Saturday, 14 October 2023 00:00

“የጥላቻ ንግግር” እና የአካባቢ ብክለት

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(1 Vote)

የ2016 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥራ መጀመርን ምክንያት በማድረግ የመክፈቻ ንግግር ያቀረቡት  ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ባስተላለፉት መልዕክት ካነሷቸው አንኳር ሀሳቦች አንዱ ‹‹የጥላቻ ንግግር››ን የተመለከተ ነበር፡፡ በተለያየ መልኩ ሊገለጽ የሚችለው ‹‹ጥላቻ››፤ ሀገራችንን ብቻ ሳይሆን ዓለማችንን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት የሚገኝ  ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ  ሀማስ በእስራኤል ላይ ለፈጸመው ጥቃትና ለተከሰተው ቀውስ አንዱ ምክንያት ‹‹ጥላቻ›› ነው፡፡
‹‹ጥላቻ›› እና ‹‹የጥላቻ ንግግር›› እንደ ብከለት (Pollution) ለምድራችን ስጋት ከሆነ ከራርሟል፡፡ ይህንን እውነታ መዲናችን አዲስ አበባን ማዕከል አድርገን ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ እንችላለን፡፡ በኅዳር ወር 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አደባባዮች፣ ‹‹ከተማችንን ከቆሻሻ ብቻ ሳይሆን ከሀሰተኛ የጥላቻ መልዕክት እንጠብቅ!›› የሚልና መሰል ይዘት ያላቸው፣ በትላልቅ ባነሮች የተጻፉ በርካታ መፈክሮች ተሰቅለው ነበር፡፡ መልዕክቱ ‹‹ኅዳርን ከማጠን›› እና የፅዳት ወር ነው ተብሎ በልማድ ከሚታሰበው ወቅት ጋር በተያያዘ የተላለፈ ነበር፡፡ የመልዕክቱ ባለቤት የአዲስ አበባ ፅዳት አስተዳደር ቢሮ ሲሆን፤ ‹‹ጥላቻ›› ከተማውንና የከተማውን ነዋሪ ከሚበክሉ ጉዳዮች አንዱ መሆኑ እንዳሳሰበው ያመላከተ ነበር፡፡
ብክለት የብዙ ሀገራት ትልቅ ስጋት ሆኖ ዓመታት ያስቆጠረ ችግር ነው፡፡ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ መስፋፋት፣ ከከተሞች ለውጥና ዕድገት፣ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የግብርናው ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪ ከመሸጋገርና መሰል ክስተቶች ጋር መልክና ዓይነቱ እየተቀያየረ የመጣው ብክለት፣ የዓለም ሕዝብና መንግሥታት አንዱ መነጋገሪያ አጀንዳ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡
ብክለትን ርዕሰ ጉዳይ ያደረጉ በርካታ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ይካሄዳሉ፡፡ በተለያዩ ሀገራት ልዩ ልዩ ግንዛቤ ሰጪና አስተማሪ መድረኮች ይዘጋጃሉ፡፡ አስገዳጅ ደንብና አዋጆች ይወጣሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን  ብክለት ከመቀነስ ይልቅ፣ እየጨመረና እየተስፋፋ ነው የመጣው፡፡  
