Saturday, 10 February 2024 09:59

ደራሲን በፀፀት!

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ-
Rate this item
(3 votes)

ደራሲ በሥራው እንጂ በሥሩ እና በዘሩ አይቀጥል ይሆን? ……
ይሄን ያሰብኩት  አንድ ሰሞን የሞከርኩት ሁሉ እየከሸፈ ስላዳገተኝ ነበር፡፡ ሙከራዬ አንዳንድ ደራሲዎች ሥራዎቻቸው ከታተሙ የዘገዩ እና ከአንባቢያን ዘንድ የጠፉ መሆናቸውን ከመታዘብ ይጀምራል፡፡ እና ምን

ይደረግ ይሆን? በተለይ እኔ ምን ይጠበቅብኛል? አወጣሁ አወረድኩ፤ በመጨረሻም መፃሕፍቱ ዳግም እንዲታተሙ የማግባባት ኃላፊነት ለራሴ ሰጠሁ፡፡ እንደ ጨዋታ አድርጌ አንዳንድ አሳታሚዎችን ሰለልኩ….
“… የማንን ደራሲ፣ የትኛውን ሥራ ብታገኝ ሳታንገራግር ታሳትማለህ?” የመጀመሪያ ጥያቄ ነበር፡፡
“በዚህ ጊዜ ካሉት ደራሲዎች ነው?”
“አ---ይ፣ ከዱሮዎቹ ደራሲዎች እንጂ”
“ከድሮዎቹማ የዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ”ን አግኝቼ አሳትም ብባል አይኔን አላሽም”
“ጥሩ! ሌላስ?”
“የመንግስቱ ለማ”
“የትኛውን መጽሐፍ?”
“ትዝታ ዘአለቃ ለማ ወልደ ታሪክ”
“እ….ሺ!”
“የመስፍን ዓለማየሁ”
“ግጥሞቹን?”
“ሳይሆን ‘ሽምግሌውና ባህሩ?’ን”
“እ….ሺ”
“የደበበ ሠይፉ ‘የብርሃን ፍቅር’ ከተገኘ”
“ጥሩ መርጠሃል”
“የፀጋዬ ገብረመድህን”
“ግጥሙን? እሳት ወይ አበባን?”
“አዎ”
“እ…..ሺ”
“የተክለፃድቅ መኩሪያ የታሪክ መፃሐፍት”
‘በቃ’ አላልኩትም፤ እራሱን ገታ አደረገ፡፡ የእኔ ሃሳብ ግን በተከፈተለት ፍኖት እየተንደረደረ ሸምጥጦ ነበር፡፡ የከበደ ሚካኤል ስራዎችስ? ‘የሥልጣኔ አየር’፣ ‘ሥልጣኔ ማለት ምንድነች?’ ‘ጃፓን እንደምን

ሰለጠነች’ ከእኛ አንባቢ ዘንድ መጥፋት ነበረባቸው? የእጓለ ገብረዮሐንስ ድርሰቶችስ? የታተመው ‘የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ’ ቀርቶ የታወጀላቸው ያለቁ ሥራዎች አልነበሯቸውም? ‘ፋውስት’፣ ‘ከተረት ወደ

ሕሊና’ እና ‘ሥነ ምግባር’፡፡ ሥለነዚህ አጓጊ ውጥኖች ማንን መጠየቅ ይቻላል? ጨለመብኝ! ቀኑ በጨለማ የተሻለ ነበር ይሆን?.....
…. አትጠራጠሩ፣ ልቦናችን እንደጆሮ ኮርቷል፣ እንኴን ኮሽታ ኡኡታ ማድመጥ ትቷል፡፡ ካልሆነ አዲስ እንዳይፃፍ መደላድል ከመንፈጋችን ባሻገር የተመረተውን ጥበብ እንዴት በወቅቱ መሰብሰብ ተሳነን? የት ነን?

ወዴት እንሄዳለን?....
…. በቀለ መኮንን ተገኝ የተረጎሙት የበርትራን ረስልና የሌሎች ምርጥ ሊቃውንት ሥራ የተካተተበት መፅሐፍ የት ይገኛል? ‘የምዕራባውያን ፍልስፍናና ሥልጣኔ ታሪክ’ ይሰኛል፡፡ የታተመው ይሁን ያልታተመው

