Monday, 22 January 2024 08:23

የምርጫ ተወዳዳሪዎችን ማገድ… እውነተኛዋ አሜሪካ ውስጥ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

የምርጫ ረብሻና ግጭት፣ ዓመጽና ወከባ… በአፍሪካና በዓረብ አገራት የተለመደ ነው። እንዲያውም ግርግር ባይፈጠር ነው የሚገርመን፤ ግራ የሚገባን።
አሜሪካ ውስጥ የምርጫ ውዝግብ ሲካረር ማየትስ? ውዝግብ ብቻ አይደለም። አልፎ ተርፎ፣ ከግራም ከቀኝም የውንጀላና የእገዳ መግለጫዎች የእለት ተእለት ዜናዎች ሆነዋል።
በአንዳች ምክንያት የተከሰሰ ፖለቲከኛ በአሜሪካ ምርጫ ውስጥ፣ ብዙ ፈተና ይገጥመዋል። በክስ ብዛት “ሪከርድ” የበጠሱት ዶናልድ ትራምፕ ግን፣ የተመራጭነት አዲስ ታሪክ እያስመዘገቡ ነው።
አዎ፣ ለማመን ይከብዳል! በአንድ በኩል ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ እንዳይወዳደሩ ለማገድ ብዙ የክስ መዝገቦች በዓይነት በዓይነት እየተከመሩ ነው። ጭራሽ ያለ-ፍርድ ቤት ዳኝነት፣ ትራምፕን ከምርጫ ለማገድ የሚፈልጉ የክልል ባለሥልጣናትም ተፈጥረዋል። ስለ አሜሪካ የምናወራ አይመስልም አይደል? አንጎላ ወይም ዩጋንዳ ከአሜሪካ ጋር የተምታቱብን ይመስላል። ዋናውን ተፎካካሪ ከምርጫ ማገድ! ሆ!?
በሌላ በኩል ደግሞ፣ አንድ ሁለት ክስ የመጣበት ፖለቲከኛ፣ በዜጎች ዘንድ ስሙ ጎድፎ፣ ነባር ደጋፊዎቹን አጥቶ፣ የመመረጥ ተስፋው ተገፍፎ፣ የመመረጥ ዕድል እንደማይኖረው ዐውቆ፣ ድምፁን አጥፍቶ ከምርጫ ውድድር ሹልክ ብሎ እንዲወጣ ነበር የሚጠበቀው። ዶናልድ ትራምፕ ላይ ግን፣ ክስ በበዛባቸው ቁጥር፣ ከነባር ቲፎዞዎች የሚያገኙት ድጋፍ ይደነድናል። የክስ መዝገቦች በላይ በላይ ሲከመርባቸው፣ እንደ ጀግና እየታዩ ተጨማሪ ደጋፊዎችን ይማርካሉ።
ሰኞ ዕለት በአየዋ ክልል የተካሄደውን የማጣሪያ ምርጫ ተመልከቱ። ታይቶ የማይታወቅ ታሪክ ነው የተፈጠረው። ዶናልድ ትራምፕ የክስ መዓት ቢከመርባቸውም፣ በማጣሪያ ምርጫው ላይ ከፍተኛ የድምጽ ብልጫ እንደሚያገኙ ቀድሞውንም ተገምቶ ነበር። ግን ብልጫ” ብቻ አይደለም። ታይቶ በማይታወቅ ሰፊ ልዩነት ነው የማጣሪያ ምርጫውን ሀ ብለው የጀመሩት። እስከዛሬ በአየዋ ክልል ታሪክ ውስጥ፣ በ14 በመቶ ብልጫ ማሸነፍ እንደ ትልቅ ተዓምር ነበር የሚቆጠረው። ሥልጣን ላይ ላለ ፕሬዚዳንት ካልሆነ በቀር፣ ለሌሎች ተወዳዳሪዎች የማጣሪያ ምርጫው ከባድ ፈተና ይሆንባቸዋል። ትራምፕ ግን፣ ከ25 በመቶ የሚበልጥ ሰፊ የብልጫ ልዩነት አስመዝግበዋል።
