጠቀም የDeconstruction  ሙከራውን ለማሳየት ያደረገው ጥረት ቢበረታታም ፣ ተሳክቶለታል ማለት ግን አይደለም፡፡ ይህ ጽሑፍ በደራሲው የተሞከሩ ሙከራዎች እንዴትና በምን ምክንያት እንዳልተሳኩ ግላዊ ምልከታ የሚታይበት ነው፡፡
መግቢያ
“እንላለን እንደዚህ … ገሃዱ ዓለም የሥነ ጽሑፍ ነፀብራቅ ነው፡፡ ገ.10”
ይህ ከላይ ያስቀመጥኩት ደራሲው ማለፊያ ብሎ በሰየመው ምዕራፍ ላይ ያለ statement እንደ መነሻ አድርገን ወደ ሌሎች ጉዳዮች እናልፋለን፡፡ የዚህ ሀሳብ ግልባጭ (ሥነ ጽሑፍ የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ ነው) በቀደምቶቹ ፈላስፎች (ፕሌቶ እና አርስቶትል) ዘንድ Mimesis በሚል ስያሜ የለፋ ርዕስ ነበር፡፡ ነበር ያልኩበት ምክንያት እነርሱን ተከትሎ ኪነጥበብን ለመረዳት የሚያስችሉ አያሌ ድንጋጌዎችን ያቀረቡ ህሩያን መኖራቸውን ከማሰብ ነው፡፡ ይሄ ፕሌቶ በሪፐብሊክ ፣ አርስቶትል በፖኤቲክ ላይ ያቀረቡትና ሰፊ ትንታኔ የሰጡበት የኪነጥበብን የቅጂነት ባህሪ Noal Carol ለአያያዝ እንዲመች አድርጎ እንዲህ አቅርቦታል፡፡
‹‹X is an art work only if it is an imitation.››
ዓለም ስለ ኪነጥበብ ያላትን ግንዛቤ እያሻሻለችና እያደሰች የሄደችበት ርቀት እንዲህ የሚባል አይደለም፡፡ አንዱን ስታነሳ፣ አንዱን ስትጥል ብዙ ምዕራፎችን እልህ አስጨራሽ በሆኑ Discourses አድርጋና፣ እልፍ ሀሳቦች ደልድላ ነው የዛሬ ከፍታ ላይ የደረሰችው፡፡ ሪፕረዘንቴሽናሊስቱን፣ ኒዎሪፕረሰንቴሽናሊሰቶቹ ተው ሲሉ፣ እነሱን ኤክስፕረሽኒስቱ ተው እንዲያ አይደለም ሲል፣ እንዲህ ሲል እንዲያ ሲል ብዙ ተጉዟል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሁሉ መሀል ጥያቄዎች ቢነሱበትም አጥጋቢ የሆነ ጽሑፍ ያልተገኘለት የmimesis ጉዳይ ነው፡፡ ከዘመናት በኋላ ግን የዚህ አካሄድ መሰናክል ሆኖ የቀረበው የRomantisism አቀንቃኙ ኦስካር ዋይልድ ነው፡፡ ዋይልድ በ1891 ዓ.ም በሶቅራጢሳዊ ዲያሎግ እየተመራ ባዘጋጀው ድራማ ቀመስ The Decay Of Lying በተሰኘ Essay ላይ በይፋ ፀረ-ሚሚሲስነቱን አወጀ፡፡ ኦስካር በዚህ ኢሴይ ውስጥ ባሉት ቪቪየንና ሲሪል በተባሉ ገፀባህርያት በኩል ያሳለፈውን አቋሙን ለማስረገጥ የሄደበት ርቀት እፁብ ነው፡፡ (    A great Artist invents a type, and life tries to copy it, to reproduce it in popular form, like an enterprising publisher እስከማለት ሁላ ደርሶ ነበር) ዋይልድ ይሄን statement ለማሳየት The Picture Of Dorian Gray የሚል ልብወለድ ጽፎ አስነብቧል፡፡ ዋይልድ ጥበብን ከሕይወት ጥገኝነት ለማስለቀቅ ብዙ ጥሯል፣ ስለጥበብ ኃያልነት ሲሰብክ፣…. ጥበብ በፈቀደች ጊዜ ተዓምርን ትሰራለች ፤ አርዌን ከምድር ሆድ በዐይን ጥቅሻ ታስፈነጥራለች ፣ ብቻ ትሻ እንጂ ፤ ለጥበብ ሁሉ ይቻላል ፤ ለሕይወት ይሆንላታልን? ብሎ ይሞግታል፡፡ ይህን ስቴትመንቱንም  … Life imitates Art far more than Art imitates life በሚል መፈክር መራው፡፡
ሰንበት ለሰው እንጂ፣ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም
(ፀሐይ ከጨለማዬ ምን አለሽ?)
