Sunday, 12 November 2023 20:04

የስፒከር ጥቅሞችና ቅሪት አፅሞች

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 • ኢትዮጵያ ውስጥ “አሮጌ የድምጽ ማጉያ” ልዩ አገልግሎት ተፈጥሮለታል፡፡ በየመንገዱ ቁርጥራጭ ብረታብረት ለመልቀም ይውላል።
   • ቶማስ ኤዲሰን፣ የድምጽ መቅረጫና ማጫወቻ ቴክኖሎጂ የፈጠረ ጊዜ፣ ለአይነ ስውራን ያገለግላል የሚል ተስፋ ነበረው። ሰዎች ቴክኖሎጂውን     የሙዚቃ ማዳመጫ ብቻ ሲያደርጉት ደንግጧል።
   • ግርሃም ቤል፣ የስልክ ቴክኖሎጂን የፈጠረው፣ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ስልጠና ለመስጠት የሚያግዝ የሚያግዝ መስሎት ነበር፡፡ እንዳሰበው   አልሆነም።
   • ለጌም መጫወቻ ይጠቅማል ተብሎ የተፈጠረና የተመረተ የኮምፒዩተር እቃ፣ ዛሬ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ዋና አንጎል ሆኗል። አምራቹ     ኩባንያም የትሪሊዮን ዶላር ኩባንያ ሆኗ ል - ከስድስት ዓመት በፊት የ10 ቢሊ ዮን ዶላር ኩባንያ እንዳልነበረ።
               

         ግርሃም ቤል… የስልክ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ለእይታ ያቀረበው… የዛሬ 135 ዓመት ገደማ አይደል? አጃኢብ ተባለ፡፡ የሰው ድምጽ ከሩቅ ቦታ፣ በቀጭን ሽቦ ውስጥ ገስግሶ በቅጽበት ረዥም መንገድ ተጉዞ እናንተው ዘንድ ይደርሳል፡፡ ተአምር ነው?  
የሰው ቋንቋ እዚህ ሰምታ፣ ከሩቅ ላለ ሰው መልእክቱን የምታወራ እቃ ናት የግርሃም ቤል ፈጠራ፡፡ እንደ ጆሮ የሰውን ቋንቋ ትሰማለች፤ እንደ ልሳን ትናገራለች፡፡
ዓለማቀፍ የቴክኖሎጂ ባዛር ላይ፣ ተአምረኛውን ፈጠራ የተመለከቱና ሞክረው ያዩ ሰዎች፣ ለማመን እየተቸገሩ እንደ ጉድ ሲያደንቁ፣ ግርሃም ቤል በቦታው አልነበረም፡፡ ከዘወትር ስራው መቅረት አይችልም፡፡ በጆሮ ህመም የተጎዱና መስማት የተሳናቸው ልጆችን ያሰለጥናል፡፡
 ነበር ግርሃም ቤል፡፡ የከንፈርና የአገጭ እንቅስቃሴዎችን በማየት የሰዎችን ንግግር መረዳት ይቻላል የሚል እምነት ነበረው ግርሃም ቤል፡፡ በዚህ ዙሪያ ሲመራመርም ነው ወደ ስልክ ቴክኖሎጂ ጎራ ያለው፡፡ መስማት ለተሳቸው ሰዎች አንዳች ጠቃሚ ዘዴ ለመፍጠር ነበር አላማው፡፡ ቴክኖሎጂው ግን እንዳሰበው አልሆነም፡፡ ደግነቱ፣ ከገመተው በላይ ነው የቴክኖሎጂው ፋይዳ፡፡


ብዙም ሳይቆይ በአንድ ዓመት ልዩነት ደግሞ ቶማስ ኤዲሰን የድምፅ መቅረጫ ቴክኖሎጂ ይዞ መጣ።
ቶማስ ኤዲሰን፣ የብዙ ፈጠራዎች ባለቤት ነው፡፡ ዓለምን ሁሉ ከጓዳ እስከ አደባባይ በብርሃናት አድምቋል፡፡ አምፖል ፈጥሯልና፡፡ የድምፅ መቅረጫ መሳሪያው ደግሞ፣ ለአይነ ስውራን ጥሩ አገልግሎት እንደሚሰጥ ገምቶ ነበር ቶማስ ኤዲሰን። ማየትና ማንበብ የማይችሉ ሰዎች፣ በድምጽ የተቀረፀ መጽሐፍ ማዳመጥ ይችላሉ ማለት ነው።  ግን እንደገመተው አልሆነም፡፡
አብዛኞቹ ሰዎች ቴክኖሎጂውን ለሙዚቃ ብቻ ነው የሚጠቀሙበት ብሏል ኤዲሰን - በመገረምና በትዝብት ስሜት፡፡ ቴክኖሎጂውን ያባከኑበት ነበር የመሰለው፡፡