ዋናውን የምርጫ ተፎካካሪ ከፖለቲካ ውድድር ለማገድ፣ እስከ ዛሬ በአሜሪካ ታይቶ የማይታወቅ ዘመቻ መፈጠሩ፣ ራሱን የቻለ አዲስ ታሪክ ነው። ይሄ በሌሎች አገራት የተለመደ ነው። በአሜሪካ ግን እንዴት? በክስ ብዛትና በፍርድ ቤት ቀጠሮ የተዋከቡ የምርጫ ተፎካካሪ፣ ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘታቸው ደግሞ ሌላ ተዓምረኛ ታሪክ ነው። በብዙ ወንጀል የተጠረጠረና የተከሰሰ ሰው እንዴት ተወዳጅነቱ ይጨምራል? በሌሎች አገራት፣ የተከሰሰና የታሰረ ፖለቲከኛ እንደ ጀግና ሊቆጠር ይችላል። ለአሜሪካ ግን አዲስ ታሪክ ነው - ጨርሶ ለአሜሪካ የማይመጥን ቀሽም ታሪክ።        
የሆነ የተበላሸና የተዛባ ነገር መኖር አለበት። በዚያ ላይ የብልሽቱ ፍጥነት! ወይስ “ፌክ” አሜሪካ ተፈጠረች? እውነተኛዋ አሜሪካስ የት ገባች?
የአሜሪካ የምርጫ ውዝግቦች እጅግ እየከረሩና እየተበራከቱ የመጡት ከ10 ዓመታት ወዲህ ይመስላል። የምዕተ ዓመታት ፖለቲካ እንዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይበላሻል ብሎ ማን አሰበ? እንደምታውቁት፣ የፖለቲካ ውዝግብ እየተዘወተረ ጩኸት እየጨመረ ሲመጣ፣ እርስ በርስ መወነጃጀል ይበረክታል። ይህም በተራው ተመልሶ የእልህና የጥላቻ ስሜቶችን እያባባሰ ያዛምታል።
ተወዳዳሪ ፖለቲከኞች፣ “ትክክለኛ ሐሳብ ይሄውላችሁ። የተሻለ እቅድ ይዣለሁ” ብለው ከመፎካከር ይልቅ፣ ስኬታማና ፍሬያማ ስራ ለማከናወን ከመትጋት ይልቅ፣ እርስ በርስ የመወነጃጀል እልህ ውስጥ ይጠመዳሉ። አንዱ ሌላኛውን ለማጥላላትና ለማዋረድ እንቅልፍ አጥቶ ያድራል። ሥልጣን ይዞ፣ ተቀናቃኞቹን የማሳደድ ክፉ ምኞት ይጠናወተዋል። ተቃዋሚም በተራው፣ ገዢውን ፖርቲ ለመገንደስ ሲያልም ያድራል።
በትንሹም በትልቁም፣ በማንኛውም ሰበብ አንዱ ሌላኛውን እያዋረደም፣ በዚያው ልክ፣ አንዱ ለሌላኛው እጅግ አደገኛ ሆኖ ይታየዋል። ያብጠለጥለዋል፤ ግን ደግሞ ይፈራዋል።
“ለአገር ሕልውና ትልቅ አደጋ ነህ” እያለ አንዱ ሌላኛውን ይወነጅላል።
“አንተ ራስህ፣ ዲሞክራሲን የምታጠፋ ክፉ አደጋ ነህ” ብለው ያወግዙታል።
