Monday, 19 February 2024 08:08

ኑሮ ዘለሰኛ!

Written by  -ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(2 votes)

እዩት እዚያ ማዶ ብርሃን ያድላሉ፣
አሁን እኔ ብሄድ አለቀ ይላሉ፤
ሃያሲ አብደላ ዕዝራ እየመላለሰ የሚተነትነው የልመና ግጥም ነው። ግጥሙን መላልሶ ይወርደውና አይኖቹን ጨፍኖ ይማልላል።
    “አየህ? አየህልኝ?... እዚህ ግጥም ውስጥ በግልፅ ሳይሆን ተሸፋፍኖ፣  ተከዳድኖ የቀረበ አንዳች ጭብጥ አለ። ዕጣ ፈንታ!! አየህ እንዴት እንደተንኳሽ? አየህልኝ እንዴት እንደተኳኳለ? በሁለት አርኬ ግጥም ይሄን ያህል፣ እንደ ህዋ ውስጡ ቢገቡ ፍጥረት ሁሉ የሚጠፉበት ርዕሰ ጉዳይ እንዴት ተጠቀለለለት? የትኛው ዘመናዊ ገጣሚ እዚህ የአገጣጠም ከፍታ ላይ ደርሷል? እንዴት ያለ ጉልበት ነው? ይሄ የኔ ብጤ ሌሎች ቅኔዎች ይኖሩት ነበር ይሆን?...”
አቀርቅሮ፣ መላልሶ ወደ ማሰላሰሉ ይነጉዳል።
ሥነ-ግጥም በሉት ወለሎ፤ ወይ ሌላ ጥበብ ምንጩ ደረቅ ትምህርት እና ዕውቀት ሳይሆን በህይወት ፍም ላይ እያጤኑ መብሰል ነው ሲሉ የሚከራከሩ አሉ። ትክክል ሳይሆን አይቀርም። ይሄ የአብደላ ዕዝራ የኔብጤ የአይነስውርነት ዕጣ ፈንታውን፣ ያለበትን የልመና ፍዳ፣ ከእነዚህ የተደመደሙ ፍርጃዎች ለመላቀቅ ያለውን ያልተሳካ ምኞት…. ከጥቆማዎቹ ተነስተን እንድንረዳ ያስገድደናል። ዕውነትም ሌሎቹ ቅኔዎቹ እና ማንነቱ (ባይደረስባቸውም) ያጓጓሉ።
ብላቴን ጌታ ማኃተመ ስላሴ ወልደመስቀል በስብስብ ሥራቸው ውስጥ እንደዚኛው የረቀቁ  አይሁኑ እንጂ አንዳንድ የልመና ግጥሞችን ከትበው አስተላልፈውልናል። ልመና የተነወረ ተግባር መሆኑ ሳይዘነጋ አጅበውት የሚመጡ ጥበቦች ካሉ ማጤን  እንደ ጠቃሚ ጎን ሊወሳ ግድ ነው።
ሰርቼ በበላሁ ነበረ ምኞቴ፣
ብርሃኔ ተይዞ ቢነሳኝ ጉልበቴ፣
አልቅሼ እበላለሁ እንደ ልጅነቴ፤
ይሄም ግጥም አንዳች የሚከነክንና የሚኮረኩር ጉዳይ ማንሳቱ ጠንካራ ጎኑ ነው። ሰርቶ መብላትን እየቃበዙ፣ በለምኖ መኖር መታበት የዚህ ገጣሚ አይነስውር ዋነኛ ጭብጥ ነው። ከአይነ ስውርነት ባሻገር የአካልን ሰርቶ ለመኖር አለመብቃት የሚያወሳ ሌላ ገጣሚ በብላቴን ጌታ ማኅተመ-ሥላሴ ስብስብ ውስጥ ይገኛል።
እዩት እጄ ሞቶ፣ እዩት እግሬ ሞቶ፣
ያስለፈልፈኛል ሆዴ ብቻ ቀርቶ፤
መነሻ ጉዳዬ ከልመና ቆሻሻ መድፊያ ገንዳ ውስጥ የተገኙ የግጥም ዕንቁዎችን እየለቀሙ ማሳየት አልነበረም። የነገር ደራሽ ይዞኝ ነጎደ እንጂ…
