Thursday, 23 November 2023 21:27

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግና አጓጊነቱ

Written by  -ዞራን ዓባይ-
Rate this item
(14 votes)

ፕሪሚየር ሊጉ በሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ቅዳሜ 9:30 ላይ ማንችስተር ሲቲን ከሊቨርፑል ያገናኛል። በወቅቱ እግር ኳስ ውስጥ በታክቲክ አረዳዳቸውና አተገባበራቸው አንቱታን ባተረፉት አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዎላ እና አሰልጣኝ ጀርገን ክሎፕ መሀል የሚደረገው የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ገና ከወዲሁ አጓጊ የሆነ ሲሆን ጨዋታውም በአሰልጣኞቹ በሚተገበረው የረቀቀ ታክቲክ እና ከፍ ባለው የተጫዋቾች ብቃት ደምቆ እንደሚያልፍ ይጠበቃል።


ጋርዲዎላ እና ክሎፕ እርስበእርሳቸው ከየትኛውም አሰልጣኝ ጋር ከተገናኙበት በበለጠ ሁኔታ 28 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን፤ ክሎፕ 11 ጊዜ በማሸነፍ ብልጫ ሲኖረው፣ ጋርዲዎላ ደግሞ 10 ጊዜ መርታት ችሏል። ይህ የሚያሳየው በመሀላቸው ያለውን አስደናቂ ፉክክር ሲሆን ጨዋታውም ለመገመት ምን ያክል አስቸጋሪ እንደሚሆን ይነግረናል።


ኳስን በመቆጣጠር እና ተጋጣሚ ላይ ብልጫ ወስዶ ጫና ውስጥ በማስገባት ጨዋታዎችን በማሸነፍ የሚታወቁት ሲቲዎች፤ በቅዳሜው ጨዋታ በጣም ፈጣን እና ለመቋቋም አስቸጋሪ በሆነው በክሎፕ ልጆች ፕሬሲንግ እና መልሶ ማጥቃት እንደሚቸገሩ ይጠበቃል። በዚህም አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዎላ የሊቨርፑልን ፈጣን የፊት መስመር ለመቆጣጠር የሚመርጡት አሰላለፍ እና ታክቲክ ገና ካሁኑ አነጋጋሪ የሆነ ሲሆን፣ በተቃራኒው ደግሞ አሰልጣኝ ክሎፕ ኳስ በመመስረት፣ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶችን በማሸነፍ እና ከበረኛ እስከ አጥቂ ድረስ ከፍ ባለ ግላዊ ብቃት የታጨቀውን የጋርዲዎላን ሰራዊት በምን ዓይነት መንገድ ጫና ውስጥ እንደሚከቱ የሚጠበቅ ነው።


የወቅቱ የፕሪሚየርሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ኤርሊንግ ሀላንድ እስካሁን በሊጉ ባደረጋቸው 47 ጨዋታዎች 49 ግቦችን ለማንችስተር ሲቲ ያስቆጠረ ሲሆን፣ በቅዳሜው ጨዋታ ሊቨርፑል ላይ ጎል የሚያስቆጥር ከሆነ በፕሪሚየር ሊጉ ትንሽ ጨዋታ አድርጎ 50 ጎል ያስቆጠረ ተጫዋች የሚለውን ሪከርድ በእጁ ያስገባል። ኤርሊንግ ሀላንድ በፕሪሚየር ሊጉ በተቃራኒ ተጫዋቾች ጎል ያላስቆጠረባቸው ክለቦች ሁለት ሲሆኑ ሊቨርፑል ደግሞ አንደኛው ነው (ብሬትንፎርድ ደግሞ ሌላኛው ነው)።


በጨዋታው የፔፕ ጋርዲዎላው ሲቲ በጉዳት ምክንያት የብዙ ተጫዋቾችን ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን ይኼም ለሊቨርፑል እንደመልካም አጋጣሚ እና ዕድል ሆኖ ተወስዷል። ሲቲ ከተረጋገጠው ዴብሩይን፣ ጆን ስቶንስ፣ ማቲዮ ኮቫቺች እና ሰርጂዮ ጎሜዝ ሌላ የግብ ጠባቂውን ኤደርሰን፣ የናታን አኬን እና የማቲያስ ኑኔዝን ግልጋሎት እንደማያገኙ ይጠበቃል። በተጨማሪም፣ ኤርሊንግ ሀላንድ ሀገሩን ሲያገለግል ቀላል ጉዳት ያስተናገደ ሲሆን ለጨዋታው ግን ብቁ እንደሚሆን ይጠበቃል።


በሊቨርፑል በኩል ሪያን፣ ኩርትስ ጆንስ፣ ኮናቴ እና ጆ ጎሜዝ ለቅዳሜው ጨዋታ ከጉዳት አገግመው ይደርሳሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይኼም ለሊቨርፑል ተጨማሪ የተጫዋች አማራጭ እና ጥሩ ዕድል እንደሆን ይጠበቃል። ሮበርትሰን በረጅም ጊዜ ጉዳት ለቅዳሜው ጨዋታ አለመገኘቱን ተከትሎ አሰልጣኝ ክሎፕ ጎሜዝን በግራ ተመላላሽ በኩል ይጠቀማሉ የተባለ ሲሆን፣ ሲሚካስ ደግሞ ጨዋታውን በተቀያሪነት ሊጀምር እንደሚችል ይጠበቃል።


