Monday, 05 February 2024 22:10

አዳም ረታ እንደ ኤግዚስቴንሻሊስት ልብ ወለድ ደራሲ

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(2 votes)

(ክፍል አንድ)
መግቢያ
ይህ ኂሳዊ መጣጥፍ ኤግዚስቴንሻሊዝም ተብሎ በሚጠራዉ በዠን-ፖል ሳርተር እና አልበርት ካሙ ፍልስፍና አንጻር የአዳም ረታ የልብወለድ ድርሰቶችን የሚፈክር ነዉ፡፡ የአዳም ረታ የድርሰት ሥራዎችን ከኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና አንጻር በመፈከር ረገድ ይህ የእኔ ሥራ የመጀመሪያ አይደለም፤ ሌሎች ሰዎችም በዉጭ ሐገር ቋንቋ ተመሰሳይ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ስማቸዉን ለመጥቀስ፡ፀደይ ወንድሙዘ ኬዝ ኦፍ ኤግዚስተንስ ኢን ፍቅር እስከ መቃብር፣ ካድማስ ባሻገር ኤንድ ግራጫ ቃጭሎች፡ ፍሮም ኤግዚስቴንሻሊስት ፐርስፔክቲቭ በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. 2007 ዓ.ም፣አክሊሉ ደሳለኝኤግዚስቴንሻሊዝምኢን ዘ ሴሌክትድ ክሬቲቭ ወርክስ ኦፍ አዳም ረታበሚል ርዕስ እ.ኤ.አ.2010 እናአዳም ረታ አዝ ኤ ሊትረሪ ኤግዚስቴንሻሊስት፡ ቴክስችዋል ኤንድ ዲስክሪፕቲቭ ክሪቲሲዝምበሚል ርዕስ እ.ኤ.አ.2010 ዓ.ም፣ አረጋዊ ገ/ሚካኤልአን ኤግዚስቴንሻሊስት ሪዲንግ ኦፍ አዳም ረታስ ኖቭል መረቅበሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. 2017፡፡ ይህኂሳዊ መጣጥፍ ሙሉ በሙሉ በሌሎች አጥኝዎች ባልተዳሰሱ የአዳም ሥራዎች ላይ አትኩሮቱን ያደረገ ነዉ፡፡
አዳም ረታ ከሌሎች የአገራችን ልብ ወለድ ጸሐፍት በተለየ መልኩ በርካታየኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ጭብጦችን በጥልቀት የዳሰሰ ልብወለድ ጸሐፊ ነዉ፡፡በመሆኑም፣ደራሲዉን በልበ ሙሉነት ከኤግዚስቴንሻሊስት ልብ ወለድ ደራሲያን ጎራ መፈረጅ ይቻላል፡፡
አዳም ረታ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ የፈጠረ፣ በሕይወት ከሚገኙ የዓለማችን ታላላቅ ልብወለድ ደራሲያን መካከል አንዱ ሆኖ መጠራት የሚችል ደራሲ ነዉ፡፡ ደራሲዉ ለአራት አሥርት ዓመታት በዘለቀ የሥራ ዘመኑ፣ በግሉ አራት ረጅም ልብወለዶችን ግራጫ ቃጭሎች (1997)፣ መረቅ (2007)፣ የስንብት ቀለማት (2008) እና አፍ (2010) እና ስድስት የአጫጭር ልብወለድ መድበሎችን ማሕሌት (1981)፣ አለንጋና ምስር እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች (2001)፣ እቴሜቴ ሎሚ ሽታ (2001)፣ ከሰማይ የወረደ ፍርፍር እና ሌሎች አጫጭር ልብወለዶች (2002)፣ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ (2003)፣ ሕማማትና በገና እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች (2004) ለህትመት አብቅቷል፡፡ ከሌሎች እዉቅ ልብወለድ ጸሐፍት ጋር ደግሞ አባ ደፋር እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች (1977)፣ ጭጋግና ጠል እና ሌሎች (1990)፣ አማሌሌ እና ሌሎችም (2009) እና አዲስ አበባ ኖይር (2012) የተሰኙ የአጫጭር ልብወለድ መድበሎችን ለህትመት አብቅቷል፡፡
አዳም ረታ በእኛ ሀገረ ልብ ወለድ ጠጠር ያለ ቁም ነገርና ፍልስፍናዊሐቲት የሚቀርብበት ኪናዊ ድርሳን መሆኑን በገሀድ ካሳዩየዘመናችንልብ ወለድ ደራሲያን መካከል አንዱ ነዉ፡፡ደራሲዉ በአገሪቱ ሥነ ጽሑፍ እድገትም የአንበሳዉን ሚና ተጫዉቷል፡፡
የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ጭብጦች በአዳም ረታ ድርሰቶች ዉስጥ
ከላይ በመግቢያዬ እንደጠቀስኩት አዳም ረታበድርሰት ሥራዎቹ ዉስጥ በርካታ የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ጭብጦችን በጥልቀትዳሷል፡፡ደራሲዉ የኤግዚስቴንሻሊዝምፍልስፍናጭብጦችን የዳሰሰባቸዉ የልብ ወለድ ሥራዎቹአለንጋና ምስር እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች፣ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ፣ እቴሜቴ ሎሚ ሽታ እናከሰማይ የወረደ ፍርፍር እና ሌሎች አጫጭር ልብወለዶች ሲሆኑ በእነዚህ ሥራዎች ዉስጥ የተዳሰሱት ጭብጦች ደግሞ ፍፁማዊ አርነት (radical freedom)፣ ኃላፊነት (responsibility)፣ ጭንቀት (anguish)፣ ግብዝነት (bad faith)፣ ሐቀኝነት(authenticity)፣ባይተዋርነት (abandonment)እናወለፈንድ (absurdity)ናቸዉ፡፡እነዚህ ጭብጦች በጥብቅ የተሰናሰሉ ናቸዉ፡፡ቀጥሎ የቀረበዉ ጽሑፍ እነዚህን ጭብጦች በዝርዝር ይተነትናል፡፡
፩. ፍፁማዊ አርነት
