Sunday, 03 September 2023 21:27

የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር ተመሥርቶ ስራ ጀመረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የአምባሳደር ሆቴልና አፓርትመንት ሥራ አስኪያጅ በፕሬዚዳንትነት ተሾመዋል


        የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም በለሙያዎች ማህበር ባለፈው ማክሰኞ ነሀሴ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ላምበረት አካባቢ በሚገኘው በሀይሌ ግራንድ ሆቴል በይፋ ተመስርቶ ስራ ጀመረ። ማህበሩ ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለልጣን ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ መመስረቱን በዕለቱ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተብራርቷል፡፡
ማህበሩ የአምባሳደር ሆቴልና አፓርትመን ማናጀር የሆኑትን፣ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከ15 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበቱትን፣ በግላቸው የሆቴልና ቱሪዝም ስልጠና ሲሰጡ የቆዩትንና በርካታ ሆቴሎች በማደራጀትና በማማከር ንቁ ተሳትፎ ያደረጉትን አቶ አሸናፊ ሙሉጌታን በፕሬዚዳንትነት ሾሟል፡፡
የማህበሩ መስራች አባላት በሆቴልና ቱሪዝም በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ እውቀትና ብቃት  ያላቸው እንዲሁም ለኢንዱስትሪው እድገት የሚቆረቆሩ እንደሆኑ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ገልፀዋል፡፡
መስራቾቹ ማህበሩ ከመመስረቱ በፊት “በሙያዬ ለሀገሬ” የተሰኘ የበጎ ተግባር ንቅናቄ ሲያካሂዱ መቆየታቸውን ያብራሩት ፕሬዚዳንቱ በዚህ ንቅናቄ በአዲስ አበባና የተለያዩ ክልሎች በተለይም በኮቪድ 19 ወቅት በርካታ በጎ ተግባራትን ሲያከናውኑ እንደቆዩ ተገልጿል፡፡
ይህም የበጎ ተግባር ንቅናቄ ህልማቸው የነበረውን ይህን ማህበር ለማቋቋም መንደርደሪያ እንደሆናቸው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ከዚህ በኋላ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ያለውን የስነ ምግባር፣ የእውቀትና ክህሎት ክፍተት እንዲሁም የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍን ትኩረት ማነስ ለመቅረፍ በርትተው እንደሚሰሩ የገለፁት የማህበሩ ሃላፊዎች ማህበሩ ለባለሙያዎች የመብት መከበርና ተጠቃሚነት፣ የስልጠናና የትምህርት እድሎች እንዲሁም የመሰረተ ልማት ግንባታ መሟላት የበኩሉን አስተዋፅኦ በማድረግ፣ ለኢንዱስትሪው እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ቃል ገብቷል፡፡ አዲስ አበባ ከኒውዮርክና ከጄኔቭ ቀጥላ ሶስተኛዋ የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ መሆኗን የጠቀሱት የማህበሩ ሃላፊዎች፤ ለዚህች ትልቅ ከተማ የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት መዘመን፣ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ጎብኚዎች የሚመችና የሚመጥን ሙያዊ ልህቀትና ክህሎት እንዲኖር ማህበሩ ከአባላቱ ጋር አበክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ ማህበሩ እስከ ምስረታው እለት ድረስ ከ280 በላይ አባባትን መመዝገቡንም አስታውቋል፡፡
በምስረታ በዓሉ ላይ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ፣ የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) እና ሌሎች በርካታ የዘርፉ ተዋንያንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል፡፡


Read 693 times