የዚህ መፅሐፍ ክፍል ሁለት የት ነው ያለው? ማንን እንጠይቃለን? ይጨልምብናል፤ ቀኑ በጨለመብን የተሻለ ይሆናል?
ለራሴ ወደሰጠሁት ተልዕኮ ፊቴን መለስኩ፡፡ አሳታሚ ከተገኘ ቢያንስ ፍቃድ ያገኘሁባቸው የደራሲ ቤተሰቦች ዘንድ ሄጄ መፅሐፍቱ እንዲታተሙ ፈቃዳቸውን መጠየቅ፤ መዋዋሉ የእነሱ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ይሄኔ የደራሲዎቹ

ቤተሰቦች የሚጠየቀው ክፍል ግራ አጋብቷቸው ሥራዎቹን ታቅፈው ተቀምጠው ይሆናል፡፡
ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ በአራት ኪሎ በኩል የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ነበርን፡፡ ዘመዱን አውቀዋለሁ፡፡ ቀጥታ ሄድኩ፤ አፈላለኩ፤ አገኘሁት- አዋየሁት፡፡
“የጋሼ ወራሾች ልጆቹ ናቸው”
“ለአንተ…. መጠየቅ ይኖርብኛል ግን?” ገብቶታል….
“አክስቴና አጎቴ ናቸው” ሲል መለሰልኝ፡፡
“እና እነሱን አገናኘኛ”
“ውጭ ነው የሚኖሩት፡፡ ወንዱ ልጅ ግን መጥቷል”
“እሱን አገናኘኛ”
“ስልኩን ልፈልግልህና አናግረው”
“ጥሩ”
ስልኩንም ባለስልኩንም አገኘኋቸው፡፡ ነገሬን አቀረብኩ፡፡
“እንዲህ ያለ ነገር የምትፈቅደው እህቴ ናት” በሚል ሁሉም ነገር ተዘጋጋ፡፡
“የእርሷን ስልክ እንዴት አገኛለሁ?”
“በቅርብ ትመጣለች ያኔ ይደርሳል” ተባልኩ፡፡
እጠብቃለሁ፡፡ ጠብቄም አልሆነም፡፡ እንደተባለው በቅርብ ባይሆንም ቆየት ብላ መጣች፡፡ መረጃው እንደደረሰኝ ስልኳን አፈላልጌ ደወልኩ፡፡ ግራ የሚጋባ ምላሽ ተሰጠኝ፡፡ “ይሄንን የሚፈቅደው ወንድሜ ነው”
“እንዴ፣ ወንድምሽ’ኮ አንቺ እንደምትፈቅጂ ነበር የነገረኝ”
“አ….ይ፤ እሱ ነው”
ነገርዬው ላይ ሽሽት እንዳለ ገባኝ፡፡ “አደፍርስ” ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በ1962 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚያ በኋላ አልተደገመም፡፡ እንደውም የመጀመሪያ ዕትሙም ሳያልቅ ደራሲው በሚሰጡት አስተያየቶች ስለተበሳጨ

ሰብስቦ አስቀምጦት ነበር፡፡ ዳኛቸው ካለፈ በኋላ የተሰበሰቡትን መፃህፍት ሜጋ አሳታሚ ድርጅት ውስጥ አግኝተናቸው ገዛን፡፡ እና አሁን? “አደፍርስ” እንደሚፈለግ ሲነገራቸው ልጆቹን ምን አሸሻቸው?
ፊቴን ወደ መስፍን ዓለማየሁ ቤተሰቦች መለስኩ፡፡ ባዩሽ ዓለማየሁ (ነፍሷን ይማርና) ልጁ እንደሆነች አውቃለሁ፡፡ ወደ እሷ ዘንድ አመራሁ፡፡ ነገሩን አፍታትቼ ስነግራት፤
“ውይ እኔ’ኮ አይደለሁም፤ ወንድሜ ነው ይሄን ጉዳይ በኃላፊነት የያዘው” አለችኝ፡፡
ተመሳሳዩ የቴኒስ ኳስ ዕጣ-ፈንታ የተደገመ መሰለኝ፡፡
“የት አገኘዋለሁ?”
“ዓለማየሁ መስፍን ይባላል፡፡ የሚሰራው…”
ተስፋ በማጣት ተመትቼ ወደ ተጠቆምኩበት መስሪያ ቤት አመራሁ፡፡ “ይሄ ሁሉ ግን ለምን?” የምትለው የሰሎሞን ዴሬሳ ጥያቄ ውልብ አለችብኝ፡፡ ህሊናን የምታስተኛ የምንግዴ ጥያቄ ናት” “ምን አለፋህ?”