የፖለቲካ ውጥረቶች እንዲህ እየተካረሩ የጸብ ስሜቶች ሲንተከተኩ፣ በጎራ የሚቧደኑና እንደ መንጋ በጭፍን ስሜት የሚንጋጉ ሰዎች ይበረክታሉ። ሁሉንም ችግሮች እዚያኛው ፓርቲ፣ እዚያኛው ፖለቲከኛ ላይ እየጫኑ የመራገምና የመፍረድ ፉክክር ውስጥ ይገባሉ። ያኛው ገዢ ፖርቲ ከዚህ አገር ቢወገድ፣ ያኛው ባለሥልጣን ከወንበሩ ቢነቀል፣ ያኛው ተቃዋሚ ቢታገድና ቢሰረዝ፣ ያኛው ተቀናቃኛ ፖለቲከኛ ቢከሰስና ቢታሰር… አገር ሁሉ አማን ይሆናል፤ ሕዝብም ያልፍለታል… ብለው በጭፍን ጥላቻ ሲናገሩ፣ ጤናማ ንግግር መስሎ ይታያቸዋል።
ጭፍን የጥላቻ ንግግር እንደ ጤናማ የፖለቲካ ንግግር የሚታይባት አገር፣ እጅግ የታመመች አገር እንደሆነች አይገባቸውም። ተቀናቃኝ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች እርስ በርስ፣ “እንደ ወራዳ” ወይም “እንደ አደጋ” የሚተያዩ ከሆነ፣ ገና ድሮ ነገር ተበላሽቷል። አገሬው ገና ድሮ ወርዷል። አገሬው በገዛ እግሮቹ ወደ አደጋ መንሸራተት ወይም መንደርደር ጀምሯል።
ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች “ፀረ ሰላም”፣ “ከሐዲ የአገር ጠላት”፣ “ፀረ ዲሞክራሲ”፣ “አምባገነን”… እያሉ የሚሰዳደቡ ከሆነ፣ አገሬው ትልቅ አደጋ ውስጥ እየገባ ነው ወይም ለይቶለት ገብቷል ማለት ነው። እንዲህ እንደ ደመኛና እንደ አደገኛ የሕልውና ጠላት የሚተያዩ ከሆነ፣ ከመጠፋፋት ውጭ ምን መፍትሔ ይኖራቸዋል? በጊዜ ወደ ህሊናቸው ካልተመለሱ፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ አይቀርላቸውም። በጭፍን መወነጃጀል፣ “መደበኛ የፖለቲካ ጨዋታ” ይመስላቸዋል። ግን፣ መደበኛ ከሆነ፣ ጤናማ አይሆንም። በብዙ የአፍሪካና የአረብ አገራት ውስጥ አይተነው የለ!
ዛሬ ዛሬ በአሜሪካ ፖለቲካ ላይ የምንታዘበው አዝማሚያስ?
አዎ የፖለቲካ ውዝግቦች በርክተዋል። መወነጃጀልም እንደዚያው።
ለአብዛኞቹ ውዝግቦችና ችግሮች ዋናው ተጠያቂ ዶናልድ ትራምፕ ናቸው ብለው የሚያስቡና ጣታቸውን የሚቀስሩ ፖለቲከኞች ጥቂት አይደሉም። የአሜሪካ ፖለቲካ የተቃወሰው ትራምፕ ወደ ፖለቲካ ከገቡ በኋላ ነው ብለው ያወግዛሉ፤ ይወነጅላሉ። ከትራምፕ በተጨማሪ በደፈናውና በጅምላ የሪፐብሊካን ፓርቲ ፖለቲከኞችን የሚያወግዙም አሉ። ግን፣ ነገሩን ሁሉ አንድ ሰው ላይ መጫንና መፍረድ ይቀልላል። እናም፣ ትራምፕን ላይ ይፈርዳሉ።
