Saturday, 25 November 2023 20:04

በቡና ፍቅር የወደቀው ራስታ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ብሬዳ ኒል ከኪንግ ሻይሎህ ሳውንድ ሲስተም

ብሬዳ ኒል ይባላል፡፡ በትውልዱ እንግሊዛዊ ቢሆንም ቋሚ መኖርያው ግን በሆላንድ አምስተርዳም ነው፡፡  የሳውንድ ሲስተም ኦፕሬተር፤ የሬጌ ሙዚቃ ባለሙያና ዲጄ ሆኖ በመስራት ከ35 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ከሬድ ላየንና ማጀስቲክ ቢ ጋር በመሆን የኪንግ ሻይሎህ ሳውንድ ሲስተምን King Shiloh Sound system መስርቷል፡፡ ሳውንድ ሲስተሙ በአውሮፓ፤ በሰሜን አሜሪካ፤ በደቡብ አሜሪካና በሌሎች የዓለም ክፍሎች በሚካሄዱ የሙዚቃ ዝግጅቶችና የሬጌ  ፌስቲቫሎች ቋሚ ተሳታፊነት ይታወቃል፡፡ብሬዳ ኒል ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ  የመጣው ለሰባተኛ ጊዜ ነው፡፡ ከታዋቂ የሬጌ ሙዚቀኞች መካከል በተደጋጋሚ በመምጣት የልዩ ክብረወሰን ባለቤት ያደርገዋል፡፡ለሙዚቃ ስራና ለጉብኝት ከሰባት ጊዜ በላይ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ ነው፡፡    ራስተፈርያኖችና የሬጌ ሙዚቀኞች ወደ አፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ ስለመምጣት በብዛት እንደሚዘፍኑ ይታወቃል፡፡ ግን ለብዙዎቹ አይሆንላቸውም፡፡ ታዋቂው የሬጌ  ድምፃዊ ሉችያኖ ወደ ኢትዮጵያ ከ5 ጊዜ በላይ በመምጣት ይታወቅ ነበር፡፡   
ብሬዳ ኒልና የኪንግ ሻይሎህ ሳውንድ ሲስተም ቡድን ዘንድሮ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ትልቅ ራእይ ሰንቀው ነው፡፡  ኢትዮጵያን በሳውንድ ሲስተም ዝግጅቶችና የሬጌ  ፌስቲቫሎች የቱሪዝም መስህብና መናሐርያ በምትሆንበት አቅጣጫ ላይ ለመስራት ነው፡፡ ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ የሬጌ ድምፃውያን፤ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በመተባበር ተከታታይ የሙዚቃ ዝግጅቶችን በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ተዟዙሮ ለማዘጋጀትም አቅደዋል፡፡
የኪንግ ሻይሎህ ሳውንድ ሲስተም ቡድን ከሆላንድ አምስተርዳም በመነሳት ከሳምንት  በፊት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ በመጀመርያ 7ኛውን አዲስ ደብ ክለብ የሬጌ ሙዚቃ ዝግጅት ከታዋቂዎቹ የሬጌ ሙዚቀኞች ራስ ጃኒ ፤ ቴዲ ዳን፤ ከአፍሪካ ወንድምና ሌሎች ሙዚቀኞች ጋር በመሆን አካሂደዋል፡፡ በማግስቱ ደግሞ በ23ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ  ላይ  ሳውንድ ሲስተሙን በመትከል በሙዚቃ ጨዋታቸው አስደናቂ ትኩረት አግኝተዋል፡፡ የሳውንድ ሲስተም ቡድኑ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ የተሳተፈው ለ3ኛ ጊዜ ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ በሚገኝ አደባባይ ላይ ግዙፉ ሳውንድ ሲስተም ተተክሎ በብሬዳ ኒልና ሌሎች አጋሮቹ የቀረበው ጨዋታ የጎዳና ላይ ሩጫው ተሳታፊዎችን በከፍተኛ ደረጃ አዝናንቷል፡፡ የታላቁ ሩጫ ተሳትፎ የሳውንድ ሲስተሙን የጎላ ሚና  ያረጋገጠ ሲሆን ኪንግ ሻይሎህ ሳውንድ ሲስተምን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ማስተዋወቅ የተቻለበት ነው፡፡  በተለይ ብሬዳ ኒል የኢትዮጵያ ቡና የስፖርት ክለብ ማልያ ለብሶ  ሙዚቃዎቹን ማጫወቱ በርካቶችን ያስደሰተ ነበር፡፡ በጎዳና ላይ ሩጫው የተሳተፉ የቡና ደጋፊዎች፤ የእግር ኳስ አድናቂዎች፤ የሬጌ አፍቃሪዎች በሳውንድ ሲስተሙ ዙርያ በነበረው ማራኪ ድባብ እጅግ ተደስተዋል፡፡ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስለነበራቸው  ለስፖርት አድማስ አስተያየት ሲሰጥ ‹‹ በሳውንድ ሲስተም ቡድናችን እኔን ጨምሮ ሁለትና ሶስት አባላት በአትሌቲክስ ውስጥ ያለፉ ናቸው፡፡ በታዳጊነት እድሜዬ  እግር ኳስና ውሃ ዋና ባዘወትርም ፕሮፌሽናል  አትሌት ለመሆን ነበር የሞከርኩት ፡፡ በረጅም ርቀት አትሌቲክስ  ወጣትነቴን ካሳለፍኩ በኋላ ነው ስፖርቱን በመተው ወደ ሙዚቃ የገባሁት፡፡ አትሌት ሆኜ  በማሳለፌ እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡ ፅናትን ተምሬበታለሁ፡፡ ዛሬ በሳውንድ ሲስተም ባለሙያነት ለምሰራቸው ተግባራት ሙሉ የአካል ብቃት ያዳበረኩበት ነው፡፡  አንዳንድ ግዜ በምናዘጋጀው የሳውንድ ሲስተም ሙዚቃ 6፤ 8  እና  10 ሰዓታትን ተወጥረን የምንሰራበት ሁኔታ አለ፡፡ በአጠቃላይ ሳውንድሲስተምን እንደ ማራቶን ውድድር መመልከት ይቻላል፡፡ አትሌቲክስ የአዕምሮና የአካልን ዲስፒሊን የሚጠይቅ ነው፡፡ ሳውንድ ሲስተምም እንደዚያው ነው፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ በነበረን ተሳትፎ በአትሌቲክስ እና በሳውንድ ሲስተም መካከል ያለውን መተሳሰርና መመሳሰል ያስተዋልኩበት ነው፡፡›› በማለት ተናግሯል፡፡ በ23ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ የኪንግ ሻይሎህ ሳውንድ ሲስተም መስራት ከፍተኛ ድምቀት መፍጠሩን በስፍራው ተገኝተን ለመታዘብ ችለናል፡፡ ከሳውንድ ሲስተሙ ጋር የነበሩ ባለሙያዎች የጎዳና ላይ ሩጫውን ተሳታፊዎች በሬጌ ሙዚቃ ከማነቃቃታቸውም በላይ ከሩጫው ባሻገር በዳንስ የሚፈለገውን እንቅስቃሴ እንዲሰሩ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡
ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በኋላ ብሬዳ ኒልና የኪንግ ሻይሎህ ሳውንድ ሲስተም አባላት ለመገናኘት የበቁት ከኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ጋር ነው፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ  በአበበ ቢቂላ ስታድዬም የተካሄደው የአዲስ አበባ ሲ ካፕ የዋንጫ ጨዋታ ምክንያት ሆኗል፡፡ ብሬዳ ኒል በታላቁ  ሩጫ ላይ የቡናን ማልያ ለብሶ ሙዚቃ ማጫወቱ ብዙዎቹ የክለቡ ደጋፊዎች በማህበራዊ ሚዲያው በተለይ በቲክ ቶክ በአድናቆት ተከታትለውታል፡፡ ስለዚህም ከሲቲ ካፑ የፍፃሜ ጨዋታ በፊት ማለዳ ላይ ከቀንደኛ የቡና ደጋፊዎች ጋር የኪንግ ሻይሎህ ሳውንድ ሲስተም ቡድን አባላት ተገናኝተዋል፡፡ ብሬዳ ኒልን ያረፈበት ሆቴል ድረስ መጥተው አድናቆት የገለፁለትና በክለቡ ደጋፊነት እንዲመዘገብ የጠየቁት አንጋፋው የክለቡ ደጋፊ አዳነ ሽጉጤ እና  ከወቅቱ የክለቡ ደጋፊዎች አስተባባሪ ሆነው  አብርሐም ናቸው፡፡
ብሬዳ ኒል  በወጣትነት ዘመኑ በአትሌቲክስ ፕሮፌሽናል ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በክለብ ደረጃ ለረጅም ጊዜያት የተወዳደረ ሲሆን እንግሊዝን በኦሎምፒክና በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን የመወከል ፍላጎት የነበረው ቢሆንም ሩጫውን ብዙም አልገፋበትም፡፡ ከአትሌቲክሱ ባሻገር ለእግር ኳስም ልዩ ፍቅር ነበረው፡፡ በተለይ በታዋቂው የእንግሊዝ ክለብ ሊድ ዩናይትድ ደጋፊነቱ ይታወቅ ነበር፡፡ የሳውንድ ሲስተም ባለሙያ ሆኖ ለመስራት ወደ ሆላንድ አምስተርዳም ገብቶ ከከተመ በኋላ ደግሞ ለአያክስ ክለብ ድጋፉን በመስጠት እግር ኳስን ሲከታተል ቆይቷል፡፡‹‹ ከስፖርት ጋር የተዋወቅኩት ገና በታዳጊነቴ ነው፡፡ ያደግኩት ከእግር ኳስ ጋር ነው፡፡ አባቴ ስፖርት በጣም ይወዳል፡፡ ስለዚህም በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ወደ ስታድየም ተያይዘን እንሄዳለን፡፡ የምደግፈው ክለብ ሊድ ዩናይትድን ነው፡፡ በተጨማሪም የበርንሌይና የሌችስተር ሲቲ ክለቦች የሚያደርጓቸውን  ጨዋታዎች በየስታድየማቸው እየተገኘን እንመለከታለን፡፡ እድገቴ በሙሉ ከስታድዬም ጋር የተገናኘ ነው፡፡ የስፖርቱ ባህልና ስሜቱ ዛሬም ውስጤ    አለ፡፡›› ሲል ይናገራል፡፡
ከሰባት ዓመት በፊት ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ፤ በሬጌ ሙዚቃ ውስጥ የተስፋፋውን የሳውንድ ሲስተም ባህል ለማስተዋወቅ ነበር፡፡ ከዚህ ስራው ባሻገር ለስፖርቱ ባለው ፍቅር ስለ አገሪቱ የእግር ኳስ ክለቦች መጠየቅ ነበረበት፡፡ አብረውት ከሚሰሩ ባለሙያዎች መካከል ሽሜ የሚባለው በተለይ ስለ ኢትዮጵያ ቡና ክለብ አብራራለት፡፡ የህዝብ ክለብ መሆኑና ደጋፊዎቹ በዝማሬያቸው፤ በቀለማቸውና በስታድዬም ውስጥ በሚፈጥሩት ድምቀት የሚስተካከላቸው አለመኖሩን  በደንብ ገለፀለት፡፡ ብሬዳ ኒል ስለ ቡና ክለብ የመጀመርያውን ማብራርያ ከሰማ በኋላ ስታድዬም ገብቶ የክለቡን ጨዋታ መመልከት የፈለገው፡፡ ከኢትዮጵያዊው ሽሜ  የቡናን ጨዋታ ስታድዬም ገብተው ለመመልከት በቁ፡፡ ከዚያ በኋላ ብሬዳ ኒል ከኪንግ ሻይሎህ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊ ሆኖ ቀረ፡፡ወደ ኢትዮጵያ ቡና የስፖርት ክለብ ስለተሳበበት አጋጣሚ ሲገልፅ  ‹‹እግር ኳስ ያደግኩበት ስፖርት ብቻ አይደለም ፤ በተለያየ የዓለም ክፍል እየተዘዋወርኩ ባህሉን የተማርኩት ነው፡፡  ወደ አዲስ አበባ ስመጣ የአፍሪካን እግር ኳስ  የማወቅና የመረዳተ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ከመላው ዓለም ጋር ለማነፃፀር ነው፡፡ ሽሜ የተባለው ወዳጄ ይህን ፍላጎት ተረድቶ እሽ እንሂድ አለኝ፡፡ የተ ስለው እኔ የምደግፈው ቡድን ቡና ነው በማለት እንባ እየተናነቀው ስለክለቡ ብዙ ነገረኝ፡፡  የቡና ደጋፊዎች መደበኛ የከተማ ነዋሪዎች መሆናቸውን፤ ደሃው የህብረተሰብ ክፍል ለክለቡ ቅርብ መሆኑን፤ ጠንካራ ሰራተኞችና በላባቸው ለፍተው የሚያድሩ ህዝቦች ክለብ መሆኑን በተለያየ መንገድ አስረዳኝ፡፡ በመጨረሻም ስታድየም ገብተን የቡናን ጨዋታ እንድንመለከት ሃሳብ አቀረብኩለት፡፡ ተያይዘን ወደ ስታድዬም ጉዞ ቀጠልን መንገድ ላይ የቡና ደጋፊዎች የክለባቸውን ማልያ ለብሰው በህብረ ዝማሬ ታጅበው ወደ ስታድዬም ሲጓዙ ተመለከትኩ፡፡ ስታድዬም ስገባ የደጋፊዎቹ ማራኪ ዝማሬዎችና እንቅስቃሴዎችን በአይኔ በብረቱ ስመለከት በቡና ክለብ በእጅጉ ተማረኩኝ፡፡ ደጋፊዎቹ ክለባቸውን የሚያበረታቱበት የጠለቀ ስሜት የሚገርም ነው፡፡ እግር ኳስ የህይወት ነፀብራቅ መሆኑን የምትመለከትበት ድንቅ ክለብ ነው፡፡›› በማለት  ለስፖርት አድማስ  አብራርቷል፡፡
ብሬዳ ኒል ለኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ያለው ፍቅር እየጨመረ የሄደው የክለቡን ማሊያዎች በቡኒና ቢጫ ቀለማት ከገዛ በኋላ ነበር፡፡ በአውሮፓ፤ በሰሜን አሜሪካ፤ በኤሽያና በአፍሪካ በሚሰራቸው ትልልቅ ኮንሰርቶች ላይ ለብሶት ታይቷል፡፡ የሳውንድ ሲስተም ጨዋታውን ሲያቀርብ ከሚለይባቸው አለባበሶች  xንዱ ሆኖለታል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በዓለም ዙርያ ባቀረባቸው ኮንሰርቶች የቡናን ማልያ በመልበስ በከፍተኛ ደረጃ ክለቡን ሊያስተዋውቀው በቅቷል፡፡ በተለይ ከ2019 እኤአ ወዲህ በመላው ዓለም በሰራቸው ኮንሰርቶች ነው፡፡ በቡና ማሊያ ዝግጅቶቹን ማቅረቡን የተመለከቱ የሳውንድ ሲስተም ቡድኑ አባላት ማልያውን በመልበስ ስሜቱን መጋራታቸው ክለቡን በመደገፍ እንዲቀጥል መነቃቃት ስለፈጠሩለት እጅግ አስደስቶታል፡፡ በፈረንሳይ ፓሪስ በሚካሄደውና በቀን ውስጥ ከ45ሺ በላይ ተሳታፊ በሚያገኘው ደብ ካምፕ  የሳውንድ ሲስተም ፌስቲቫል ላይ የቡናን ማልያ ለብሶ ነበር፡፡ በሳምንት ውስጥ ከ250ሺ በላይ ጎብኝዎችና ታዳሚዎችን በሚያሳትፈው የስፔኑ ሮተተቶም ሰንስፕላሽ የሬጌ ፌስቲቫል ላይም የቡና ማሊያውን ለብሶ ለመጫወት በቅቷል፡፡ ዘንድሮ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በሰሜን አሜሪካ በነበረው ቆይታም ጋር በተያያዘ የቡናን ማሊያ ታጥቆ ነበር፡፡ በሜክሲኮ ከተማ በሚካሄድ የሬጌ ፌስቲቫል ላይ የሰራው የሚወደውን ክለብ ቡኒ ማልያ በመልበስ ሲሆን ከወር በፊት ሎስአንጀለስ ውስጥ በግዙፍ ክለብ ባቀረበው ዝግጅትም የሰራው በተመሳሳይ አለባበስ ነበር፡፡ በሎስ አንጀለስ ዝግጅት ላይ ሁለት ኢትዮጲያውያን ታዳሚ እንደነበሩ ለስፖርት አድማስ ያስታወሰው ብሬዳ ኒል የቡና ክለብ ደጋፊዎች እንደሆኑና የክለባቸውን ማልያ ለብሶ መጫወቱ እንዳኮራቸው ገልፀውልኛል ብሏል፡፡