ደራሲው ፀረ-ሚሚሲስ የሚያሰኘውን አቀራረብ ይዞ መምጣቱ በራሱ የሚያስመሰግነው ቢሆንም፣ በአቀራረብ ብልሃቱና የአገባብ ሂደቱ ከትችት አልዳነም፡፡ በማለፊያ ምዕራፍ ላይ ደራሲው የሚከተለው የልቦለድ አጻጻፍ beyond Story እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ለዚህ ማሳይያ የሚሆን ምሳሌ፡-
ከመሰረታዊ ግንዛቤያዊ ፍቺው አልፎ መታየቱ (ገፅ 10)
የገሃዱን ዓለም እንደወረደ ከመዘገብ ተሻግሮ የራሱን ምትሃታዊ ዓለምና አድማስ ይፈጥራል (ገፅ 10)
ታሪኩ ባለው አቅም ልክ ሲያዝን አብሮት እንዲያዝን፣ ሲደሰትም እንደዚያው ያስደርገዋል (የአርስቶትል ካታርሲስ) (ገፅ 13)
እኚህ ደራሲው ከላይ ገሃዱ ዓለም የልብ ወለድ ነፀብራቅ እንደሆነ ለማሳየት ያመጣቸው አስተያየቶችን ፣ከእነ ፕሌቶ አሳብ ጋር ተርታ ብናቆመው ልዩነት አይገኝበትም፡፡ ከላይ የፃፍኳቸውና እነሱን መሰል ጉዳዮችን መግቢያው ላይ ነግሮን የጀመረው ደራሲው፤ መጽሐፉ ውስጥ ስንገባ ቃል የገባልን ሁሉ እንደሌለ እንገነዘባለን፡፡ ደራሲው ጦርነትን (ከጦርነትም ቀለሃው ጨሶ ያልወጣለት የአሁናችንን ጉዳይ) ተንተርሶ ከመጻፍ ባለፈ ለሀተታ በቀረበ መንገድ በሚያቸክ ትረካ ያደከመን ሳያንስ፣ ከመሰረታዊ ግንዛቤያዊ ፍቺው አልፎ ሲለን ሣተ፡፡ እዚህ ጋር ከመላው ዋይልድ ሀሳብ ጋር ይጋጫል፡፡ ልቦለድ የራሱን ይፈጥራል እንጂ አይቀዳም፡፡ (Wordsworth went to the lakes, but he was never a lake poet) ከዛ በመቀጠል ልቦለድ የራሱን ምትሃታዊ ዓለም ፈጥሮ ዓለምን ማስከንዳትና ገረዱ ማድረግ እንዳለበት ይነግረናል፡፡ ይህን የደራሲውን ሀሳብ በራሱ ልቦለድ ውስጥ ባላገኘውም የሀሳቡ አንሺ ዋይልድ ያለውን አስታውሼ ወደ ተመጣጣኝ ምሳሌው አልፋለሁ፡፡ [Literature always anticipate life, it doesn’t copy it, but mould it to its purpose. Oscar Wilde]  ኩንዴራ The farewell party በተሰኘው መጽሐፉ ላይ የምናብን ዓለም ተጠቅሞ የገሃዱን ዓለም በአንድ ስንዝር የቀደመበት Artificial Insemination መፍጠሩ ነው፤ ምናልባት የራስን ምትሃታዊ ዓለም መፍጠር ማለት፡፡ እኚህን እንደምሳሌ አነሳሁ እንጂ በደራሲው የተነሱ ሀሳቦች ሁሉ የንድፈ ሀሳብ ችግር ሳይኖርባቸው ግን ደራሲውን ስላልተዋሃዱት ብቻ በልቦለዱ ውስጥ የማናገኛቸው ሆነዋል፡፡
ሕይወት ከጥበብ የምትቀዳ ከሆነች፣ ገጸባህርያትና ኩነቶች ከሕይወት ሊሆኑ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ሕይወት ከሕይወት ብሎ ነገር ሊኖር ስለማይችል፤ (በዴካርትኛ Consciousness is conscious እንደማለት ይሆናል) እርስ በርሱ ጥል ነው፡፡ እንደዛ ከሆነ ደራሲው ጦርነትን ልክ እንደ Existential situation አድርጎ ሲያመጣ የተነሳበትን ረስቷል (ፀረ-ሚሚሲስ አቋሙን)፡፡ በዚህም ሳቢያ ልብወለዱ አጉራ ዘለል በሆኑ ባዕዳን ድርሳናት እንዲደፈር ሆኗል፡፡ ደራሲው ከልቦለዱ ይልቅ ለታሪክ አጋጣሚው ያዘነበለ ይመስላል፡፡ (The Novelist neither historian nor prophet; he is an explorer of existence. Kundera) ደራሲው በቋንቋ ችሎታው የሚታማ አይደለም፡፡ ይህንን ተጠቅሞ ጥሩ ነገር መስራት የሚያስችል አቅም እንዳለው የማይካድ ነው፡፡ ነገር ግን በገለፃ ያበዱ ገፆች ለታሪክ ባዳ ሆነው ሲታይ ያስደነግጣል፡፡ ይህንን አስመልክቶ ሰሎሞን ዴሬሳ በጎሕ መጽሔት ቅፅ 2 ኅዳር/1994 ዓ.ም፣ ደራሲና፣ ድርሰት፣ አንባቢ በሚል ርዕስ ስር የፃፈውን እናስታውስ፣
“ደራሲው ሀሳቦች አሉት፡፡ እነዚህን ሃሳቦች ወደ አንባቢው አንጎል ማስተላለፍ ይፈልጋል፡፡ ወይም በድል አድራጊነቱ፣ በተሸናፊነቱ፣ በሀዘኑ፣ በፍስሐው የስሜት ተካፋዮቹ እንድንሆንለት ይመኝ ይሆናል፡፡ በዚህን ጊዜ በዝንጉነትም ሆነ በሌላ ምክንያት የእውቀቱን ስፋትና የቋንቋ ችሎታውን እንደ አሩሲ ጨሌ መደርደር የጀመረ እንደሆነ የጥረቱን ምክንያት ደራሲው በገዛ እጁ (አባለገው) ጠወየው ለማለት ይቻላል፡፡”
በቀደመው ዘመን የልቦለድ አጻጻፍ ስርዓት ውስጥ ያሉትን አንዳንድ ሕግጋት በመጣስ ደራሲው ራሱን ከዘመናዊው የልቦለድ አጻጻፍ ጋር ለማሰለፍ ጥረት ያደርጋል፡፡ በዚህ ይሁነኝ ብሎ በመረጠው ጎዳና ላይ ያረጀው ዘዴ naturalism እና realism ናቸው፡፡ በእውናዊው የአጻጻፍ ስልት ውስጥ የነበሩትን ደራሲው ሊያሟላቸው ግድ እንደሆኑ ታስበው ከተቀመጡ  አኋኋኞች (Constitutive elements) መሀል የገፀባህሪያት ቁመና፣ የአነጋገርና የአካሄድ ሁኔታን ወደ ጎን በመተው አዲስ አቀራረብን ተከትሏል፡፡ ይህ ማለት ደራሲው ጉዳዩን ሲነግረን ሥጋና ደም ይዘን እንድንከተለው የሚያደርግ ማስገደጃ ብልሃት ነው፡፡ ይህ ዘዴ በዘመናዊ ልብወለድ ድርሰት ውስጥ የተለመደ ቢሆንም፣ በኛ ሀገር ሥነ ጽሑፍ እምብዛም ነው፡፡ ይሄን ዘዴ መከተል ግን የሚያስከፍሉት ነገሮች በዚህ ልብወለድ ውስጥ ተዘንግተው ይታያሉ፡፡ ምስልና ምት፡፡ ይህ ልቦለድ ምስል ከሳችነቱና ምቱ ፈዛዛ ስለሆነ፣ አይደለም አድሮ ሊታወስ እየተነበበ ከስር ከስር እንዲረሳ ሆኖብኛል፡፡
ሌላው በዚህ ልብወለድ ድርሰት ውስጥ ሊነሳ የሚችለው ትችት፣ መሰረቱን ከገፀባህሪው ምንነትና ማንነት ላይ በመመርኮዝ ነው፡፡ ገፀባሕሪው ፍፁም መሲአዊ በሚመስል መልክ ከተራራ ላይ ሆኖ የሚጮህ ይመስላል፡፡ ይህ ዝንባሌ ደግሞ ከክርስትና አስተምህሮቶች የመጣ እንደሆነ ያስጠረጥራል፡፡ ገፀባሕሪው ያንን ሁሉ ልዕለ ተፈጥሮና የደቂቃን ነገር በኩነኔና በሀዘን መነጥር ሲታዘብ፣ ድንቁርናውንና ፀሊም ተስፋውን ከኮነነው ሕዝብ ጋር ስሜትና ዘመን አለመጋራቱ ያስተቸዋል፡፡ ማማ ላይ ሆኖ ተረከው እንዳንል (ሁሉን አወቅነቱ ከመንፈስ ስብራት ያድነዋል? እንባላለን) ዋልጌና ኋላ ቀር ሕዝብ መሀል በመኖሩ ማገሩን ተሸሽጎ የሚያልፍ አይጠፋም (አረ የሚሸናም አይጠፋ፣ በዚህ መሀል ባለጌ ጊዜ የብል ለምድ ለብሶ ገብቶ ማበስበሱ አይቀርምና) ከመውደቅ አይመለጥም፡፡ ዘመናዊ ደራሲ ዓለምን እንደ ፈጣሪ መልዕክተኛ ሪፖርት፣ የሰው ልጆች እንዲህ ሆነዋል፣ የሰው ልጆች እንዲህ ቢያደርጉ፣…. ላላላላ -- በማለት ደህና ራቅነው አይደርስብንም ወዳልነው ብሉያዊ አጨዋወት ሊመልሰን አይገባም፡፡
