Sunday, 17 September 2023 21:14

ከ14ኛው ዳይመንድ ሊግ ፍፃሜ በፊት

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

• ዮሚፍ፤ በሪሁ፤ ጥላሁንና ሰለሞን፤ ለጠቅላይ አሸናፊነት ይፋለማሉ።
  • ፍሬወይኒ በ1500 ሜትር ዋንጫውን መውሰዷ አይቀርም።
  • 15 የዳይመንድ ሊግ ዋንጫ አሸናፊዎች ከኢትዮጵያ ተገኝተዋል።
  • 3 የዳይመንድ ሊግ ሪከርዶችም በኢትዮጵያውያን እንደተያዙ ናቸው

         14ኛው ዳይመንድ ሊግ ዛሬ ነገ በአሜሪካዋ ዩጂን ከተማ በሚካሄዱ ውድድሮች ፍፃሜውን ያገኛል፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለት የውድድር መደቦች ሁለት የዳይመንድ ሊግ ዋንጫዎች ሚቀሳጁበት ከፍተኛ እድል አላቸው። በሴቶች 1500 ሜትር ፍሬወይኒ ሃይሉ ከፍፃሜው በፊት ባስመዘገበችው ከፍተኛ ነጥብ ዋንጫውን የማሸነፍ እድል ይኖራታል። በ5ሺ ሜትር ወንዶች ደግሞ ዮሚፍ ፤ በሪሁ፤ ጥላሁንና ሰለሞን፤ ባስመዘገቡት ተቀራራቢ ነጥብ በፍፃሜው ለጠቅላይ አሸናፊነት ይፋለማሉ።
ፍሬወይኒ ሃይሉ በሴቶች 1500 ሜትር ከፍፃሜው በፊት ያስመዘገበችው 35 ነጥብ ሲሆን ይህም የዳይመንድ ሊግ ዋንጫውን ለማሸነፍ እና 30ሺ ዶላር ለመቀዳጀት ከፍተኛ እድል ይሰጣታል፡፡ በዳይመንድ ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በሁለተኛ ደረጃ የምትገኘው የአውስትራሊያዋ ጄሲካ ሁል 26 ነጥብ ያላት ሲሆን፤ ኬንያዊቷ ፌዝ ኪፕዬጎን እና የአየርላንዷ ሴራ ማጊን በ24 ነጥብ ተከታይ ናቸው። ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ብርቄ ሃየሎም በ19 ነጥብ ስድስተኛ፤ ድርቤ ወልተጂ በ14 ነጥብ ሰባተኛ እንዲሁም ሂሩት መሸሻ በ13 ነጥብ አስረኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በወንዶቹ 5ሺ ሜትር የኢትዮጵያውያኑ ፍጥጫ የተጠበቀው አራት አትሌቶች  በያዙት ተቀራራቢ ነጥብ ነው፡፡ ከፍፃሜው በፊት ዮሚፍ ቀጀልቻ በ23 ነጥብ መሪነቱን የያዘ ሲሆን በሪሁ አረጋዊና ጥላሁን ከበደ በ21 ነጥብ እንዲሁም  ሰለሞን ባረጋ በ18 ነጥብ ተከታታይ ደረጃዎችን ይዘው ይገኛሉ። በውድድር መደቡ የዓመቱ ሻምፒዮን ሆኖ ለመጨረስ 4ቱም እድል እንደያዙ ናቸው። ሐጎስ ገብረህይወት በ14 ነጥብ እንዲሁም ለሜቻ ግርማ በ8 ነጥብ የፍፃሜውን ውድድር ይሳተፋሉ፡፡
በ5ሺ ሜትር ሴቶች የኢትዮጵያ አትሌቶች የዳይመንድ ሊጉን ዋንጫ ለማሸነፍ  ብዙም እድል የላቸውም፡፡ የኬንያዋ ቤትሬስ ቺቤት በ31 ነጥብ እየመራች ሲሆን ሌላዋ ኬንያዊት ካቤት በ22 ነጥብ ትከተላለች፡፡ መዲና ኢሳ በ18 ነጥብ፤ ለምለም ሃይሉ በ15 ነጥብ እንዲሁም ፍሬወይኒ ሃይሉ በ12 ነጥብ የፍፃሜውን ውድድር ይሳተፋሉ፡፡
በወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ሞሮካዊው ኤል ባካሊ በ32 ነጥብ መሪነቱን በመያዝ ወደ ዋንጫው የተጠጋ ሲሆን የኬንያው አብርሃም ኪብዮት በ26 ነጥብ ጠቅላይ አሸናፊነቱን ለመውሰድ ይፎካከረዋል፡፡ በሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል  ላይ ደግሞ የዳይመንድ ሊግ ዋንጫው በ32 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን በምትመራው ቢትሬስ ቼፕኮች እጅ እንደሚገባ የተረጋገጠ መስሏል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ  ሲምቦ አለማየሁ በ22 ነጥብ እንዲሁም ዘርፌ ወንድም አገኘሁ ከጃኩሊን ቼፕኮች ጋር በእኩል 14 ነጥብ በማስመዝገብ የፍፃሜ ውድድራቸውን ያደርጋሉ፡፡