ፍፁማዊ አርነት በሳርተርኤግዚስቴንሻሊዝምዉስጥ ትልቅ ስፋራ የሚሰጠዉ ጽንሰ ዐሳብ ነዉ ነዉ፡፡ከሃያኛዉ ክፍለ ዘመን ታላላቅ የምዕራቡ ዓለም ፈላስፎች መካከል አንዱ የሆነዉ ሳርተርም ከሁሉም የዓለማችን ፈላስፎች በላቀ ስለ ሰዉ ልጅ ነፃነት የተፈላሰፈ ፈላስፋ ነዉ፡፡ ሳርተር የአርነት ጠበቃ (defender of freedom) ነዉ፡፡ለእሱ በሰዉ ልጅ ሕይወት ዉስጥ እጅግ የላቀ ዋጋ ያለዉ ነገር አርነት ነዉ (ሄርስችፊልድ፣ 1968)፡፡በሳርተር ፍልስፍና ዉስጥ አፅንኦት የሚሰጠዉየአርነት አይነትተጨባጭ አርነት (practical freedom) ነዉ፡፡ ይህ አይነቱ አርነት ከሥነ ኑባሬያዊ አርነት (ontological freedom) የተለየና ገደብ ያለዉ ነዉ፡፡
አርነት የሳርተር የሥነ ኑባሬ ነባቢ አእምሮ (ontological theory)የማዕዘን ድንጋይ ነዉ፡፡ይህ አርነት ፈፅሞ ሊሸሹት የማይችሉት የሰዉ ልጅ መገለጫ ባሕርይ (unescapable definition) ነዉ፡፡ለሳርተር፣ ሰዉ መሆን ማለት ነፃ መሆን ማለት ነዉ፡፡ ሳርተር ቢንግ ኤንድ ነቲንግነስ (2018) ዉስጥ እንደ ጻፈዉ፣ አርነት የሚገደበዉ በራሱ በአርነት ብቻ ነዉ፡፡ በመሆኑም፣ የሰዉ ልጅ ከአርነት ቀንበር ነፃ መዉጣት አይችልም (man is not free to not be free)፤ ነፃ እንዲሆን ተረግሟልና፡፡  
     የሳርተር ሥነ ኑባሬ ነባቢ አእምሮ መነሻ ህልዉና (existence) የንጥረ ባሕርይ (essence) ወይም ማንነት ቀዳሚ ነዉ (existence precedes essence) የሚለዉ መፈክር ነዉ፡፡ሳርተር የሰዉ ልጅ ህልዉና ከማንነቱ ቀዳሚ ነዉ የሚለዉን የሥነ ኑባሬ አስተምህሮቱን የገነባዉ ፈጣሪ በህልዉና የለም ብሎ ስለሚያምን ነዉ፡፡እንደ እሱ እሳቤ፣ ፈጣሪ በህልዉና ባለመኖሩ ምክንያት፣ የሰዉ ልጅ እንደ ግዑዛን ፍጥረታት ቀድሞ የተሠራ ንጥረ ባሕርይ ወይም ተፈጥሮየለዉም፡፡የሰዉ ተፈጥሮ የሰዉ ልጅ ወደ መኖር ከመጣ በኋላ በራሱ ትልም መሠረት የሚሠራ ነዉ (ሳርተር፣ 2007)፡፡
እንደ ሳርተር (2007) እሳቤ፣ የሰዉ ልጅ ንጥረ ባሕርይ ወይም ማንነት ከህልዉናዉ ቀዳሚ ነዉ (essence precedes existence) የሚለዉ የኢማኑኤል ካንት እሳቤ የተሳሳተ አተያይ ነዉ፡፡ በመሆኑም፣ ይህን አተያይ አበክሮ ይቃረናል፡፡የካንት እሳቤ የንጥረ ባሕርይያዊነትን (essentialism) ዲበአካላዊ አስተምህሮ የሚሰብክ ነዉ፡፡ የንጥረ ባሕርይያዊነት አስተምህሮ ወሳኛዊነትን የሚሰብክ እሳቤ በመሆኑ ለአርነት ቦታ የለዉም፡፡ ሳርተር ከካንት በተቃራኒ፣ የሰዉ ልጅ ወደ ህልዉና ከተወረወረ በኋላ ማንነቱን እንደ አናጺ በትልሙ (projection) መሠረት የሚያንጽ ነፃ ፍጡር(subjectivity) እንጅ ልክ እንደ ዕደ ጥበባት እንደ ቢለዋ፣ ብዕር ወይም የእጅ ሰዓት ቋሚ ተፈጥሮን ይዞ ወደ ህልዉና የመጣ ፍጡር አይደለም ይለናል፡፡ ለሳርተር፣ የሰዉ ልጅ ወደ መኖር መጥቶ ማንነቱን ከመፍጠሩ በፊት ምንም (nothing/empity) ነበር፡፡   
