Saturday, 12 August 2023 20:54

“በንግግር ቋንቋ ልደት ላይ፤ የበሳል ድርሰት ሞት” (በማወቅ ወይስ በአለማወቅ?)

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(1 Vote)

 ከአለማችን ሀገራት ኖርዌይ በልቦለድ ድርሰት ዘርፍ ዝናን ያተረፉ አያሌ ደራሲያን ከጉያዋ  ወጥተዋል፡፡ ዮናስ‘ሊ፣ ኤሌክስ አንደር ኪላንድ፣ አርኒ ሀርቦርግ፣ ሄነሪ ኢብሰን…የመሳሰሉ፡፡ የእነዚህ ገናና ደራሲያን የስነጽሑፍ ፈለግ በአብዛኛው የዳበረ ሀገር በቀል ቋንቋቸው ሳይሆን የተዋረሰ ድቅል የሚጽፉበት የንግግር ዘይቤያቸው እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ኖርዌይ ለስነጽሑፍ የምትጠቀምበት ቋንቋ የዴንማርክን ገዢ መደብ ቋንቋን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በ19‘ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የኖርዌይ ቋንቋ፣ “የንግግር ቋንቋ” ብቻ በመባል ይጠራ ነበር። ይህ ሁኔታ የኖርዌይን ህዝቦች ስሜት በጣም የሚነካና የሚያስቆጣም ነበር። በመሆኑም የኖርዌይ ምርጥ የፈጠራ ሰዎች በመሰባሰብ የኖርዌይን የስነጽሑፍ ቋንቋ ፈጠሩ። በዚህ የቋንቋ ፈጠራ ተግባር ላይ ከፍተኛ ሚና የተጫወተው ሄነሪ ኢብሰን የተባለ ታላቅ ደራሲያቸው ነው፡፡ በዚያው ዘመን ውስጥ ከኖርዌይና ከዴንማርክ የተውጣጣ አንድ የስነጽሑፍ ቋንቋ ተፈጠረ፡፡ በአንጻሩ  ደግሞ ሌሎች ደራሲያን፣ ያልበተረዘና ያልተከለሰ የኖርዌይ  ቋንቋ ያስፈልገናል ብለው ለብቻቸው  ጎራ ለዩ፡፡ በመጨረሻም  የመንግስቱና የሀገሪቱ የመግባቢያ ቋንቋ ከኖርዌይና ከዴንማርክ የተውጣጣ  “ሪክማሎም” የተባለ ቋንቋ ሆነ፡፡
…ይህን የታሪክ ሁነት መነሻና ተገን አድርጌ በንግግር ቋንቋ  ተጽፈው  ነገር ግን ስነጽሑፋዊ ብስለት እርቋቸው፣ በፈጠራ ድርሰት ስም እየተሞሸሩም - እየተጌጡም እንደ ጉድ የሚቀርቡልንን ስራዎች በገባኝ ልክ፣ በተረዳሁት መጠንና እንደ ንባቤ ወሰን…ለመዳሰስ ካሰብኩም-ካሰላሰልኩም ሰነባብቻለሁ፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በዝተውና ተንሰራፍተው፣ በመጻሕፍት ገበያውም ሰፊ ሽፋንን አግኝተው በመነበብ ላይ መሆናቸው በግልጽ ይስተዋላል፡፡ ይህም ለንባብ ተፈላጊ ከመሆናቸው በላቀ ለሽያጭም አጓጊ ህትመቶች እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቋሚ ነው፡፡ (ምናልባት ‹‹ጥሩ አንባቢ›› እንጂ ‹‹ብቁ አሳቢ›› እንዳንሆን ያደነዘዙን እነዚህ ይሆኑ?)