    … ባለ ብሩህ አእምሮ የኔብጤዎችን ከግጥማቸው አንጻር አንስቶ ማመናተል፣ የኛ የቅርብ የቅርቦቹ ጅማሮ አይደለም። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ተግሳፅ”  ብሎ የሰየመው መጽሐፉ ውስጥ እንዲህ የሚል የአብሰልስሎቱ ግልባጭ ሰፍሯል።
“ነዳይ ያልነው ባለፀጋ ነው።
“በብልፅግናው ልክ ችጋሩ እንደዚያው  ይበዛልና። አንድም ባለፀጋ ነዳይ አእምሮ ነው። በብልፅግናው ልክ ከዕውቀት መቸገሩ እንደዚያው ይበዛልና።”
የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መልዕክት ግልፅ ነው። ከማያስብ ባለፀጋ፣ የሚያስተውል ነዳይ ይበልጣል የማለት ያህል ነው። በእርግጥም በሌሎቹ ጥቅሶቹ ደጋግሞ የሚያወሳው ይህንኑ ነው። መንፈሳዊ ሰው ስለሆነ አለማዊውን ድሎት የሚያናንቅ አዝማሚያ አለው። “በዚህ ዓለም ስደተኛ መጻተኛ መሆን ይገባናል” ይላል። መልሶ ደግሞ “የምፅዋትን ስራ አፅንተን እንያዝ” መልዕክቱ ነው።
ነባሩ፤ ምናልባትም በግጥምና በዋሽንት እንዲሁም በአዚያዚም ጥበብ ላይ የተመሰረተው ልመና ጠፍቶ በማሳቀቅና ይሉኝታን በማውለቅ የተንሰራፋው ንጥቂያ አከል የምጽዋት ጥያቄ ላይ ደርሰናል። ችግሩ፤ እንደ አሸን የፈላ ተመጽዋች ከቤቱ ወጥቶ አደባባይ ላይ እንዲሰየም አስገድዷል። የዚህ ዘመን ለያዥ ለገናዥ ያስቸገረ የልመና ጠባይን ያጠናው ያለ አይመስለኝም። ልክ የዛሬ ስድሳ ዓመታት ገደማ በልመና ላይ አንድ ጥናት ተካሂዶ ነበር። ይህን ጥናት “ብርሃን” የተሰኘ መጽሔት በ1968 ዓ.ም በቁጥር 15 ዕትሙ ይዞት ወጥቷል። ሲቆነጠር እንዲህ ይላል፡-
“እንደፈረንጆቹ አቆጠጣር በ1974 ዓ.ም የድኩማን መርጃ ድርጅት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ቆጠራ ካደረገ በኋላ የለማኞች ብዛት 11,000 እንደሚደርስ ታውቋል። ከዚህ ውስጥ 5,000 የሚሆኑት ወጣቶች ናቸው።”
ያኔ ነዋሪው ስንት ሆኖ የለማኙ ቁጥር እዚህ ደረሰ? ያሰኛል። በጥናቱ ላይ በገደምዳሜ እንደተገለጸው ከሆነ ተቸግሮ፣ አቅም ጠፍቶ፣ ዕድሜና ጤና ማጣት ገፋፍቶት ለልመና እጁን ከሚዘረጋው እኩል ወጣቱ፣ መስራት የማይፈልገውና ምፅዋትን የማይጸየፈው ዓይን አውጣ ቁጥሩን እጥፍ አሳድጎታል። ይሄን- ይሄን ስንመለከት በጊዜው የተካሄደው የባህል አብዮት መክሸፉ የዚህን ዘመን ዋልጌ ቁጥር ከፍ እንዳደረገው እንረዳለን።
