Monday, 15 January 2024 13:19

የኢትዮጵያ አርትና የአብዮቱ ዘመን

Written by  -በቀለ መኮንን /ረ/ፕ/
Rate this item
(0 votes)

--የእምነቱና የመርሁ ተገዥ የሆነ ጠቢብ የታደለ ነው። አብዮቱ ግን ገና በብዙ አቅጣጫ የሚመረመር ጉዳይ አለው። የነበረ ሁሉ ምስክርነቱን ለራሱ ቢፅፍና የታሪክ ሰው ደግሞ በደርዝ በደርዝ አስስተካከሎ ቢያደረጀው የትውልድ መማሪያ ለመሆን ይበቃል። አሁን ችግራችንኮ ታሪክ አደራጁ የታሪክ ባለሙያ ተቀምጦ ሁሉም ሰው ታሪክ ፀሀፊም ታሪክ አደራጅም ሆነ።--”


በየካቲት ወር ስልሳ ስድስት ሲሞሸር በጭብጨባ ተቀብለን፣ በግንቦት ወር ሰማንያ ሶስት ሲባረርም በጭብጨባ የሸኘነው የኢትዮጵያ አብዮት ከፈነዳ እነሆ ሰሞኑን አምሳ አመት ሞላው። አብዮቱ በኛ ዘመንም ሆነ ከኛ ዘመን በፊት በነበሩ የታሪክ ሰነዶች ካልተመዘገቡ ከፉና ደግ ክስተቶችና  የህይወት መልኮች ጋር አስተዋውቆናል። የሀገሪቱን የፖለቲካል ኤኮኖሚ ውሀ ልክ (እስከዛሬም መረጋጋት
እስከሚሳነው) ከመሰረቱ የነቀነቀ ፤ በዚያም ሳቢያ የእምነትና የሃይማኖትን ፤ የትምህርትን፤
የማህበራዊ መስተጋብርን ፤ በጠቅላላው የባህልን መዋቅር ሁሉ ከዚያ ቀደም ባልተሞከረ ስፋትና ትልቀት
ያነኮረ ነበር የኢትዮጵያ አብዮት።
በርግጥ አብዮቱ በድንገት ተጠንስሶ በድንገት የገነፈለ ግብታዊ ክስተት አይደለም። ለዘመናት ሲንፈቀፈቅ የኖረ ሙቀት መግላሊግቱን ለመክፈት የሚበቃ ሰበብ በተፈጠረበት ወቅት ፈነዳ እንጂ። መቸም አብዮት ግድቡን እንደሰበረ ባህር ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ በመንገዱ ላይ የሚገጥመውን ሁሉ ጠራርጎ የመውሰድ ምህረት የለሽ ፤ ፋታ የለሽ አውሬነት ባያጠቃው ኖሮ ፤ እንዲሁ በቁሙ ዙሪያው ተቆልፎበት እስከ ወዲያኛው እያንቀላፋ ላለ ባለ ዘርፈ ብዙ መከራ አገር፣ የመድሀኒትነት ፋይዳ የለውም ለማለት ይቸግራል።
አብዮቱ ከላይ ባነሳሁዋቸው የህይወታችን መንገዶች ፤ ስለ እምነት ስለ ፖለቲካ ስለ አገር ስለ ትምህርት ስለ ጦርነትና ስለ በርካታ ሌሎችም ጉዳዮች ያለንን ነባር አስተሳሰብና መስተጋብር ከመሰረቱ ለውጦታል።


አመጣጡ ለበጎም ሆነ ለክፉ የለውጥ ሂደት ሁሉ ያለ ዋጋ እውን ሆኖ አያውቅም ። እንደኔ ምስክርነት በአብዮቱ ፊታውራሪነት የመጡ ለውጦች ሁሉ ከዋጋቸው በላይ የማይረሳ መስዋዕትነት ያስከፈሉ ቢባል በዘመኑ ኖሮ ያየ ሁሉ የሚስማማ ይመስለኛል። ኢትዮጵያን በመሰለ የሺዎች ዘመናት ነባር ህብረተሰብ ውስጥ ምንም አይነት አማላይ አይዲዮሎጂ አምጥቶ የረጋውን መበጥበጥ ለማንም ከባድ ባይሆንም ፤ ነባሩን አስጥሎ ወይም ከነባሩ ጋር አስማምቶ አዲሱን ማንበር ግን እንዲህ የዋዛ ተግባር አይደለም። ጥልቅ አስተዋይነት የረቀቀ ጥበብና እውቀትን
የሚጠይቅ እድለኝነት ጭምር ነው። ሆኖም ግን ከዚህ በተገላቢጦሽ በእውር ድንብር ፤ በግዙፍ ጡንቻ ላይ ለከት የለሽ ጭካኔ ጨምሮ የህዝብን እጅና ጭንቅላት አምሳ አመታት ሙሉ በመጠምዘዝ የተረፈን ነገር ቢኖር ያላባራ ትርምስና ሁለንተናዊ ኪሳራ ብቻ ነው።
ታሪክም ሆነ ፍልስፍና እንደሚያስተምሩን፣ በየትኛውም ዘመንና ቦታ የተከሰቱ ፖለቲካዊም ሆነ ጥበባዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በጎ ወይም ክፉ መልክ ይዘው በነጠላው ተከስተው አያውቁም። አንዱ ከሌላው ደምቆ አንደኛው ሌላውን ደፍቆ ይኑር እንጂ ክፉ የመኖሩን ያህል በጎ ትርፍም በጎ ውርስም አይታጣበትም።
በዚህ አንፃር ከኢትዮጵያ አብዮት የተረፉን ቁስሎችና ጠባሳዎች ገና በቅጡ ተዘርዝረው ሳያልቁ በየጊዜው አዳዲስና ትኩስ ቁስሎች እያፈራን፣ የየትኛውንም ዘመንና የኑሮ ስርዓት ትርፍና ኪሳራችንን ለማስላት እንኳ ትንፋሽ ማግኘት አልቻልንም። በምስቅልቅል ላይ ምስቅልቅል፣ በረብሻ ላይ ረብሻ ኑሯችንን እየወረረው እነሆ ራሳችንን ፋታ እንደነሳን አለን። የኢትዮጵያ አብዮት እንደፈነዳ ጉዞውና አቅጣጫው ለመሪዎቹም ሆነ ለኛ ለተመሪዎቹ ግልፅና ቀድሞ የታወቀ አልነበረም። ወዲያውኑ ከወደ ምስራቅ በተፈፀመብን ወረራ ምክንያት የምዕራቡ አለም ቁንጮ
የሆነችው አገር በክፉ ቀናችን ላይ ጀርባዋን በማዞሯና እንዲያውም ክፍያ የተፈፀመበትን የጦር መሳሪያ በመከልከል አፍንጫችሁን ላሱ እንዳለችን አይዘነጋም ። በዚያን የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ተቀናቃኟ የምስራቁ አለም ቁንጮ አለኝታነቷን በገለጸችበት ቅፅበት፣ አገራችንም በምሏሹ ማርክሲስት ሌኒኒስት በመሆን የጎራው ተሰላፊ መሆንዋን አረጋገጠች። እና ኢትዮጵያ የሶሻሊዝምን አይዲዮሎጂ እንዴት መረጠች ቢባል በድንገት በጊዜና በሁኔታ አስገዳጅነት የመጣ ለመሆኑ በጊዜው የነበርን ሁሉ ያይን ምስክሮች ነን።
ሶሻሊዝም ከመፅሀፍ ቅዱስ ቃል በቃል የተገለበጠ በሚመስል መልካም መፈክሮቹና መመሪያዎቹ በገባበት አገር ሁሉ በመጀመሪያዎቹ ወራት ያላስጨበጨበው ህዝብ የለም። ውሎ ሲያድር የነዚያ ቅዱስ ቃሎች ባለቤቶች ማርክስና ኤንግልስ ሌኒንና የየአገሩ መሪዎች መሆናቸው መነገር ሲጀምር ህዝብ የመጀመሪያው የላብ ጎርፍ ያጠምቀው ይጀምራል። ትንሽ ቆየት ይልና ከየቤተ እምነቱና ከሀሳቡ ፈጣሪውን አሳልፎ ሰጥቶ ማርክስና ሌኒንን በምትኩ እንዲቀበል ሲገደድ ምፅአት እንደቀረበ ገምቶ አንገቱን ይደፋል። በሀይማኖቱ ተደግፎ ለሚኖር ጥንታዊ ማህበረሰብ የቀረበለት አይዲዮሎጂ ቋቅ ማለት የጀመረው ገና ሁለት መንፈቅ ሳይሞላ እንደነበር አይተናል። ሰምተናል።