ዝንጀሮ መጀመሪያ መቀመጫዬን እንዳለችው ሁሉ ለደራሲም ገፀባሕሪያቱን ሲያሻው የሚገድልበት፣ ሲያሻው የሚያድንበት የተደላደለ የታሪክ መቀመጫ ያስፈልገዋል፡፡ አርኪሜዲስስ ከዚህ የተለየ ምን አለ “Give me a lever and fulcrum and a place to stand and I can move the earth.” አይደል ያለው፡፡ ቅርፁንም ፣ መልኩንም ምኑንም ለመነጋገር መጀመሪያ መቆሚያ አስተማማኝ ስፍራ ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ቦታ ስም ነው ታሪክ፡፡ ወልድ አብን ቢተርክ ከዙፋኑ ሆኖ አይደለም፡፡ ገፅ በገፅ ተተፍቶበትና ተገፍቶ ነው፡፡ ስላልተሸከሙት መስቀል ከላይ ወይ ከናዲር ሆነው ቢቀድዱ አይደልና ጣሩ ቅርፁን ለመለየት አይቸግርም? የዚህ መጽሐፍ አንዱ ጉድለትም ተረፈ ፍካሬ ኢየሱስ ከሚመስል የመከራ ድርሳን ባለፈ እንዲህ የሚባልለት የታሪክ ጉዞ ማጣቱ ነው፡፡ ገፀባሕሪውም የሀገሩን ሰቀቀን የቤተክርስትያን ጉልላት ላይ ሆኖ እንደሚታዘብ መዝገቡ ያለ ነው፡፡ ሀዘኑ ሁሉ እንዳፈረሰ ዲያቆን፣ ምክሩ ሁሉ የካህን፡፡ የባሩድ ጢስ እንዳያፍነው በተከናነበው ነጠላ በኩል ያንሾካሾካቸው ከሚመስሉ መስመሮች ውጪ እንዲህ የሚባል ታሪክ ማጣቱ ልቦለዱን ሽባ አድርጎታል፡፡ ሰፋ ባለ ርዕስ ብመለስበትም ነገሩን ለማንሳት ያህል በመራፅዮን የደራሲው የትረካው አቀራረብ Stream of consciousness ከሚባል ወገን እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ይሄ ፍፁም የተሳሳተ አረዳድ ነው፡፡ የደራሲው አቀራረብ ከStream of consciousness ለኑዛዜ የቀረበ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ በሰፊው እስክመለስበት ኩንዴራ ያላትን ብለን ወደ ሌላው ልቀጥል፣ (The novel is not the authors confession, it’s an investigation of human life in the trap the world has become. The unbearable lightness of being)
በመጨረሻም፡- ደራሲው ሊቀርበን በሄደበት ርቀት ልክ እንዲርቀን የሚያደርገውን ፍኖት መርጧልና ስላለመገናኘታችን እንማልዳለን፡፡
2. አንታራም ልብወለድ
የልቦለዱ አወቃቀር ሳየው የማሕሌት ጉዳይ ደራሲው ልብወለዱን ጽፎ ከጨረሰ በኋላ የታሰበበት ይመስላል፡፡ ከመሰረቱ ማሕሌትን የልብወለዱ መስሪያ ጡብ አድርጎ ቢጠቀመው ኖሮ፣ አሁን ያለውን ዓይነት ድርሳን ይወጣዋል ብዬ አላስብም፡፡ እዚህ ጋር ራሴን የምጠይቀው ጥያቄ አለ፡- ማሕሌታዊ ነው ሳልባል ባነብበው ፣ ማሕሌታዊ መሆኑን የምደርስበት ፍንጭ አገኝ ነበር?
