Sunday, 03 September 2023 21:04

ተጨንቀው ያመጡትን ዕንባ ዝንብ ይልሰዋል!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 አንድ አዞ ከሚስቱ ጋር በጣም ጥልቅ፣ ጨለማና በፈጣኑ የሚወርድ ወንዝ ውስጥ ይኖር ነበር፡፡ አንድ ቀን ሚስትየው “የዝንጀሮ ልብ አምሮኛል፡፡ በጣም በጣም ርቦኛል፡፡ እንደምንም ብለህ አንድ እንኳን አምጣልኝ እባክህ” ትለዋለች ለባሏ፡፡
“ዝንጀሮ የሚኖረው መሬት ላይ፣ እኛ የምንኖረው ውሃ ውስጥ፤ እንዴት አድርጌ ዝንጀሮ ለመያዝ እችላለሁ? ከራበሽ ሌላ ነገር ብዪ እንጂ የዝንጀሮ ልብ ላገኝልሽ አልችልም፤ የእኔ ቆንጆ!” አላት፡፡
“የኔ ጌታ! እኔ ዕውነቴን ነው የምልህ፤ ልብ ካላገኘሁ መሞቴ ነው፡፡ እንደምንም ብለህ አንድ ፈልግልኝ” ብላ ዓይኗን ከርተት ከርተት እያደረገች ለመነችው፡፡
ባልየው ከወንዙ  ዳርቻ የሚኖር አንድ ቆንጆ ዝንጀሮ እንዳለ ያውቃል፡፡ ግን ያ ዝንጀሮ ጀግና፣ ቀልጣፋና ብልህ መሆኑንም ጭምር ያውቃል፡፡ እሱን፤ እንኳን ገድሎ ልቡን ማግኘት ይቅርና አባርሮ መያዝ እንኳ እንዴት ከባድ ድካም መሆኑን ያውቀዋል፡፡
ያም ሆኖ ባለቤቱ በጣም ስለተማጸነችው ምርጫ አጣ፡፡ ስለዚህም ያንን ዝንጀሮ ማታለል አለብኝ ብሎ አሰበና ዘዴ ዘየደ፡፡ መላው እንዲህ ነው፡- በየቀኑ ከወንዙ ዳርቻ ወጥቶ ፀሀይ ላይ ለጥ ብሎ መተኛት፡፡ ዝንጀሮው ወደ እዚያ ሲመጣ ምንም ፍላጎት ያለው ሳያስመስል ማጨዋወት፡፡ በቃ፡፡
ዝንጀሮው መጣ፡፡ አዞው ማጨዋወቱን ቀጠለ፡፡ ዝንጀሮው ግን በጣም ቀርቦ አልጫወት አለ፡፡ ከአዞ ጋር ብዙ መቀራረብ አጉል እንደሆነ ገብቶታል፡፡ የአዞን ጥርስ ስለት አሳምሮ ያውቀዋል፡፡
እንዲህ እንዲህ እያሉ ሰነባበቱና አንድ ቀን አዞው እንዲህ አለ፤
“በዚህኛው የወንዙ ዳርቻ ያለውን ዛፍ ፍሬ ብቻ ለምን ትበላለህ? በወዲያኛው ዳርቻምኮ በጣም የሚያማምሩ የበሰሉ ፍሬዎች አሉ!”
