Saturday, 25 November 2023 20:05

የዓለማችን የሮኬትና የሳተላይቶች ጌታ ምን ይላል?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

በሕዋ ካሉት 10ሺ ገደማ ሳተላይቶች መካከል 5100 ያህሉ የሱ ናቸው
ዓላማው ግን ሌላ ነው። የሰው ዘር እንዳይጠፋ ተጨማሪ ዓለም በማርስ ማቋቋም


የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ፣ ሁለት ትልልቅ ዓለማቀፍ ዜናዎች ተወርተዋል፤ ተከስተዋል። አዲስ የሮኬት ቴክኖሎጂ “ከስኬት” ጋር ፈንድቷል። እስከ ዛሬ ያልታየ ግዙፍ የሮኬት ፈጠራ ነውና በርካታ ሚሊዮን ተመልካቾች በቀጥታ ስርጫት የሮኬት በረራውንና ፍንዳታውን ተከታትለዋል።
ስኬታማው በረራ በፍንዳታ አብቅቷል። ወይም ደግሞ “ቢፈነዳም” በስኬት ተመዝግቧል።
አንድ ሮኬት ቢፈንዳ ወይም  ቢሳካ፣… አዲስ ነገር ነው? በእርግጥ “ተራ ሮኬት” አይደለም። ግዙፍ ነው። ሮኬቱ ወጪ ብቻ ዜና ቢያወሩለት አይበዛበትም። ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጥቶበታል።  እሺ፤ ይሁንለት፣ የአዲሱ ሮኬት ሙከራ የዓለማችን ዜና ነው እንበል።
ነገር ግን የዓለማችን ትልቅ ዜና የሚሆነው በምን ምክንያት ነው?
በምድር ዙሪያ ሕዋውን በሳተላይቶች የመቆጣጠርና የማጥለቅለቅ ጉዳይ ይመስላል- ሩጫው። ሕዋውን የተቆጣጠረ ዓለምን ከላይ ሆኖ ይቆጣጠራል ይላሉ።
የሮኬቱን ባለቤት ብትጠይቁት ግን፣ አዲሱ የሮኬት ቴክሎጂ “ለሰው ልጆች ሁሉ የህልውና ጉዳይ ነው” የሚል መልስ ይሰጣችኋል።
እንዴት በሉ። በሚሊዮን ከሚቆጠሩ የህዋ አለቶች መካከል አንዱ፤ የሆነ ጊዜ ላይ ከምድራችን ጋር መላተሙ አይቀርም ይላል ሰውየው። እንዲህ ዐይነት መዓት በምድራችን ላይ ከደረሰ፣.. አያድርገው እንጂ፣ ሰውን ከምድረ ገፅ የሚያጠፋ “ምፅአት” ይሆናል ባይ ነው ሰውየው”
ከዚያ በፊት የሰው ዘር ወደ ማርስ ወይም ወደሌላ ፕላኔት መስፋፋት አለበት። ይህን አለማ እውን የሚያደርግ ግዙፍ የሮኬት ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል። እናም የሮኬቱ ስኬት ለሰው ልጆች ሁሉ፤ የህልውና ጉዳይ ነው በማለት ያብራራል።
ሰውየውን ዓለም ያውቀዋል። ኤሎን ሞስክ ይባላል።
የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለሀብት ነው።
