Sunday, 27 August 2023 19:38

ሰይጣንና ፈጣሪው

Written by  ኪሩቤል
Rate this item
(2 votes)

--እውነቴን ነው ፈጣሪዬ… የዚህን ሀሳብ ሚስጥር የሰው ልጅ ቢረዳው፣ የምድር መልክ ይቀየራል ብዬ አስባለሁ፡፡ አንዳንዴ ሀሳብ ግብት ይለኛል፡፡ በየሚዲያውና በየቅዱስ ስፍራዎች ውስጥ የሰው ልጆች ሰይጣናቸውን ሊያስለቅቁ ሲሄዱ አያለሁ፣ ደብተራዎች በየገደሉ እየተተራመሱ እፅዋቶችንና እንስሶችን እየሰበሰቡ ይሰዉለታል--“

ዛሬ ለነፍሴ ልገብርላት ያሻኝ እውቀት አለና፣ መልስ ፍለጋ ባለቤቱ ጋ ደርሼ መማጠኔን ጀመርኩ፡፡ ፈጣሪዬ ሆይ… ከፈጠርካቸው ፍጥረታት መካከል፣ በብዙ የሀይማኖት መፅሀፍት ውስጥ ካንተ እኩል ስሙ ስለሚጠራለት፣ ካንተ እኩል በምድር ገፅ ላይ ገድሉ ስለሚዘከርለት፣ ካንተ እኩል ካልሆንኩ ብሎ ከዙፋኑ ስለተወገደው… የእጅ ስራህ ስለሆነው…አዎ… ስለ ሰይጣን ልጠይቅህ ነው የመጣሁት፡፡
ስለ ሰይጣን ማጥናት የፈለኩበት ቀን ትዝ ባይለኝም…ብላቴና ሳለሁ ቤተሰቤን ጨምሮ ስለሱ እኩይ ተግባራት እየተነገረኝ ነው ያደኩት። ካንተ ጋርም እንደተጣላችሁና እስካሁንም እንደማትነጋገሩ ነው የማውቀው፡፡ ከዚህ ቀደም ይህን ጥያቄ ጠቆም አድርጌልህ ቢሆንም፣ አሁንም ደግሜ ላነሳው ወደድኩ፡፡ ሰይጣንን ማነው ከዛ ክብሩ እንዲወድቅ የመርገምት ሀሳብ የጨመረበት? የሚለው ጥያቄ ሁልጊዜ ሚስጥር እንደሆነብኝ ነው፡፡ በራሱ ሀሳብ የሚሳሳት ፍጥረት አለ የምንል ከሆነ፣ በቀጥታ ጥያቄው ሊሆን የሚችለው ማነው እንደዚህ የሀሰትና የግብዝነትን ባህሪ  ከቶበት የፈጠረው? የሚል ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ትንሽ ይቆየኝና ቅደም ተከተሌን ጠብቄ ጥያቄዬን ላፍስስ፡፡
ፈጣሪዬ ሆይ… ለመሆኑ ሰይጣን የሚሉት ፍጥረት… የሰው ልጅን በምንነቱ ላይና በፍላጎቱ ውስጥ መሰልጠን የሚሻው ይህ ፍጥረት፤ ለመሆኑ መቼ ነው የፈጠርከው? ነገራት ከመከሰታቸው በፊት ቀድመህ የምታውቅ…የእውቀቶች ሁሉ መሰረት የሆንከው አባቴ ሆይ… ምን እና እንዴት እንደሚያስብ እያወከው ይሆን ሰይጣንን የፈጠርከው?