መልሱ ቀላል ነው፡፡ አይደልና ካለስያሜ ተሰብኬም ባገኘሁት የሚል ነው፡፡ ምክንያቱ ምን ይሆን ብዬ ለመመርመር ስሞክር ከታች ያሉትን እንደመነሻ አግኝቻለሁ፡፡ እነሱን ከመዘርዘሬ በፊት በዋናነት ልብወለዱን ያደናቀፈው የአወቃቀር ችግር መሆኑን ገልጬ ልለፍ፡፡ ደራሲው ልብወለዱንና ማሕሌትን አንድነት የሚያመጣበት ሁነኛ መስመር ያጣ ይመስላል፡፡ በዚህም ምክንያት ልብ ሊያለሰልስ በተፈጠረ ሙዚቃ ምትክ Cacophonic ጩኸት በየመስመሩ ይበትናል፡፡ ይሄ ደግሞ የArcheological clarity ችግር ነው፡፡ በዚህ መነሻነት የልብወለዱ የመጨረሻ ገፅ ላይ ተኩኖ መነሻን ለማየት ያስቸግራል፡፡ ይህ የማሕሌት ባህሪ አይደለም፡፡ አይደልና ሦስት ምዕራፍ ከደጁ ርቀው ይቅርና ከምዕታት በኋላ ልብ የሚተመትም የነዝናዥ ትውስታ ጌታ ነው፡፡ በደራሲው የማዋቀር ችግር ምክንያት ማሕሌትን ተረሺ እስከማድረግ ደርሷል፡፡ ሌላው ቢቀር እንዴት ከበሮው ልብ አይነዝርም ነበር?
አሁን ከላይ ወዳነሳናቸው ዝርዝር ጉዳዮች ልለፍ፡፡
አንደኛ ማሕሌትን በቁስ ውክልናው ብቻ ለመድረስ መሞከሩ ላይ ነው፡፡
እዚህ ጋር ደራሲው የዘነጋው ማሕሌት በተለያዩ ቀለማት ውስጥ ራሱን የሚገልጥ Sheet music መሆኑንም ጭምር ነው፡፡ ይህንን የማህሌት ባሕሪ ሳያስተውል ደራሲው በመግቢያው ላይ (ሥነ ጽሑፍ ነገረ ሰብኅን ለመመርመር የማይዛመደው፣ መጠቀሚያ ገንዘቡ የማያደርገው የጥናት መስክ የለም፡፡ ይህ በምድራችን ላይ ኃያል መሳሪያ ያደርገዋል፡፡ ገፅ 13) ባነሳው ጉዳይ መንስኤነት ማምጣቱ አደጋ አለው፡፡ በዚህ የደራሲው ሙከራ ውስጥ እርስ በእርሱ የሚጋጭና ጥንነት የሌለው ዝምድና ይታይበታል፡፡
ከገፅ 210 ጀምሮ ስለድርሰቱ ቅርፅና የትዕምርት አጠቃቀም ሲያወራ እንዲህ ይላል፡፡
ስለ አንደኛው ምዕራፍ ሲያወራ፤ “ከአንቀጹ ጠጣር ፍልስፍናዊ ባሕርይ አንፃር በግዕዝ ተወክሏል፡፡ (የአናቅጹ ጥጣሬ ምስክርነት ያገኘው በራሱ በደራሲው መሆኑን ልብ ይሏል)
ከዚሁ ሳንወጣ መቋሚታው ደግሞ ድምፅ አልባነቱን ተከትሎ እንደተሰየመና ውክልናውንም ያገኘው “በሦስተኛ መደብ የሚተረክ ተረክ ድምፁ በወል አይታወቅም” ከሚል መደምደሚያ መሆኑ በጣም ያሳዝናል፡፡
እዚህ ጋር ልብ ልንለው የሚገባን አንድ ጉዳይ ድምጹ በወል አለመታወቁ ድምጽ አልባ ከሆነው መቋሚያ ጋር ዝምድናው ለየቅል መሆኑ ነው፡፡
ስለ ሁለተኛው ምዕራፍ ሲያወራ፤ “ተራኪው እንደ መቋሚያ ዝም አይልም፡፡ ይልቁንም እንደ ጸናጽል የሚለይ ድምጽ ያወጣል፡፡ ይንሿሿል፡፡”
በመቋሚያ ዘመን ተራኪው ማን ነበር? ምን እየተደረገስ ነበር?