መውረስ ማሰር መግደል ማፈስ ማውገዝ ማውደም መረሸን መፈረጅ እና እነዚህን የመሳሰሉ ማስፈራሪያና ማዘዣ ማስደንገጫና ማርበትበቻ ቃላት ከነፅንሰ አሳቦቻቸው በጉልበት በሁላችን ጆሮ እየተሰነቀሩ መስረፅ ጀመሩ። አብዮቱ ካድሬ በሚባሉ አዳዲስ የአይዲዮሎጂ ሰባኪዎች ወይም ራሴ እንደምጠራቸው የፖለቲካ ወጌሻዎች አማካይነት አዳዲስ ቃላትና አዳዲስ የሰዋስው ስርዓቶችም አስተምሮናል። ስርዓተ መንግስት ሲለወጥ ቋንቋና የቋንቋ ስርዓትም አብሮ እንደሚለወጥ ምሁራኑ ይናገራሉ። ከዚያማ ያለ ምንም ደም ተብሎ የተጀመረው አብዮታችን፣ ደም በደም ሆኖ መጠናቀቁን አለም ሁሉ ከኛው እኩል ታዝቦታል።
 በሁሉም የድሀ አገሮች ፖለቲካ እድገትና ውድቀቶች የሃያላኑ እጅና ተፅዕኖ በዘዋሪነት እንደሚሳተፍ ብዙ የዋሀን ኢትዮጵያውያን አይገባንም ነበር። የሰማነውም የተማርነውም የቅኝ ግዛት ሴራና ቅሬተ አካሉ በሌሎች አፍሪካውያን ዘንድ እንጂ ኢትዮጵያን ፈፅሞ እንደማይመለከታት ነበር። ይሄ የዋህነት ዛሬም እንደተንሰራፋ አለ። በዚያ መካከል ከአብዮቱ መስመር ጋር ተጋጭቶ ካድሬዎቹንና የተሞሉትን ፕሮፓጋንዳ እስካልተቃረነ ድረስ ባብዮቱ መድረክ ብዙ መንቀሳቀስ ይቻል ነበር። ከዚያ ሁሉ አበሳ መካከል መልካም የሚባሉ (መሪዎቹን እስካላስቀየሙ) ተግባራትም አይተናል። ከትልልቆቹ ማይምነትን ከመቀነስና ሰዎችን ወደተሻለ አካባቢ ከማስፈር ጀምሮ እስከ ማህበራዊ ግንኙነት ትስስር በየደረጃው የተከናወኑ አዎንታዊ መልካም የሚባሉ ተግባራት ነበሩ። በዚህ ተርታ ከሚጠቀሱት ውስጥ የስነጥበብ እንቅስቃሴ መስፋፋት አንዱ ሆኖ የሚጠቀስ ነው። ሙዚቃ ፤ ስዕል ፤ ተውኔት እና የመሳሰሉት ሁሉ በቀበሌ በከፍተኛና በከተሞች እንዲሁም በመስሪያ ቤቶችና በማህበራት ሳይቀር መደራጀታቸው በየትኛውም አካባቢ ለነበረ ኢትዮጵያዊ ወጣት ሁሉ የተሰጥዖው መፈለጊያ ማጠናከሪያና መታወቂያ ሆኖ አገልግሏል።
ይህ አጋጣሚ የተፈጠረው አብዮቱ ለስነጥበብ ስስ ልብ ስላለው ወይም የጥበባት አድናቂ ስለሆነ ሳይሆን ወይም ስነጥበብን ከሌሎች መስኮች ሁሉ ለይቶ ለመጥቀም አስቦ ሳይሆን በግልፅ እንደሚታወቀው አዲሱን አይዲዮሎጂ በሰፊው ህዝብ ውስጥ በስፋትና በጥልቀት ለማስረፅ ፤ እንደየትኛውም መንግስት የፍላጎቱ ምቹ ማስፈፀሚያ ይሆናል ብሎ በማሰብ ነው። መሪሩን አሳብና አስተሳሰብ በማር እየጠቀለሉ