ስለዚህ ፍጥረት በጥልቀት ከማውራቴ በፊት መች ላይ በሀሳብህ ውስጥ እንደተከሰተ ላውቅ ይገባኛልና እጠይቃለሁ፡፡
ካንተ እና ባንተ ሀሳብ ውስጥ ብቻ ተፈብርከው የሚፈጠሩትን ፍጥረታት በሙሉ ጊዜ ሰጥቼ ማሰላሰሌን እወደዋለሁ፡፡ ክብርህንና ሀይልህን የሚገዳደር ሊገኝ ይችላል ብዬ ባላስብም…ስለዚህ ሰይጣን ስለተባለው የእጅ ስራህ ሳስብ ግን ብዙ አይነት ሀሳቦች በጭንቅላቴ ይመጣሉ። ልጠይቃቸው የምፈራቸው ማህበረሰቦችም እንዲሁ በእጅ ስራህ ላይ ሲወያዩ አድምጫለሁ። የቻልኩትንም ያህል ለማንበብ ሞክሬያለሁ…
ሰይጣን በምድር ላይ የሚከሰቱ ጥፋቶች ሁሉ መሰረት ነው ይላሉ፡፡ የሰው ልጅ እስካሁን ድረስ የሚፈልገውን እንዳያደርግና ዘላለማዊ ሞትን እንዲሞት ያደረገው ያ … አመፀኛው መልዓክህ እንደሆነ ያወራሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ሰይጣን በህይወት ያለና ቅርፅ ያለው ፍጥረት ሳይሆን፤ የሀጥያት ሀሳብ (የሰው ልጅ የወደቀው ሀሳቡ) ምሳሌም ነው ይላሉ፣ ዞር ስልም ሰይጣን የሰው ልጅ ክፉና ደጉን እንዲያውቅ የረዳና ከመሃይምነት ጎዳና ያዳነው ብቸኛው የአመፃ ጉልበታችንም ነው የሚለኝም አላጣም…ባስም ሲልም ደግሞ ሰይጣን የሚባል ፍጥረት የለም፤ የምድር ላይ ሰይጣን የሰው ልጅ ነው የሚል ይመጣል፡፡
እውነቴን ነው ፈጣሪዬ… የዚህን ሀሳብ ሚስጥር የሰው ልጅ ቢረዳው፣ የምድር መልክ ይቀየራል ብዬ አስባለሁ፡፡ አንዳንዴ ሀሳብ ግብት ይለኛል፡፡ በየሚዲያውና በየቅዱስ ስፍራዎች ውስጥ የሰው ልጆች ሰይጣናቸውን ሊያስለቅቁ ሲሄዱ አያለሁ፣ ደብተራዎች በየገደሉ እየተተራመሱ እፅዋቶችንና እንስሶችን እየሰበሰቡ ይሰዉለታል፤ ለዚሁ ፍጥረት ቤተ መቅደስ ገንብተው የሚሰግዱለትና የሚያሰግዱለትም አሉ፤ ሌሎቹ አለምንና በውስጧ ያሉትን የፈጠረው ራሱ ሰይጣን ነው ብለው ያምናሉ ይሰብኩትማል፡፡ በሰይጣን ስም ተብሎ የተደረገ ጦርነት ማንበቤ ትዝ ባይለኝም፣ የጦርነቶች ሁሉ መሰረት እንደሆነ ታምኖ በሀይማኖት ሰዎች ይገዘታል፡፡ በምድር ላይ የሚጠላው…የሚሸሸውና የሚፈራው ቁጥሩ የትየለሌ ነው፡፡
ይህን የሚናገሩት አብዛኞቹ ልክ አንተን በአይን እንዳላዩህ ሁሉ እሱንም አየሁት የሚለን የለም፡፡ ሰዎች ከመደበኛው ባህሪያቸው ውጭ ሆነው በየቅዱስ ስፍራው ሲንፈራፈሩ እና ገፀ ባህሪያቸው ተቀይሮ ሌላ አይነት ማንነት ተሞልተው እንግዳ ነገራቶችን ሲያወሩ ተመልክቻለሁ፡፡ ሆኖም ለምን የሚለው ጥያቄ ይመጣብኛል፡፡ ለምንድነው ሰይጣን ይህን የመሰለ ባህሪ ሊይዝ የቻለው? ያን ሁላ ዘመን አብሮህ ሲኖር እንዴት ሆኖ ነው አንድስ ጥሩ ነገር እንኳን ተምሮ መተግበር ያቃተው? ከውድቀቱስ በፊት ታማኝ አገልጋይህ ስለመሆኑ እና ይሰራቸው ስለነበሩ ጥሩ ተግባራት አንዳችም ስለምን አልተፃፈም?
