Saturday, 02 December 2023 20:15

“የጡት ካንሰር መታከም የሚችል የካንሰር አይነት ነው” ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሐናን አለባቸው

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

 ከዚህ ቀደም በነበረው እትም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የቀዶ ጥገና ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የጡት፣ የእንቅርት እና ተያያዥ እጢዎች ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሐናን አለባቸው ስለጡት ካንሰር የሰጡትን ሙያዊ ማብራሪያ ለንባብ ማቅረባችን ይታወሳል። የዚህ ቀጣይ ክፍል እንሆ ለንባብ ቀርቧል። የጡት ካንሰር በዓለምአቀፍ ደረጃ ከ8 ሴቶች መካከል በ1 ሴት እንዲሁም ከ833 ወንዶች ውስጥ በ1 ወንድ ላይ እንደሚያጋጥም ይገመታል። ይህ ካንሰር የጉዳት መጠኑ ሳይጨምር ህክምና እንዲያገኝ እራስን መፈተሽ[መመርመር] ይመከራል። ዶ/ር ሐናንአለባቸው እንደተናገሩት አንዲት ሴት እራሷን እንድትመረምር የሚመከረው የወርአበባ ካየች በኋላ ባለው ከ5 እስከ 9 ቀናት ውስጥ ነው። የህክምና ባለሙያዋ እንደተናገሩት እነዚህ ቀናት የተመረጡት በወርአበባ ወቅት ባለው የሆርሞን መለዋወጥ ምክንያት የጡት መጠን ስለሚጨምር በጡቱ ላይ ያለውን ለውጥ ለመለየት አዳጋች በመሆኑ ነው። የወርአበባ ኡደት ካበቃ በኋላ የሆርሞን ለውጥ ባለመኖሩ እራስን ለመመርመር አመቺ ጊዜ ይሆናል። የወርአበባ ማየት ያቆመች ሴት ከሆነች ደግሞ በወር ውስጥ አንድ ቀን በመምረጥ እራሷን መፈተሽ ትችላለች። እራስን መፈተሺያ[መመርመሪያ] መንገዶች
* መስታወት ፊትለፊት በመሆን የሁለቱ ጡት ቅርፅ ተቀራራቢ መሆኑን ማረጋገጥ
* የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ መግባት ወይም አለመግባቱን መለየት
* ቀኝ እጅን ወደ ላይ በመዘርጋት በቀኝ በኩል ያለውን ጡት በግራ እጅ አማካኝነት እንዲሁም በግራ በኩል ያለውን ጡት በቀኝ እጅ ዙሪያውን(ክብ) መዳሰስ ከላይ የተጠቀሱትን የምርመራ ሂደቶች ሰውነትን ከታጠቡ በኋላ ማድረግ ይመከራል። በህክምና ተቋም የሚሰጡ ምርመራዎች
* በህክምና ባለሙያ አማካኝነት ምርመራ ማድረግ
* ማሞግራፊ; በእጅ ከሚደረግ ምርመራ ጋር ሲነፃፀር 3 ዓመት በመቅደም ችግሩን ለማወቅ ያስችላል። እድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች ይህን ምርመራ በየ 1 ዓመት እንዲያደርጉ ይመከራል።
* የአልትራሳውንድ ምርመራ
* ኤም አር አይ; እድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች ለሆኑ እና በቤተሰብ ውስጥ የካንሰሩ ታሪክ ላላቸው ሴቶች በይበልጥ ይህ ምርመራ ተመራጭ ነው። ቅድመ ካንሰር(ደረጃ 0)፣ ደረጃ 1፣ ደረጃ 2፣ ደረጃ 3 እና ድረጃ 4 በመባል የጡት ካንሰር ይከፈላል። የጡት ካንሰር ደረጃ 1 እና ደረጃ 2 የሚባለው የእጢው መጠን 2 እና ከ2ሴንቲ ሜትር በታች ሲሆን ነው።