የንግግር ቋንቋ በተለምዶ በቃለምልልስ ለሚቀርብ ጽሑፍ ካልሆነ በስተቀር ለጥበባዊ ድርሰት አስፈላጊ ነው ተብሎ አይታመንም። (ደረጃውን ያወርደዋልና) ይሁን እንጂ እዚህ ዘመን ላይ አንድም በድፍረት፣ አንድም በእውቀት…በፈጠራ ድርሰት ሽፋን በእውቅ እየታነጹ  ለገጸንባብ  ማቅረብ ከተለመደ ሰንበትበት ብሏል፡፡ ደራሲና ተርጓሚ ሳህለስላሴ ብርሃነ ማርያም፣ “ፍኖተ ህይወት” በተሰኘ ግለታሪካቸው ውስጥ የ20‘ኛው ክፍለ ዘመን የአሜሪካ ደራሲያን በተራና በግልጽ የንግግር ቋንቋ በስፋት ይጽፉ እንደነበር አትተዋል። በዚህም እሳቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድረውባቸው እንደነበር ተርጓሚው እንዲህ ያስረዳሉ፤ … “ወጣት ይፍረደው የተባለውን ድርሰቴን የጻፍኩት በተራ የንግግር ቋንቋ መሆኑን ከዚህ ቀደም ገልጫለሁ፡፡ ይህ የሆነው በዚያን ጊዜ በስፋት የማነበው የአሜሪካኖቹን ስነጽሑፍ ስለነበርና ብዙዎቹም የአሜሪካ ደራሲያን በተራና በግልጽ ቋንቋ ይጽፉ ስለነበር ይመስለኛል፡፡“ (ገጽ.27) በርግጥ ሳህለስላሴ የበኩር ፈጠራ ስራቸውን በተራ የንግግር ቋንቋ ያጻፋቸው የንባብ አዎንታዊ ተጽእኖ ይሁን እንጂ፣ ከዚህ ባለፈ በትርጉምና በሌሎች ስራዎቻቸው የምንሰጣቸው የላቀ ቦታ ግን እዚህ ጥያቄ ውስጥ እሚገባ አይደለም፡፡ ….ወደዚህ ዘመን ስንመጣ ከፍ ሲል ለመጠቆም እንደሞከርኩት በድርሰት ስም በአዘቦት የንግግር ቋንቋ እሚቀርቡልን በአመዛኙ በተጽዕኖ፣ አሊያም ደግሞ ከንባብ ጉድለት ቢሆን እምብዛም ባልከፋ ነበር፡፡ ይሁንና  ንባባችን እሚነግረን እውነታ ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ዛሬ-ዛሬ በስነጽሑፋዊ የቋንቋ ብስለት ምዘና ስንሰፍራቸው ዘወትር ሚዛናቸው ቀልሎ፤ ከምን ወገን ለመመደብ እምንቸገርባቸውና ለመፈረጅም ቢሆን እሚያዳግቱን ስራዎች በቁጥር አያሌ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ተርታ መድበን ከምንጠቅሳቸው መካከል ለዛሬ በዚህ ቅኝቴ ለማየት የመረጥኩት፤ ምንም እንኳን  በቋንቋ ረገድ ደከም ያለ የንግግር ቢሆንም፣ የዘመኑንና የትውልዱን አንኳር ተጠየቃዊ ጉዳዮች በራሱ ሚዛን ላይ ሰፍሮ  በፍልስፍና መነጽር ከጊዜ አውድ አንጻር የሚመለከት፣ ዘመንን ታሳቢ አድርጎ አስተዋይ ትውልድ ለማፍራት የሚያስፈልጉ ማህበራዊ አንኳር ጭብጦችን በጥያቄ እያነሳ ለመፈተሽ  እሚሞክር ስለሆነ “አለማወቅ”ን መቃኘቱ ተገቢ ይሆናል፡፡
