Saturday, 01 July 2023 00:00

በመጀመሪያም ጥፍር ነበር!

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(0 votes)

“Nails are not about being noticed, they are about being remembered.” - Tammy Taylor
‹ሽሮ ወጥ ውስጥ ሽሮ አለ ወይ?› ብለህ የምትጠይቅ የአዳም ዘር ሁላ እዚህ ስር የምልህን እንደማትቀበለኝ አውቃለሁ…
…ይኼው ነው፤ አንዳንዴ መስከን ይታክተኝና ወላ የትላንት ዳናዬን እቃኝ እቃኝና… አለ አይደል ሲደብተኝ… በሽቄ፤ በጣም በሽቄ እግዚሔር የዓለምን ስንክሳር በመወጠን የፈጀውን ጊዜ ጥፍር በመሥራት ፈጅቶት ቢሆን እላለሁ፤ በጣም በግኜ ነው ታዲያ። ማርያምን። የንግግሬ ጭብጥ ግራ ያጋባቸው ግራኞች እንደቀባጠርኩ ይወስዳሉ… ግዴለኝም፡፡ እናም ስለምነግራቸው ጥፍር ወሻካች አድርገው ሊስሉኝ ይዳዳቸዋል…
 ምንም ብትል አይገደኝም…
…ከወራት በፊት ነው ታዲያ፤ ፀሐይና ጨረቃ የሚያረግዱለት፣ ጻድቃን የሚያሸበሽቡለት ልዕለ-ጥፍር አስተዋልኩ፤ እንደ ምሥራቅ በር ብርሃን የሚተፋ ጥፍር ነው፤ በሚረጨው የብርሃን ዘሃና የተስፋ ጸዳል ሌጣ ልቤ ትሞቅ፣ ትሞቅና (ትይዘው ያጣች፣ መሬት የጠበባት) የሚያባብል፣ ደስ የሚል ሕመም ይጣምናታል፤ ወዲያው ደግሞ ሰማይ ጠቀስ መቅበዝበዝና መንቀጭቀጭ ይፈራረቁብኛል፤ ጫንቃዬ ውሃ ቋጥሯል አቅሌን ስቼ ስፈርጥና ስነሳ… በቀን እንደሚቃዥ ገመምተኛ ንውዝ ሆኜ ነው ታዲያ።
ጣቶቿን ከፈትፈት፣ ዘርጋ ስታደርጋቸው አምሥት የአልማዝ ኮፊያዎች ከጣቶቿ ጫፍ ላይ ጠልቀዋል… ወይም በቀኝ እጅዋ አምሥት ክዋክብት ሥርዐት ጠብቀው ተሰድረዋል፤ በግራ እጅዋም አምሥት ክዋክብት። ንጉሥ ሰሎሞን ጣቶቹ ላይ አጥልቆአቸው ጋኔን ሽባ እንደሚያደርግ ይነገርላቸዋል፤ በኋላ ከእጁ ያፈተልኩና መልሶ እሱ ሽባ ሆነ፤ በድጋሚ አጠለቃቸውና ኃይልን ተቀዳጀ፤ እግዚሔርም ወዶአቸው ሲያበቃ (እሱም መውደድ ያምረዋልና)፡- ‹‹ልበ ጽፍር›› አለ አሉ።   
እና አለ አይደል… ቆንጆ ነገር መቼም ቢሆን ቆንጆ ነው፤ ቁንጅናን ጊዜና ቦታ አይገድበውም። ቁንጅና ጊዜንና ቦታን ማቸነፍ ነው፤ ከዚያ ሕልው መሆን በዋናነት እልብ ግምጃ ውስጥ፤ በሰዎች ልብ ውስጥ ስፍራ የማግኘትን ያህል ክቡድ ነገር የለም፤ የልብ ቁምነገር ማዕድን ከማውጣት እንዲከብድ ዕሙን ነው፤ ይኼ ጥፍር በልቤ የተቆረረለት ስፍራ አለው፤ የአድዋን ዓይነት ጦርነት ለመቀስቀስ የሚያበቃ ነው እውነቱ፤ ከንቱ ካልሆንክ በቀር የቁንጅናውን ሕቡዕ ሚስጥር መመርመር ታፋፍማለህ። ደክሞኝ እስክወድቅ ድረስ በተዐምራቱ ተደነኩ፤ ወይም እንደ ጢያራ ዓይነት ሕልም አለምኩ…