ውዝግቦች ሁሉ በትራምፕ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ናቸው፤ ውዝግቦች የተባባሱት አቶ ትራምፕ ወደ ፖለቲካ ከገቡ ወዲህ ነው ይላሉ። እንደዚያ ቢሆን ይሻል ነበር። የአሜሪካ የፖለቲካ ውዝግብ፣ በትራምፕ ዘመን የተፀነሰና የተወለደ ከሆነ፣ ያን ያህልም አሳሳቢ አይሆንም ነበር። ብዙም ስር ያልሰደደ ጊዜያዊ አምባጓሮ፣ በአንድ ሰው ላይ ብቻ ያተኮረ ያልሰፋ ያልተንሰራፋ አነስተኛ ችግር ይሆን ነበራ።
አገሬውን ከዳር እስከማኸል የሚያንቀጠቅጥ ርዕደ መሬት፣ አገሬውን የሚያጥለቀልቅ የማዕበል ንረት አይምጣ እንጂ፣ ጊዜያዊና ጥቃቅን የወረት ችግሮች ለመፍትሔ አይከብዱም ብንልም ያስኬድ ነበር።
የተወዛጋቢዎቹ የምንሰማቸው መፍትሔዎችም፣ ላይ ላዩን ስናያቸው፣ እጅግ በጣም ቀላል መፍትሔዎች ይመስላሉ።
ቀላል መፍትሔ ቁ.1፡
አወዛጋቢው ሰውዬ ከአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ከወጡና ከምርጫ ሜዳው ከተባረሩ፣ ሁሉም አማን ይሆናል፤ ቢያንስ ቢያንስ “እፎይታ” ይገኛል ብለው የሚያስቡ ፖለቲከኞችና ምሁራን በአሜሪካ ሞልተዋል።
ሲኤንኤን ወይም ኤምኤስአንቢሲ ላይ በጥላቻና በብስጭት ሲያወሩ የሚውሉና የሚያድሩ የፖለቲካ “ተንታኞችን” ወይም ፖለቲከኞችን ለአንድ ቀን ብትመለከቱ፣ ከበቂ በላይ እየደጋገሙ ይህን ቀላል መፍትሔ ይነግሯችኋል። ዋሺንግተን ፖስትን ማንበብም ትችላላችሁ።
ብቸኛውና ቀላሉ መፍትሔ፣ ትራምፕን ከፖለቲካ ጨዋታ ማስወጣት ነው ብለው ያምናሉ። “አላበዙትም እንዴ?” ያሰኛል። ግን፣ “እንዲያውም ለዘብተኛ ነን” እንደሚሏችሁ አትጠራጠሩ።
ዶናልድ ትራምፕ እሥር ቤት እስኪገቡ ድረስ በሰላም አንተኛም ብለው የሚያስቡና የሴራ ምኞት የሚያማልላቸው የፖለቲካ ዘማቾችና አጫፋሪዎች ጥቂት አይደሉም። የክስ መዓት ሲደረድሩ ቀኑ ነግቶ ይመሽባቸዋል። ምን ዓይነት የጥላቻ አባዜ ቢገጠማቸው ይሆን? ኃያል ቢሆን ነው።
እጅግ ቢጠናወታቸው ነው እንጂ፣ “ያልወደዱትን ፖለቲካኛ፣ የጠሉትን ተወዳዳሪ ለማሣሠር እንቅልፍ አጥቶ ማደር ምን ይባላል? ዋናውን ተፎካካሪ ከምርጫ ለማገድ ወይም ለማሳገድ፣ ለአሜሪካ የማይመጥን የፖለቲካ ዘመቻስ ምን የሚሉት ፖለቲካ ነው? ጭፍን የጥላቻ ፖለቲካ እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?መ
“በጭራሽ የጥላቻ ፖለቲካ አይነካካንም” ብለው የሚናገሩና መከራከሪያ መልስ የሚሰጡ ይኖራሉ። ዶናልድ ትራምፕን ለማሣሠር ወይም ለማሳገድ የምንዘምተው በጥላቻ ስሜት አይደለም ብለው ሺህ ጊዜ ቢናገሩ ያሳምናል?
