Sunday, 27 August 2023 19:09

የሚነጋ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ይነጋ ነበር ጭብጦዬን ስጡኝና ልብላ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

አንድ የአረቦች ጥንታዊ ተረት አለ፡፡
አንድ እጅግ በጣም የናጠጠ የሀብታም ቤተሰብ ውስጥ የተወለደ ልጅ ነበር፡፡ ወላጆቹ ከልጅነቱ ጀምሮ እጅግ አድርገው ያሞላቅቁታል፡፡ እሱ ጠይቆ እምቢ የሚባል ምንም ነገር የለም፡፡ ‘ግመሎች ግዙልኝ’ ሲል በመቶ የሚቆጠሩ ግመሎች ወዲያው ተገዝተው ይቀርቡለታል፡፡ ‘የምኖርበት ቤት ሰለቸኝ’ ሲል ሌላ ግቢ፤ ሌላ ህንፃ መገንባት ይጀመራል፡፡ ‘አጫዋች ይለወጥልኝ’ ሲል ያገሩ ድንክዬ ተሰብስቦ በል ከነዚህ መካከል ምረጥ ይባልና የፈለገው ድንክዬ ይቀጠርለታል፡፡ ት/ቤት ሄዶ አስተማሪ ካልተስማማው ያ አስተማሪ ወዲያውኑ ከዚያ ክፍል ይቀየርና ሌላ አስተማሪ ይመጣለታል፡፡
ልጁ እያደገ ሲመጣ የአውሬ አደን ያፈቅራል፡፡ አንድ ቀን አደን እንሂድ ይልና የቤቱን ባሪያዎች በሙሉ ወደ ጫካ ይዞ ይሄዳል፡፡ ከዚያም
“በየአቅጣጫው ሄዳችሁ አድኑ፡፡ ከዚያም የገደላችሁትን አውሬ ወደዚህ ይዛችሁ ኑ፡፡ ብዙ አውሬ ላመጣ ጀግና አባቴ እንዲሸልመው አደርጋለሁ፡፡” ይላል፡፡ ሁሉም ይሰማራሉ፡፡ ልጁም ማደኑን ይቀጥላል፡፡ በመካከል አንድ ዱኩላ ከሩቅ ይመለከታል፡፡ ልጁ ያነጣጥራል፡፡ እንደአጋጣሚ ግን ዱኩላው ከሌላ አቅጣጫ በተተኮሰ ጥይት ይመታና ይወድቃል፡፡ ድኩላውን የገደለው ከባሪያዎቹ አንዱ ኖሯል፡፡ ግዳዩን ተሸክሞ ይዞ ሊያስቆጥር ይመጣል፡፡ በእለቱ ብዙ አውሬዎች ከገደሉት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ነባር ባሪያ ነው፡፡ የሀብታሙ ልጅ ግን እጅግ ብግን ብሎ ተናዶ ከዚያ ጫካ ወጥቶ ወደ ቤቱ ተመልሶ ሄዷል፡፡
ሁኔታው ግር ያላቸው ባሪያዎችም የገደሏቸውን አውሬዎች ተሸክመው ወደ ቤት ተመለሱ፡፡
የልጁ አባት አራስ - ነብር ሆነው ነው የጠበቋቸው፡፡ ባሪያዎቹ ገና እንደተመለሱ፤
“ለመሆኑ ከመካከላችሁ ድኩላ የገደለ ባሪያ ማነው?”
ዱኩላውን የገደለው ባሪያ ከመቀመጫው ተነስቶ፤
“እኔ ነኝ ጌታዬ ሆይ” አለ፡፡
ጌትዬውም፤
“ለመሆኑ ምናባክ ቆርጦህ ነው ልጄ ያነጣጠረበትን ዱኩላ የገደልከው?”
ባሪያው - “አይ ጌታዬ፤ የጌታዬ ልጅ ማነጣጠሩን አላየሁም፡፡ ለዚያም ‘በጫካው በየአቅጣጫው ተሰማሩና ብዙ የገደለ ይሸለማል’ ብሎ የጌታዬ ልጅ በሰጠን ትእዛዝ መሰረት ሁላችንም እየተሻማን ግዳይ ስንጥል  ነበር የቆየነው፡፡”
ጌትዬው  - “ቢሆንስ ታዲያ እርስ በርሳችሁ ተሻምታችሁ ግደሉ አለ እንጂ እሱ ያነጣጠረበትን ግደል ተብለሀል? ለመቀጣጫ 60 ጅራፍ ትገረፋለህ!”
