Monday, 22 January 2024 08:54

በዓሉ ግርማን በ”ቤርሙዳ“

Written by  መልካሙ ተክሌ (melkamutekle@gmail.com)
Rate this item
(0 votes)

ቤርሙዳ ትራይአንግል በአትላንቲክ ውቅያኖስ የሚገኝ የሰዎች፣ የአውሮፕላኖች፣ የመርከቦች ደብዛ  ይጠፋበታል፣ እዚያ የገባም አይገኝም  የተባለለት ሥፍራ ነው፡፡ ቤርሙዳ የገባ አይወጣም፡፡ ይኑር ይሙት አይታወቅም፡፡ የእኛው ሀገር ውድ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማም እስካሁን ሕይወቱ አለፈ ብሎ ያረጋገጠም ሆነ የለም በዚህ አለ  የሚለን አልተገኘም፡፡
ታላቁ ደራሲ በሕይወት በዚህ ምድር በይፋ በኖረበት ወቅት የነበረውን አስመልክቶ ግን የጥናት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ የጋዜጣና መጽሔት ጽሑፎች ተዘጋጅተዋል፡፡ መጻሕፍትም ተጽፈዋል፡፡ ከነዚህ አንዱና በጥልቀት የተዘጋጀው የዶክተር እንዳለጌታ ከበደ  “በዓሉ፤ ሕይወቱ እና ሥራዎቹ” ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ በጥልቅ ምርምር ቢጻፍም ሥለ በዓሉ ግርማ አሟሟት  እርግጠኛ የሆነ ነገር ያስቀመጠ አይመስልም፡፡ ትልቅ ማጣቀሻነቱ ግን አያከራክርም፡፡
ዘንድሮ ደግሞ ይህንኑ ታላቅ የብዕር ሰው በዓሉ ግርማ በተመለከተ አንድ የትያትር ሥራ ለመድረክ በቅቷል፡፡ በሐገር ፍቅር ትያትር ቤት ዘወትር እሑድ ከሰዓት በኋላ እየታየ ያለውን “ቤርሙዳ” የተሰኘ ስለ በዓሉ የሚያወሳ ትያትር የጻፈው ጸሃፌ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ ሲሆን፤ ያዘጋጀው ዶክተር ተሻለ አሰፋ ነው፡፡
ትያትሩ ላለፉት ሦስት ወራት በመታየት ላይ ነው፡፡ ይህንኑ ትያትር ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም ለማየት 8 ሰዓት አካባቢ ሰልፍ ያዝኩና 15 ደቂቃ ያህል ተሠልፌ፣ ትያትር ቤቱ ለአንድ ተመልካች የሚያስከፍለውን 90 ብር ከፍዬ ገባሁ፡፡
በአንድ ወቅት ትያትር ድርቅ መታው፣ ተመልካች ነጠፈ ይባል ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የተዋንያን  ቁጥር ከተመልካች ቁጥር በልጦ ያየሁባቸው የመሠሉኝ አጋጣሚዎችም አይጠፉም፡፡ “ቤርሙዳ” ግን የተመልካች ድርቅ አልመታውም፡፡ አዳራሹ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞላ ባይባልም በርካታ ተመልካቾች  ነበሩ፡፡
ከእነዚህ ተመልካቾች መካከል ሃምሳ ያህል በግምት ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ተደራጅተው በትልቅ መኪና የመጡ ታዳጊዎችም ነበሩበት፡፡ ታዳጊዎች ለእድሜያቸው የሚመጥን ትያትር በሀገሪቱ ወይም በመዲናይቱም ጭምር አለ ለማለት ባያስደፍርም፣ “ቤርሙዳ” ግን በነሱ ልክ የተሠፋ አይደለም፡፡ ውጪ ተሰልፈን ሳለ መግቢያ ሲቃረብ  እነሱም ከመኪናቸው ወርደው ሲሰለፉ፣ እንደኛው ሊታደሙ መስሎን በትላልቆቹ ጎራ አብረን የተሰለፍነው  ይረብሸን ይሆን? የሚል ስጋትም አጭሮብናል፤ ፎቁ መመልከቻ ላይ መቀመጣቸው በጀ እንጂ፡፡ ትያትሩን ያን ያህል ባይረብሹም አልፎ አልፎ ማውካካታቸው አልቀረም፡፡
 እንዳልኩት ግን ትያትሩ  ለነሱ የማይመጥን ነው፡፡ ፊልም ቢሆን ከ… ዕድሜ በታች ማየት የተከለከለ የሚል ማስጠንቀቂያ የታከለበት ይሆን ነበር፡፡ ማስጠንቀቂያውን በትያትርም ማምጣት ይቻላል፡፡ አልተደረገም፡፡ በዚህም ለነሱ የማይመጥኑ አሰቃቂ ድርጊቶች፣ በትያትሩ አስፈላጊ የሆኑ ለእነሱ ግን የማይገቡ ቃላትን እንዲያዩ፤ እንዲሰሙ ሆነዋል፡፡ ለዚህ ኃላፊነት ደራሲው ወይም አዘጋጁ ይውሰዱ ለማለት አይቻልም፡፡ ትያትር ቤቱ ግን ሙሉ ተጠያቂነት አለበት፡፡
ትያትሩ
“ቤርሙዳ” ከመጀመሩ በፊት ራሱን ጨምሮ በትያትር ቤቱ በሳምንት ውስጥ የሚታዩ ትያትሮች ማስታወቂያዎች ተለቀቁ፡፡ ይህም ለተመልካች አማራጭ ለማቅረብ ጥሩ ቅስቀሳ ነው፡፡
“ቤርሙዳ” ራሱ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ማስታወቂያ ለመጠቀሙ እርግጠኛ ባልሆንም፣ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን በተለይም በፌስቡክ  ተመልካችን የሚጋብዙ ማስታወቂያዎች ተሠርተዋል፡፡ ከደራሲው ውድነህና ከአዘጋጁ ከዶክተር ተሻለ ብቃት በተጨማሪ እኔን እንድመለከተው ያደረገኝ ይኼው የፌስቡክ ማስታወቂያ ነው፡፡
“ቤርሙዳ”፣ በበዓሉ ሕይወት ዙርያ በተለይ ”ኦሮማይ” የተሰኘ ድርሰቱ ላይ ተንተርሶ የተሠራ፣ ተመልካች ሊያየው የሚገባ ትያትር ነው፡፡ በታሪክም እንደምናውቀው ደራሲውና አዘጋጁም አሳምረው እንዳቀረቡልን፣ በዓሉ ያመነበትን ነው የጻፈው፡፡ በዚህም ሰበብ ሕይወቱ ለአደጋ ተጋልጧል፡፡ ይህ ከሆነ ከዐርባ ዓመት በኋላ ዛሬም “በዓሉ ሞቷል፣ በዓሉ አለ” ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር አልተቻለም፡፡  ያመነበትን በመጻፉ ነው እስከዛሬ የበዓሉ ደብዛ የጠፋው፡፡