ዝንጀሮውም፤ “ያማ የማይገኝ ነገር ነው፡፡ እንዴት ብዬ እዚያ ድረስ እሄዳለሁ? ያውም እንዲህ ፈጥኖ በሚፈሰው ወንዝ አቋርጬ እንዴት ብዬ እሻገራለሁ?” አለ፡፡
አዞ፤ “ለእሱ እኳ እኔ አለሁ፤ አዝዬህ በአንድ አፍታ አደርስሃለሁ፡፡” አለና ሰፊ አዟዊ ፈገግታ አሳየው፡፡
ዝንጀሮውም፤ “እንደዚያማ ከረዳኸኝ በጣም እድለኛ ነኝ፡፡ ደግሞም አምንሃለሁ፡፡ አንተ ሽማግሌ አዞ ነህ ሽማግሌ አይዋሽም”
አዞው ከውሃው ወጣ ብሎ ወደ ዳርቻው ተጠጋለትና ዝንጀሮ ፊጥ ብሎ ወገቡ ላይ ሰፈረ፡፡ አዞው ጥሩ ዋናተኛ በመሆኑ ዝንጀሮውን በጥሩ ምቾት ይዞት ይፈስስ ጀመር፡፡
ሆኖም ግማሽ መንገድ እንደሄዱ እዚያ ጨለማና ጥልቅ ወንዝ ውስጥ ይዞት ስምጥ አለ፡፡
ዝንጀሮም፤ “ኸረ! ሰመጥንኮ! ቀስ በል እባክህ!” አለው፡፡
አዞውም፤- “አሁን አለቀልህ፡፡ በቃ ልገልህ እኮ ነው! ለመሆኑ እዚያኛው ዳርቻ ድረስ አዝዬህ የምሄደው በምን ዕዳዬ ነው? ለጽድቅ ብዬ እንዳይመስልህ ወዳጄ፤ ገድዬህ ልብህን ለመውሰድ ፈልጌ ነው፡፡ ባለቤቴ የዝንጀሮ ልብ ካልበላሁ ሞቼ እገኛለሁ ብላኝ ነው”
ዝንጀሮውም ጥቂት አሰበና፤ “አያ አዞ! የልብህን ስለነገርከኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ቢያንስ ምን እንደምትፈልግ አሁን ገባኝ፡፡ ግን አንድ ነገር ማወቅ አለብህ፤ ዝንጀሮዎችኮ ልባቸውን በደረታቸው ውስጥ ይዘው ከቦታ ቦታ አይዘዋወሩም፡፡ ምክንያቱን መቼም ሳታውቀው አትቀርም፡፡ ያው ከዛፍ ዛፍ ሲዘሉ ልባቸው እንዳይታጠፍና እንዳይሰባበር ብለው ነው፡፡ እኛኮ ልባችንን በሰውነታችን ውስጥ ይዘን አይደለም የምንንቀሳቀሰው፡፡”
አዞም በነገሩ ተገርሞ፤ “ታዲያ የት ታስቀምጡታላችሁ?” ሲል ጠየቀው፡፡
“እዚያ ጥለነው የመጣነው ጫካ ውስጥ ነዋ! ከዛፎቹ ፍራፍሬዎች መካከልኮ ነው የምንደብቀው” አለና መለሰ፡፡
አዞ፤ “ይገርምሃል፤ ይህንን በጭራሽ አላውቅም ነበር!”
ዝንጀሮ፤ “እንዴ ዓለም ያወቀውን ነገር?! በእርግጥም አንዳፍታ መልሰህ ብትወስደኝኮ፣ ከፍራፍሬዎቹ መካከል ያስቀመጥኩበትን ቦታ አሳይህ ነበር፡፡”
አዞ፤ “ወይ አቶ ዝንጀሮ! በጣም ደግ እንስሳ ነህ አንተ!” አለና ይዞት ወደ ጫካው መመለስ ጀመረ፡፡ እንዲያውም ልብ ለማግኘት በጣም  ስለጓጓ፣ ከቅድሙ በጣም ፍጥነት ጨመረ፡፡ ‘በቃ ሚስቴ የዝንጀሮ ልብ ልታገኝ ነው -አረፍኩ!’ አለ ሳያውቀው ጮክ ብሎ፡፡
ከወንዙ ዳርቻ ሲደርሱ ግን ዝንጀሮ ሆይ፣ ከአዞው ጀርባ ተፈናጥሮ ዘሎ መሬት ዱብ አለ፡፡ ከዚያም፤
“አንተ ጅል ሽማግሌ አዞ! ለመሆኑ በየት አገር ነው ‘ዝንጀሮ ልቡን ጫካ ያስቀምጣል’ ሲባል የሰማኸው?” ደግሞ ባስቀምጥስ ናና ስረቀኝ ብዬ የማሳይህ ይመስልሃል? አየህ አንተ ግዙፍ ነህ፣ ጠንካራ ነህ፣ ኃይለኛና ሁሉን የሚቆራርጥ ጥርስ ያለህ ነህ፡፡ ሆኖም አንጎል የለህም፣ ልብ የለህም፡፡”
ዝንጀሮ ይህን ብሎ ወደ ጫካው እየበረረ ተሰወረ!