ምንም አይነት ፍጥረት በፈጣሪው ፊት አላዋቂና ጥበብ የሚያሻው እንደሆነ ነው የሚገባኝ፤ ሆኖም ለሰይጣን የተሰጡት የተለያዩ ትረካዎች ጥያቄን የሚያጭሩ ሆነው ነው ያገኘኃቸው፡፡ ለምን አታጠፋውም እና እኛ በሰላም አንኖርበትም እያልኩ፣ እንደሌሎቹ ጠያቂያን ያሰለቸህን ጥያቄ አልጠይቅህም…
ሆኖም ይህ ፍጥረት… በተደላደለው ክብርህ ስር የተገዛ፣ ጥበብህ ከሚፈስበት ዙፋንህ ጎን ሆኖ በእውቀትህ የሰከረ፣ አለማቶች ላይ ላሉት መላዕክት ገዢ ተደርጎ የተሰራ፣ በቅዱስ መፅሀፍ ውስጥ ብርሀን አምጪነቱ የተተረከለት…የፍቅርህን ስፋት ማንም ካየው በላይ ተመልክቶ እና ኖሮት ለመገኘቱ ምክንያቱ አድርጎ ይኖር የነበረ ፍጥረት… እንዴት አድርጎ ነው ድንገት ብድግ ብሎ አንተን ካልሆንኩ ማለት የፈለገው? የምሬን እኮ ነው ፈጣሪዬ…እኛ እንኳን ሳናይህ በሰናፍጭ እውቀታችን ክብርህን ልንመሰክር ዘላለም የማይበቃን መስሎ የሚታየን ፍጥረቶችህ፣ በዚህ እውቀት ውስጥ ሆነን ስንፈራህ…ግርማህ የት ድረስ እንደሆነ እና የጥበብህ ልክ በራስህ ካልሆነ በማንም እንደማይተረጎም አጥብቆ ይረዳው የነበረው የእጅ ስራህ ሰይጣን…እሱ ደግሞ ምን ያህል ይፈራህ የነበረ ይሆን?
በዚህ ፍጥረት ላይ ያንተ እውቀት ያሻኛል፡፡ ለመሆኑ ለኛ ሰጥተህናል እንደተባለው ሰይጣን የራሱ ነፃ ፍቃድ ነበረው? ከነበረው ራሱ ምን ሊያደርግለት? አንተ አጠገቡ ካለህ ሌላ ምን ሊፈልግ ይችላል? የእውቀት ፍፃሜ እንደሆንክ እያመነ፣ አንተን ቢሸሽ የትም እንደማይደርስ እየተረዳ እንዴት ሆኖ ነው በእንዲህ አይነት ተራ ሀሳብ ውስጥ ራሱን ጥሎ ያገኘው? ራሱን ያውቀው ነበር? ሰይጣን ሆኖ እንደተፈጠረ ይረዳው ነበር?
ሳደምጠውና ሳነበውም የነበረው ታሪክ በዚህ አያበቃም፡፡ ከዛም ረግመህ ከዙፋንህና ከክብሩ እንዳበረርከው ነግረውኛል፡፡ ከዛም ባለፈ እስካሁኗ ደቂቃም ድረስ እንዳኮረፍከውና እንደምታሳድደውም አድምጬ ተረድቻለሁ። እሱ የደረሰበት የሰው ልጆች እንዳይደርሱ የሚሰብኩም ብዛት ያላቸው መንፈሳዊ ሰዎችንም አስነስተህበታል፤ እሱንም እየተፋለሙ ህይወታቸውን ሰውተዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ላጠፋው ጥፋት ይቅር ስላላልከው ብቻ ነው። በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍጥረትህ ጋር ስትጣላ ከሱ ጋር አሀዱ ብለህ እንደጀመርክ የሚዘክር ድርሳንም አንብቤያለሁ፡፡ የቱ ነው ትክክሉ? የሚሉት ነገር ውስጥ ቁምነገር አግኝተህበታል? የእውነት አሁንም ድረስ የሰው ልጅ ከሰይጣን ለመራቅ በመታገል ነው ህይወቱን ጀምሮ የሚጨርሳት? እንደዛ ከሆነ ሰይጣንም የሰው ልጅም የሚያርፉት መቼ ነው? አንተስ ራሱ እረፍትህና ምኞትህ ይሄው አይደል?