የሮኬትና የመንኮራኩር ፈጠራ ላይ የተሰማራውም የሰው ዘር እንዳይጠፋ በማሰብ እንደሆነ ይልፃል። እንግዲህ የቅዳሜው አዲስ የቴክኖሎጂ ሙከራ ትልቅ ዜና ነው ቢባል ምን ያንሰዋል? ቢሆንም… ሙከራው ትልቅ  ቢሆን እንኳ የሰውየው ማብራሪያ ያን ያህል አሳማኝ ባይሆንልን አይገርምም።
እሱ ግን በቃሉ እንደፀና ነው።  ያኔ ስራውን ከመጀመሩ በፊትም፣ ከገባበት በኋላም፣ ዛሬም ጭምር፣ ቃሉን አልቀየረም። የሰው ዘር በድንገተኛ አደጋ እንዳይጠፋ ወደ ሁለት ወደ ሦስት ፕላኔቶች መሰራጨት እንዳለበት ያምናል። ሐሳቡንም ይናገራል።
ችግሩ ግን፣ ሐሳቡን የሚሰማና ለተግባር የሚስማማ አላገኘም።
የአሜሪካ፣ የአውሮፓ፣ የጃፓን የህዋ ተቋማትን ሲያያቸው፣ ስራቸውን ዘንግተው የተቀመጡ መስለው ታዩት። የሮኬት ቴክኖሎጂ ለ40 ለ50 ዓመታት ስንዝር አልተነቃነቀም።
መቼስ ምን ይደረግ? የሰው ዘር መጥፋት የለበትም፤ በግል እሰራዋለሁ ብሎ ጀመረው። ቀላል አልሆነለትም።
2008 ላይ ኪሱ ሁሉ ባዶውን ቀርቶ ያጣ ነጣ ድሀ ለመሆን የቀናት ዕድሜ ነበር የቀረው። ደግነቱ ስራው ለከንቱ አልነበረም።
Space X የተሰኘው የኤሎን ሞስክ ኩባንያ ከስሮ ዝርያው አልጠፋም። በትንሽ ሮኬት የተጀመረው የአዲስ ፈጠራ ጉዞ፣ እየተሻሻለና እያደገ፣ ዛሬ የሮኬት ገበያውን የሚቆጣጠር ቀዳሚ ኩባንያ ሆኗል።
እናም፣ በሮኬትና በመንኮራኩር ቴክኖሎጂው ዓለምን እያስከነዳ፣ እየመራ እየመጠቀ የሚገኝ ሰው፣ ሀሳቦቹን ወደ ተግባር እየቀየረ ስኬቱን ያስመሰከረ ሰው የዜናውን ትልቅነት ሲነግረን እንደዘበት አናንቀን ብንተወው ሞኝነት ነው።
ደግሞስ በእስከዛሬ ስኬቱ ዓለምን እየቀየረ እንደሆነ ማን ይክዳል?
በሮኬትና በመንኮራኩር ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በህዋ በረራ ዙሪያ፣ የሰውዬው ኩባንያ የዓለማችን ቀዳሚና ተመራጭ ኩባንያ ሆኗል።
በአለማችን ዙሪያ ከሚሽከረከሩ ወደ አስር ሺ የሚጠጉ ሳተላይቶች መካከል ግማሽ ያህሉ የሰውዬው ናቸው:: ከግማሽ ይበልጣሉ እንጂ።
5100 ገደማ ሳተላይቶችን በምድር ዙሪያ በማሰማራት ዓለማቀፍ የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት መስጠት የቻለ ሰው ነው።
ይህም ብቻ አይደለም።