የቤል እና የኤዲሰን የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና መነሻ ዓማዎች ቢለያዩም፣… ተቀራራቢና ተወራራሽ መሆናቸው አልቀረም፡፡ እንደዋና ዋናዎቹ የኤሌክትሪክ ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በሂደት አንዱ ፈጠራ ለሌላኛው የማሻሻያ መንገድ እየከፈተ ዛሬ በዓለም ዙሪያ በየቤቱ ተዳርሰዋል፡፡ ተመሳይነትን እንዴት እንደወረሱ እንይ፡፡
የጆሮ ማዳመጫ ወይም ትልቅ የድምፅ ማጉያ ውስጡ ተከፍቶ አይታችሁ ይሆናል። በመጠን ቢለያዩም በሁለት ነገሮች ይመሳሰላሉ።
“ቫርኒሽ” የተቀባለ ሽቦ ታያላችሁ፡፡ በስልት የተጠቀለለ ነው ሽቦው።
ሁለተኛ ነገር፣… ማግኔት ታገኛላችሁ።


ድምፅ ማጉያና ድምፅ መቅረጫ፣ ከኤሌክትሪክ ሞተርና ከጀኔሬተር… ጋርም ይመሳሰላሉ፡፡ በነዳጅ የሚሰሩ ትንንሽ ጀኔሬተሮች ወይም በህዳሴ ግድብ ላይ የተገጠሙ የኤልክትሪክ ማመንጫ ቴክኖሎጂዎች፣… የማግኔት ኃይል ይኖራቸዋል፡፡ የሽቦ ጉንጉን ይኖራቸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ፣ እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ ቅያሶችና ጉራንጉሮች ላይ ቁርጥራጭ ብረታብረት… ሚስማርና ቆርኪ እየለቀሙ ለመሸጥ የተሰማሩ ልጆችን ተመልከቱ፡፡ አሮጌ የድምፅ ማጉያ (ቅሪተ ዐጽም) በገመድ አንጠልጥለው መሬት ለመሬት ሲያስሱ አልታዘባችሁም? የተጠመደ ፈንጂ፣ ያልፈንዳ ቦምብ አስሰው ለማክሸፍ የተሰማሩ ይመስላሉ።
ግን፣ ቅንጥብጣቢ ብረታ ብረት በማግኔት ለመልቀም ነው የሚንከራተቱት። የድምፅ ማጉያ ውስጥ ማግኔት አለ፡፡ የቴክኖሎጂው ፈጣሪዎች በጭራሽ በሀሳባቸውና በግምታቸው ባያስገቡትም፣ የድምፅ ማጉያ ቴክኖሎጂ ለብረት ለቀማ እየዋለ ነው፡፡
በአንድ በኩል አያስገርምም።


ያለ ብረታ ብረት በየትኛውም አገር ውስጥ የኢኮኖሚ እድገት አይኖርም፡፡ ኑሮ አይሻሻልም። ብረታ ብረት  የማይነካው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የለም፡፡ ከማረሻ እስከ ትራክተር፣ ከኢንዱስትሪ እስከ ትራንስፖርት፣ ከቆርቆሮ እና ከድስት እስከ ግድብ፣… የትኛውም ስራ፣ ያለ ብረት ስንዝር አይነቃነቅም፡፡ ባለበት ጸንቶ መቆየትም እንኳ አይችልም፡፡
አይቀሬ ነገሮች ይቅሩብን የሚያስብል አባዜ ምንድነው?
ኑሮን ማሻሻል ለሚፈልግና እንደ ኢትዮጵያ 120 ሚሊዮን ህዝብ ለያዘ አገር የግድ አስፈላጊና አይቀሬ ነገሮች አሉ፡፡
ብረታ ብረትና ሲሚንቶ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና ትራንስፖርት፣ በቅርቡ ትልቅ መነጋገሪያ ርዕስ የሆነው የባህር በር፣…
እውቀትን የሚያስጨብጥ ትምህርት፣ ከጨዋነት በተጨማሪ የሥነ ምግባር መርህ፣
 ከተረጋጋ ፖለቲካና ከአስተማማኝ ሰላም ባሻገር የእያንዳንዱን ሰው መብት ለማስከበር ያለመ ህግና ስርዓት…
እነዚህ ሁሉ የግድ ያስፈልጋሉ፡፡ ጥቃትን ከሩቁ መከላከልና ህልውናን መጠበቅ ከፈለግን ኑሮን ማሻሻልና በኢኮኖሚ መበልፀግ ከፈለግን ማለቴ ነው፡፡


እናም ከየጉራንጉሩ ሚስማርና ቆርኪ ለቅመው ለመሸጥ የሚንከራተቱ ልጆችን ብናይ አይገርምም፡፡ ብረታ ብረት ያስፈልጋል፡፡
በሌላ በኩል ግን ይገርማል።
ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ካለባቸው ከደርዘን የዓለማችን አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ከመሬቷ ላይና ከከርሰ ምድር የብረት ማእድን ሳይጠፋ፣ ማእድን አውጥቶ አገርን የሚገነባ ጀግና መጥፋቱ ይገርማል።
ለነገሩ፣ ተጣጥሮ፣ የራሱን ዐቅም ሁሉ ተጠቅሞ፣ አእምሮውንና ሐሳቡን፣ ዕድሜውንና ገንዘቡን ሁሉ በጥበብና በትጋት ለብረት ማእድን “ለመሰዋት” የሚችልና ከልብ የሚፈልግ ጀግና ቢኖር እንኳ፣… መች ቦታ እንሰጠዋለን?
ማለቴ፣… በሐሳባችን አይመጣም። ፋይዳውን ከመጤፍ አንቆጥረውም። ለእንዲህ አይነት ሰው ብዙም ክብር የለንም። በአጭሩ በኛ ዘንድ ቦታ የለውም።


