Monday, 22 January 2024 08:48

ሠላሳዎቹ” - በወጣት ጸሃፍቱ አንደበት

Written by 
Rate this item
(2 votes)

“እድል መሰጠቱ በራሱ በጣም ትልቅ ነገር ነው”



ነዋል አቡበክር እባላለሁ። በሙያዬ የሚዲያ ባለሞያ ነኝ። በ“ሠላሳዎቹ“ የአጫጭር ልብወለዶች መድበል ፅሁፎቻቸው ከታተመላቸው 30 ወጣት ፀሀፍት አንዷ ነኝ። ‘’የክራሩ ክር’ የሚል ድርሰቴ በመድበሉ ውስጥ  ታትሞልኛል፡፡
ድርሰትሽ በ“ሠላሳዎቹ “ የአጫጭር ልብወለዶች መድብል ውስጥ በመካተቱ ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብሽ? ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ዕድል ገጥሞሽ ያውቃል? የራስሽን መጽሐፍስ አሳትመሻል?
ለመጀመሪያ ጊዜ ስሜ በመጽሐፍ ላይ ሰፍሮ ሳየው እጅግ ነበር ደስ ያለኝ። ሥነ ፅሁፍን ለሚወድና ፅሁፍ ለሚሞክር ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ‘የሱ’ የሚባል ፅሁፍ ኖሮት ለመነበብ ሲበቃ ያለው ስሜት ይሄ ነው የሚባል አይደለም። የፃፍከውን ነገር የምታከብራቸው ባለሞያዎች አንብበውት፣ አምነውበትና ወደውት ወደ ህትመት መላኩን ስታውቅ፣ የሚያስፈራና በራስ መተማመን የሚጨምር ስሜት ነው የሚሰማህ፡፡ መፅሐፉ ከተነበበ በኋላም ሰዎች የሚያበረታታ አስተያየት ሲሰጡህ ውስጥህ የሚፈጥረው ትልቅ ተስፋ አለ። ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ውድድር ላይ ተሳትፌም ሆነ የራሴን መጽሐፍ አሳትሜ አላውቅም።
. የአጫጭር ልብወለዶች ስብስቡን እንዴት አገኘሽው ?
የ“ሰላሳዎቹ“ አጫጭር ልብወለዶች ስብስብ’፣ ድንቅ ወጣት ፀሀፊያንን ለማንበብ እድል ያገኘሁበት፣ ብዙ አይነት ቀለም የተመለከትኩበት፣ ታሪክ በመንገር አቅማቸው በአተራረካቸውና በሀሳባቸው የተገረምኩባቸውን ፅሁፎች ያገኘሁበት መጽሐፍ ነው።
የወጣት ጸሃፍት ሥራዎች እንዲህ ተሰባስበው በጋራ መታተማቸው ምን ፋይዳ አለው ብለሽ ታስቢያለሽ?
በጣም ትልቁ ነገር እድል መስጠቱ ነው ብዬ አስባለሁ። ወጣቶች በራሳቸው አምነው የሚሉት ነገር ኖሯቸው ለመፃፍ እንዲነሱ የሚያደርግ እድል መሰጠቱ በራሱ በጣም ትልቅ ነገር ነው።  ከዚያ በተጨማሪ እንደ አንባቢ ይሄ መጽሐፍ የዘመናችንን መልክ የምናይበት አንዱ መንገድ ነው። በተቀራራቢ እድሜ የሚገኙ ነገር ግን የተለያየ ህይወትና አመለካከት ያላቸው ፀሀፍት ሃሳብና ስሜት፣ ህመምና ተስፋ ወዘተ-- በአንድ መጽሐፍ ተሰድረው ማንበብ ችለናል። እንደ ጀማሪ ፀሀፊ፣ ፅሁፍን የማሳተምና የመነበብ እድል ማግኘት የሚሰጠው ሞራልና ተስፋ በምንም የሚሰፈር አይደለም።
 ወጣት ጸሀፍት ከሥነ ፅሁፍ ጋር ስለሚኖረን ግንኙነት ለመወሰን እራስን መመልከቻ ነውም ብዬ አስባለሁ።
ከራስም  ከታላላቆቻችንም  ለመማር እድል ይሰጣል።
ከዚህም ባለፈ በጣም ያስደነቁንና የት ነበሩ ያስባሉንን አዲስ ፀሀፍትም  አፍርቷል፤ አበርክቷል ብዬ አስባለሁ።
 በጀርመን የባህል ማዕከል ድጋፍ ከተሰጣችሁ አጭር ሥልጠና ምን አዲስ ትምህርት ቀሰምሽ?
በርግጥ በስራ አጋጣሚ ከተማ ውስጥ ስላልነበርኩ በሥልጠናውን መሳተፍ አልቻልኩም ነበር። ነገር ግን ፅሁፉን ለመፃፍ ከማሰብ ጀምሮ እስከ መጨረሻው የአርትኦት ስራ ድረስ በጣም ብዙ እውቀትን አግኝቻለሁ። እኔ በአፃፃፍ ብዙ የምሳብበትን የአፃፃፍ አይነት ከማወቅና ከመረዳት ጀምሮ ስለ አማርኛ ሰዋሰው ፤ ቃላት መረጣ ፤ ሀሳብ አሰፋፈር ብዙ ነገር አስተምሮኛል።
ብዙ ጊዜ  ጀማሪ ፀሀፊ ስትሆን ልትፅፍ የፈለከውና አእምሮህ የሰጠህን ሀሳብና ቃል ነው ወረቀት ላይ የምታሰፍረው። በዚህ በኩል መንገድ የሚያሳይህ፣ ስህተትህን የሚያርምህና እራስህ እንድታስተካክል እድል የሚሰጥህ ስታገኝ ብዙ ታተርፋለህ፡፡ ለዚህ ደግሞ የጀርመን የባህል ማዕከልን ፣ አርታኢዎቻችንን፣ አስልጣኞቻችንንና አዘጋጆቹን ከልብ እናመሰግናለን።
 ከአገራችን ወይም ከውጭ አገራት የአጭር ልብወለድ ጸሐፍት ማንን ታደንቂያለሽ ?
ከሀገር ውስጥ ተመስገን ገብሬ፣ ከውጭ የፍራንዝ ካፍካ ፅሁፍ ይስበኛል።

Read 704 times