የሚል ማሳረፊያ የሚመስል ግን የማያሳርፍ ጥያቄ። መፃህፍቱ እንዲታተሙ ማስቻል እኔ ለምጽፋቸው ሐሳቦች እንደ ግብ የሚቆጠሩ ናቸው። ሥነ-ምግባር፣ ሀገር ወዳድነት፣ ኃላፊነትን መቀበልና ታማኝነትን ማሳየት

በጥሬው የሚሰበኩ ነገሮች አይደሉም። ወደ ኋላ መለስ ብሎ የመፈተሽ ተግባርን ግድ የሚሉ ናቸው። ሀገርና ሀገሬው እነዚህን መፃህፍት ተራቁቶ እያየሁ ምንም ሳላደርግ እጄን አጣጥፌ መቀመጤ የራሴን ልፋፌ

በራሴ እንደመቃወም ይቆጠራል። ስለዚህ … ደረስኩ። አስጠራሁት። ወጣት ነው።  ደርበብ ያለ ሁናቴ ይታይበታል። ሲናገር ዝቅ ባለ ድምጽ ነው። ጆሮዬን ወደ አፉ እያማተርኩ አይመጥኩት።
“እኛ ምንም አይነት ጽሁፍ የለም። ከቤት ሲወጣ ይዟቸው ነው የሄደው።”
“አዲስ ሳይሆን የታተሙትን የመፍቀድ ጉዳይ ነው።”
“እኔ እንጃ እስኪ ባዩሽንም አናግሬአት…”
ቅብብሎሹ እውን የሆነ መሰለኝ። ከአለማየሁ ጋር ወዳጃሞች ሆነን ደጋግመን መገናኘት ጀምረን ነበር ነበር። ግን  እንዴት እንደሆነ  ሳይገባኝ መጽሐፉ እንዲታተም ማድረግ ሳይንሆልኝ ቀረ።
    … ይሁንና የመስፍን ዓለማየሁ ጉዳዩ ከሌላ አሳታሚም ጥያቄ ሆኖ ወደ እኔ ዘንድ እንደመጣ አስታውሳለሁ። አቤል ሠይፉ መስፍን ያልታተሙ ግጥሞች እንዳሉት ሰምቶ ማሳተም እንደሚፈልግ ሹክ

አለኝ።
“ታዲያ የት እናገኛቸዋለን?” ስል ጠየኩት
“አረጋሽ ሠይፉ ጋር እንዳሉ አብደላ እዝራ ሲያወራ ሰምቻለሁ።”
“አረጋሽ ሠይፉ’ኮ አልፋለች”
“አዎ፣ እህቷ ግን አለች። ወደ እንጦጦ አካባቢ”
    “እንሂድ፣ እንሂድ ….” ተባባልን።
በተለምዶ ሳንባ ነቀርሳ የሚባለው አካባቢ ነው። ቤቱን ብናገኘውም በማንኳኳት የሚበገር አልሆን አለን። ሠፊው ግቢ የዋጠው አንዳች ድምጽ ያለ ቢመስለንም ማንም ሰው ዝር ሳይል ቀረ። ከረጅም ጥበቃ በኋላ

ያለ ምላሽ ባዶነት እየተሰማን ተመለስን።
አንዳንድ ሙከራዎች መከናወን ለሚገባቸው የከሸፉ ተግባሮች መጽናኛ ሆነው መዘናጋትን ልቦና ላይ ይተክላሉ። ለምን ደጋግመን አልሞከርንም? ለምንስ ዳተኝነት የታየባቸውን የደራሲ ቤተሰቦች ወጥረን

አልያዝንም?...እኔ‘ጃ!
…ብቻ የተሳካልን የደበበ ሰይፉ “የብርሃን ፍቅር”ን ድጋሚ እንዲታተም ማድረግ ብቻ ነበር። ወንድሞቹ አበበ ሰይፉ እና አዶናይ ሰይፉ አጽፎ የማጥሪያ ንባቡን ከማከናወን አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ከፍተኛ

ትብብር አድርገውልናል። አበደላ እዝራ የመግቢያ ፅሁፍ እንዲያዘጋጅ አድርገን አካተናል። አሁን ድረስ የሚከነክነኝ ሌሎቹ ግን ለምን? የሚለው ጉዳይ ነው። ሌሎቹ የደራሲ ቤተሰቦች የመዝጊያ እና የመገፍተሪያ

ምክንያታቸው ብዙ ሆኖ ነው ያገኘነው። “ጥራት ባለው ሁኔታ ውጭ ለማሳተም ወስነ፣ ፕሮፎርማ እያሳባሰብን ነው” ያለ ቤተሰብ፤ በአስር ለሚቆጠር አመታት በምክንያቱ ላይ አጥፎ መተኛቱ ሲያስገርመን ኖሯል።