ይህንና መሰል ጉዳዮችን ይዞ ቅርፅ ለመስጠት መቸኮሉ፣ ደራሲውን ምን ተይዞ ጉዞ እንድለው ያስገድደኛል፡፡ ከእነኚህ ቅርፆች የተረዳሁት፣ አንድ ቀን አድባር ፈቅዳልኝ እኔም ዘለግ ያለ ድርሰት ለመድረስ ብበቃና ድርሰቱ እንደቀበቶ ዞሮ የሚገጥም ታሪክ ቢኖረው ቀበቶአዊ ብዬ መሰየም እንደምችል ነው፡፡ ደራሲው ልቦለዱን የጠወየው ጠንካራ ያደርገዋል ብሎ ባሰበው መንገድ ነው፡፡ ማሕሌት በዚህ ልቦለድ ውስጥ Achilles Hill ነው፡፡ ደራሲው ማሕሌታዊ ትርክቱን ለመታከክ የሞከረው በreference መጻሕፍትና በትዕምርት አጀብ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የሚያዛልቅ አይደለም፡፡
እንደ ማጠቃለያ፡- ማሕሌትን ከጥንት ሀገር አምጥቶ ሳያዘፍኑ መሸኘት ተገቢ ነውን? አይደለም በእውነት፡፡ ቁምነገሩ፡- ከበሮውም፣ ጽናጽሉም፣ መቋሚያውም እፊታችን ሆኖ ድምጹን የተቀማበት ሰሞነ ሕማማት ከማሕሌት ለዚህ ልቦለድ በቅርፅነት ይቀርባል፡፡
ማጠቃለያ
“ይህ መጽሐፍ የድርሰት ቅርፁን በሃይማኖት አጥር ውስጥ ካሉ የዜማ ስልቶችና ምልክቶች፣ እንዲሁም የዝማሬ ቁሶች ይዋስ እንጂ አንድምታው ልብወለድ ነው፡፡ በይዘቱም ሃይማኖታዊ ድርሳን አይደለም፡፡ ገፅ 217”
የዚህ ልብወለድ ድርሰት ገፀባሕርይ እንደ ቴዲ አፍሮ ግጥም “አዳም የት ነህ?” የሚል ከትናንት ሕይወቱ ዛሬ ላይ የሌለው፤ ለአምላኩ ያስለመደው አኮቴት እንቅልፉን በውኃ የሚያፍን ጥሪ የሚያባንነው ነው፡፡
“ወደ ኋላ ስመለከት በአርባ ቀኔ ተጠምቄያለሁ፡፡ ከክርስቶስ ጋር ሞቼ ተነስቻለሁ፡፡ አሁን ጋን ከየውሃት ጠባይዕ ርቄያለሁ፡፡ ገፅ 73”›
“ነፍሴ ኮብልላ የጠፋችው በግዕዝ፣ በዕዝል፣ በአራራይ የዜማ ስልት ነው፡፡ ልቤ ከማሕሌት፣ ከመወድስ፣ ከመረግድና ጽፋት የከበሮ ምት ጋር አብራ አርግዳለች፡፡ ገፅ 68”
“ለእኔ እዚህ ዓለም ላይ የንፅህና ተምሳሌት ብላቴና ሳለሁ ቀድደው ያለበሱኝ፣ ቆርሰው ያጎረሱኝ ካህኑ አባቴ ናቸው፡፡ ድርገት ሊወርድ ሲል ከእቅፍ ወርጄ ከሕፃናት ጋር የጌታዬን የመድኃኒቴን የኢየሱስ ክርስቶስን እውነተኛ የጽድቅ መብል፣ አማናዊ ሥጋና ደሙን ልቀበል እሰለፍ ነበር፡፡  ገፅ 78”