እንደማጉረስ። የወዝ አደሩ የበላይነት ፤አለማቀፋዊ ወዛደራዊነት ፤የኢምፔሪያዝምና የፊውዳሊዝም ጠላትነት፤ የገበሬው የሴቶችና የወታደሩ አጋርነት እና ሌሎችም መሰል ርዕስ ጉዳዮች የፈጠራ ሁሉ ማዕከላዊ ማጠንጠኛዎች እንዲሆኑ በቀጭን ትዕዛዝ ይሰጡ ነበር።


ይሄ ትዕዛዝ በቀበሌና በመስሪያቤቶች የተወሰነ ሳይሆን በመደበኛ ትምህርት ቤቶች ሳይቀር በፅሁፍ እንድናውቀው ይደረግ ነበር። ይሁን እንጂ አንዳንዴ በአብዮትና በፀረ አብዮት መካከል ያለችን ቀጭን የምታስቀጣ ድንበር መለየት የሚያስቸግርበት ጊዜም ነበር። ለምሳሌ በሰባዎቹ መጀመሪያ ለቀበሌያችን አንድ ክብረ በዓል ሰርቼ ያቀረብኩት የካርቱን ስዕል በቀበሌው ሊቀመንበር ውድቅ እንደተደረገብኝ አስትታውሳለሁ። ከክልከላው ይልቅ የክልከላው ምክንያት አስቂኝ ነበር። “ ይህ አይነቱ የስዕል አሰራር የኢምፔሪያሊስቶች ስልት ስለሆነ በፍፁም እንዳይለጠፍ “ የሚል ነበር። በሁዋላም በሰባዎቹ አጋማሽ የስነጥበብ ትምህርት ቤት ተማሪ ሆኜ ተመሳሳይ ጭፍን ያላዋቂ ውሳኔ አይቻለሁ ። ይሄኛው ደግሞ ከማይምነት ትንሽ ከፍ ብሎ በተቻለ መጠን የእውቀት ድጋፍ እንዲኖረው ለማድረግ የተሞከረበት አጋጣሚ ነው። ዕጩ ተመራቂው ለምረቃው ዳኝነት ለተቀመጡ መምህራን ባቀረበው ድርሰት ውስጥ ጣቱን ሽቅብ እያመለከተ ከመካከል የቆመ ወጣት ወደ ሰማይ ሲያመለክት ይታያል ። የሰው ልጅ ወደ ሰማይ እያንጋጠጠ በአምልኳዊና ተአምራዊ አስተሳሰብ ከሰማይ መና እንዲጠብቅ ማሳየት ህብረተሰቡን ማዘናጋት ጎታችና ሜታፊዚካዊ አስተሳሰብ ነው የሚል ክስ ተሰነዘረበት። አልፎ ተርፎም በችሎታው ተሸላሚነቱ እንዲቀርና ከደረጃው ዝቅ ብሎ እንዲመረቅ ሞራላዊ ድንጋጤም እንዲደርስበት ተደርጓል ። ከዚያም በከፍተኛ ድብታ ውስጥ ገብቶ የህይወቱ ማለፊያ ምክንያት ጭምር መሆኑ የምናውቅ እናውቃለን ።
ከዚህ ድንቁርናና ጭካኔ በመለስ የቀበሌና የከፍተኛ መድረኮች ለጥበባዊ ልምምዶች የከፈቱት በር ብዙ ታዋቂ ጠቢባንን ማፍራት ችሏል። ከሁሉ ከሁሉ በጥበባቱ ለመዝናናት ወዶም ሆነ ተገዶ የሚሰበሰበውህዝብ ከጊዜ ወደጊዜ የጥበብ አድናቆት እያደረበት ማድነቅን መለማመዱ አልቀረም። በአድናቂ ፊት
መከወንም ሆነ በሺዎች ፊት አግራሞትን ጭብጨባን ማግኘት በተለይ በወጣትነት ወራት ልዩ ኩራትና የፅድቅ ስሜት ያጎናፅፍ ነበር። በነገራችን ላይ በርከት ያሉ ቅስቀሳዎች ስብሰባዎች የእናት አገር ጥሪዎች እና ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው መደበኛና መደበኛ ያልሆኑ ፕሮግራሞች ላይ ሙዚቃ ስዕልና ተውኔት
የጉዳዮች ሁሉ አጃቢዎች እንዲሆኑ የተፃፉም ያልተፃፉም ህጎች ስለሚያዙ የሙያውን ክህሎት ከፍ