…እግዚሔር የፀሐይ መግቢያ ላይ ይኼን የመሰለ ጥፍር እየሠራሁ ነውና ከፀሐይ መግቢያ በፊት ተገኙ ብሎ ቢያሳውጅ እኔ ፀሐይን ቀድሜ ከስፍራው እገኛለሁ ብዬ አለምኩ፤ ያንን ቆንጆ ጥፍር ወላ እንደ መልካም ፍራፍሬ አቅል የሚያስጥል ወይም የሚበላ መሳይ ጥፍር ምንነት መረመርኩ፡-
ድርሳን 1፡- እግዚሔር ምድርን ፈጥሮ ሲያበቃ ሰማይን በጠረባ ዘረጋ፤ ከላይ የተዳሰው ሰማይም ቱባ ጭለማ ከምድር ላይ ጣለ። ይኼኔ እግዚሔር የብርሃን ምንጭ እንዲሆን ይኼንን ጥፍር ፈጠረ።
ድርሳን 2፡- እግዚሔር የሰው ልጆችን ፈጥሮ ሲያበቃ ምድርን በውብ ነገር መሙላት እንዳለበት አሰበ፤ አስቦም አልቀረ የውበት ሁሉ ቁንጮ የሆነውን ጥፍር ፈጠረ…
…እልልልልልል! ያን ቀን ታዲያ ምድርና ሰማይ ከፍ ዝቅ በማለት አረገዱ አሉ! ታዲያ ሲመስለኝ ከዚህ ከምነግርህ ጥፍር ውጪ ሁሉ ነገር ከንቱ እንዲሆን ዕሙን ነው። የምጽዐት ቀን ከማይደመሰሱ ነገሮች አንዱ ይኼ ጥፍር ብቻ እንደሆነ እመን።    
አንተ ስለዚህ ጥፍር ካላወክ ማርያምን ከንቱ  ነህ፤ ግን ጥፍሩ የማነው?...
…ጥያቄውን አላስኮርፍም...
…እናገራለሁ…
…ከተወለደች ጀምሮ ያደረች የማትመስል… አለ አይደል እንደ ጸደይ ሰማይ የፈካች፤ ወላ የጽጌያት መስክ የምትመስል እንስት ነች፤ ታዲያ ዘየረቺኝ (ዝየራዋ አይለያችሁ)፤ እጅዋን በቀስታ ከኪሷ አውጥታ ነው፤ ኦቾሎኒ ከተጠቀለለበት ከትራሱ ተቀርፎ ሲወጣ የሚያገኘውን ውበት ያህል ጸጋን የተላበሰ ጥፍር የቀኝ እጆቼ መሀል ገባ፤ ከጅምሩ ኃይል ነበራትና… ጥፍሯም ኮሬንቲ ቅልቅል ስለነበር ነዘረኝ፤ የምር ጫረቺኝ። ምን መሰለህ… ልጅ ሆኜ ሽልንግ ተሰጥቶኝ ወይም ሽልንግ አግኝቼ የገዛዋትን ከረሜላ ከመቃሜ በፊት እንደማገላብጣት ደጋግሜ አገላበጥኩ፤ በስስት ነው ግን እንዲያ ያለ ነገር የጎረምሳ ግብር ተደርጎ ተዟዙሮ እንዳይተረጎምብኝ እየፈራሁ።
በውስጤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ክብርት ማርያም ሆይ በመላእኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እልሻለሁ አልኩ… ከዚህ ጥፍር ውጭ ማርያምን የማመሰግንበት ዕድል እንደሌለኝ አውቄአለሁ፤ ስክርክር ብዬ፤ ውሌን ስቼ አቅበዝብዞኛል ደግሞ። እንዲያ ያለ ጥፍር አይቼ አላውቅም ነበር፤ ስብ፣ ወዛም ላት መሳይ ቡና ጠጥተናል። ስኒዎቼ ከጥፍሮቿ ብርሃን አልበው ብርሃን እየተፉ ይኖራሉ፤ ቤቴን እያበሩ። የገለጠቺው የመጻሕፍ ገጽና እዚያ ላይ የሰፈሩ ፊደላት የሚንጨለጨል ዘሃ እየነዙብኝና ትርጉሙ እንደረቀቀብኝ አለሁ። እመነኝ አንተም እንዲህ ያለ ጥፍር አንዲትም ቀን አይተህ አታውቅም።
