Friday, 20 October 2023 11:45

ሰሞንኛ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከትናንት ወዲያ አንድ ጓደኛዬ ለልጁ ልደት ጠራኝ፤ ቤቱ ስደርስ፥ ከማላውቃቸው እንግዶች ጋራ ደነበኝ፤   ሁለት አረጋዊ  ባልና ሚስት  ከወጣት ልጃቸው ጋር ጎን ለጎን ተቀምጠዋል፤ ልጅቷ  እንደ አበባ ማስቀመጫ ብርጭቆ ጥድት ያለች ናት፡፡  ከልጅቱ አጠገብ አንድ ጎልማሳ ተጎልቷል፤ ሰውየው መልከ መልካም ነው፤ ጢሙን ደግሞ ከጎን በቅርጽ አሳድጎታል፤ የድሮ የባቢሎን ንጉስ ይመስላል፡፡ ልጅቱን ክፉኛ እንደ ከጀላት ያስታውቃል፤ ትኩረቷን ለማግኘት ሲጥመለመል አየዋለሁ፡፡  የልጅቱ አባትና እናት አንድ አንድ ጥያቄ ጠየቁኝ፤ በዋዛ መለስኩ፡፡ እናትየው በረጅም ሳቅ ተባበሩኝ፡፡  አባትየው፤ “ተው በሳቅ እንዳትገለን” ሲሉኝ፤ በነፍስ ግድያ እንዳልጠየቅ ብዬ ጨዋታዬን ገታሁ፡፡   ጎልማሳው ግን በሳቁ ውስጥ አልተሳተፈም፤ በብዙ ቁጣ፥ በብዙ መከፋት፥ ሲያፈጥብኝ ከቆየ በሁዋላ፥
“እንዲህ አጭር አትመስለኝም ነበር” የሚል ቃል ሰነዘረ፡፡
“አጭር ነኝ ብዬ አላስብም” በማለት ተፈጥሮዬን  አስተባበልኩ፡፡
“ምንድነኝ ብለህ ነው እምታስበው?”  አለ ጎልማሳው፡፡
“በቁመት  ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ጋራ እኩያ ነን፤ እና  ብዙ ጊዜ ራሴን “ንጉስ -አከል” ወይም king-sized ብዬ ነው እምጠራው”
አባትየው በመልሴ በጣም ተደነቁና አምስት ሺህ ብር  ሸለሙኝ::
 ልጅቷ ፈገግ አለችልኝ፡፡
 “አግብተሀል?” አሉኝ እናቲቱ፡፡
“አላገባሁም” አልኩኝ ቀልጠፍ ብዬ፡፡
 “መንግስት ካልመደበላቸው በቀር አጭሮች ከየት አምጥተው ያገባሉ?” አለ ጎልማሳው፡፡“ልክ ነው ሴቶች አስቀድመው  የሚያዩት ረጅም ወንድ ነው” ብዬ ጀመርሁ፤ ጎልማሳው በድል አድራጊነት  ፈገግ ብሎ ወደ ልጅቱ ተመለከተ፡፡
“በዚህ ምክንያት፥ አጭር ወንዶች የሴቶችን ቀልብ ለመግዛት መላ መፍጠር ይገደዳሉ፤ ወይ አሪፍ ፈልሳፊ፤  አሪፍ ሙዚቀኛ ፥ወይ አሪፍ አትሌት፤ ወይ አሪፍ ሀሳብ አፍላቂ!፤ ወይ አሪፍ ባለሀብት ለመሆን ይታገላሉ፤ አጭር ወንዶች የሴቲቱን ቀልብ ለመሳብ የፈጠሯቸው ጸጋዎች አንዳንዶቹ የስልጣኔ ማድመቂያ ለመሆን በቅተዋል፤ ረጅም  ሸበላ ወንድ  በተፈጥሮው ስለሚረካ ሴቲቱ መጥታ እስክትወድቅለት  ይጠብቃል፤ አጭር ወንድ ግን የጅንጀና ጥበብን ፈልስፏል፤  ዞሮ ዞሮ ረጃጅሞች የሚበሉት እራት ከአጭሮች የተረፈውን ነው” በማለት ዲስኩሬን ዘጋሁት፡፡   
ሰውየው  በጣም ተናደደ::
ሳይደበድበኝ ጨዋታውን ወደ  ሰሞኑ ፖለቲካ አዞርኩት፡፡  አረጋዊውና ሚስቲቱ እስራኤልን ሲደግፉ፣ ልጅቱ ደግሞ የፍልስጤም ተቆርቋሪ መሆናቸውን ተገነዘብኩ፤ የኔን ሀሳብ ጠየቁኝ፡፡ “ኢትዮጵያዊ  ጎራ ለይቶ እሚነታረክበት ምክንያት አይገባኝም፤ አበሻ ቢችል አስታራቂ ባይችል ተመልካች መሆን ነው ያለበት፤ እኛ እኮ የእብራውያንንና የአረቦችን ባህል እኩል በሚባል ደረጃ የወረስን ህዝብ ነን” አልኩ፡፡
“የሰለሞንና የማክዳን ታሪክ አላነበብህም መሰል” አሉኝ አባትየው፤ በሽልማት የሰጡኝን አምስት ሺህ ብር  መልሰው እየወሰዱ፡፡
“የሰለሞንና የማክዳ ታሪክ ከእስራኤል ጋራ ያለንን ዝምድና የሚተርክ መጽሐፍ ነው፤ ግን ከአረብኛ  የተተረጎመ መጽሐፍ መሆኑንም  አንርሳ” ካልኩ በሁዋላ ወደ ወደ ጎልማሳው ዞሬ፤
“በዚህ ጉዳይ አንተ ምን ታስባለህ?” አልኩት፡፡
“እኔ ፖለቲካ ላይ የለሁበትም፤ እልል ያልሁ  ዘመናዊ ጫማ ነጋዴ ነኝ፤”
  ከጥቂት ዝምታ በሁዋላ ይቺን አስከተለ፤
“ረጅም ተረከዝ ያለው ጫማ ስትፈልግ ወደ ሱቄ ጎራ ማለት ትችላለህ”
(በእውቀቱ ስዩም)

Read 1007 times