ጡት አከባቢ ላይ በሰፊው ተሰራጭቶ የሚገኝ የጡት ካንሰር ደረጃ 3 ይባላል። ደረጃ 4 የጡት ካንሰር ደግሞ ወደ ሳንባ፣ የጀርባ አጥንት፣ ጉበት እና ወደ ተለያየ የሰውነት ክፍል የተሰራጨ ነው። በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኝ ከጡት በተጨማሪ የወገብ እና የጀርባ ህመም፣ ትንፋሽ የማጠር እና አይን ቢጫ የመሆን ምልክት ሊያሳይ ይችላል። የዓለም የጤና ድርጅት እኤአ በ2020 ባወጣው መረጃ መሰረት ምርመራ ተደርጎላቸው በጡት ካንሰር እንደተጠቁ ከተረጋገጡ ሴቶች መካከል 7.8 ሚሊዮን የሚሆኑት ለ5 ዓመታት ከካንሰሩ ጋር በህይወት መቆየት ችለዋል። የጡት ካንሰር ደረጃው ከፍ ሳይል ህክምና ካገኘ የማገገም እና የመዳን እድሉ ከፍተኛ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። የጡት ካንሰር ህክምና አይነቶች የሚባሉት ቀዶ ጥገና፣ ኬሞቴራፒ፣ ሆርሞናል ቴራፒ እና የጨረር ህክምና ናቸው። ዶ/ር ሐናን አለባቸው እንደተናገሩት ደረጃ 1 እና 2 ላይ ለሚገኙ የጡት ካንሰር ታካሚዎች የቀዶ ጥገና ህክምና ተመራጭ ነው። በቀዶ ጥገና አማካኝነት ካንሰር ያለበትን የጡት ክፍል ብቻ በማስወገድ ህክምናው ይሰጣል። ይህን ህክምና ያገኙ ታካሚዎች በመቀጠል የጨረር ህክምና ማግኘት ይኖርባቸዋል። ነገር ግን እንደ የህክምና ባለሙያዋ ንግግር በኢትዮጵያ የጨረር ህክምና የሚገኘው በጥቂት የህክምና ተቋማት ውስጥ ነው። ስለሆነም የጨረር ህክምና ለማግኘት ወረፋ በመኖሩ በቀዶ ጥገና ጡቱ ሙሉበሙሉ
እንዲነሳ ይደረጋል። ለደረጃ 3 የጡት ካንሰር ታካሚዎች ከቀዶ ጥገና በፊት የኬሞቴራፒ ህክምና ይሰጣል። ይህም የሚደረገው የካንሰር ህዋሳትን ከሰውነት ውስጥ ለማስወገድ ነው። "አንዳንድ ታካሚዎች እብጠት ከጠፋ የቀዶ ጥገና ህክምና እንደማያስፈልግ ይናገራሉ። ነገር ግን የቀዶ ጥገናው አስፈላጊ ነው። እብጠት መጥፋቱ ወይም ጥሩ ምላሽ ሰውነት መስጠቱ በቀጣይ ላለው ህክምና ጥሩ ምላሽ ይሰጠናል ማለት ነው እንጂ ካንሰሩ ሙሉበሙሉ ጠፍቷል ማለት አይደለም" ብለዋል ዶ/ር ሐናን አለባቸው። ደረጃ 4 ላይ ለሚገኙ የጡት ካንሰር ታካሚዎች የቀዶ ጥገና፣ ኬሞቴራፒ እና የጨረር ህክምና ይሰጣል። በዚህ ደረጃ ላይ ያለ የጡት ካንሰር ከጡት በተጨማሪ በሌሎች የሰውነት ክፍል ላይ ስለሚሰራጭ ካንሰሩን ሙሉበሙሉ ለማስወገድ አይቻልም። ነገር ግን በሚሰጠው ህክምና አማካኝነት የካንሰሩን ጉዳት መቀነስ ይቻላል። ሀሳባቸውን ያጋሩን ወ/ሮ ብርቂቱ ሚደቅሳ "በአንደኛው ጡቴ ላይ እጢ ወቶብኝ ህክምና አድርጌ ነበር። ነገር ግን አሁንም የማበጥ ነገር አለው። ወደ ካንሰር እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለው" ብለዋል። አክለውም በተደጋጋሚ እጢ የሚወጣ ከሆነ የመዳን እድሉ አነስተኛ ይሆናል ብለው እንደሚሰጉ ተናግረዋል። "ሁሉም
እብጠት ካንሰር አይደለም" በማለት ዶ/ር ሐናን አለባቸው ተናግረዋል። በተለይ እድሜያቸው ከ15 እስከ 25 ዓመት የሆኑ ሴቶች ላይ ጉዳት የማያስከትል እጢ መኖሩን ባለሙያዋ አክለዋል። ነገር ግን እንደ ባለሙያዋ ንግግር የእጢውን አይነት በህክምና ባለሙያ ማረጋገጥ ያስፈልጋል። "እድሜዬ ሀያዎቹ ውስጥ ነው። አክስቴ የጡት ካንሰር ተጠቂ ስለነበረች በዘር ይተላለፋል ስለሚባል ከ2 ዓመት በፊት የጡት ካንሰር ምርመራ አድርጌ ነበር። ችግር እንደሌለብኝ ተነግሮኛል" ያለችን ደግሞ ወጣት በእምነት ያሬድ ናት። በእምነት በአሁኑ ወቅት በሁለቱም ጡቶቿ አከባቢ ማሳከክ እና ሽፍታ መፈጠሩ የጡት ካንሰር