    *  *  *
‹ውበት ምንድነው/ውበት በምን ይገለጻል?› ብያት ‹በመቃ አንገት ያለቺኝ አንዲት ስጋጋ አለች፤ አንገት ተሽከርክሮ ሀሳብ ከማስለወጥና የተሸከመውን ጭንቅላት ከማናወዝ የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው ንገሯት፤ አሎሎ ዓይን የምትሉት መስፈርት ደግሞ አይዋጥልኝም፤ ወላ ‹የደም ገንቦ› ይሉት ብሒል እንዴት አድርጎ ውበትን እንደሚገልጽ አልገባኝም፤ ለእኔ ደም የውበት ሳይሆን የአስደንጋጭ ነገር ወላ የሽብር መገለጫ ነው፤ ደም ብሎ ቆንጆ ነገር ዘበት ነው፤ አፍንጫ፣ አንገት፣ ጸጉር፣ ዳሌ ሽንጥ፣ ባት… ለዓይን እንጂ ለልብ አይሞሉም፤ ጥፍር ነው ቁምነገር። ታሪክን መለስ ብለህ ብትቃኝ የጦር መሣሪያ በሌለበት የሰው ልጆች በጥፍር ይዋጉ እንደነበር ይነግርሃል፤ አየህ ጥፍር ከውበትም ይዘላል። አንበሳ የጎሳውን ክብር የሚያስጠብቀው በጥፍሩ ነው፤ ጥፍርህን ስለህ ስለ ጥፍር በመፈተሽ ሰብአዊ ክብርህን አስጠብቅ።
ዮዲት ጉዲት ያንን ሁሉ ጉድ የፈጸመቺው ነገስታት መክረው ጥፍሯን ከከረከሙ በኋላ እንደሆነ ሊቃውንት ይናገራሉ፤ ጥፍር የመዘዘው መዘዝ ማቆሚያ እንደሌለው ሲገባህ መጻሕፍ ቀጽለህ ወይም ግስ ገሰህ ማኅሌታይ ትቆማለህ፤ እንደ ሞኝ ስትሰማ ከምትደነግጥ ድርሳናት ብታገላብጥ ለነፍስህ ትተርፋለህ። እንቢኝ ካልክ ታሪክ ጥፍር ሆኖ ይወጋሃል።    
የሰው ልጆች ስንባል መቼም ኪሳራ ነንና እግዚሔሩን ማክሰራችን አይቀርም። ሞት አትቀርም፤ ጽዋ ቀማሽ ነን፤ ግና እንደ እግዚሔር ‹‹አባት ሆይ ይህቺ ጽዋ ትለፈን›› የምንልበት ዕድል ባይኖረንም፣ ማለቴ ሳልፈቅድ ተወልጄ ሳልፈቅድ አልሞትም የማለት መብት መነፈግህ ቢያንገበግብህም፣ ነፍስህ ሥጋ ሐር ልብሷን ጥላ እሰማይ ትተማለች፤ የመወለድና የመሞት ድንበር የቱ ጋ እንደሆነ ያልለየች የእኔም ነፍስ አንድ ቀን ያከትምላታል…
…ታዲያ ያን ቀን እግዚሔር ኪሩቤልና ሱራፌል መከዳው ላይ ተንፈላሶ ሲጨርስ ወደ እኔ ሰጎ (አዲስ ነገር በሌለበት)፡-
‹‹በምድር ላይ ሳለህ ምን የረባ ነገር ጣፍክ?›› ይለኛል፤ በለዘብተኛ ድምጸት ልዝዝ ብሎ፤ ለዘብተኛ ስለሆነ፤
‹‹እንጃልህ!›› እለዋለሁ
ይበሽቃል፡፡
በሽቆ ሲያበቃ ዓይኑ እንባ ይከትራል፡፡
‹‹እንደው ምንም?›› ልቡ ግልጥ ስላልሆነ ባልገባው ስልት ያውጣጣኛል፡፡