ከማድረግ ባለፈ ቀጭን ጌታ የሚያደርግ ገቢም ማስገኘቱ አይዘነጋም።
በስዕል ጥበብ በኩል የፖስተርን ጥበብ በኢትዮጵያ ያስተዋወቀ አብዮቱ መሆኑን ስንቶቻችን እናውቃለን። ለወትሮው ካብዮቱ በፊት ጥምቀትና ገና ዕንቁጣጣሽና ቡሄ ጠብቆ ነበር ሰው ሁሉ በስፋት የሚገናኘው ። አብዮቱ ግን ወጣትና ጎልማሳ ከዚያም አልፎ ዜጋውን በሙሉ እለት በለት በምክንያት እየሰበሰበ ቶሎ ቶሎ በማገናኘቱ ወጣቱ በፍቅር ጎልማሳና አዛውንቱ በወዳጅነት እንዲጣመር ምክንያት ሆኗል ። በርግጥ
መጠራጠር መጠቋቆም መቀባባትን የመሰሉ የክፋት ጎኖቹም እንዳሉ ሆነው።
የአብዮቱ አንዱ ግብዝነት የግለሰብ ፍቅርን የሚከለክል ስለነበር ስለ ፍቅር መዝፈን የሚበረታታ አልነበረም። ወይም እንደምንም ፍቅርን የመሰለ ዘፈን የሚያሳትም ካለ የአብዮቱን ወይም ቢያንስ የሀገር ፍቅርና ቀረርቶ መሰል አላል ጣል እንዲያደርግ ግድ ነበር። በቀበሌ ሱቆች ፓስታ ለመግዛት አንዳንዴ ሳሙና የግድ እንደሚሆነው ። ይህንን በሚመለከት ያኔ እማርበት በነበረው የስዕል ትምህርት ቤት ውስጥ
ተማሪዎች ሁሉ የመንግስት አይዲዮሎጂ ከሚጠብቅብን አቅጣጫ በተቃራኒ የምንሄድበት አግድም ብልጠት አሁን ሳስበው ይገርመኛል።
 ለነገሩ አብዮቱ በሁሉም ህዝብ ዘንድ ለመጠላት ብዙ ጊዜ አልወሰደበትምና ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሆዱን በሆዱ ይዞ በተለመደው ቅኔ ለበስ ግምባሩ ብቻ ይግባባ ነበር። በስዕል ትምህርት ቤት ውስጥ ቁጥራቸው በርከት ያለ አርበኞች የስዕል ድርሰት ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ የቀረበው ባብዮቱ ጊዜ ነው ። ሰበቡም ካብዮቱ ርዕሶች ውጪ ሲሰራ በአብዮቱ ሹመኞች ዘንድ ቁጣም ኩርፊያም የማያስነሳ እሱ ብቻ ስለሆነ ነው ። በተረፈ የግል ህይወትና የግል ህልሞች መስራት ለመከልከል እድል የማይሰጡ ርዕሶች ነበሩ። በሌላ በኩል ይሄ ሁሉ ድብብቆሽ በራሱ ጥበብን የሚጠይቅ ማሰብን የሚፈልግ እግረመንገዱን ብልህነትን የምንማርበት ሳንወድ የገባንበት ልዩ የብልሀት ፍለጋ ዘዴ ነበር ማለት ይቻላል።


በመጨረሻም የሶሻሊት ሪኢያሊዝም ማለትም የሶቪየት ሶሻሊዝም ኦፊሴላዊ የስነጥበብ ፍልስፍና ከሌሎች የሶቪየት ሸቀጦች ጋር በኢትዮጵያ አስገዳጅ ጥሎሽ ሆኖ ነበር። ብዙ የውጭ ሀገር ፀሀፊዎችና ተመራማሪዎች አንዳንድ የሀገር ውስጥም ሰዎች የዘመኑ የጥበብ መመሪያ ሆኖ ሲያገለግል ነበር ሲሉ ይደመጣሉ። በዘመኑ ኖሮ የመጀመሪያ ምስክር እንደሆነ ሰው ይህ አባባል ፈፅሞ የተሳሳተ መሆኑን