ግን ለምን? ሲሆን ቤተሰብ ከዚህ ማለፍ አልነበረበትም?...
    … ከዚህ ጋር ተያይዞ የውጭዎቹን ደራስያን ቤሰተቦች ለመመርመር ሞከርኩ። የደስታየቭስኪ ባለቤት አና፣ አሳታሚ ድርጅት አቋቁማ መጽሃፍቱን ለአንባቢ ከማቅረቧ ባሻገር ትዝታዎቿ ላይ ተመስርታ

“Dostoevsky Reminiscences” የተሰኘ መጽሐፍ አበርክታለች። እዚህ መፅሐፍ ውስጥ የምናገኘው ደስታየቭስኪ ቅን፣ ሌሊት ተነስቶ የልጆቹን ብርድ ልብስ እየጎተተ የሚያለብስና ብዙም ንጭንጭ

የሌለው አባወራ ነው። የተወዛገበ ማንነቱ በቤተሰቡ ፊት ዋጋ አልነበረውም? እንድንል ያደርገናል። ሌላው ጀርመናዊ ደራሲ በቤተሰቦቹ ድጋፍ የታደለው ቶማስ ማን ነው። ባለቤቱ ካቲያ ማን ሥዎቹን ተከታትላ

ከማሳተሟ በተጨማሪ “Unwritten Memories” የተሰኘ መጽሐፍ አበርክታልናለች። መጽሐፉ የቀረበልን ከቃለ- ምልልሷ ላይ ተገልብጦ ነበር። ለምን? ተብላ ስትጠየቅ፤ “ከቤተሰቡ አንድ መጻፍ የማይችል

ሰው መኖር አለበት በሚል ነው።” የሚል የሹፈት ምላሽ ሰጥታለች። በስደት የተጎሳቆለውን የደራሲውንና የእሷን ህይወት ደስ በሚል ለዛ ታስነብበናለች። ተጓድሎ የተቋጨ የደራሲውን ኑሮ አሟልቶ ለማወቅ ካቲያን

ማንበብ ግድ ሆኗል።
ሌላ ደግሞ የቶልስቶይን ነጭናጫ ባህርይ በደንብ ለመረዳት ልጁ sergei Tolstoy የፃፈውን “TOLSTOY REMEMBERED” የተሰኘውን መጽሐፍ ማንበብ ተገቢ ነው። ከቱርጌኔቭ፣ ከጎርኪ፣ ከቼሆቭ እና

ከባለቤቱ ከሶፊያ ጋር የነበረው ውሎ እንዴት ያለ ነበር? የሁላችንም ጥያቄ ሳይሆን አይቀርም። ይሄም በሰርጌይ ትውስታ ምላሽ አግኝቷል።
ቤተሰብ ስለ ደራሲ ቤተሰብ የሚያየውን፣ ቤተሰብ የሚረዳውን፣ ቤተሰብ የሚወስደውን ትዝብት ማግኘት ግሩም ቃና ያለው ሌላ ንባብ ነው። ደራሲ በፃፈው ብቻ ሳይሆን በመሰረተውም ቤተሰብ መባረኩን

የሚያሳየን ሌላ ሳይሆን ይህ ነው። ስለ ደራሲው በቤተሰቡ የሚፃፍ ነገር አለመኖሩ አንድ ጉዳይ ይሁንና፣ እንዴት ጽፎ ያለፈውን ተከታትሎ የሚያሳትምለት ይጠፋል? እንዴት? ለረጅም ጊዜ አብሮኝ የኖረ ጥያቄ

ነው፤ እንዴት? ደራሲ በሥራው እንጂ በሥሩ እና በዘሩ እንዳይቀጥል ተረግሞ ይሆን? እንዴት?
ከአዘጋጁ፡-
ዓለማየሁ ገላጋይ አስራ ሰባት ያህል መጻህፍትን ለህትመት ያበቃ የብዕር ሰው ሲሆን፤ የሚበዙት የህትመት ውጤቶቹ የፈጠራ ሥራዎች ናቸው። ረጅምና አጫጭር ልቦለዶች፤ የማህበራዊና የጥበብ ትንተናዎችም

አሉባቸው። በጋዜጠኝነት ልምድና ተሞክሮ ያካተተው ዓለማየሁ ገላጋይ፤ በሥነ-ጽሁፍ ሃያሲነቱም በእጅጉ ይታወቃል።     

 

Read 1511 times