‹‹እንዴ!›› እምር ብዬ እነሳለሁ
እሱም እንደ አዲስ ለመስማት አፉን ይከፍታል፤ በልጥጦ ነው ታዲያ፤
‹‹ጌታዬ፣ እንደ ፀሐይ መውጫው የተስፋይቱ ከተማ ብርሃን የሚታለብ ጥፍር አይቼአለሁ፤ ከዚያ አንተና እናትህንም አመስግኜአለሁ›› እላለሁ
ቀጥሎ የደስታ እንባ እናነባለን፤ ከዚያ ነጋሪት ያስጎስማል፤ ገላዬን በነጭ ወይን እንዲያጥቡ መልአክትን ያዛል፤ የሙክት በግ ቅልጥም እየቀለጠምኩ እሰነባብትና የገነት መግቢያ ትኬት የማገኝበትን አጭር ጽሑፍ ለአንዱ መልአክ ያቀብላል፤ የዚህች እንስት ጥፍር የፅድቅ በር እንዲሆን እሙን ነው።     
ሳይረፋፍድ ናና ይኼንን ጥፍር ጎብኝ፤ ቆንጆ ለማየት ጎርኪ ጎጃም መጥቶ ጎመን ይተክል እንደነበር መረጃው አለኝ። እኔም አንድ ሰሞን ዳሳነች ሄጄአለሁ፤ አራት መቶ ዓመት ያስቆጠረ ቆንጆ ከንፈር ለመጎብኘት፤ አርባምንጭን ስለምወዳት ስመለስ ሃያ ሰባት ቀን እዚያ ከረምኩ፤ በቆይታዬም ከሃያ ሰባቱ ምንጭ ጠልቄ ጠጣሁ፤ አሥራ ሦስቱ ስለሚቀሩኝ ሌላ ቀን ደግሜ መሄዴ አይቀርም።   እንደ ማንኛውም ሰው ቅርስን ከመንከባከብ ይልቅ መመዝበር ሊቀናህ ይችላል፤ እኔ ግን ጠብቄ አኑሬአለሁ፤ የእውቀት ጥግ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሕይወት መምራት ሊመስልህ ይችላል፤ አልነበረም ግን ይኼንን ጥፍር ካላወክ ምድረ-በዳ አንጎል ነህ፤ በቴክኖሎጂ መርቀቅ ነገሮችን ውብ ለማድረግ ነውና ሁሉም ነገር የሚጀምረው ከውበት ነው። ከፈለክ አሳቅለኝ - እግዚሔሩም ቢሆን የሚያደላው ለእኔ ነው።
ወላ እሱም በሰው አየኝ-አላየኝ እየተገላመጠ ይኼንን ጥፍር የሚገረምም ይመስለኛል፤ ዓለምን የሚቃኝ በመምሰል ጥፍር እየፈተሸ በረከት ያድል ይሆናል። ዋናው ነገር ፍሬድሪክ ኒቼ እንዳለው፤ we are condemned to be perfect/ብልሆች እንዳንሆን ተረግመናል ነው፤ ማለቴ ይኼንን ጥፍር ሳያውቁ እውቀት ብሎ ነገር ጉንጭ ማልፋት ነው…         
…አንዳንድ የሥነ-አዕምሮ፣ የሥነ-ልሳን እና የሥነ-ልቡና ሕልዮቶች የሰውን ልጅ ታቡላ ራዛ ቢሉም ግና ይህቺ ሴት  ግርማ-ሞገስ ያለው ጥፍር ይዛ ተፈጥራለች። ቁምነገር ከጥፍር ላይ ነው፤ ያውም ጸዳልማ ጥፍር፤ ጥፍሯ ተስፋ እንደሆነ መዝግቡልኝ። ብርሃንና ተስፋ በሌሉበት አዕምሮ ምንም አይሠራም። ልዕለ ጥፍር…
…ታዲያ ትዝ ሲለኝ ለእራሴ በለኾሳስ…
ጥፍሯ ግን ሲገርም፤
ላንባ አያስመኝም፤
እላለሁ! ተንሲኦ ለጸሎት ሰማይና ምድር ሲያልፉ ለማያልፍ ጥፍሯ እናርግድ ማኅሌታይም እንቁም!!   


Read 638 times