የሮኬትና የመንኮራኩር ቴክኖሎጂ ላይ አዳዲስ ፈጠራዎችን በተከታታይ እየጨመረ የህዋ ጉዞ ላይ አዳዲስ ታሪኮችን ፈጥሯል። 200 ኩንታል የሚመዝን የሳተላቶች ጭነት ወደ ህዋ ለማምጠቅ ከ300 ሚሊዮን እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቅ ነበር። አንድ ኪሎ ዕቃ ወደ ጠፈር ለማጓጓዝ፣ ከ15ሺ እስከ 25ሺ ዶላር ነበር ሂሳቡ።
ዛሬ፣ ዋጋው ቀንሷል።  ከ5000 ዶላር በታች ሆኗል ሂሳቡ።
ይህን አስገራሚ ለውጥ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከሐሳብ ወደ ተግባር ያደረሰ ነው- ተዓምረኛ ሰው። በቅናሽ ዋጋ አስተማማኝ የሕዋ ጉዞ መስጠት የቻለው በአዳዲስ የሮኬት ቴክኖሎጂዎቹ አማካኝነት ነው። በዚህም ብዙ ደንበኞችን አግኝቷል፣ ገበያው ደርቷል።
ከዚህ ጎን ለጎን፣ የራሱን ሮኬቶች በመጠቀም የራሱን ሳተላይቶች እያመጠቀ፣ ዓለማችንን በሳተላይቶች መረብ አስተሳስሯል።
ድሮ ድሮ፣ በጥቅሉ “አገራት” እና “መንግስታት” ነበሩ ሮኬትና የሳተላይት ጌቶች።
ዛሬ የሁለቱም ጌታ ኤሎን ሞስክ ነው።
ግን አትርሱ።
የሕዋ ጉዞና የሮኬት ቴክኖሎጂ ላይ ስራዬ ብሎ የተሰማራው ለምን እንደሆነ ሰምታችኋል። ለሰው ልጆች ተጨማሪ የኑሮ ዓለም ለመፍጠር ነው ሐሳቡ።
ምድራችንን በሳተላይቶች መረብ ማስተሳሰር፣… ለኤሎን ሞስክ የእግረ መንገድ ስራ ነው። ለዋናው ዓላማ፣ ለትልቁ ሕልም የገቢ ምንጭ ለማግኘት፣ 5ሺ ሳተላይቶችን ማምጠቅ ጠቃሚ ነው ብሏል።
በእርግጥ የሳተላይቶቹ ብዛት ለነቻይና ለነራሺያ ትልቅ የስጋት ራስ ምታት ሆኖባቸዋል። ሕዋውን በሳተላይቶች  መረብ የተቆጣጠረ ዓለምን ይቆጣጠራል ብለው ያስባሉና።
የኤሎን ሞስክ ሕልም ግን ወደ ማርስ ወደ ሌላ ፕላኔት ነው። እስካሁን ብዙ የስኬት ታሪክ ሰርቷል። ነገር ግን ብዙ ስራ ይቀራል።  በአነስተኛ ወጪ፣ በቅናሽ ዋጋ የህዋ በረራ ማካሄድ ብቻ በቂ አይደለም። በአንድ ጊዜ፣ ብዙ ጭነት ማጓጓዝ ብዙ ተሳፋሪዎችን ማመላለስ የሚችል ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል።
ነባሮቹ የሮኬት ቴክኖሎጂዎች፣…. ዋጋቸው በጣም ውድ ነው። የጭነት አቅማቸው አነስተኛ ነው። Space Shuttle የተሰኘው የህዋ ሮኬትና መንኮራኩር፣ በ2011 ከአገልግሎት የወጣው፣ በተደጋጋሚ ለአደጋ በመጋለጡ ብቻ አይደለም። ወጪው ከባድ ነው። በአማካይ ለአንድ በረራ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጥቶበታል ማለት ይቻላል።
133 በረራዎችን አካሂዷል።