ለመሆኑ ይቅር በለኝ ብሎህ ያውቃል? ደክሞት አሳርፈኝ ያለህ ቀን ይኖር? ወይስ ፈፅሞ አልተጣላችሁም? ስሰማም የነበረው ነገር በሙሉ ውሸት ነው? እንዴት ሆኖ የይቅር ባይነትን መንፈስ ለሰው ልጅ ነፍስ የሚያድለው ፈጣሪዬ ከመጀመሪያ ስራው ጋር ተጣልቶ እስካሁን ይቅር አላለውም ብዬ ልመን? አያሳዝንህም? የእውቀቱ መቀጨጭ ያመጣው የስንፍና ሀሳቡን ተመልክተህለት እንዴት ይቅር አላልከውም? ምንም እንደማያመጣ እያወቅህ፣ እንደ እኩያ ባላጋራ አድርገህ እንዴት ልትመለከተው ቻልክ? የፈጠርካቸው የሰው ልጆችስ ከዚህ ምን ሊማሩ ይችላሉ ብለህ ታስባለህ?
ባህሪህን መስሎ ለመኖር የሚመኘው የምድር ላይ ልጅህ ከይቅር ባይነቱ ውጭ ሆኖ ዘላለማዊ ቁጣን በጭንቅላቱ ቢያመርት አታዝንበትም? ምድር ላይ ሳለሁ የሰራሀቸውን በሙላ ማፍቀር እፈልጋለሁ፡፡ በቀናት ድማሬ ውስጥ የማከማቸውን ባንተ ላይ ያለኝ እውቀቴን ሳልጠራጠር ነው ማመን የምፈልገው፡፡ ስለዚህ የጌቶች ጌታ የሆንከው መልስልኝ…የምር ለዘላለም ይቅር ሳትል መኖር ትችላለህ? የገዛ እጅ ስራህን በቁጣ ውስጥ ሆነህ ዘላለም ታሳድደዋለህ? በፍቅርና በጥበብ የሰራኸው ድንቅ ስራህን እንዳልፈጠርከው አድርገህ በፍጥረቶችህ መካከል ታዋርደዋለህ? ከህሊና በላይ የሆነው ፍቅርህ ውስጥ የትኛው ፍጥረት ቢሆን ነው ቁጣን አጭሮብህ ዘላለም ተናዳጅና አሳዳጅ ሊያደርግህ የሚቻለው?
ሰይጣን ምድርን እንዲገዛት ተሰጥቶታል ይሉኛል፣ በከፈትክለት ነፃ ፍቃድህ ውስጥ ሰርጎ ገብቶ ከሰዋዊ ዙፋንህ ያስወግድሀል ይሉኛል፡፡ ልጆችህን አድኖና አስቶ ነፍሳቸውን ወደ ሲኦል ይዞ እንደሚበር ነው የተነገረኝ። ሆኖም እኔ ይህን እጠይቃለሁ… ነፍሴ ራሱ የማናት? የኔ ልላት የሚቻለኝ ስፈጥራት ነውና …ሰርቼ ያላገኘሁትን ነገር እንዴት የኔ ነው ልልስ ይቻለኛል፡፡…ነፍሴ ከፈጣሪዬ የተሰጠኝ የፈጣሪ መልክ እንደሆነ ነው የምረዳው፡፡ ታዲያ ይህች እኔ ያልፈጠርኳት… ከዛም ባለፈ የፈጣሪዬ አንድ ክፍል ናት ብዬ የማስባት ነፍሴን ይህ ሰይጣን የተባለው ፍጥረት ይዟት የት ሊሄድ አስቦ ነው? እያሳደደ ያለው፤እኔን ሳይሆን አንተን ይሆን? ሲጀመር የኔ ነፍስ ያንተ አካል ከሆነች እንዴት ሆኖ ነው ሰይጣን ባንተ ድንቅ ስራና ማንነት ላይ ስልጣን ሊኖረው፣ ሊያዝና ሊወስን የሚቻለው? እንዴትስ ባለ ጥበብ ነው በኔ ጭንቅላትና ነፍስ ውስጥ መግባትና ማደር የተቻለው? ይህን እውቀቱን ከየት አመጣው? ክብሩንስ ስትወስድበት እንዴት ድንቅ ስራህን የሚያኮላሸው እውቀቱን አልሰለብክበትም? ስለምን ካንተ አሽሽጸኸው አንተን በሚያወድሰው ህዝብህ ላይ ወረወርከው?