ምልክት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት እንዲያድርባት አድርጓል። ዶ/ር ሐናን አለባቸው እንደተናገሩት እንደ በእምነት በቤተሰብ ውስጥ የጡት ካንሰር ታካሚዎች(ታሪክ) ያላቸው ሰዎች እድሜያቸው ከ25 ዓመት በላይ ከሆነ በየ1 ዓመት ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራል። የጡት ካንሰር ምልክቶች ሳይኖሩ በጡት ላይ የማሳከክ እናየሽፍታ ምልክቶች መኖር ብቻ የጡት ካንሰር ምልክት አለመሆኑን የህክምና ባለሙያዋ ተናግረዋል። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንዲት ሴት "2ኛ ደረጃ የጡት ካንሰር እንዳለበኝ ተነግሮች ህክምና እየተከታተልኩ ነው። ነገር ግን የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ የምግብ ጣእም የመለየት ችግር እና የማዞር ስሜት ይሰማኛል። በሁለቱ የእጅ ጣት ጥፍሮቼ ላይ የመጥቆር ምልክት አለኝ" ብለዋል። ዶ/ር ሐናን አለባቸው እንደተናገሩት የኬሞቴራፒ ህክምና የሚወስዱ ሰዎች የፀጉር መነቃቀል፣ የጥፍር መጥቆር እና ሌሎችም የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህ ለውጦች ህክምናው ሲያበቃ ይስተካከላሉ። ችግሮቹ ከሚጠበቀው በላይ ከሆኑ ግን የህክምና ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል።
የጡት ካንሰር መከላከያ መንገዶች; ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ፣ እንቅስቃሴ ማድረግ እና ክብደት ከሚፈለገው በላይ አለመጨመር፣ አደንዛዥ እፅ እና አልኮል አለመጠቀም፣ ልጅ መውለድ እና ጡት ማጥባት፣ የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ማድረግ እና እራስን መፈተሽ ናቸው።
 ዶ/ር ሐናን አለባቸው እንደተናገሩት በብዙ ታካሚዎች ዘንድ ወደ ህክምና ተቋም ከመሄድ ይልቅ ወደ የባህል ህክምናዎች እና ወደ የሃይማኖት ቦታዎች የመሄድ ልማድ አለ። ካንሰር ሳይታከም በቆየበት ልክ የመባዛት ባህሪ እንዳለው የህክምና ባለሙያዋ በመጥቀስ የሃይማኖት ተግባራትን ከህክምና ጎንለጎን ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ የትዳር አጋሮች ድጋፍ አለማድረግ (አለመረዳት) ህክምናው ላይ ችግር እንደሚፈጥር ነው ዶ/ር ሐናን አለባቸው የተናገሩት። እንደ ባለሙያዋ ንግግር የትዳር አጋር እና የሌሎች ሰዎች ድጋፍ ለካንሰር ታካሚዎች አስፈላጊ ነው። በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የቀዶ ጥገና ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የጡት፣ የእንቅርት እና ተያያዥ እጢዎች ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሐናን አለባቸው የጡት ካንሰር መታከም ከሚችሉ የካንሰር አይነቶች ውስጥየሚመመደብ መሆኑን ተናግረዋል። አክለውም "ካንሰሩ ደረጃው ከፍ ሳይል ህክምና እንዲያገኝ ወንድም ሆነ ሴት እራስን የመፈተሽ ባህል ማዳበር አለበት። እንዲሁም ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች በየዓመቱ የማሞግራፊ ስክሪን እንዲነሱ" የሚል መልእክት አስተላለፈዋል።



Read 363 times