ማረጋገጥ እፈልጋለሁ። በርግጥ ሶሻሊስት ሪያሊዝም መንግስት ከሌሎቹ ሶቪየቶቹን ሊያስደስቱ ቃል  ከገባባቸው ቅድመ ግዴታዎች አንዱ የአይዲዮሎጂ ስንክሳር መሆኑ የሚካድ አይደለም። የሆነው ሆኖ ሶሻሊስት ሪያሊዝም ራሱን የቻለ የአይዲዮሎጂ መሰረት ያለው የአተያይና የአሰራር ሶቪየታዊ ፍልስፍና ክንፍ ነው። ከፋም ለማ ፍልስፍናው ጥናትና ልምምድን የሚጠይቅ መመሪያ ነው። በዚህ ረገድ የአብዮቱ
መሪዎችም ሆኑ ፍልስፍናውን ተከትለዋል የሚባሉት ( ገብቷቸወ የተከተሉ ካሉ ) ማናቸውም ይህንን ጥናት አውቀውና አምነው የሰሩም ያሰሩም መኖራቸውን እጠራጠራለሁ። ቁንፅል ድርጊቶችና ክንዋኔዎችን
በመጥቀስ ለምሳሌ የሊቀመንበሩን ከንፈር ቆጠብ በማድረግ ጠጉራቸውን ከፍጥረቱ ውጭ ዞማ በማስመሰል የመስራትን ልማድ ጠቅሶ ወይም ያለቀሰን ህዝብ በሳቅ ተንፈቀፈቀ ብሎ የተዘፈነበትን መድረክ በማስታወስ ሶሻሊስት ሪያሊዝም ይሰራበት ነበር ብሎ መደምደም አይቻልም። እንኳንስ በዚያ
ዘመን ዛሬም ቢሆን ከሞላ ጎደል ባብላጫው ባለስልጣንም ሆነ ባገራችን ተደራሲ ዘንድ የስነጥበባት ፍልስፍናዎች የማንም ቁብ ሆነው አያውቁም። አብዮቱም በድንገት ያየውን ስዕል በድንገት ከኪሱ ባወጣት ግምት የኢምፔሪያሊስት እንዳለው የቀበሌያችን ሊቀመንበር ሁሉ በመሰለኝና በደስ አለኝ
ባይደናበር ኖሮ ከዚያ አስቸጋሪ ዘመን አልፈው ለዛሬ የሚበቁ የጥበብ ሰዎች ባልኖሩን ነበር ።
ፍልስፍናውም በጥናት ሰርፆ ቢሆን ኖሮ ሶሻሊዝም ቀርቷል በተባለ ማግስት በቀላሉ አብሮ ብን አይልም ነበር።
በየትም ዘመንና አገር ሁሌም የትኞቹም መንግስታት በጥበባት በኩል ጉዳይን ማስፈፀም ቀላልና ውጠጥታማ መሆኑን ያውቃሉ። ያምናሉ። የዚያኑ ያህል ክህሎታቸውን ሸጠው የታዘዙትን ድምፅ
በማሰማት የለት እንጀራቸውን እየጋገሩ የሚኖሩ እንዳሉ ሁሉ ጥበብ ከስራ በላይ የህይወታቸው ክፍል ሆኖ የታዘዙትን ሳይሆን ያመኑትን እየተጠበቡ የሚኖሩም አሉ ። አንዳንዴ ሹም የሚፈልገውና ጠቢብ ያመነው የሚገናኙበት ጊዜም እንዳለ ማወቅ ያስፈልጋል።
የእምነቱና የመርሁ ተገዥ የሆነ ጠቢብ የታደለ ነው። አብዮቱ ግን ገና በብዙ አቅጣጫ የሚመረመር ጉዳይ አለው። የነበረ ሁሉ ምስክርነቱን ለራሱ ቢፅፍና የታሪክ ሰው ደግሞ በደርዝ በደርዝ አስስተካከሎ ቢያደረጀው የትውልድ መማሪያ ለመሆን ይበቃል። አሁን ችግራችንኮ ታሪክ አደራጁ የታሪክ ባለሙያ ተቀምጦ ሁሉም ሰው ታሪክ ፀሀፊም ታሪክ አደራጅም ሆነ። መጨረሻው የቱ መማሪያ የቱ መፋረጃ መሆኑ ሳይለይ ሁሉንም መፈናከቻ አርገውት እነሆ ከግራም ከቀኝም ድንጋይ ይዘን ቆመናላ !
ያም ሆነ ይህ በአምሳ አመታት ጉዞ ከተማርነው የተማረርነው አይበልጥም ???

Read 339 times