እኚህንና መሰል ጉዳዮችን በማየት ገፀባሕሪው እንዴት ያለ እንደሆነ ለመገመት ከባድ አይደለም፡፡ ችግሩ እዚህ ጋር አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ ያለው ከወዲህ ነው፣… የዚህ ሁሉ መዓትና የመጠፋፋታችን ስር መሰረታችንን ከማጣት እንደሆነ ይነግረናል፡፡ እንዲህ የሆንነው መነሻችንን ስለተውን፣ ስልጣኔን እንደክፉ አርዌ ከደጅ መመለሳችን እንደሆነ ሲነግረን ምቹውን አፀድ ከተቃኘበት አፀድ ማሻገር ሲሳነው ይስተዋላል፡፡ ደራሲው ጦርነትን ታክኮ ይለፍ እንጂ ሀዘኑንና ቁጭቱን የሚያባብልበትን መንገድ ከመስቀል ማውረድ ተስኖታል፡፡ በዚህም ደራሲው Secular መሆን እንደተሳነው እንገነዘባለን፡፡
ሌላው ፡- ከርዕሱ በመነሳት “ፀሐይ ከጨለማዬ ምን አለሽ?” ጽግው ዜጋን ከመፍጠር አንጻር የጥንት የግሪክ ፈላስፎችን ሀሳብ ወደጎን በማድረግ (የብርሃን ሕሊና አፈላላጊ የሆነውን የፕሌቶን ሀሳብ ለምሳሌ) የራስን ጨለማ አልምዶና ገርቶ አብሮ መኖርን ማስቻል ከሚሰበክበት የማኪያቬሊያን ጎራ የተሰለፈ ይመስላል፡፡ በዚህ ምርጫውም የልብወለዱን ገፀባሕርይ ጥልቅ ባይተዋርነት ውስጥ ይጥለዋል፡፡ ዓለምን ከዛ ሆኖ ማየት ቢፈልግ ከፀሐይ ጧፍ ዘመዱ እንድትሆን ተደርጎ ተጥሏል፡፡ ይህ የደራሲውን Melancholia ቤኬት አለውልህ ሲለው እንዲህ፣… Art is the apotheosis of solitude.
ስለሌሎች ጉዳዮች ለምርቃት …
የገፀባሕሪው ገጣሚነት የቱ ጋር ነው? ከማዕረግነት የዘለለ ምን መታያ አለው? በሰሎሞን ግጥም ነው ራሱን የሚገልጠው? አንድ ባለቅኔ ገፀ ባሕሪስ ደራሲውን ባለቅኔ የማድረግ ስልጣን የለውም ወይ?
የዚህ ሁሉ ኩነኔ ሞቲፍ ምንድን ነው?
ደራሲው ልብወለድ እየፃፈ እንደሆነ ድንገት በየመሀሉ እየባነነ እንደሚያስታውስ የሚያስታውቁ የጭብጥና የፍሰት ተዛምዶ የሌላቸው ደንቃራ ገፆች ምስክር ናቸው፡፡
ገፀ ባሕሪው አባ (የማደጎ አባቱ) የሚላቸው፣ ከልቡ ተፍቆ የረገፈውን በማሕሌት የታጀበ ልጅነት የሚያስታውሱ ያሬዳዊ ተምሳሌት ያላቸው ይመስላሉ፡፡
የገፀባህሪው theme ያለው አባ ውስጥ ይመስለኛል፡፡ የእርሱ ተክለ ሰውነት ሁሉ በአባ ውስጥ ተገልጸዋል፡፡ እሳቸው የእሱ Ideal self ናቸው፡፡
የአባን የማደጎ አባት አለመሆን እስከመጨረሻ ይዞ መጥቶ አፈንድቶ መሄድ ምን የሚሉት ነው? የልቦለድ አፕሪል ዘ ፉል መሆኑ ነው? ምንድን ነው? ክሊፍአንገር መሆኑ ነው? ልቦለድን አድፋፋው ማለት ይሄኔ ነው፡፡
ለዛሬ በዚህ ይብቃንና በምዕራፍ ሁለት ስለ Stream of consciousness and psychological novel እናወራለን፡፡ ለውይይት በሩ ክፍት ነው፡፡….

Read 348 times