     የሳርተር ኦንቶሎጂ እንደሚያትተዉ፣ የሰዉ ልጅ ህልዉናዉ ከማንነቱ ወይም ተፈጥሮዉ ቀዳሚ በመሆኑ ዕጣ ፈንታዉን በራሱ እጅ የመጻፍ ሥልጣን አለዉ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የሰዉ ልጅ ያለ ረዳት የሚኖር ባይተዋር ፍጡር (abandoned) በመሆኑ አርነቱን ተጠቅሞ ራሱን የመፍጠር ሙሉ ኃላፊነቱ ጫንቃዉ ላይ የወደቀ ነዉ (ሳርተር፣ 2018)፡፡ በሳርተር ኤግዚስቴንሻሊዝም ዉስጥ አርነት እና ኃላፊነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸዉ፡፡ባይተዋርነት በሳርተር ግብረ ገብ ዉስጥ የሚገኝ ዐቢይ ጭብጥም ነዉ፡፡ ይህ ጭብጥ የሳርተርን ኢ-አማኝ (atheism) የሚሰብክ ነዉ፡፡ ሳርተር ፈጣሪ (God) በህልዉና አለ ብሎ አያምንም፡፡ ፈጣሪ በህልዉና ባለመኖሩ ምክንያትም የሰዉ ልጅ እንዴት መኖር እንደሚገባዉ ፍፁማዊ (a priori) የግብረ ገብ ሕግጋትን የደነገገለት አካል የለም፡፡ በእዚህም የተነሳ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን የግብረ ገብ እሴት ፈጥሮ ሕይወቱን የመምራት ኃላፊነቱ አለበት፡፡ ሳርተር የዶስቶቭስኪን ንግግር ጠቅሶ እንደሚነግረን፣ ፈጣሪ በህልዉና ከሌለ ሁሉም ነገር የተፈቀደ ነዉ (ሳርተር፣ 2007)፡፡     
     እንደ ሳርተር (2018) እሳቤ፣ ግዑዛን አካላት (being-in-itself) ተሟልተዉ የተፈጠሩ ፍጡራን በመሆናቸዉ ዕጣ ፈንታቸዉን መወሰን አይችሉም፡፡ የእነዚህ አካላት ንጥረ ባህርይ ከህልዉናቸዉ ቀዳሚ ነዉ፡፡ ግዑዛን አካላት የሳቢያ እና ዉጤት ሕጎች (causal laws) ተገዢ ናቸዉ (ገቲንግ፣ 2001)፡፡ በተቃራኒዉ፣ የሰዉ ልጅ ከሳቢያ እና ዉጤት ሕግ እግር ብረት (causal determination) ነፃ ነዉ፡፡ የሰዉ ልጅ (being-for-itself) ዕጣ ፈንታዉን የመወሰን ሥልጣን ያገኘዉ ተሟልቶ ያልተፈጠረ ፍጡር በመሆኑ ነዉ (ፍሮንዲዚ፣ 1981፤ ዳግል፣ 2011)፡፡