የመደበኛ ትምህርት አንዱ ርዕሰ ጉዳይ ተደርጎ የሥርዓተ ትምህርት አካል የሆነው ብክለት፤ ዓይነቱ፣ የችግሩ መነሻና ምንጩ፣ መስፋፊያ መንገዶቹ፣ ችግሩን መቀነሻና ማስወገጃ መንገዶች ሰፊ ስልጠናና ትምህርት ይሰጥበታል፡፡ የብክለት ዓይነቶቹም፤ የዐፈር፣ የውሃ፣ የአየር፣ የድምፅ … እየተባሉ በየፈርጁ ተከፍለው ይጠናሉ፡፡ ብክለት የሚታይና የሚዳሰስ ብቻ ሳይሆን፤ ምንጩ የማይታወቅ ሆኖ ግብሩ ብቻ የሚታይም አለ፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ያለው መረጃና ትንታኔ ሰፊና ብዙ ነው፡፡
‹‹ሀሰተኛ መልዕክቶች›› እና ‹‹የጥላቻ ንግግሮች›› ሕዝቧን ለተለያየ ጉዳቶች እየዳረገባት ያለችው ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ ይህንን ጨምሮ መልከ ብዙው ብክለት እያስከተለባት ያለውን ጉዳትና አፈጻጸሙ በምን መልኩ ተግባራዊ እየሆነ እንዳለ፣ በመዲናችን አዲስ አበባ አደባባዮች በየዕለቱ በርካታ ትዕይንቶች ይታያሉ፡፡
አዲስ አበባ፤ የማይግባቡ፣ ሰሚ ያጡ፣ መፍትሔ አልባ ጩኸትና ግርግሮች በዝተውባታል፡፡ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማሕበራዊና በባሕላዊ ዘርፎች አነጋጋሪ የሆኑ በርካታ ጉዳዮች በየዕለቱ እናያለን፤ እንሰማለን፡፡    
ኮንስትራክሽን፣ ከመሠረተ ልማት፣ ከሕዝብ ፍልሰት፣ ከመኖሪያ ቤት ዕጥረት፣ ከ‹‹ጨረቃ ቤቶች›› ፈረሳ፣ ከሥራ አጥነትት፣ ከትራንስፖርት መጨናነቅ፣ ከልመና መስፋፋት፣ ከአንዱ ወደ ሌላው ቦታ መንቀሳቀስ ከመከልከሉ ጋር በተያያዘ፣ ብዙ ጉምጉምታ፣ የተለያየ የመረጃ ስርጭት፣ የጥላቻ ንግግር መሰል ችግሮች አሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ መቆጣጠር ያልተቻለው የሕዝብ ቁጥር መጨመር ትልቁን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
እቅድ አልባ የሕዝብ ዕድገት ሊያስከትል የሚችለው ችግር ምን እንደሚመስል አዲስ አበባ አንዷ ማሳያ ከሆነች ከራርማለች፡፡ 100 ሚሊዮኖቹን ተሻግሯል የሚባለው የሀገራችን ሕዝብ ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት ለብዙ ችግሮች፣ ቀውስና አዳዲስ የብክለት ዓይነቶች መፈጠር  ምክንያት ሆኗል፡፡ቤት አልባዎች በከተማዋ አደባባዮች ብቻ ሳይሆን በየተራራው፣ ጫካው፣ ወንዝ ዳርና ቱቦዎች ሁሉ ይኖራሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ‹‹የጨረቃ ቤቶች›› በየዕለቱ እንደ እንጉዳይ በቅለው ያድራሉ፡፡ ‹‹ሕገ-ወጥ ናችሁ›› በሚል ሰበብ የማፍረሱ ሂደትም ሀገርን፣ ሕዝብንና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ይጎዳል፡፡ ‹‹የጨረቃ ቤት›› ከፈረሰባቸው ከፊሎቹ ከወዳደቀ ካርቶንና ላስቲክ አንዱ ጥግ መጠለያ ቀልሰው የሚያሳልፉት ኑሮ በየዕለቱ ለብክለት መፈጠር አስተዋጽኦ ማድረጉ ሳይታለም የተፈታ እውነት ነው፡፡