በትያትሩም ያመነበትን የጻፈው ደራሲ በደህንነት ሲመረመር፣ ውሃ በርሜል ውስጥ በጭንቅላቱ ሲነከር፣ ሲገረፍ ይታያል፡፡ (የራሱን ጨምሮ) ስለ ሌሎች ስቃይና እንግልት ለዋናው መርማሪ ሲነግር፤ “አይጡ ተባዩ አስቸገረኝ” ሲል መርማሪው፤ “አይጡ ማነው? ተባዩ ማነው?” ይለዋል፡፡ ዝም ጭጭ ሲል፤ “አብዮቱ አፋኝ ነው እያልከን ነው?” በማለት እያንዳንዷን ነገር ይተረጉምበታል፡፡ በገሃዱ ዓለም ራሱ በዓሉ ከሚወደው ሙያና ቤተሰቡ የለየው “ኦሮማይ” መጽሐፉ ትርጉም ተሰጥቶት እንዲህ ለማለት ፈልገህ ነው ተብሎ ይመሥላል፡፡
ገጸ ባሕርያቱና ተዋንያኑ
በዓሉን በፎቶግራፍ እንጂ በአካል የማየቱ ዕድል አልነበረኝም፡፡ በእነ ውድነህ “ቤርሙዳ” ግን ተዋናዩ አንዱዓለም ትወናውን የበለጠ ማሻሻሉ እንዳለ ሆኖ በሚገባ ተውኗል፡፡ ከተዋናዩ ትወና በተጨማሪ የገጽ ቅብ ባለሙያዎች ይበልጥ በዓሉን በዓሉን  እንዲሸት ስላደረጉ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል፡፡
መርማሪውን  ደምሴ
የደኅንነቱን ዋና መርማሪ ሆኖ የሠራው ተዋናይ ደምሴ በየነ  ነው፡፡ ከወቅቱ ወታደራዊ አለበባሱ በተጨማሪ እንደ መርማሪነቱ ተመርማሪውን በዓሉን ሲመረምር ዘወትር “ጓድ በዓሉ ጓድ በዓሉ” ማለቱ ጊዜውን ያስታውሰናል፡፡ “ጓድ በዓሉ መጽሐፍህን አላነበብከውም እንዴ?” ሲልም ይሳለቃል፡፡
ጓድ መንግሥቱን ዝናቡ ገብረሥላሴ
“አቡጊዳ” በተሰኘው የሙሉዓለም ታደሰ ፊልም ቁርጥ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያምን ሆኖ የሠራው ዝናቡ በቤርሙዳም ይህንኑ ደግሞታል፡፡ በእርግጥ ዋና ገጸባሕርይ መንጌ ሳይሆኑ በዓሉ በመሆኑ በዝናቡ ገጽ መንጌን በብዙ ትእይንቶች አላየናቸውም፡፡
ፀጋዬ ኃይለማርያም በሰሎሞን ሀጎስ
የኦሮማዩ ዋነኛ ገጸባሕርይ ጋዜጠኛ ፀጋዬ ኃይለማርያም ነው፡፡ የ “ቤርሙዳ” ዋና ገጸባሕርይ ራሱ በዓሉ ነው፤ የወከለው ፀጋዬ ኃይለማርያም አይደለም፡፡ ፀጋዬን ደግሞ ሰሎሞን ሀጎስ ደኅና አድርጎ ተውኖታል፡፡ ከፊያሜታ ጋር የፀሐይቱ ባራኺን “መጀመርያ ፍቕሪ” የኤርትራ ትግርኛ ዘፈን ሲያስነኩት፣ ያንን ጊዜ አሁን አመጡት!
ፊያሜታ ጊላይን በልዋም ደብሮም
ፊያሜታን ሆና የተወነችውን ወጣት ልዋም ካሁን ቀደም (በሥራዎቿም በአካልም) አላውቃትም፡፡ በ ”ቤርሙዳ” መድረክ ላይ በቆየችበት አጭር ጊዜ ግን የሰፈሬ ልጅ፣ አብሮ አደጌ እስክትመስለኝ ድረስ ልዋም ፊያሜታን አምጥታታለች፤ በእኔ አስተያየት፡፡ ፊያሜታ ሆና በመተወኗም ምስጋና ይገባታል፡፡
ስለ ሌሎቹ ተዋንያንም ሆነ ስለ ተውኔቱ ሌላም ማለት ይቻል ነበር፡፡ ለጊዜው ግን ቦታና ጊዜ ይገድበናል፡፡ እኔ ያጎደልኩትን ትያትሩን የተመለከቱ አንባቢያን  እንደሚሞሉበት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ 

Read 527 times