Sunday, 10 December 2023 20:24

በ2023 የዓለም አትሌቲክስ ሽልማት

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች በተለያዮ ዘርፎች ዋንኞቹ ተፎካካሪዎች ናቸው ትግስት የኮከብ አትሌት ሽልማቱን ለ7ኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ታመጣ ይሆን? ፌዝ ኪፕየገን ለአሸናፊነት ከፍተኛ ግምት ወስዳለች


          የ2023 የዓለም ኮከብ አትሌት ሽልማት በሞናኮ የሚካሄድ ሲሆን በዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ አሸናፊዎችን መላው ዓለም በጉጉት እየጠበቀ ነው። የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ከዋናው የሽልማት ስነስርዓት በፊት በተለያዩ የሽልማት ዘርፎች ያሸነፉትን ሰሞኑን እያስታወቀ
ነው። ስዊዘርላንዳዊው ለውረንት ሙውሊ የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ፣ የቶጎዋ ቻናይሌ ሳለይፉ የዓመቱ ምርጥ ሴት እንዲሁም ማቲያ አቦሰቶ የዓመቱን ምርጥ ፎቶግራፍ ሽልማቶች አሸንፈዋል። በሳምንቱ መግቢያ በሞናኮ በሚካሄድ ስነስርዓት ላይ በሁለቱም ፆታዎች የዓለም ኮከብ አትሌቶች ሆነው የሚመረጡት ከልዩ ሽልማታቸው ባሻገር 100 ሺ ዶላር የሚሸለሙ ይሆናል። ከኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ትግስት አሰፋ በሴቶች ምድብ ለመጨረሻ እጩነት ከቀረቡ አትሌቶች የምትገኝ ሲሆን ሰባተኛውን የዓለም ኮከብ አትሌት ሽልማትን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ነው። በሌላ በኩል ለተሰንበት ግደይ ለዓመቱ የስፖርታዊ ጨዋነት እንዲሁም መዲና ኢሳ ለዓመቱ አዲስ ኮከብ አትሌት ሽልማቶች በመጨረሻ እጩነት መግባታቸው ይታወቃል።
በዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ኃይሌ ገ/ስላሴ በ1999 እ.ኤ.አ፤ ቀነኒሳ በቀለ በ2004ና በ2005 እ.ኤ.አ፣ መሠረት ደፋር በ2007 እ.ኤ.አ፣ ገንዘቤ ዲባባ በ2015 እ.ኤ.አ እንዲሁም አልማዝ አያና በ2016 እ.ኤ.አ ላይ አሸንፈዋል።በማራቶን ውድድር ከሁለት ዓመት ያነሰ ልምድ ያላት ትግስት
አሰፋ በ2023 የውድድር ዘመን በማራቶን ያስመዘገበችው የላቀ ው ጤ ት ለሽልማቱ አድርሶታል። የበርሊንን ማራቶን በማሸነፍ እና አዲስ የዓለም ማራቶን ሪከርድ በማስመዝገብ ያስመዘገበችው ስኬት ነው። የዓለም ሪከርድን 2 ደቂቃዎች ከ14 ሰከንዶች በመቀነስ በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻሏ በርቀት አይነቱ ከ40 ዓመት በኋላ የተመዘገበ አስደናቂ ስኬት ሆኖ ተወስቷል፡፡ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ለሽልማቱ ከፍተኛ ግምት የወሰደችው ግን
ኬንያዊቷ ፌዝ ኪፕዬጎን ናት። በመካከለኛና በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች የዓመቱን ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቧ ለሽልማቱ እንደሚያበቃት ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ ፌዝ በ1500 ሜትር እና በ5000 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ከመሆኗም በላይ 3 የዓለም ሪከርዶችን በ1500 ሜትር፤ በማይልና
በ5000 ሜትር ማስመዝግቧም ይታወቃል፡፡ በ400 ሜትርና በ400 ሜትር መሰናክል የምትወዳደረው ፌምኬ ቦል ከሆላንድ በ400 ሜትር መሰናክል የዓለም ሻምፒዮንነትና የዓለም የቤት ውስጥ ሪከርድን በማስመዝገቧ ፤ ጃማይካዊቷ የአጭር ርቀት ሯጭ ሸሪካ ጃክሰን በ200 የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን በመብቃቷ እና በ100 ሜትር የብር ሜዳልያ በማግኘቷ እንዲሁም በሁለቱም ርቀት የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ ስለሆነች ኮሎምቢያዊቷ የስሉስ ዝላይ ተወዳዳሪ ዩሉምር ሮጃስ በውድድር ዓመቱ የዓለም ሻምፒዮናነት ክብርና የዳይመንድ ሊግ ዋንጫን በመቀዳጀቷ የመጨረሻ እጩ ሆነው
የቀረቡ ናቸው።በወንዶች ምድብ የመጨረሻ እጩ ሆነው ከቀረቡት አምስት አትሌቶች መካከል የለንደንና የቺካጎ ማራቶኖችን ያሸነፈውና የዓለም ሪከርድን ያስመዘገበው ኬንያዊው ኬልቪን ኪፕቱም ቀዳሚ ግምት ወስዷል። ህንዳዊው የጦር ወርዋሪ ኔራጅ ቾፕራ፤ አሜሪካዊው የመዶሻ ወርዋሪ ራያን ሮብሰን፤ ስዊድናዊው የምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳሪ ሞንዱ ዱፕላንቲስና በ100 ሜትርና በ200 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን የሆነው አሜሪካዊው
ኖህ ላይነስ ሌሎቹ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡


Read 388 times