“ማንኛውም ሰው፣ ድኻም ይሁን ሃብታም፣ የምርጫ ተወዳዳሪም ይሁን ባለሥልጣን፣ ወንጀል ከፈጸመ፣ ወደ ሕግ ዳኝነት መቅረብ አለበት። ተቆርቋሪነታችንም ለሕግ የበላይነት ነው፤ ዶናልድ ትራምፕ ዓመጽ ቀስቅሰዋል፤ ዓመጽ ፈጽመዋል። የምርጫ ውጤት ለመሰረዝ ሞክረዋል። በተቃውሞ ሰልፍ የአገሪቱ ምክር ቤት በዓመጸኞች እንዲወረር አነሳስተዋል። የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ለማስገበር ቃለ መሐላ የፈጸመ ሰው፣ በዓመጽ ተግባር ላይ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ከተሣተፈ፣ በምርጫ እንዳይወዳደር ይታገዳል። ሕግ ነው። ዶናልድ ትራምፕ፣ ለአገር ሕልውናና ለዲሞክራሲ አደጋ ናቸው” ብለው ማብራሪያና ማሳመኛ ይደረድራሉ።
ዶናልድ ትራምፕን መግታትና ከምርጫ ሜዳው ማገድ ካልተቻለ፣ በምርጫ አሸንፈው ሥልጣን ከያዙ፣ እንደገና ወደ ዋይት ሃውስ ከገቡ፣ “የአሜሪካ ዲሞክራሲ” ያበቃለታል ብለው በፍርሃት ይናገራሉ። ወይም ራምፕ ለዲሞክራሲ አደጋ ናቸው እያሉ ያስፈራራሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ እንዲህ ዓይነት ንግግር የሚያናድዳቸው ሌሎች በርካታ አሜሪካውያን በበኩላቸው፣ በዶናልድ ትራምፕ ላይ የሚካሄደው ዘመቻ ለአገርና ለትውልድ ትልቅ አደጋ ነው ብለው እንደሚያምኑና ክፉኛ እንደሚጨነቁ ይገልጻሉ።
ቀላል መፍትሔ ቁ.2 (የትራምፕ ደጋፊዎች ስጋትና መፍትሔ)።
ዶናልድ ትራምፕን ከፖለቲካው ዓለም ለማስወጣትና ከምርጫ ለማገድ የሚካሄደው ዘመቻ፣ “ጭፍን የጥላቻ ዘመቻ ነው፤ ይህም አገሪቱን የሚያፈርስ አደጋ ይሆናል” ብለው ያምናሉ - ብዙ የሪፐብሊካን ፓርቲ ፖለቲከኞች። የትራምፕ ደጋፊዎች፣ በክስ ወከባውና በእገዳ ዘመቻይ ይበግናሉ። “አሜሪካ መጫወቻ ሆነች” በማለት በስጋት ይብሰለሰላሉ። በንዴት ይንገበገባሉ።
ለአደገኛው የፖለቲካ ውዝግብም ቀላሉ መፍትሔ፣ በትራምፕ ላይ የሚካሄዱ የውንጀላና የማሳደድ ዘመቻዎችን ማስቆም ነው ይላሉ። ለትራምፕ ተቆርቋሪ የመሆን ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ አገርን የማዳን ጉዳይ ነው ብለውም ያስባሉ። አስተማማኙ ዘዴም፣ ቀላል ነው። ዶናልድ ትራምፕን እንደገና በፕሬዚዳንትነት መምረጥ ነው - መፍትሔው።
እንግዲህ አስቡት።
በአንድ በኩል፣ ዶናልድ ትራምፕን ከምርጫ ውድድር ለማገድና ለማስወጣት በየክልሉ የክስ መዝገቦች እየተከመሩ ነው።  
እንዲያም፣ የኮሎራዶ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ተፎካካሪ መሆን አይችሉም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል። በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው ክስተት ነው ተብሏል።