ሁልጊዜም ልመና የመሳሰሉ ማኅበራዊ ጠንቆች የሚስፋፉት  የባህልና የዕምነት ድጋፍ ሲያገኙ እንደሆነ እሙን ነው። ይቺን ዓለም በአብርሃም ድንኳን መስለን፣ መተዛዘኛና መገባበዣ ብቻ አድርገን ካቀረብናት፤ ደጋሹ የብዙ ዜጎችን ቅልጥም ሰብሮ ደጃፉ ላይ የተኮለኮሉ ነዳያን ማድረጉ ግድ ይሆናል። በዚህ ዘመን በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ የሚታየው ይህ ነው። ህፃን አዛውንት፣ እናት፣ አባት፣ ወጣት፣ ጥሩ የለበሰ፣ የተጎሳቆለ፣ ባለትዳር፣ ላጤ በስብስብ፣ በነጠላ… ከተለማኙ፣ ለማኙ በቁጥር ልቆ የተዘረጉ እጆችን በደረታችን እየቀዘፍን እንድንዋኝ ተፈርዶብናል። በተመጽዋቹ ከመንገፍገፍ አልፎ በግል ጠባያችን ላይ የሚንፀባረቅ መጤ ባህርያት ሳናበቅል አልቀረንም። ለሰው ችግር አለመደንገጥ፣ የሚለምን ፊትለፊታችን ሲቆም የመጭበርበር ፍርሃት አብሮ መከሰት…
… አሁን፣ በቅርቡ ከአንድ ወዳጄ ጋር ሻይ ቡና እያልን አንዲት ጥሩ የለበሰች ቆንጆ ልጅ እግር ወደኛ መጣች፡፡ በግርታ ስንመለከታት፤
“ድንገት ፔሬድ መጥቶብኝ ነው፤ ሞዴስ መግዣ የለኝም ስጡኝ” አለች።
ያስደነግጣል፤ በቀደመው ህይወታችን እህቶቻችን እንዲህ ያለ አጋጣሚ ላይ ሲሆኑ አብሮ መደንገጥን አዳብረናል። ጓደኛዬ ሁለት መቶ ብር ሰጥቷት “ግዢና መልሱን አምጪ”። አላት፡፡ በዛው ጠፋች።
“አውቅ ነበር እንደምትቀር” አለኝ ወዳጄ
“እና? ለምን ሰጠሃት?”
“ችግሯ የጠቀሰችው ባይሆንም ሌላ ችግር እንዳለባት ግን ግልፅ ነው። እዚህ ያደረሳት መኖርን አደጋ ላይ የጣለ አንዳች ቤተሰባዊ እንከን ይኖራታል።”
“ወዶ አይስቁ ሳይሆን ወዶ አይለምኑ” እንበል ይሆን?
እራሴን ከወዳጄ አንፃር አይቼ አፈርኩ። በሰዎች ችግር ላይ የመሳተፍ ዋነኛ ባህሪዬ ከዕለት ወደ ዕለት እየቀነሰ ሄዷል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ፣ በተደጋጋሚ ባዘንኩላቸው ሰዎች የመታለል አጋጣሚ ላይ መውደቄ ነው። ልመና የተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ይኖሩታል። አንዳንዴም ከመስራት የተሻለው ገቢ ልመና ላይ ስላለ ይሆናል። አንድ ሰው ይሄንን የልመና መግፍኤ እንደምን አድርጎ መረዳት ይችላል?
አውጠነጠንኩ።
የጎጃሙ ገዢ ራስ ኃይሉ ተክለሃይማኖት ግዛታቸው ውስጥ ከወዲያ ወዲህ ሲሉ አንዲት ሴት “ልዑል ሆይ! ልዑል ሆይ!!” ስትል ጮኸች
“አቅርቧት” አሉ
ቀረበች…
“ምን ሆንሽ?”አሏት!