በዋንዳ ስፖንሰር የሆነው የዘንድሮው ዳይመንድ ሊግ ባለፉት 6 ወራት 4 አህጉራትን አውሮፓ፤ ኤስያ፤ ሰሜን አሜሪካና አፍሪካን በማካለል በ14 ከተሞች የተሰናዳ ሆኗል። ከአሜሪካዋ ዩጂን በፊት ውድድሩን ያስተናገዱት ዶሃ፤ ራባት፤ ሮም ፍሎረንስ፤ ፓሪስ ፤ ኦስሎ፤ ሉዛን፤ ስቶክሆልም፤ ሲየልሳ፤ ሞናኮ፤ ለንደን፤ ዙሪክ፤ ዣይንሜንና ብራሰልስ ናቸው፡፡ በየከተሞቹ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ ከ1 እኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃ ለሚያገኙት  በቅደም ተከተል 8፤7፤6፤5፤4፤3፤2፤1 ነጥብ የሚሰጥ ሲሆን ለአንደኛ 10ሺ ዶላር ለሁለተኛ 6ሺ፤ ለሶስተኛ 3ሺ500 ፤ለአራተኛ 2ሺ፤  ለአምስተኛ 1ሺ250፤ ለስድስተኛ 1ሺ፤ ለሰባተኛ 750 እንዲሁም ለስምንተኛ 500 ዶላር ይሸለማል። የዳይመንድ ሊግ ዋንጫው በ14 ከተሞች በሚገኙ ውጤቶች በሚመዘገበው ነጥብ መሰረት ለአሸናፊው የሚሰጥ ሲሆን በየውድድር መደቡ የዓመቱ ሻምፒዮን ሆነው ለሚጨርሱት 30ሺ ዶላር ይበረከታል፡፡ ከፍፃሜው በኋላ በየውድድር መደቡ በሚመዘገበው ደረጃ መሰረት ለሁለተኛ 12ሺ፤ ለሶስተኛ 7ሺ፤ ለአራተኛ 4ሺ፤  ለአምስተኛ 2500፤ ለስድስተኛ 2ሺ፤ ለሰባተኛ 1500 እንዲሁም ለስምንተኛ 1ሺ ዶላር የሚከፋፈል ይሆናል፡፡
ከ14ኛው የዳይመንድ ሊግ ፍፃሜ በፊት ባለፉት 13  የውድድር ዘመናት ኢትዮጵያ 15 የዳይመንድ ሊግ ዋንጫዎችን ለማሸነፍ በቅታለች፡፡ 87 የዳይመንድ ሊግ ዋንጫዎች በማሸነፍ አሜሪካ ግንባር ቀደም ስትሆን ኬንያ 54 እንዲሁም ጃማይካ 24 በመሰብሰብ እስከ 3ኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡ ለኢትዮጵያ የዳይመንድ ሊግ ዋንጫን ያሸነፉት በ5ሺ ሜትር ኢማና መርጋ በ2010 እና በ2011 እ.ኤ.አ፤ የኔው አላምረው በ2013 እኤአ፤ ዮሚፍ ቀጀልቻ በ2015 እኤአ ሐጎስ ገብረህይወት፤ በ2018 እኤአ ሰለሞን ባረጋ እንዲሁም በ2021 እኤአ በሪሁ አረጋዊ ናቸው፡፡ በ800 ሜትር በ2012 እና በ2013 እኤአ መሐመድ አማን እንዲሁም በ3ሺ ሜትር መሰናክል በ2019 እኤአ ጌትነት ዋለ አሸናፊዎች ነበሩ፡፡ በሴቶች ደግሞ በ5ሺና ሶስት ሺህ ሜትር በ2013 እኤአ መሰረት ደፋር፤ በ2015 እኤአ ገንዘቤ ዲባባ እና በ2016 እኤአ አልማዝ አያና እንዲሁም በሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል በ2014 እኤአ ህይወት አያሌው እንዲሁም በ2022 እኤአ የወርቅ ውሃ ጌታቸው የዳይመንድ ሊግ ዋንጫን አንስተዋል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር እንደሚያመለክተው 3 የዳይመንድ ሊግ ሪከርዶችም በኢትዮጲያውያን እንደተያዙ ናቸው፡፡ የመጀመርያዎቹ ሁለት ክብረወሰኖች በጎልደን ሊግ ዘመን አሁን በማይካሄደው የ10ሺ ሜትር ውድድር የተመዘገቡ ሲሆን በ2014 ቤልጅዬም ላይ ቀነኒሳ በቀለ በወንዶች 26፡43.10 እንዲሁም ጥሩነሽ ዲባባ በ2012 እኤአ ላይ በዩጂን 30፡24በሆነ ጊዜ ያስመዘገቧቸው ናቸው።



Read 923 times