ሲቲዝኖች በጨዋታው በ4-1-4-1 አስተላለፍ ይዘው ይገባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ኦርቴጋ፣ ዎከር፣ አካንጂ፣ ዲያዝ፣ ግቫርዲኦል፣ ሮድሪ፣ ፎደን፣ በርናንዶ፣ ግሪሊሽ፣ ዶኩ እና ሀላንድ ቋሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። በአንጻሩ ሊቨርፑሎች 4-3-3 አስተላለፍን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ የተገመተ ሲሆን፤ አሊሰን፣ አርኖልድ፣ ኮናቴ፣ ቫንዳይክ፣ ጎሜዝ፣ ማክአሊስተር፣ ሪያን፣ ሶቦዝላይ፣ ሳላህ፣ ጋክፖ እና ዲያዝ ደግሞ በቋሚነት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።


ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ ብዙ አቋማሪ ድርጅቶች የቅድመ ማሸነፍ ግምታቸውን ለሲቲ የሰጡ ሲሆን የሁልጊዜ የሲቲ ፈተና የሆነው ሊቨርፑል ግን ለሲቲ ከባድ ፈተና እንደሚሆን አልካዱም። በጨዋታው ሲቲዝኖች በጉዳት ምክንያት የብዙ ወሳኝ ተጫዋቾቹን ግልጋሎት ማግኘት ባይችሉም የሲቲ ደጋፊዎች ግን አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዎላ እስካለ ድረስ ምንም ማድረግ እንደሚችሉ ያምናሉ።


ከአሰልጣኞቹ የታክቲክ ጦርነት በመቀጠል ጨዋታውን ያደምቀዋል ተብሎ የሚጠበቀው የተጫዋቾች አንድ ለአንድ ግብግብ ሲሆን ሀላንድ ከቫንዳይክ፣ ዶኩ ከአርኖልድ፣ ኑኔዝ ከዲያዝ እንዲሁም ሞህ ሳላ ከግቫርዲዮል የሚያደርጉት ትንቅንቅ ከወዲሁ የብዙውን ልብ አሸፍቷል።


ማንችስተር ሲቲ በዘንድሮ ዓመት ሻምፒዮን በመሆን በተከታታይ አራት ጊዜ ፕሪሚየር ሊጉን ያሸነፉ  ብቸኛ ክለብ ለመሆን እና አዲስ ታሪክ ለመፃፍ ጉዞ እያደረጉ ሲሆን፣ በዚህ ጉዞዋቸው ውስጥ እንቅፋት ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ ቡድኖች መሀል ዋነኞቹ ሊቨርፑሎች ናቸው።


ፕሪሚየር ሊጉን በአንድ ነጥብ የበላይነት ብቻ እየመሩ የሚገኙት ሲቲዎች፤ ይኼን ጨዋታ የሚያሸንፉ ከሆነ ከወቅቱ አስፈሪ ተቀናቃኛቸው ከሊቨርፑል ራሳቸውን በአራት ነጥብ ከፍ አድርገው የሚያስቀምጡ ሲሆን፣ በአንጻሩ ሊቨርፑል ጨዋታውን የሚያሸንፍ ከሆነ ከ2015 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቲን በኢትሀድ በፕሪሚየር ሊጉ ያሸነፉበት አጋጣሚ ሆኖ የሚመዘገብ ይሆናል፤ በተጨማሪም ሊጉን የመምራት ዕድል ያገኛሉ።


ዘንድሮ ለታማኝ ደጋፊዎቻቸው ትልቅ ነገር ለመስጠት ቆርጠው የተነሱት ሊቨርፑሎች፤ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ያሳዩት አስደናቂ አጀማመር በቅዳሜው ጨዋታ ጥሩ ሞራል እንደሚሆናቸው የተነገረ ሲሆን፣ የተጫዋቾቻቸው ከጉዳት መመለስ እና የሲቲ ተጫዋቾች ጉዳት ደግሞ ትልቅ የማሸነፍ ዕድል እንደሚሰጣቸው ይታመናል።


በመጨረሻ ግንኙነታቸው ሲቲ ሊቨርፑልን 4 ለ 1 ያሸነፈ ሲሆን ሀላንድ ጨዋታው በጉዳት አምልጦት ነበር። ካለፉት 5 ጨዋታዎች ውስጥ ሲቲ አራቱን አሸንፎ አንዱን ከቸልሲ ጋር አቻ የተለያየ ሲሆን ሊቨርፑል ደግሞ ካለፉት 5 ጨዋታዎች  ሦስቱን አሸንፎ አንዱን ተሸንፎ አንዱን ደግሞ አቻ መለያየት ችሏል።


ጨዋታውን በዳኝነት ክሪስ ካቫናህ ይመሩታል። የጨዋታው ግምት ማን.ሲቲ 2 - 2 ሊቨርፑል።

Read 649 times