ሀገሪቱ እንዲህ ዓይነቱን ችግር ከስሩ መቅረፍ ያስችለኛል ብላ ከዓመታት በፊት የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ብታወጣም፤ የኢሕአዴግ መንግሥት በተከተለው የዘር ፖለቲካ ምክንያት ሕዝቡ “ዘርና ሀይማኖትን ማስፋፋት” በሚል ዓላማ በፍጥነት ስለተዋለደ፣ የሕዝቡን ዕድገት ቁጥር መግታት አልተቻለም፡፡ የሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥር ዕድገት ብቻ ሳይሆን ፖለቲከኞች የሚፈጥሩትን ቀውስ ለመሸሽ፣ አዲስ አበባን ‹‹በኖህ መርከብነት›› የተመለከቱ ‹‹ስደተኞች›› በመበራከታቸው ምክንያት ከተማዋ በብዙ ብክለቶች ተጠቂ እንድትሆን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡   
መቆጣጠር ያልተቻለ የሕዝብ ዕድገት ከሚያስከትላቸው ችግሮች ሌላኛው የሥራ እጦት ነው፡፡ ‹‹ከአንድ ዲግሪ አንድ ግሮሰሪ›› እንደሚሻል መሰበክ ከተጀመረ ሦስት አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት የሰማነው ‹‹አስደንጋጭ የማትሪክ ፈተና ውጤት›› የትምህርቱ ዘርፍ ጀምሮት የነበረው የቁልቁለት መንገድ የታሰበለት የውድቀት ግብ ላይ መድረሱን ነው የሚያመለክተው፡፡ ይህ ኪሳራ ቀደም ብሎም የፈጠረው ችግር ,ነበር፤  በቀጣይም የሚፈጥረው ቀውስ ይኖራል፡፡
ከድግሪ ይልቅ ባለግሮሰሪ መሆንን ፈልገው፣ የንግዱን ጎዳና የመረጡ የጎዳና ነጋዴዎች ቁጥር ከመቀነስ ይልቅ ከዕለት ዕለት እየተበራከተ መጥቷል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ባለፈው 2015 ዓ.ም ከ80 ሺህ በላይ የጎዳና ነጋዴዎችን ከጎዳና ማንሳቱን በያዝነው ሳምንት በመንግስት መገናኛ ብዙኃን አሳውቋል፡፡ የጎዳና ንግድ ለከተማ መቆሸሽ ትልቅ ሚና አለው፡፡ ለድምፅ ብክለትም ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡
የከተማዋን አደባባዮች ‹‹ከሕገ ወጥ ነጋዴዎች›› ለማፅዳት የሚወሰዱ እርምጃዎች ምን ይመስላሉ? በአፈጻጸሙ ‹‹ሀሰተኛ መልዕክቶች›› እና ‹‹የጥላቻ ንግግሮች›› እንዳይፈጠሩ ምን ዓይነት ጥንቃቄ እየተወሰደ ነው ?  የሚለውን ጠይቆ ተገቢውን ምላሽ ማኖር ቀውስን ላለማባባስ ይረዳል፡፡ እንደሚታወቀው የጎዳና ንግድን በተመለከተ መንግሥት በተለያየ ጊዜ ችግሩን ይቀርፍልኛል በሚል ‹‹የአርከበ ሱቅ››፣ ‹‹የሰንደይ ማርኬት››፣ ‹‹የታከለ ባሶች›› … መሰል ሙከራዎች ቢያደርግም፣ ብክለትን ከመቀነስ አንጻር ካስገኙት ጥቅም ይልቅ ያስከተሉት ጉዳት ይበልጣል ነው የሚባለው፡፡ የጎዳና ነጋዴዎችን ከጎዳና የማጽዳቱ ሂደት ዛሬም ‹‹አንሳ ወይ ሃምሳ›› በሚል ድርድር የሚመራ መሆኑም ለችግሩ አለመቀረፍ አስተዋጽኦ ማድረጉ አልቀረም፡፡   