ብሬዳ ኒል በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በአበበ ቢቂላ ስታድዬም የተካሄደውን የቡና እና የሃድያ ሆሳዕና የሲቲ ካፕ ጨዋታ ከመመልከቱ በፊት  ከአንጋፋው የቡና ክለብ ደጋፊ አዳነ ሽጉጤ እና ከደጋፊዎች አስተባባሪው አብርሃም ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡ የቡና ደጋፊዎች አውሮፓዊው ክለባቸውን በዓለም ዙርያ ስላስተዋወቀላቸው አመስግነውታል፡፡ እሱም ለክለቡ ያለው ፍቅር የገለፀላቸው ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ በመጣ ቁጥር የሚያስደስተው የቡናን ጨዋታ ስታድዬም ገብቶ መመልከት መሆኑንም ነግሯቸዋል፡፡ ከዚህ ቆይታው በኋላ ብሬዳ ኒል አራት ኪሎ አምባሳደር የሚገኘውን የክለቡን የስፖርት ትጥቆች መሸጫ መደብር ጎብኝቶም ነበር፡፡ በስፖርት ትጥቅ መሸጫው መደብር የክለቡን የተለያዩ የስፖርት ትጥቆችና ምርቶች በመጎብኘት ከመደሰቱም በላይ ከሳውንድ ሲስተም አጋር ባለሙያዎች ጋር በርካታ የማስታወሻ ማልያዎች፤ የስፖርት ትጥቆችና ቁሶችን ለመሸመት በቅተዋል፡፡
 ብሬዳ ኒል፤ ማጀስቲክ ቢ እና  አይታል ዩዝ ከኪንግ ሻይሎህ ሳውንድ ሲስተም ዛሬ ቅዳሜ ላይ የመጀመርያውን አርባምንጭ ሬጌ ፌስቲቫል ያቀርባሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣ ብሎ  በተዘጋጀ ፌስቲቫል ላይ ዲጄ ሀርቲካል ከኬንያ፤ ራስ ጃኒ፤ ቴዲ ዳንና ራስ ኪውንተሰብ ከኢትዮጵያ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡
የኪንግ ሻይሎህ ሳውንድ ሲስተም አባላት ወደ አውሮፓ ሲመለሱ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ኦፊሴላዊ ደጋፊ የሚሆኑበትን እቅድ ይዘው ነው፡፡ የሳውንድ ሲስተሙን ሌሎች አባላት ወደ ክለቡ ድጋፍ ለማምጣት ቃል ገብተዋል፡፡ በቀጣይ በመላው ዓለም በሚያቀርቧቸው የሙዚቃ ዝግጅቶች የክለባቸውን ማልያዎችን እየለበሱ ማስተዋወቅ እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል፡፡ ብሬዳ ኒል ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው ወደፊት ከቡና ክለብ አስተዳደር እና ከደጋፊዎች ጋር በመተባበር የሳውንድ ሲስተም ዝግጅቱን ክለቡን በሚጠቅም ፕሮጀክት ለማቅረብ ይፈልጋል፡፡ በተለይ  ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ ስታድዬም የሳውንድ ሲስተም  ጨዋታውን ለማቅረብ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው የገለፀ ሲሆን የቡና ክለብ ስታድዬም ለመገንባት በሚያደርጋቸወ እንቅቃሴዎች የበኩሉን ድጋፍ ለመስጠት፤ ክለቡን ለማጠናከር በሚዘጋጀው የጎዳና ላይ ሩጫ ልዩ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚፈልግም ተናግሯል፡፡

Read 691 times