***
ልብ ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ልብ መግዛት የሚችል ደግሞ ጥሞና ስክነትና ብልህነት ያለው ነው። በአጉል ድፍረትና በጉልበት የሚመጣን ኃይለኛ ሰው፣ ብልሀት ያለው አነስተኛ ሰው በቀላሉ ይረታዋል፡፡ በሙሉ ልብና በስክነት የተሰላ የጊዜ፣ የቦታና የተግባር ቅንጅት ካለ አገር ታድጋች፡፡ ህዝብ ይጎለብታል። ማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ድርጅት አሊያ ግለሰብ ደህና ልብ ካላገኘ ህዝባዊ አደራን በአግባቡ አይጠብቅም፡፡ ጉልበተኝነትን ከብልህነት ይልቅ ይመርጣልና የበታቾቹን ሁሉ ለመጉዳት ይነሳል፡፡ የዚህ ዓይነቱ መሪ፣ ኃላፊ ወይም የበላይ አለቃ እንደ አዞው በእጁ የገባውን ልብ ጭምር ያጣል፡፡ የፎከረበትን ያፍርበታል፡፡ በስንት መስዋእትነት የተገኘውን ድል እንደ አዞው ሁሉ እርባና - ቢስ ያደርገዋል፡፡
በሀገራችን የተካሄዱ ለውጦች ሁሉ፣ የተካሄዱ እንቀስቃሴዎች ሁሉ፣ የተደረጉ ጦርነቶች ሁሉ የሚጠቁሙት አንድ ቁምነገር አለ፡፡ ሁሉም አሳይቶ - የመንሳት (Missed opportunity) መንገድን ያመላከቱ እንጅ ድልን ያስጨበጡና በእጅ ያቆዩ አይደሉም፡፡ በሰላም በክብ ጠረጴዛ ለሚያልቅ ጉዳይ ሁሉ ጦር ይመዘዛል፡፡ ከሩቅ ያነጣጠሩበትን ባላንጣ በመቀየም ሰበብ ቅርብ ያለውና ልንሰራበት የምንችለው እድል ያመልጣል፡፡ በጊዜያዊነት ስልጣን ላይ የወጣ ዘለዓለማዊ ነኝ ብሎ ተደላድሎ እስኪቀመጥ፣ በኩርፊያ ጊዜና ቦታ እንዲያመቻች እንፈቅድለታለን፡፡ ከመደራደር ይልቅ መግደርደርን በመምረጥ፣ ተገቢው ሰው በተገቢው ቦታ እንዳይቀመጥ አጋጣሚውን እናባክናለን፡፡ ፓርቲና ፓርቲ መክረው ዘክረው፣ ልብ ገዝተው፣ አቅም አበጅተው፣ ለለውጥ እንዳይሰለፉ እርስ በርስ ሲታኮሱ ለበያቸው ሲሳይ ይሆናሉ፡፡ በፍጭቱ ውስጥ ቀንቶት ሥልጣን የያዘውን ሁሉ እንደትክክለኛ፣ በለስ ያልቀናውን ደግሞ እንደ ስህተተኛ እየቆጠሩ ቢያንስ በሀሳብ ደረጃ እንኳ ርቱዕ አቅጣጫን አለመያዝ አሳዛኝ ነው፡፡ በወህኒ ፀፀት በስተቀር ደጅ በህይወት እያሉ ስህተትን ማረም ተችሎ የሚያውቅ አይመስልም፡፡