‹‹አንሳ ወይ ሃምሳ›› ከመባረር ማባረር ጋር በተያያዘ፣ በ1970ዎቹ አጋማሽ በመርካቶ የሚታወቅ ድርድር ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ‹‹ሀምሳ›› ለሳንቲም ነበር፡፡ ዛሬ ‹‹ሃምሳ›› ለብር ነው ይባላል፡፡ ከ40 ዓመት በፊት የጎዳና ነጋዴዎችን ለማጥፋት የተጀመረው ‹‹የሕግና ደንብ›› አገልግሎት፤ አሁን በከተማ አስተዳደሩ ካሉት ትላልቅ ተቋማት አንዱ ደረጃ ላይ ቢደርስም፤ ‹‹እሳት የማጥፋት›› ሥራው ዘላቂ መፍትሔ አለማስገኘቱ ሀገሪቱና የማይለቃት ‹‹አዙሪት›› አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ለዓመታት የተደረገው ሙከራና ጥረት የአዙሪቱ ሰለባ ባይሆን ኖሮ፤ በአደባባዮቻችን ለሚታየው የድምፅና የቆሻሻ ብክለት መቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረው ነበር፡፡
በቀድሞ ዘመን በርካታ የአዲስ አበባ ልጆች ከውሃ ዋና ጋር የተዋወቁባቸው የአዲስ አበባ ወንዞች፤ በነዋሪ ተወርረው ከየቤቱና ኢንዱስትሪዎች የሚወጣ ተወጋጅ ፍሳሽ ሰለባ ከመሆናቸው በፊት፤ ንፁሕና ለመጠጥ ሁሉ የሚያገለግሉ ነበሩ፡፡ ውሃ የዓለም ሕዝብንና መንግሥታትን ወደ ጦር ግንባር የሚጋብዝ እጥረት ያለበት የተፈጥሮ ሀብት ነው፡፡ ስለዚህ እውነታ ከቀድሞ ዘመን በተሻለ በቅርቡ ከዐባይ ወንዝ ብዙ ተምረናል፡፡ እንዲህም ሆኖ የሸገር ተፋሰስን አልምቶ ወደ ቀድሞው ክብራቸው የመመለሱ እቅድ በማሳያ ጥቂት ሥራዎች መቅረቱ ያሳዝናል፡፡
የድምፅ ብክለትን በተመለከተም፤ ችግር አደባባይ ያቆማቸው የእኔ ብጤዎች፣ ለከተማችን የድምፅ ብክለት የድርሻቸውን ከማበርከታቸውም በተጨማሪ፤ ባህላዊው ተመጽዋችነት በምን መልክና ደረጃ መዘመን እንደቻለ ማሳያ ሆነው ሊቀርቡ የሚችሉ ‹‹ለማኞች›› በመዲናዋ አደባባዮች በስፋት ያታያሉ፡፡ በማይክራፎን፣ በኪራይ መኪና፣ ተጨማሪ የሰው ኃይል በማሰማራት … እየታገዙ የሚካሄዱ የልመና ዓይነቶች እየተበራከቱ ነው፡፡‹‹በበረሃ እንደሚጮኸው ዮሐንስ›› የነፍሳችን ጉዳይ አስጨንቋቸው ይሁን ‹‹የኮሚሽን ሥራው›› ጥሟቸው እውነታው የቱ እንደሆነ መግለጽ ቢያስችግርም፤ አደባባዮቻችንን ያጥለቀለቀው የሀይማኖት ስብከት የችግሩ ሌላኛው ገጽታና ማሳያ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ የሚታየው የጥላቻ ንግግርና ‹‹ስብከት›› ተከማችቶ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ከወዲሁ ማስቆም የሚችል የሚመለከተው አካል አለመኖሩ አሳሳቢ  ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለፓርላማ መክፈቻ ባቀረቡት ንግግር ላይ ያነሱት ‹‹የጥላቻ ንግግር›› ሙሉ ለሙሉ ጠፍቶም ይሁን ቀንሶ፣ የተመኙት ለውጥ እንዲመጣ ‹‹ለጥላቻ›› ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ ማወቅ ይጠይቃል፡፡ በጥላቻ ንግግርና በመሳሰሉት የተለያዩ የብክለት ዓይነቶች እየተጠቃች ያለችው አዲስ አበባ፤ ከፍ ብሎም ሀገራችንንና ሕዝቦቿን ከጥፋት ለመታደግ፣ በዚህ ዙሪያ የወጡ ዓለም አቀፍ፣ ሀገር አቀፍና ከተማ ተኮር ሕጎች አቧራቸው ተራግፎም ቢሆን የመፍትሔ አካል መሆን ከቻሉ፣ ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ፣ ሀገርና ሕዝብን ከጉዳት መታደግ ይቻላል፡፡

Read 422 times