ለመሆኑ ሰይጣን የሚኖረው የት ነው? እኔ ጭንቅላት ውስጥ ነው? በአየሩ ላይ ነው? ከምድር ሰርጥ ውስጥ ነው? በእንስሳትና እፅዋት ውስጥ ነው? ለመኖርስ ምቾት የሚያገኘው ከየትኞቹ ውስጥ ነው? በአሁን ላይ ሁሉም ቦታ የምትገኘው ፈጣሪዬ ሆይ… እነዚህን ሀሳቦች ሳስብ የሚመጣብኝ ጥያቄ አለ…፡፡ የእውነትም አንተ ሁሉም ቦታ ከሆንክ ሰይጣን የት ስፍራ ኖሮት ስራውን መስራት ቻለ? አንተ የእያንዳንዳችን ነፍስ ላይ ዘላለማዊ ስልጣን ካለህ ሰይጣን በእንዴት አይነት ብልሀት ነው ማደሪያህን ተቆጣጥሮ ፍልስፍናውን መዝራት የሚችለው? በአንድ ሰው ጭንቅላት ውስጥስ እንዴት እያደረጋችሁ ነው አንዱ ሲወጣ አንዱ ቦታውን እንዲወርሰው እያደረጋችሁ ያላችሁት? የራሳችን ማብቂያ የሌለው ፍላጎታችን የፈተና እስር ቤታችን ሆኖብን ሳለ ስለምን ሀያሉ መልዓክህ የነበረውን ለኛ መፈተኛ ብለህ ላክብን? ወይ እኛ እንድናርመው አስበህ ይሆን? ወይስ ደግሞ አይቶን ከስህተቱ እንዲማር?
ለኔ ሲገባኝ ስንወለድም ሆነ ስንፈጠር መጥፎና ጥሩ ብለህ ፈርጀህ እንደማትፈጥረን ነው የምረዳው፡፡ ሰይጣንንም በዚሁ መልካም ሀሳብ ውስጥ አድረህ በቅድሚያ እንደፈጠርከው አልጠራጠርም፡፡ ሆኖም የሰው ልጅም ሆነ ሰይጣን ከፈጠርከው በኋላ እረፍት እስኪነሳህ ድረስ ከስርዓትህ ውጭ ለመውጣት መታገል ውስጥ ገባ…አንዱ ካንዱ ጋር እያበረ፣ የትግስትህን ልክ መገዳደሩን ተያያዘው፡፡ አምላኬ ሆይ…እንዴት ሆኖ ነው ከፍጥረቶችህ ሁሉ አርቅቀህ የሰራሀቸው ድንቅ ስራዎችህ አንተን በማስቀየም ስራ ውስጥ ዘወትር ተጠምደው የምናያቸው? የተዋበው ስራህ ምንስ ቢገጥመው ነው የክብርህ ነጣቂ ለመሆን ጊዜ ያልፈጀበት? ሀያሉ ክንድህ በአንድ ጊዜ ጥፋትን ማውደም ሲችል እንዴት አድርጎ ነው ሰይጣንን እስካሁን ታግሶ ያቆየው? ወይ ከነአካቴው አልፈጠርከው ይሆን? ምናልባት ሰይጣንን የፈጠርነው እኛው የሰው ልጆች እንሆን?