ያም ባሪያ ሰው ሁሉ በተሰበሰበበት በዚያ ሞራ በጠጣ ጅራፍ ጀርባው እስኪላጥ ተገረፈ፡፡ ከዚያ በኋላም ጌታው እንዲህ አለው፤ “በል አሁን ለባሪያ ጓደኞችህ ከዚህ የጅራፍ ግርፍ ምን ትምህርት እንዳገኘህ ንገራቸው፡፡”
ባሪያውም፤ “ወንድሞቼ ሆይ፤ ለሁለተኛው ጌታችሁ ያነጣጠረበትን ኢላማ ሳታውቁ፤ በጭራሽ አደን እንዳትጀምሩ!!”
***
እኔ ብቻ ካላደረግሁት አይጥመኝም የሚል ጌታ አያድርስ፡፡
አለቃና ምንዝር፣ መሪና ተመሪ፣ አዛዥና ታዛዥ፣ ጠርናፊና ተጠርናፊ ልብ ለልብ የማይተዋወቁበት ስርዓት ብዙ ጥፋት ያደርሳል፡፡ በተለይም ኃላፊው እንደሀብታሙ ልጅ (የባለቤቱ ልጅ እንዲሉ) የጠየቀው ሁሉ - የሚፈፀምለትና ያቀደው ዕቅድ ሁሉ ትክክል ነው ይተግበርለት የሚባልለት ከሆነ፣ ዕቅዶች፣ መመሪያዎችና ፖሊሲዎች የበጎ ፈቃድ ውጤት እንጂ ተጨባጩንና ነባራዊውን ሁኔታ መሰረት ያደረጉ አይሆኑም፡፡ በተለይ የበላዬ ያነጣጠረውን ያላወቀ የበታች ሰው ወዮለት! መልካም ሰርቶ ምስጋናን ቢጠብቅ ጅራፍ ራቱ ነውና ጀርባውም ልቡም ይደማል፡፡ ከንቱ ምኞት ብቻ ነው ቀሪ ሃብቱ፡፡ አቅም የሌለው ሎሌ ቀና ሀሳብ ይዞ ቢነሳ ጌታህን ተጋፋህ ነው የሚባለው፡፡ መሪው ያቀደውን ሳይገነዘብ ተመሪው ኢላማ ላልም  ቢል ዳር የማይደርስበት ስዓት ውስጥ የእውር የድንብሩን የሚጓዝ ነው፡፡ መደማመጥና መረዳዳት ያለበት ሥርዓት አይሆንለትም፡፡ ግንኙነቱም “የባለቤቱ ልጅ” ያለው የሚደመጥበትና የሚሰራበት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ “ከጅራፉ ግርፍ ምን እንማራለን?” ከመባባል የታሪክ ምፀት በቀር ለሀገር ፋዳ ያለው ተግባር ለማከናወን አያስችልም፡፡
ከቶውንም የራሱን አቅም በአግባብ ሳይለካ “ትላልቅ ራዕዮች አሉኝ” የሚል ኃላፊ፣ አለቃ ወይም ማንኛውም የፖለቲካ መሪ፣ “መርፌ በቂጡ ያለውን ክር የሚጎትትበት አቅም ሳይኖረው ጨርቅ ለመውጋት ወደፊት ይገሰግሳል” የተባለው ዓይነት ነው፡፡ ከራዕዩ ጋር ሙጭጭ ቢል ከነራዕዩ ይሞታታል እንጂ ግዘፍ - የነሳ ተግባር ለማየት አይበቃም፡፡
የስራ ግንኙነቶች የመርህ ሳይሆኑ የአዛዥና የታዛዥ፣ “የገምጋሚ” እና “ተገምጋሚ” በሆኑበት አሰራር የተሰናሰለና የተቀናጀ የስራ ውጤት ይኖራል ብሎ መጠበቅ ከንቱ ድካም ነው፡፡ የበላዩ ሰው በልቡ ምን እንዳሰበ ሳይናገር፣ የላዕላይ - መዋቅሩ ቡድን የሚያወርደው ትዕዛዝ የደባ ያህል በሚስጥር የሚፈበርከው ከሆነ በአፈፃፀሙ ሰፈር ላይ ሽብር እንደሚፈጥር ግልጥ ነው፡፡ የበለጠ መከፋፈል የበለጠ አንጃ ይብስ የመሰነጣጠቅ አጋር የሚፈጥረው ግልጽነት - አልባ የሆነ የደባ ዳቦ ነው፡፡  የድብቅ አስራር ለህቡዕ ፓርቲ እንጂ ፀሀይ ለሚሞቅ ግብር (over-ground activity)፣ ለቢሮክራሲያዊ ተቋም፣ ለኮሚሽን ወይም ለንግድ ድርጅት የሚፈይደው ነገር ከአፍ የወደቀችን ፍሬም አያህል፡፡ ግልጽነት የሰፈነበት ስርዓት ለመመስረትና መልካም አስተዳደርን (Good Governance) ለማምጣት የማሴርንና የማድባትን ባህል ማስወገድ ዋና ስራ ነው፡፡ የባለቤቱ ልጅ ነኝና እኔ ያልኩትና ለብቻዬ ያነጣጠርኩት ኢላማ ይበቃል ማለትን ማስወገድም ሌላኛው ዋና ስራ ነው፡፡ የተቧድኖ ምስጠራን (Group Conspiracy) ማስወገድ ታላቅ ተግባር ነው፡፡ (ቢያንስ ጊዜው አልፎበታል፡፡)
“ብልት በሰራው ጥፋት ፍሬ ይቆረጣል” ይሏልና ኃላፊዎችና ዋና ዋና የተባሉ የፖለቲካ ሰዎች ባጠፉት ምንዝሮችና ዜጎች በግምገማም ሆነ በአማን-ዘራፍ መቀጥቀጥ የለባቸውም፡፡ ዝቅ ብሎ በቅርብ በሚሰራው ሥራ፣ ከፍ ብሎም በአገር ደረጃ በሚከናወነው ተግባር በዓይነተኛ ሁኔታ የሚበደሉት ጉዳዩ የማያገባቸው ከነገሩ ጦም እደሩና ጎመን በጤናን የሚያዘወትሩ ናቸው፡፡ በታሪክ የሚታየውም ይሄው ሀቅ ነበር፡፡
የማይቀርን ነገር ማወቅና የራስን አካሄድ ከመመዘን እንጂ ባላውቅ ይሻላል ብሎ መሸሽ ከቶም ግብዝነት ነው፡፡ ቢያንስ ራሷን አሸዋ ውስጥ ከደበቀችው ሰጎን የተሻለ ዘዴ ይጠበቅብናል፡፡ የምሁራን ሰፈር የእውቀት አምባ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የራሱን አገር ምሁራን የማያከብር አገር ከሌላ አገር ሊቃውንት ጋር ስለ ትምህርት ማሻሻያና ስለ አገር ብልጽግና ቢፈራረም፣ ከስር እየናደ ከላይ ይቆልላል የተባለው ዓይነት መሆኑ ነው ትርፉ፡፡ እርስ በርስ የማይተማመን አመራር በየስብሰባው ከመማማልና “ቃለ-ጉባኤ ድረሽ” ከማለት በቀር ለሀገር የበሰለ ገበታ ሊያቀርብ አይችልም፡፡ ለየራስ ጎጆ መውጫ ሙስናዊ ድርጎ ከመሰብሰብ በቀር፡፡ ይልቁንም ዓለም አቀፉን ሂደት በሚገባል አለማጤን፣ “ላም የሰጠኝ ወተቱንም ይለብልኝ” ብሎ እጅን መስጠት ተገቢ አይደለም፡፡ “ላይቀርልሽ ታጥበሽ ታጥነሽ በጠበቅሽ” እንዲሉ ከመደረግ የማይቀሩ ነገሮችን ሲሆኑ ከመጮህና ደንበር-ገተር ከማለት ከወዲሁ የማሰብና የመምከርን ጠቀሜታ አለማስተዋል አገርና ህዝብን ያጎሳቁላል፡፡ የተሻለ ነገር ይቀጫል፡፡ በሰፊ ምኞት ባህር ከመዋዠቅ በተጨባጭ የሚዳሰስ የሚነካውን ነገር አዳምጦ አጢኖ ይዞ መገኘት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡
“የሚነጋ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ይነጋ ነበር ጭብጦዬን ስጡኝና ልብላ” ብሎ እቅጩን ተናግሮ በጊዜ ተገቢው ቦታ ማደር ለሀገርና ለህዝብ ታላቅ ፋይዳ ያለው ቁም ነገር መሆኑን አለመዘንጋት ነው፡፡

Read 1620 times