ለቴክሎጂው፣ ለግንባታና ለእድሳት የወጣው ወጪ ደግሞ ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው።
ዛሬ ግን ታሪክ እየተለወጠ ነው። ኤሎን ሞስክ ባቋቋመው በግል ኩባንያ አማካኝነት ቴክኖሎጂውና ወጪው በጥቂት ዓመታት ውስጥ ተሻሽሏል።
እንዲያም ሆኖ፣ ዋናዎቹ የሮኬት ቴክሎጂዎች፣…. “ፋልከን 9” እና “ፋልከን ሄቪ” የተሰኙ ፈጠራዎች፣ 200 ኩንታል እና 600 ኩንታል ገደማ ብቻ ነው የጭነት አቅማቸው። ወጪያቸው ከ60 እስከ 120 ሚሊዮን ዶላር ነው።
ለአንድ በረራ ማለት ነው።
ከነባሮቹ ጋር ሲነፃፀሩ፣ ዋጋቸውና አስተማማኝነታቸው አስደናቂ ነው። የሕዋ ጉዞ በየዓመቱ በዕጥፍ እየጨመረ ነው። ዋጋው ደግሞ በዕጥፍ ቀንሷል። ቢሆንም ግን ይህ ብቻ ለማርስ በረራ በቂ አይደለም።
ባለፈው ሳምንት የተሞከረው አዲስ የሮኬትና የመንኮራኩር ቴክኖሎጂ፣ ለማርስ ጉዞ ቁልፍ ቴክኖሎጂ ነው። በግዙፍነቱ፣ ከእስከዛሬዎቹ ሁሉ እጥፍ ድርብ ይበልጣል።
ከ2000 ኩንታል በላይ ጭነትን ወይም ከ100 በላይ ተሳፋሪዎችን የማጓጓዝ አቅም አለው። ከመሬት ሲነሳ፣ ክብደቱ 10 ቦይንግ 787 አውሮፕላኖች ያህል ነው። 50ሺ ኩንታል ከምድር ተነስቶ ሲመጥቅ ማየት ተዓምር ነው።
የኢንጂኖቹ (የሞተሮቹ) ቁጥር ብቻ አጃኢብ ያሰኛል።
ጠቅላላ ቁመቱ፣ 121 ሜትር ነው። ባለስንት ፎቅ ሕንጻ ያክላል? ሠላሳ ፎቅ?
ከላይ መንኮራኩር አለ። የተሳፋሪዎችና የጭነት መያዣ ቦታ እዚሁ ነው- መንኮራኩሩ ውስጥ።ከሱ ስር ደግሞ፣ ግዙፍ ሮኬት ተገጥሞለታል።
የሮኬቱ ቁመት 71 ሜትር ነው። በ9 ሜትር ውፍረት የተገነባው ሮኬት፣ “33 ኢንጂኖች የሚቀለቀሉበት እሳተ ጎመራ” ነው ማለት ይቻላል።
ማነጻጸርያ ያስፈልጋል።ድሪምላይነር የተሰኘው ቦይንግ 787 አውሮፕላን፣ ሁለት ኢንጂኖች አሉት። ከግራና ከቀኝ የተወደሩት ኢንጂኖች፣ በየፊናቸው 75ሺ የፈረስ ጉልበት አላቸው። በድምር 150 ሺ የፈረስ ጉልበት ማለት ነው።
ከመኪና ጋር ልናነጻጽረው እንችላለን። ደህና የቤት መኪኖች፣ ከ75 በላይ የፈረስ ጉልበት ይኖራቸዋል። እነ ቪ8፣ 4 ዊል ድራቭ፣… ከ200 በላይ የፈረስ ጉልበት አላቸው።
እንግዲህ ማነጻጸር ጀምረን የለ! ቦይንግ 787 ላይ የተገጠሙት ሁለት ኢንጂኖች፣ ከአንድ ሺ የቤት መኪኖች ጋር የሚስተካከልና የሚያስከነዳ ጉልበት አላቸው።
ስታርሺፕ ሮኬት ግን 33 ኢንጂኖችን ይዟል። የሮኬቱ ጠቅላላ ጉልበት፣ ከቦይንግ 787 የትና የት!