በዘላቂነት አሳይቶ-ነሳን የማለት እሮሮ በቀር ተዘጋጅቶ የመጠበቅ፣ አስቦ የመንቀሳቀስ፣ አጋጣሚን ሲሆን ቀምቶ፣ ካልሆነም የተገኘውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ለአገር የሚበጅ ነገር መሥራት አልለመድ ያለ ነገር ሆኗል፡፡ ይሄኛው አንዱ ገጹ ሆኖ፤ በሌላ በኩል ደግሞ “አታስገባኝ እንጂ ውጣልኝ ማለትስ ያስቸግርሃል” እንዲል መጽሀፍ፣ አንዴ የገቡበትን ነገር ስህተትም ቢሆን አቋሜን በጭራሽ አልለቅም ብሎ ሙጭጭ ማለት ፍፁም የተለመደ ተግባር ሆኗል፡፡ ያም ሌላው ኪሳራ ነው፡፡ አሳይቶ - ነሳኝ የማለት የፀፀተኝነት ባህል እንደ ድርቅ በተደጋጋሚ እየመታን፣ መንግስት በተለወጠ ቁጥር “የት ይደርሳል የተባለ ባህር ዛፍ ቀበሌ ቆረጠው!” ስንል እንከርማለን፡፡ አጋጣሚን በጊዜ፣ አጋጣሚን በቦታ፣ አጋጣሚን በንቃት ተጠንቅቆ ማየት፣ ሌላ ዕድል ያለማበላሸትን ዋስትና ያስጨብጣል፡፡
ያም ሆኖ አጋጣሚዎች ሳይመቻቹ፣ ህሊናዊና ነባራዊ ሁኔታዎች ሳይበስሉ፣ የተደከመበት ፍሬ መጎምራት ቀርቶ ለዐይን እንኳ ሳይጠጥር፣ ባልተባ ልሳን ዘራፍ ቢል፣ “የማይበላ ንፍሮ ሳይፈለፈል ይበስላል” ሆኖ ቁጭ ይላል ነገሩ ሁሉ፡፡ ከጧት የተማሪ እንቅስቃሴ ስሜት፣ ከረፋድ ሰክነት-አልባ የፓርቲ ንቅንቄ፣ ከከሰዓት በኋላው የትጥቅ ትግል ትኩሳት ሳንላቀቅ፤ በሥራም፣ በፖለቲካም ኃላፊነት ላይ ከተቀመጥን የበሰለውን ጥሬ እናደርጋለን፡፡ የእጃችንን ፈልቅቀው እንዲወስዱብን በር ከፍተን እናስገባለን፡፡ የዐይናችን አፎት ይጠብቅና ያየነውን እንዳላየን እንሆናለን፡፡ ከህዝብ የምንሸሽገው ይበዛል፡፡ እንደተማሪነት ስሜታዊነት ይጋልብብናል። ብስለት ሳይሆን ድፍረት ይፀናወተናል፡፡ አገር ሙሉውን ደክሞ ያፈራውን ምርት፤ ያዘመረውን አዝመራ፣ አንጡራ ሀብታችንን ቅርሳችንን ሁሉ በአንድ በመከራ የቆየችውን ሀገር በህልውና ማቆየት ከፍተኛ ኃላፊነት ነው፡፡ አለበለዚያ “ተጨንቀው ያመጡትን ዕንባ ዝንብ ይልሰዋል” ነውና ነገረ-ሥራችን ሁሉ፣ ወልዶ አሳድጎ ለባዳ ይሆናል፡፡ እንደ ዝንጀሮይቱ ‘ልቤን ጫካ አኑሬው ነው’ ማለቱ ብቻ ልብን አያድንም! ገጣሚው እንዳለው፡
“ይልቁንም አለ አንድ ሀቅ
የነገውን ነገ ነው የሚያቅ፤
ጭብጥ እንዳይፈለቀቅ
የያዝነውን እንዳንለቅ
ሻካራ እጅን ብቻ ሳይሆን፣ ልብንም ጭምር ነው ማጥበቅ!”



Read 1960 times