ቢሆንም ግን፣ ለሙያ ፍቅሩና ለራሱ ራዕይ ብሎ ፈተናውን ሁሉ ለመጋፈጥና ለማሸነፍ የሚሞክር ጀግና ሊመጣ ይችላል። ሊመጣልን ይችላል ብንል ይሻል ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው? መጣብን እንላለን፡፡
የሥራ ቦታ አንሰጠውም።
የመቆሚያ የመፈናፈኛ ቦታ እንዳያገኝ ጠምደን እንይዘዋለን።
ቶሎ ካልተሰበረ እንዘምትበታለን።
የፖለቲካ መቆስቆሻ፣ የጥላቻ ማራገቢያ ሰበብ እናደርገዋለን። ተሟሙቶ ሥራ ከጀመረም የገነባውን አፍርሰን የሠራውን እናቃጥለዋል።
 ሰላም አንሰጠውም - አገር ጥሎ እስኪጠፋ ድረስ።
እናስ? ከወላለቀ የድምፅ ማጉያ በተገኘ ማግኔት ቅንጥብጣቢ ቆርቆሮ፣ ቁርጥራጭ ሚስማር ከየጎዳናው ከየጥጋጥጉ መልቀም ብቻ!
የሆነ ሆኖ ቶማስ ኤዲሰን የድምፅ መቅረጫ ቴክኖሎጂ የፈጠረ ጊዜ፣… ሰዎች የረዥም ጊዜ ታሪካቸውን፣ የዕለት ተእለት ሀሳብና ገጠመኛቸውን እየቀረፁ ይሰንዱበታል የሚል ሀሳብ ነበረው። ማየት ለተሳናቸውና ማንበብ ለማይችሉ ሰዎችም የመረጃ ምንጭ ይሆንላቸዋል የሚል ተስፋ ነበረው። ቴክኖሎጂው ለገበያ ቀርቦ በሰዎች እጅ ውስጥ ሲገባ ግን፣ ቶማስ ኤዲሰን ደነገጠ። አብዛኛው ሰው የሙዚቃ መቅረጫና ማዳመጫ አደረገው።


የግርሃም ቤል የስልክ ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም የቶማስ ኤዲሰን የድምጽ መቅረጫና ማጫወቻ ቴክኖሎጂ፣ በጣም ተቀራራቢና የተዛመዱ ናቸው፡፡ መነሻ አላማቸውም የግርሃም ቤል መስማት ለተሳናቸው ሰዎች፣ የኤዲሰን ደግሞ ለአይነ ስውራን የታሰቡ ቴክኖሎጂዎች ስለሆኑ ይመሳሰላሉ፡፡ ቴክኖሎጂዎቹ ግን፣ ግርሃም ቤል እና ኤዲሰን ካሰቡትም በላይ የላቁና የሰፉ ናቸው፡፡ አለምን ከዳር እስከዳር ሲያዳርሱ እያየን አይደል?
የስፒከር ማግኔት በየመንገዱ የብረት ቅንጥብጣቢ ለመልቀም ያገለግላል ብለው ያሰቡም አይመስልም። የፈጠራ ችሎታቸውን በደንብ አልተጠቀሙበት ይሆናል እንጂ እንዴት ይህን መገመት ያቅታቸዋል? ግን በዚህ ምክንያት እንነዝንዛቸው ማለቴ አይደለም፡፡
ይልቅ ባለፉት 5 ሳምንታት የስፒከር ጉዳይ የአሜሪካ ትልቁ የፖለቲካ መወዛገቢያ ሲሆን አይታችኋል?
ከመስከረም የመጨረሻ ሳምንት ወዲህ፣ የአሜሪካ ኮንግረስ (ፓርላማ) “ስፒከር” ስላልነበረው፣ በጀት ማፅደቅ አልቻለም፡፡ አዋጆችም በእንጥልጥል  ቀርተዋል፡፡ ቀልደኞች ይህን አግኝተው ዝም አላሉም፡፡
“ስፒከር ባይኖር ምንድነው ችግሩ? ዛሬ ዛሬ ሁሉም ሰው የጆሮ ማዳመጫ አለው” ብለው አላግጠዋል፡፡ ከአራት ሳምንት ንትርክ በኋላ ነው የኮንግረስ አፈጉባኤ (ስፒከር) ተመርጦ የምክርቤቱ የዘወትር የተለመደ ክርክር የቀጠለው፡፡

Read 765 times