ከ100 ዕጥፍ ይበልጣል።
ቦይንጉ 150 ሺ የፈረስ ጉልበት አለው።
የሮኬቱ ጉልበት ወደ 16 ሚሊዮን የፈረስ ጉልበት ይጠጋል። 100 ሺ የቤት መኪኖች ቢተጋገዙ እንደማለት ነው።
ያው፣ የጉልበቱ ያህል፣ የሮኬቱ የነዳጅ ፍጆታ አይጣል ነው።
“መፍጀት” የሚለው ቃል ያንሰዋል።
የሮኬቱ ነዳጅ፣ “በስሊንደር” ታሽጎ ከሚመጣው የምድጃ ነዳጅ ጋር ይመሳሰላል። ወደ ፈሳሽነት የተቀየረ ጋዝ ማለት ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን ፈሳሽ ኦክሲጅንም ይጭናል። ሁለቱ ናቸው የሮኬቱ ነዳጆች።
3.4 ሚሊዮን ኪሎግራም ነዳጅ ጭኖ ይነሳል።
በሊትር እናስላው ቢባል ከ4 ሚሊዮን ሊትር ይበልጣል።
ብዙ ነው። ግን “ችግር” የለም። በአንድ ደቂቃ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ሊትሩን ነዳጅ ፉት ይለዋል-እንደ ዘበት።
ለነገሩ፣ የሮኬቱ አገልግሎት ለጥቂት ደቂቃ ብቻ ነው። ለ2 ደቂቃ ከ40 ሴኮንድ ብቻ። በዚሁ ጊዜ ውስጥ ግዙፉ ሮኬት አብዛኛውን ነዳጅ ይጨርሳል።
ስራውንም ያገባድዳል። ይህም በቅዳሜው የበረራ ሙከራ በተግባርና በስኬት ታይቷል። ግዙፉ ሮኬት ከላዩ ላይ ከተገጠመው መንኮራኩር ጋር፣ ከምድር ተነስቶ ወደ 70 ኪሎሜትር ከፍታ ተጠግቷል። 3 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ።
የጉዞ ፍጥነቱም በሰዓት 5000 ኪሎ ሜትር አልፎ ተሻግሯል።
ከባዱ ስራ አልቋል። ሮኬቱ የምድር ስበትን በጥሶ አስቸጋሪዎቹንና ቀውጢዎቹን 160 ሴኮንዶች በእሳት ጉልበት አሸንፏል። ከዚህ በኋላ ያለው የሕዋ ጉዞ፣ የመንኮራኩሩ ስራ ነው። ለብቻው ይወጣዋል።
ግዙፉ ሮኬት ከመንኮራኩሩ ይላቀቃል። ለብቻ ተለይቶ ወደ ምድር ይመለሳል።
መንኮራኩሩ፣ የራሱ 6 ኢንጂኖች አሉት። ይሄኔ ነው የሚለኮሱት።
 በእርግጥ፣ መንኮራኩሩ በሮኬት ጉልበት ከምድር ከራቀ በኋላ ፈተናው ቀላል ነው። ሮኬቱን ከኋላ ጥሎ፣ የሕዋ ጉዞውን ለመቀጠል ለመንኮራኩሩ 6 ሞተር አያስፈልገውም።
ታዲያ ለምን ስድስት ሞተር ተገጠመለት? ጨረቃ ወይም ማርስ ላይ አርፎ እንደገና ተነስቶ ለመምጠቅና ወደ ምድር ለመምጣት፣ ብዙ ጉልበት ያስፈልገዋል።
የቅዳሜው የሙከራ በረራ ግን፣ ወደ ማርስ ወይም ወደ ጨረቃ የታለመ አይደለም። ወደ 200 ኪሎሜትር ከፍታ ከተጠጋ በቂ ነው። ደግሞም ተጠግቷል። 150 ኪሎሜትር ደርሷል። የመንኮረኩሩ ፍጥነትም ወደ ታቀደለት ደረጃ ተቃርቧል -  በሰዓት 24 ሺ ኪሎሜትር ፍጥነት ላይ ደርሷል።   አዎ፣ 24ሺ ኪሎ ሜትር በሰዓት።
ይሄ ሁሉ፣ ትልቅ ስኬት ነው። የሮኬትና የመንኮራኩር ቴክኖሎጂ ላይ፣ አንዲሁም በሕዋ በረራ ላይ አዲስ ታሪክ መዝግቧል።
የሮኬቱና የመንኮራኩሩ የበረራ ሙከራ እጅግ ስኬታማ የሚሆነው ግን፣ በትክክል ወደ ምድር የሚመለሱበትን ጉዞ መቆጣጠር ቢቻል ነበር። ለጊዜው አልተቻለም። እናም፣ እንዲህ ዐይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ተመራጩ መፍትሔ አየር ላይ ከርቀት እንዲፈነዱ ማድረግ ነውና፣ መጨረሻቸው በፍንዳታ የሚጠናቀቅ ሆኗል።

Read 331 times