ጸሐፊው በሙያው የበቃ የስነልቦና እጩ ዶክተር ነው፡፡ ቀደም ሲል “አለመኖር“ የተሰኘ መጽሐፍ ጽፏል፡፡ “አለማወቅ“ የ“አለመኖር“ ቀጣይ ናሙና ነው ማለት ይቻላል፡፡ በንግግር  ቋንቋ ዘውግ ይዞልን የመጣው ስራውን  ጠቅላላ ጭብጥ  ያዋቀረው  በህክምና እና በስነልቦና ፍርግርግ የመሰረት ድልዳል ላይ ነው፡፡ ስራውን በአብዛኛው ህክምና አዘል አስተምህሮት አመዝኖበታል፡፡ ራስ ተኮር  ግላዊ የገጠመኝ ፍልስፍና ተጭኖታል፡፡ የህክምናው ሳይንስ በስነልቦና ፍልስፍና ላይ የበላይ ለመሆን የሚያደርገውን መፍጨርጨር በጉልህ እናይበታለን፡፡ ዶክተሩ፤ ድንቁርናን ከህክምና እና ከስነልቦና ባሻገር ከሰብአዊነትና ማህበራዊ እሴቶች አንጻር ይሞግታል፡፡ “አለማወቅ“ ከ“አለመኖር“ ጋር ያለውን ትስስር ይቃኛል፡፡…አዎ፣ በእውቀት ሀገር ይቆማል፡፡ በአለማወቅ ደግሞ ሀገር ይፈርሳል፡፡ በመሰረቱ እውቀት ቋሚ አይደለም፡፡ ቋሚ እውቀት የሚባል ነገር የለም፡፡ እውቀት ይበረዛል፣ ይከለሳል፡፡ ዞሮ-ዞሮ የትኛውም እውቀት መኖሪያ እንጂ ኑሮ አይደለም እንዲሉ ሊቃውንት፡፡ እንግዲህ እውቀት በጭንቅላት ውስጥ ያለ አስተሳሰብ ቢሆንም እንኳን፣ አለማወቅ ደግሞ ከሰው ልጅ ህይወት ጋር በጥብቅ የተሳሰረና በጥያቄም- በአንክሮም ሊመረመር የሚገባው ጉዳይ እንደመሆኑ፣ ድንቁርናን ለመጋፈጥ የራሱን ጭብጥ መዞ የተነሳ ብዕረኛ ነው- ዳዊት ወንድምአገኝ፡፡
ከልጅነት ወደ እውቀት በሚደረግ ሽግግር የምንማረው ዋና ነገር፣ ለጥያቄ መልስ ማግኘትን ሳይሆን ጥያቄ መዋጥን ነው…ሲል ስም አልባ ገጸባሕሪያትን መልምሎ ህይወትን፣ እውነትን፣ ፍትህን…እየጠየቀ ይዞ በሚያስጉዝ ስልት የተከተበ ስራ ነው፡፡ እናት (አባት የለም) ልጅ፣ ወንድ አያት፡፡…ልጅ ‹‹እኔ ማነኝ?›› የሚል  በአጥጋቢ የመልስ ጋጋታ የማይረካ  የለት ተ‘ለት ጥያቄ ውስጥ ናት፡፡ ልጅነቷና ወጣትነቷ ከትዝታዋ መሀል ተበታትነዋል፡፡ የጎልማሳነቷ ወግ ተዘባርቋል፡፡ የወላጆቼ ክስተት ሳልሆን ስህተት ነኝ ብላ ታምናለች፡፡ ማሰብ ማሰላሰልዋ፣ ጥያቄዎችዋ፣ መንገዶቿ ሁሉ ይሄንን አጉልተው ያስታውሷታል፡፡ የበቀለችበት ማህበረሰብ፣ የዘመኗ ርዕዮተ ዓለም ማንነቷን በምትፈልገው ልክ ስላልገነቡላት አብዝታ ትኮንናቸዋለች፡፡ አሳዳጊ ወላጆቿንም ደምራ እጇን ቀስራባቸዋለች፡፡ መጽሐፉ በጠቅላላ በልጅ እና በአያት  መካከል በቃለምልልስ መልክ የሚደረግ የማንነት ግንባታ ሂደት ነው። የማይገባትን ትኩረት አግኝታ ያደገችው ልጅ፣ ለረጋ ሳይሆን ለሰጋ ማንነት አጋልጧታል፡፡ የተወዛገበ  እና የተሳከረ የማንነት ጥያቄ ውስጥ ናት፡፡ (ማን ነበር፤ የህይወት አንዱ ውበት ያልተመለሱ ጥያቄዎች መሀል መገኘት ነው ያለው?) አያት የተምታታ ማንነት ለማስታረቅ አብዝቶ ይደክማል…“አየሽ ልጄ አንቺ አባትሽን ብታውቂና እናትሽን መልሰሽ ብታገኚ የማንነት ውዝግብሽ የሚመለስ ይመስልሻል፡፡ ልክ አይደለም፤ ማንነትሽ ይሄው ነው፡፡ የሰው ልጆች እየቆየን ስንቀየር ዘመን እየተቀየረ የሚሄድ ይመስለናል፡፡ ዘመን ግን ቋሚ ነው - ልክ እንደ ሰው፡፡ ዘመን በጊዜ ቋሚነት ላይ የተፈጠረ የሰው ልጅ ምናባዊ ፈጠራ ነው።“ (ገጽ.93) ህጻኗ ገና ከአፍላነቷ  መጻሕፍትን ጓደኛ አድርጋ  አሳልፋለች፡፡ ከአያቷ ጋር ስለ ብዙ የኑሮ ጉዳዮች ስትወያይም አድጋለች፡፡ ይህም ብዙ ነገር እንድታውቅ፣ እንድትጠይቅና እንድትሞግት አድርገዋታል፤ አስችለዋታል። በጥያቄና መልስ መካከል ‹‹ማሰብ›› የሚባል ጉዳይ አለ፡፡ ልጆች ብዙ ጊዜ ይህን አያውቁም፣ ወይም አይረዱም- ይዘነጋሉ፡፡ መልስ በቀላሉ የማይቀበሉትም ለዚህ ነው፡፡ ምላሹ አይጥማቸውም፣ ጥያቄ ይውጣሉ፤ ሌላ ጥያቄ ደግሞ ያስከትላሉ። በቃ ስታድጊ ይገባሻል! ልጅ አትረካም፡፡ የታሪኩ ዋና ግጭትና ፍጭት የሀሳብ እንጂ የድርጊት አይደለም፡፡ ቦታውንና ጊዜውን  ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ በርግጥ መጽሐፉ እግረ መንገዱን ሸጋ ሀሳብ ያነሳሳል፡፡ ቆም ብለን እንድናስብም ይጋብዛል፡፡ ይህ የማይካድና ሳይጠቀስ የማይታለፍ ጠንካራ ጎኑ ነው፡፡ ለአብነት በገጽ 480 ላይ፤“…ለእኔ ስራ የሆነው ህክምና፥ ለማክመው ሰው ግን ስራ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ስራ የሌላ ሰው ቁልፍ ችግር መፍቻ ነው፡፡ በአብዛኛው የምንዘነጋው ይህንን እውነታ ነው፡፡ የእኔ ስራ የሌላ ሰው ህይወት ነው ብለን እያሰብን መስራትን አልለመድንም፡፡ ከስራ የሚሰማን ጫናው እንጂ ምንነቱ አይደለም። ለአስተማሪ ስራው የተማሪው የወደፊት እጣ ፈንታን መወሰን እንደሆነው ሁሉ፥ የሀገር መሪም የሚመራው ሀገር የወደፊት እጣ ፈንታ ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም እንዘነጋለን፡፡ በመዘንጋት ማድረግ ያለብንን ሳናደርግ እንቀራለን!…“ ይላል። የዳዊት ስም አልባ ገና በቅጡ ነፍስ ያላወቀች ህጻን ገጸባህሪ፤ መጠየቅ የሌለባቸውን ጥያቄዎች ሁሉ እድሜዋን ባላገናዘበና የህይወት ልምዷን በማይመጥን ሁኔታ በደመ ነፍስም፣ ገደብ ባጣ ነጻነትም ትሰነዝራለች፡፡