“የሚላስ የሚቀመስ የሌለኝ ምስኪን ዘመድ አልባ ነኝ። ዘመዴ ብዬ ወደርስዎ መጣሁ፣ እጅዎን ይዘርጉልኝ” አለች።
“ጥሩ፣ ቤትሽ የት ነው?”
ተናገረች።
አሽከራቸውን ጠርተው “ሰምተሃል?” አሉት
“አዎን ጌቶች” አለ
“በል ሂድና ቤቷን ቆፍር፣ ምንም ያልተገኘ እንደሆነ ከነቅጣቴ እሰጣታለሁ” አሉ።የነዳይዋ ቤት ተቆፈረ፡፡ ብዙ የማሪያቴሬዛ ብር ተገኘ።
“የጌታ ኑሮ አስጠልቷት ልመና ካሰኛት፣ የአሻትን አትንፈጓት” አሉ ልዑሉ።
አንዳንዴ ልመና ስስት የሥነ-አእምሮ ችግር ሲሆን፤ የሚውሉበት ጎራ ነው እና እነዚህንስ እንዴት እንለያለን።
የወዳጄ ድምፅ አነቃኝ…
“… ዘንድሮ የምንጨካከንበት ጊዜ አልሆነም። ከኦታ ላይ የኔብጤው ግራ ገብቶት ከቤቱ የወጣው እየበዛ መጥቷል። “አንድ ጥናት አላነበብኩም?” ስለ ልመና?...”
“እንጃ!”
“በመምህሮች ላይ የተካሄደ ጥናት ነው። አብዛኛዎቹ መምህሮች ከሥራ በኋላ ሰዋራ ስፍራ ላይ ቆመው”
ይለምናሉ፡፡
ዝም!! ክው!!
“ወዳጄ፣ አሽቆልቁለን፣ አሽቆልቁለን እዚህ ደርሰናል፡፡” አለኝ አይኖቹ እንባ ያንቆረዘዙ መሰለኝ፡፡
ዝም!! ክው!!
“ከሰሞኑ የወጣ አንድ ሌላ ትዝብት እንደሚጠቁመው አብዛኛዎቹ የመንግስት ሰራተኞች ከየምግብ ቤቱ ትርፍራፊ እየለመኑ ነው ወደቤታቸው የሚገቡት”
ዝም!! ክውታዬ ቀጠለ….
“መንግስት፣ የመንግስት ሰራተኞች መመገቢያ ማዕከል በየመስሪያ ቤቱ እንዳቋቋመ የሚለፍፈው ለዚያ ነው”
ዝም!!
“ግን መፍትሄ አይሆንም፤ ቤተሰቦቻቸውስ? ትርፍራፊ የሚሰበስቡት እኮ ለራሳቸው ብቻ አይደለም፤ ለልጆቻቸው እና ለትዳር አጋሮቻቸውም ጭምር ነው”
“ኤጭ!! “የሚል ቃል ያለበት የገብረክርስቶስ ደስታ ግጥም በሌጣው ወደ እዝነ - ህሊናዬ፣ መጣ፡፡ “ኤጭ!!”
ትንኝ
ሰበብ እኔ ልሆን
በማላውቀው ነገር፣
ባልፈለግሁት ነገር፣
በማልወደው ነገር፡፡
ምን ጠባብ ዓለም ነው?
አክ እንትፍ
ኤጭ ወዲያ ምን ጨካኝ ዓለም ነው!
ከአዘጋጁ፡-
ዓለማየሁ ገላጋይ አስራ ሰባት ያህል መጻህፍትን ለህትመት ያበቃ የብዕር ሰው ሲሆን፤ የሚበዙት የህትመት ውጤቶቹ የፈጠራ ሥራዎች ናቸው። ረጅምና አጫጭር ልቦለዶች፤ የማህበራዊና የጥበብ ትንተናዎችም አሉባቸው። በጋዜጠኝነት ልምድና ተሞክሮ ያካተተው ዓለማየሁ ገላጋይ፤ በሥነ-ጽሁፍ ሃያሲነቱም በእጅጉ ይታወቃል።     

Read 1053 times