በአፍሪካና በአረብ አገራት፣ በደቡብ አሜሪካና በኤስያ አህጉራት፣ የምርጫ ተፎካካሪዎች ላይ ክስና ውንጀላ እየደራረቡ ከፖለቲካ ምርጫ ማገድና ማሠር ብዙም አዲስ ነገር አይደለም። አያስደንቅም። ተፎካካሪዎች ቢታሠሩ፣ ወይም ገዢው ፓርቲ በዓመፅ ከስልጣን ቢባረር አይገርምም። እንዲያውም፣ በብዙ የአፍሪካና የአረብ አገራት ውስጥ ከእሥርና ከዓመፅ ጎን ለጎን፣ ለወጉ ያህል የፖለቲካ ምርጫ መኖሩና መካሄዱ፣ እንደ ትልቅ ውለታ ሊቆጠር ይችላል።
በአሜሪካ… በዚያች የነጻነት ምድር፣ ነጻነትን ከሕግ የበላይነት ጋር የሚያጣምር ሥልጡን የፖለቲካ ጎዳናን በመቀየስና የመጀመሪያ ተጓዥ በመሆን የአርአያነት ክብር የተጎናጸፈች አገር፣  የፖለቲካ ምርጫንና የሕግ ሥርዓትን የሚያዋድድ ፖለቲካ የተስፋፋባት የተስፋ አገር ውስጥ ግን…የዓመጽና የረብሻ ወይም የክስና የእገዳ ዘመቻ ሲፈጠር ያስገርማል። አዲስ ታሪክ ነው። እንዲህ ዓይነት ነገር ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። ይህም ብቻ አይደለም።የክሶች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ፣ የዶናልድ ትራምፕ የፖለቲካ ድጋፍ እየጨመረና እየደነደነ መምጣቱም ያስገርማል
እንግዲህ፣ ከሁለቱ ቀላል መፍትሔዎች መካከል አንዱን ይዘን፣ ዶናልድ ትራምፕን ወይም ከሳሾችን መውቀስ እንችላለን። ችግሩ ግን፣ የፖለቲካ ብልሽት እንዲህ በቀላል መፍትሔ የሚታከም አይደለም። በአፍሪካ ወይም በአረብ አገራት ውስጥ፣ ስንትና ስንት ገዢዎች በዓመጽ ተወግደዋል። ስንትና ስንት ተቃዋሚዎች በግድያና በእሥር ተደምስሰዋል። የዓመፅና የእስር ዘመቻ፣ አገርን የሚያድን ሁነኛ መፍትሔ እንደሚያመጣላቸው በማመን፣ ብዙ የለውጥ አብዮቶች፣ ብዙ የማፅዳት ዘመቻዎችን አካሂደዋል - የአፍሪካና የአረብ አገራት ፖለቲከኞች። ግን የፖለቲካ ብልሽት፣ እንዲህ በቀላሉ መፍትሔ አያገኝም። እንዲያውም የተቃውሞ ዓመፆችና የመንግሥት የአፈና ዘመቻዎች በአብዛኛው፣ የፖለቲካ ብልሽት አንድ ተጨማሪ ገጽታዎች ናቸው።
ሥልጡን የፖለቲካ ጎዳና ላይ የተራመዱ የአሜሪካ ሰዎች እንዴት ይሄ ይጠፋቸዋል?
ድሮ ድሮ፣ የክስ መዓት ይቅርና፣ አንዳች የክስ ፍንጭ፣ አንዳች የምርመራ ጉዳይ የተወራበት ፖለቲከኛ፣ ከመቅጽበት የመራጮችን ድጋፍ እንዳያጣ፣ ስሙ እንዳይጎድፍ፣ ዓይንህ ለአፈር ተብሎ ከምርጫው ሜዳ እንዳይወጣ ይፈራ ነበር።
የሂላሪ ክሊንተንና የዶናልድ ትራምፕ ፉክክርን ታስታውሱ ይሆናል።በአንዳች ምክንያት ጥፋት ሳይሰሩ አልቀረም ተብለው  በየፊናቸው የተጠረጠሩ ጊዜ፣ ምርመራ እየተካሄደ ነው የሚል ወሬ የተናፈሰ ጊዜ፣ እንዴት እንደተጨናነቁና እንደተወራጩ አስቡት።የዛሬን አያድርገውና፣ ያኔ የክስ መዝገብ አይደለም የክስ ወሬም ለፖለቲከኞች አስፈሪ ነበር። ድጋፍ ያሳጣ ነበር። ዛሬ ነገሩ ተቀይሯል። በላይ በላዩ እየተደራረበ በክስ ላይ ክስ ይመጣል። ጎን ለጎን የመራጮች ድጋፍ እየበዛና እየከረረ ይመጣል።



Read 623 times