ዶክተሩ ከህብረተሰብ ኋላቀር ስልጣኔ አንጻር በአርምሞ ታስበውና ተሰላስለው ብቻ እንጂ ሁሉም የግድ በዝርዝር የሚጠየቁ ጥያቄዎች፣ ተብራርተውም የሚመለሱ መልሶች እንደሌሏቸው በተደጋጋሚ ይስታል። ላም ባልዋለበት  ኩበት ለቀማ እሚመስል  የእውር ድንብር የመልስ ግኝት ኃሰሳ ሲዳክር፣ የመጽሐፉን ቅርጽ ወደ ፍልስፍናዊ ተረክ ሲያመራው እምብዛም ልብ አይልም፡፡ ታዲዎስ ጥሩአየሁ የተባለ ፀሐፊ “ዘመናይ” በሚል ርዕስ በቅርቡ ባስነበበን ድንቅ የሆነ ወጥ ልቦለድ ስራው ውስጥ፤ ጥያቄዎቻችን ሁሉ መልስ ያገኙ ቀን የህይወት ጥፍጥናዋ ይጠፋል! ሲል በውብ ገለጻው አስረግጦ እየጠየቀ እንዲህ አስፍሯል፤ … “አንዳንዴ የማንመልሳቸው ጥያቄዎች አሉ አይደል? ሁሉ ነገር መልስ ቢኖረው ኖሮ አይሰለችም? መሰልቸት ከእኛ እርቆ ቁጭ ያለው‘ኮ እኛ ዘወትር ለሚረባውም ለማይረባውም ጥያቄ መልስ በመቆፈር ላይ ስላለን ነው፡፡ ጥያቄዎቻችን ሁሉ የተመለሱ ቀን የህይወት ጣዕሟ  የሚጠፋ ይመስለኛል። ጣዕም ማለት  ጣፋጭ ማለት አይደለም። ምሬትም ጣዕም ነው፣ ጣፋጭም ጣዕም ነው። ለህይወት ጣዕም ዘለቄታ ሲባል ደግሞ ጥያቄዎች መቆጠብ አለባቸው፡፡ ውሃ- ውሃ የሚል ኑሮ መኖር አልፈልግም፡፡” (ገጽ.138) በእርግጥ የርዕሱ ቃል በራሱ ጥልቅ የፍልስፍና ዕሳቤን የያዘ መሆኑ እሙን ነው፡፡ በብዙ መልክና ልክ ተርጉሞ ማየትም ይቻላል፡፡ በዚህ መጠን ከፍታ ያለውን ርዕስ ይዞ የተነሳ የትኛውም ፀሃፊ፣ በላቀ የቋንቋ ልህቀቱ ላይ ተማምኖ መቼቱንና ይዘቱን  ያዋቅራል እንጂ በንግግር  ቋንቋ ጭብጡን ለመገንባት አይደፍርም። ድንቁርናን ወይም ጨለማን በበቂ ለማተት የግድ የማወቅ ጉብታ ላይ መቆም ላይጠበቅ ይችላል፡፡ በታማሚ የተማረ ሀኪም ከመሆን ላቅ ያለ፣ ከህክምና የትምህርት ዝግጅት የዘለለ…በልምድ የካበተ እውቀትና ክህሎት የሚሻ መሆኑን  ግን መጠቆም ግድ ይላል፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ መረጃን ከእውቀት ያላምታታ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በሥነልቦና፣ በሥነ አዕምሮ፣ ሥነ መለኮት ዘርፎች ላይ ተወስኖ ያልተቀነበበ ከዚያም ያለፈ ብስለትና መሰጠት እንዲሁም መሰልጠን በራሱ በቂ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ከዚያም እርቆ ይሄዳል፡፡ አያሌ  የዘመን እውቀት የሰበሰበ ሊሆን እንደሚገባ አያጠያይቅም፡፡ የፀሐፊውና የመጽሐፉ ሌላኛው ድክመት ደግሞ ይሄ ነው ብሎ መውሰድም ይቻላል፡፡             