አለንጋና ምስር እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮችበተሰኘዉ የአዳም የአጫጭር ልብወለዶች መድብል ዉስጥ የቀረበዉ ኦቾሎኒ የተሰኘዉ አጭር ትረካ ከላይ የተመለከትነዉ ፍልስፍናዊ ዐሳብ በጥልቀት የተዳሰሰበት ሥራ ነዉ፡፡ኦቾሎኒ ዉስጥየተሳለዉ ዋና ገጸባሕርይ ስምዖንየእኛ የሰዉ ልጆች ባሕርይ (our character traits) በሥልጣናችን እንድንሆን ከወሰነዉ ዉሳኔ ዉጭ አለመሆኑን ተገንዝቦየቀደመ ማንነቱንበራሱ ኃይል ሲለዉጥ እናገኘዋለን፡፡ስምዖን ሰዉ በመሆኑ የተጎናፀፈዉን ፍፁማዊ አርነቱን ተጠቅሞ ማንነቱን በአዲስ መልክ ከመፍጠሩ በፊትበልጅነቱ ዘመንሰዎች መልከ ጥፉነቱን እየጠቀሱ መስደባቸዉከባድ የበታችነት ስሜት ፈጥሮበት ሕይወቱ ሐዘን ያጠለበት ነበር (አዳም፣ 2001)፡፡
ስምዖን ኋላ ላይከላይ የነገረንን ተጣብቶት የኖረዉን የዝቅተኝነት ስሜትሲኒማ ሊመለከት ከባልንጀሮቹ ጋር ፒያሳ ሲኒማ ኢትዮጵያ አቅንቶ ሳለ ሲኒማ ቤት ዉስጥ የተዋወቃት ልጃገረድ ሲታይ በነበረዉ ሲኒማ ዉስጥ የሚተዉነዉ ፈረንጅ ተዋናይ መልክ ከእሱ መልክ ጋር እንደሚመሳሰል ለእሱ እና ለወዳጆቹ በመጥቀሷ ምክንያት አሸንፎተቀባይነቱን ያረጋገጠባትን ‘ኦቾሎኒ’ ብሎ የሚጠራትን ሴት ለመጀመሪያ ጊዜ ለመተዋወቅ (ለመጥበስ)የቻለዉ በራሱ ሥልጣን ነዉ፡፡ይህ ገጸባሕርይ ኋላ ላይከኦቾሎኒ በተጨማሪ ሌሎች ሴቶችን የሚያማግጥ ሴት አዉል (womanizer) ወደ መሆን እንደተሸጋገረምከላይ በተጠቀሰዉ ትረካ ዉስጥይነግረናል፡፡አዳም እንደሚከተለዉ ጽፏል፦
እና ግን እየቆየ በራስ መተማመኔ እያደገ ሌላ ሴት እንደሚፈልገኝ፣ እንደሚያየኝ ስረዳ ትሰለቸኝ ጀመር፡፡በቀን በቀን ካላገኘሁሽ የምላት በመጀመሪያ ሁለት ቀን፣ በሚቀጥለዉ ጊዜ ሦስት ቀን እያለ ለሳምንትና ለወር የቀጠሮአችን ጊዜ መስፋት ጀመረ፡፡የገባትም መሰለኝ፡፡እኔ በተገኘዉ ክፍት ቦታ ሌሎች ሴቶችን ማማለል ወጣሁ፡፡ብዙ ቀላቀልኩ፡፡ቀድሞ ችላ የሚሉኝ የሚመስለኝን ደፈርኩ(አዳም፣ 2001፡ገጽ 270)፡፡  
… እዚያዉ አጠገብዋ ዉለታ-ቢስ ነዉ የሆንኩት፡፡ ብዙ አልተጓዝኩም፡፡ ጐንዋ ቆሜ እየዳበስኳት ነዉ የከዳኋት፡፡ክፉ አልተናገረችኝም፡፡ አልተናገረችኝም ማለት አልገባትም ማለት አይደለም፡፡እኔ ግን የገመትኩት እንደዚያ ነበር፡፡ ምን እንደነካኝ አላዉቅም፡፡ሲያጋጥመዉ አፌ ደ’ሞ ሊያታልላት ይፈልጋል …
“ትወደኛለህ?” ስትለኝ፡፡
“ኦቾሎኒዬ አይደለሽ” እላታለሁ፡፡
እህቴ ባል አግብታ አሜሪካ ስትሄድ መሸኛ ፓርቲ ተደርጎ አልጠራኋትም፡፡ያን ማታ የመጣችዉ ሌላ ከእስዋ የተሻለች የምትመስል ‘አራዳ’ ቢጤ ናት፡፡(‘አንቺ ሰዉዬ ትለዋዉጪያለሽ’ ሲሉኝ እኮራ ነበር ሀሀሀሀ!!!) (አዳም፣ 2001፡ገጽ 271-272)፡፡