ብዙ ነብያቶች ይህንኑ ፍጥረትህን ታግለው አልፈዋል፡፡ ብዛት ያላቸው የሀይማኖት ፈጣሪዎች ይህን ፍጥረትህን ጥላቻ ለሰው ልጆች ካንተ የተላከ ባሏቸው ህግጋቶች አስረው ለማስቀመጥ ብዕርን ከብራና አዋደዋል…ሆኖም የሰው ልጆች ሲያልፉ ሰይጣን ግን ስራውን እየሰራ፣ ግዛቱን እያስፋፋና በኑሮና በገዛ ፍላጎታቸው የወደቁትን ነፍሳት እየሰበሰበ ከርሱን እየሞላ ነው፡፡
ክቡር የሆነው ትዳር አሁን ላይ መላቅጡ ጠፍቶ በባሰ ሁኔታ የማንነት ቀውስ ያጠቃቸው ህፃናት የሚያድጉበት ምድር ሆናለች፣ ስነ ጥበቡ ውስጥ የጎላ ስፍራ ያላቸው የጥበብ ሰዎች የሰይጣንን ጉልበት ለመላው አለም በኩራት መስበክ ላይ ናቸው፡፡ ሰባኪያኑ በዝሙትና በንዋይ ፍቅር መንፈሳቸውን መርዘውታል? ከጥንቱ በባሰ ሁኔታ ንፁህ ሰው እየሞተ ነው፣ ቃልህን የሚሰብኩት የቅዱስ መፅሀፍት አዋቂዎች፣ ከበፊቱ በባሰ ንውርናቸው በድፍረት የተደገፈ ሆኖ ደረታቸውን ነፍተው መናፍቅነታቸውን ይሳበካሉ፣ ከሰዶምና ጎሞራ በላይ የሆነ እርኩሰት በየደቂቃው በምድራችን ላይ እየተፈፀመ ነው፣ ገንዘብ አምላክ ሆኗል…ሰውን መግደል ከጥንቱ በከፋ ሁኔታ የጀብድነትን ትርጓሜ ይዞ ቁጭ ብሏል…ሁሉም ነገር በየቀኑ ጨለማና ሞት ብቻ ሆኗል፡፡
ይህ ሁላ በሰይጣን ምክንያት የተፈፀመ ነው፣ ነው የምትለኝ አምላኬ ሆይ? ይህ ሁሉ መከራ በገዛ እጅ ስራህ የተፈፀመብን በደል ነው? የማያቆም የሚመስል…ተስፋን አውድሞ በፍርሀትና በሞት መካከል ውስጥ አድርጎን በአንድ አይናችን አጮልቀን፣ ህይወትን በጭላንጭል እንድናያት የሚያደርገን…ይህ ሁሉ ጉድ …ይህ ሁላ መከራ በሰይጣን የመጣ ነው የምትለኝ ፈጣሪዬ? ወይስ የሰው ልጅ መልካም ሆኖ መኖር የማይችል…የፍቅር መካን የሆነ ፍጥረት ነው? ወይስ እንደተባልነው ባንተ አምሳያ የተፈጠርነው ፍጥረቶች እኛ አይደለንም?
ይህንን ሁሉ መከራ ያደረሰው እሱና ጭፍሮቹ ከሆኑ በዛ ሰዓት አንተ የት ነበርክ? የት ተደበክብን? የልጆችህን ለቅሶ እያደመጥክ መታገስ ከቻልክ፣ ለምን ቀድሞውኑ በእውቀት ማነሱ ምክንያት መሰናከል የጀመረውን ሰይጣንን አልታገስከውም ነበር? ብትታገሰው ኖሮ ማን ይጎዳ ነበር? የማናችንስ ሀጥያት ምንህን ቢጎዳው ነው ከጠላኸውና ከረገምከው ፍጥረትህ ጋር ዘላለም እየነደድን እንድንኖር የፈረድክብን? የእውነት ግን ፈጣሪዬ ሆይ… ያነድሀል ያሉኝ ቦታ ወስደህ ነፍሴን እንድትማግዳት የሚያስወስንህን እኩይ ሀጥያት ለመስራት የምድርስ ዘመኔ ይበቃኛል ብለህ ነው? እንዴት አድርገህ ነው በፍቅር የፈጠርከውን ፍጥረትህን ዘላለም ለመካድ ስልጣንህን የተጠቀምከው?
ብዙ የማይገቡኝም ሆነ ያልገቡኝ ነገሮች ስላሉ ነው፣ ባለቤቱን ልጠይቅ የመጣሁት፡፡ አባት አለኝ… መልሱን አይነፍገኝም ብዬ ነው ከደጀህ የቆምኩት፡፡ በሰጠኸኝ እድሜ ሰይጣናትን ከማሳድድ ይልቅ … የክብርህን ስፋት እስከ ሰጠኸህኝ እውቀት ድረስ ለማሰስ ባስብ ነው፣ ጉልበቴን በከንቱ ላለማድከም ምክርህን መሻቴ።
አንድ ጊዜ እውነትህ ይናገረኝና …ነፍሴ ፀጥ ትበል፡፡

Read 594 times