ማሳረጊያ
ቦረቦር ዘዳር አገር የተባለ ፀሐፊ ‹‹አታንብቡ የሚሉ ደግሞ መጡብን!“ በሚል ርዕስ በበኩር ጋዜጣ ላይ እንዳስነበበን፤ የንባብ ባህላችንን ከሞት ያደረሱት በንግግር ቀላል ቋንቋ እሚጻፉ መበራከታቸውና በሳል ድርሰቶች መታጣታቸው ነው ሲል ጉዳዩን በአጽንኦት እንደሚከተለው አንስቷል፤ …“የንባብ ባህላችንን ከሞት እናድን፤ ወደ ቀደመ የዕድገት ደረጃውም እንመልስ ስንል የሚያጋጥሙን የተለያዩ  ችግሮች ይኖራሉ፡፡ በሳል ጽሑፎችን ወይም ድርሰቶች አለማግኘት ደግሞ አንዱና ቀዳሚው ችግር ሊኾን ይችላል፡፡ ኾኖም ይህ በሳል ጽሑፎችንም ኾነ ድርሰቶችን የማጣት ነገር ከንባብ ለመራቃችን፣ ሳናነብ ለመጻፍ መሞከራችን ጋር ተያይዞ የሚከሰት ችግር በመኾኑ በሳል ጽሑፎች እንዲሁም ድርሰቶች እስኪገኙ ድረስ ያሉትን በማንበብ እንዲሁም በቅርጽም ኾነ በይዘት የሚስተዋሉባቸውን ግድፈቶች እየነቀሱ በመማማር፣ ችግሩን ማቃለል ይቻላል ብለን እናምናለን!” (ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም)
እነሆ የኖርዌይን ህዝብ ስሜት ያስቆጣው “የንግግር ቋንቋ ብቻ“ ተብሎ የመፈረጁ ሁነት፣ እኛንም አንዳንዴ የማያስቆጣበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም፡፡ አዎ! አማርኛን የመግለጽ ብቃትና ልቀት አሳንሰው ስሜታዊ የሚያደርጉን፣ ደርሶ እንደ ግስላ እሚያበግኑን፤…ለአንባቢውም- ለቋንቋውም ባዕድ የሆኑ ይመስል ክሹፍ የሆኑ መጻሕፍት ተደጉሰውና በእውቅ ተሸልመው ከየዘርፉ ይቀርቡልናል፡፡ ለዚህ ማሳያ እንዲሆኑ ታቅደው የተጠረዙ እሚመስሉ ድርሳናት እዚህም-እዚያም በየዘውጋቸው አሉ፡፡ ያለው አክሊሉ ‹‹ውስብሳቤ››፣ አዱኛ ሂርጳ  ‹‹የለምን አሻራ››፣ ምህረት ደበበ ‹‹ሌላ ሰው›› ወዘተ፡፡ ቋንቋችን  ከንግግር  የላቀ  ስነጽሑፋዊ ልቀቱ የቱን ያህል ሰፊ እንደሆነ  ነጋሪም- መካሪም አያሻም፡፡ አዳም ረታን ማገላበጥ አይጠይቅም። ዳኛቸው ወርቁን አሊያም አለማየሁ ገላጋይን ዋቢ መጥቀስ ግድ አይደለም፡፡ እማኝ ለመጥቀስ እርቀን አንጓዝም፤ ሸንጎ ቀረሽ ክርክር አንዳረስም። በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ የኋለኞቹን ከፊተኞቹ በምናብ ቃኝተን ለመቆዘም የምንገደደው፡፡ “በፊደል ነው የተለከፍኩት” ያለው ሎሬታችን ታዲያ፣ ቋንቋችን ምን ያህል አዚማም ሆኖ ቢልቅበት ይሆን?


Read 530 times