እቴሜቴ ሎሚ ሽታ የተሰኘዉ የአዳም የአጫጭር ልብ ወለዶች መድበል ከላይ የዳሰስነዉ አርነት ብለን የምንጠራዉ ፍልስፍናዊ ዐሳብየተፈከረበት ሌላኛዉ ሥራ ነዉ፡፡ይህ ፍልስፍናዊ ጭብጥ በጥልቀትየተዳሰሰበት አጭር ልብ ወለድ የመድበሉ መጠሪያ የሆነዉእቴሜቴ ሎሚ ሽታነዉ፡፡እቴሜቴ ሎሚ ሽታ ዉስጥ የተሳለችዉ ዋና ገጸባሕርይ ሎሚ ሽታ ግላዊ ምርጫዋን ተጠቅማ ሕይወቷን በአዲስ ጎዳና የቀየሰች ሴት ናት፡፡ ደራሲዉ እዚህ ታሪክ ዉስጥ እንደሚነግረን፣ ይቺ ሴት ከሕግ ባሏ ታደሰ ጋር ተጋብታ ትመራዉ የነበረዉ ሕይወት ድባቴ ያጠላበትና ሙሉ ደስታ ያልነበረዉ ሕይወት ነበር፡፡ይህ የሆነዉ ደግሞ ባሏ ታደሰ ወሲባዊ አምሮቷን በምትፈልገዉልክ ሊያረካላት የሚችል ወንድ አለመሆኑ ነበር፡፡አዳም እንደሚከተለዉ ጽፏል፦
ከላይ አያለሁ፡፡በምሽት ሞተሩን አስነስቶ ሲከንፍ፡፡ ሦስተኛ ቀኑ ነዉ፡፡እያስጮኸ ሞተር ሲያስነሳ፡፡ለካስ የእኔ ሱስ ነበረበት፡፡ ደስ ይላል፡፡የወደደን ራቅ አድርጎ ወደ ሌላ ወደ ወደደ መሸጋገር፡፡እንዴት ነዉ ብልግና አይሆንም፡፡ባል መለወጥ ይባላል፡፡ለአፍታ እኔ ወደነበርኩበት ቀና ብሎ ያየ መሰለኝ፡፡ያቺ ቀልቃላ ልጅ የት እንዳለሁ ነግራዉ ይሆናል፡፡ደስ የሚሉ ዐይኖች ነበሩት፡፡ታደሰ መልካም ዓይኖች ነበሩት፡፡ልንተኛ ወይ ሊተኛ ሲል ሶፋዉ ዙሪያ እየተሽከረከረ ስራ ፈቶች የተበተቡትን ግጥም የሚባል ነገር ያነብልኝ ነበር፡፡የሚያስፈራ፡፡ ገላልጦ እያሳየ የሚያስፈራ፡ ሴት ሳይሆኑ የሴትን ልብ እናዉቃለን የሚሉ ገጣሚዎች፡፡አፍቃሪ መስዬ አሰቃይቼዋለሁ፡፡ ግን ደ’ሞ እኔ እንደ አንድ ግለሰብ የፈለግሁትን መምረጥ የመቻል መብት እንዳለኝ መዘንጋት የለበትም፡፡ምን አንቀለቀለዉ ግን?ቢጋጭከሆነ ግንብ ጋር? ወይም አህያ ገጭቶ እንደ አህያ ቢሞትስ? ምን ሆንኩ ነዉ? መጀመሪያ አጠገቡ እያለሁ ወንድ መሆን ነበር፡፡በሚያስፈልግበት ጊዜ ወንድ አይሆኑም፡፡በእሷ ምክንያት ሞተ ለመባል ነዉ? ጤነኛዉን ሰዉዬ አሳበደችዉ እንዲባልለት ነዉ? በእኔ ላይ ሊያስፈርድ ነዉ? እሷ እንዲህ አድርጋዉ እንዲህ ሆነ ሊያሰኝ? የጠበቃ ተንኮል፡፡ወይስ ገና ለገና ከዚህ ጉብታ ላይ አይቼዉ ‘እኔን! እኔን! እኔን!’ ብዬ ተንደርድሬ እንድመለስለት ነዉ? ልጅ አደረገኝ? አጠገባቸዉ ተጋድሞ ያልመተሩት ስጋ በጮሌ ድመት ሲወስድባቸዉ የሚነጫነጩ ስንት ዉሾች አሉ (አዳም፣ 2001፡ገጽ104)፡፡
     ሎሚ ሽታ ከላይ በነገረችን ምክንያትባሏን ከድታ አስናቀ የተባለ ወሲባዊ አምሮቷን ያረካላት ሰዉ ቤት መግባትንመርጣለች (አዳም፣ 2001)፡፡ ሎሚ ሽታ ለራሷ ብቻ የተተወ ሁለት ምርጫ ነበራት፡ ወይ በድብርት ተከባ ከሰማንያ ባሏ ታደሰ ጋር ዘመኗን መዝለቅ ወይ ደግሞ “የስጋዋም የመንፈሷም ምግብ” የሆነዉን አስናቀን መርጣ መኮብለል፡፡ የሎሚ ሽታ ምርጫ ሁለተኛዉ ነዉ፡፡
(ይቀጥላል)


Read 352 times