Saturday, 01 July 2023 00:00

“ሁሉም እንዳሻው አገር እያፈረሰ፣… እኛ ይጭነቀን? ምን እዳ አለብን!”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ነባሩን አገር፣ ትናንት የተገነባውን ባሕልና ስርዓት ለማፍረስ መሽቀዳደም ክፋት ሳይሆን ሙያ  መስሏል።
ነባሩን ለማጽናትና ለማሻሻል፣ አዳዲስም ለመገንባትና ለማሳደግ የሚተጋ ሰው ከየት እንዲመጣልን ፈልገን ይሆን?
ነባሩን ክፉኛ ለማጥላላት፣ የትናንት ታሪክን በጭፍን ለማንቋሸሽ የሚጣደፉት የት ላይ ቆመው ነው? ትናንት የተወለዱ፣ ከነባር ወላጆች ጠብተው ጎርሰው ያደጉ ናቸው።

ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት ክፉና ደጉን እያየች እስከዛሬ የዘለቀች ታሪከኛ “የተስፋ አገር” ብትሆንም፣ ስንቱን አደጋ መሻገርና እስከ መቼ መቆየት እንደምትችል አያሳስባችሁም?
“አሁንስ አለቀላት” በተባለችበት ዘመን ሁሉ መጎሳቆሏ መቁሰሏ ባይቀርም ህልውናዋ አልተቀበረም፤ ታሪኳ አልተቋረጠም። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በዓለም ዙሪያ ሁሉ፣ እንደ ኢትዮጵያ ለብዙ ምዕተ ዓመታት ታሪካቸው ሳይቋረጥ እስከዛሬ የደረሱ አገራት፣ ሦስት ወይም አራት ቢሆኑ ነው።
ክፉኛ እየወደቀች አፈር ለመልበስ የተቃረበችበት ጊዜ ጥቂት አይደለም። ግን ወድቃ አልቀረችም። አፈር ልሳም ቢሆን በተደጋጋሚ ከወደቀችበት እየተነሳች አንሰራርታለች። ከሩቅም ከቅርብም፣ ከባህር ማዶ ከየአህጉሩ በርካታ አዋቂዎች፣ ኢትዮጵያ ላይ ተስፋ ሳይቆርጡ በየዘመናቸው በክብር መጻፋቸው ለዚህ ነው።
እውነት ነው፤ የተስፋ ምድር ናት። ነገር ግን፣ ምንም ብናድርግ፣ ምንም ብትሆን፣ ቢንጧት፣ ማእበል ቢመታት፣ አንገጫግጨን ብናላትማት፣ እየተቃወስን ብናናውጣትና ተረባርበን ብንጥላት እንኳ፣ ወድቃ አትቀርም ማለት ነው? አክርረን ብናሳምማት እንኳ አትሞትም? ጠፍታ አትጠፋም?
ፍርሃታችንን ለማለሳለስ፣ የተስፋ ጭላንጭል እንዳናጣና ራሳችንን ለማፅናናት፣… “ወድቃ አትወድቅም” እንላለን።
አገርን የሚሸረሸር፣ የሚሰረስርና የሚቦረቡር፣ የሚሰነጣጥቅና የሚያፍረከርክ እልፍ የጥፋት ዓይቶችን በዘፈቀደ እለት በእለት እየፈጸሙ፣ ከህሊና ወቀሳ ለማምለጥ የሚፈልጉ ሰዎችንም፣ “ጠፍታ አትጠፋም” ብለው ራሳቸውን ያታልላሉ።
ሌላው ሰው ሁሉ እንዳሻው እያፈረሰ፣ ተቀናቃኞቻችን ሁሉ እንዳሰኛቸው እየፈመነጩባት፣ “እኛ ለብቻችን ጨዋ የአገር ተቆርቋሪ ብንሆን ዋጋ የለውም” ብለው የጥፋት እሽቅድምድም ውስጥ የሚገቡም ሞልተዋል።
“ሌላው ሁሉ በብሔር በብሔረሰብ ሲደራጅ አገርን እንደሚበታትን ብናውቅም፣ በዘር መቧደን መጥፎ ነው ብለን መቃወማችን ውጤት አያመጣም። በየዋህነት ከጨዋታ እንወጣለን። ወይ ወገን የለሽ የጥቃት ሰለባ እንሆናለን። ተቀናቃኞቻችን እንዳደረጉት፣ በብሔር ብሔረሰብ ከመቧደን ውጭ አማራጭ የለንም” የሚሉ ሰዎችንም እናያለን።
ከዚህ የባሱም አሉ።
የአገር ሰላምና የአገር ህልውና… የሌሎች ሰዎች ሃላፊነት ነው ብለው ያስባሉ። ለጊዜው አንዳች ጥቅም የሚያስገኝላቸው ከሆነ ወይም ከመሰላቸው፣ ተከታይና ቲፎዞ የሚመጣላቸው፣ ተቀናቃኞችን ለማበሳጨት የሚያገለግል፣ ሰፈር ምድሩን የሚያነቃንቅ፣ ሕዝቡን የሚያስጨንቅ፣ ኃይል ሆኖ ለመታየትና ለመግነን የሚጠቅም ከመሰላቸው፣ የአገር ምሰሶና ማገሮችን ለመከርከርና ለመስበር አመነቱም።
በማፍረስና በመገንደስ ነው ኃይልና ዝና የምናገኘው ብለው ያስብሉ። የመሰረትና የማዕዘን ድንጋይ ለመፈንቀል ለመናድ ይሽቀዳደማሉ። አገርን ያስተሳሰረ የጨዋነት ድርና ማግ እየበጣጠሱ ለመጣል ይወዳደራሉ።
ኧረ አገር እያፈረሳችሁ እየበተናችሁ ነው የሚላቸው ቢመጣ ግድ የላቸውም።
ለምን ይፈርሳል? ለምን ይበተናል? ስንበጥስ እናንተ መጠገን ያቅታችኋል? እኛ እንዳሻን እናደርጋለን። ተቆርቋሪዎች ይጭነቃቸው…
እንዲህ ዓይነት ፖለቲከኞች ዛሬ ዛሬ እጅግ ብዙ ናቸው። ንግግራቸውና ተግባራቸው አንዳች ነገር ለመስበርና ለመበጠስ የተነጣጠረ ነው።
እና እኛ ምን እዳ አለብን፣ የበጠሱትን ለማያያዝ የሰበሩትን ለማቃናት የመጨነቅና የመጠበብ እዳ አለብን? እንደዚህ ማሰብ ከጀመርን በኋላ፣ እንደ አፍራሾቹና እንደ በጣሾቹ ለመሆን ብዙም አይቀረንም። ማመካኛና ማሳበቢያ እያዘጋጀን ነዋ። እነሱ እንዳሻቸው እያፈረሱ እኛ ምን እዳ አለብን በሚል ሰበብ፣ የማፍረስ ጨዋታው ውስጥ እንገባለን።
ምናለፋችሁ፣ ለክፋትና ለጥፋት ሰበብ አናጣም። ሞልቶ ተርፎ።
የመፍትሔ ሃሳቦችን ለማጣጣልና ተስፋ ለመቁረጥም አልፍ ሰበቦች እናመጣለን።
ትክክለኛውና ተገቢው የአገር ሥርዓት ምን ዓይነት እንደሆነ በቅጡ ለመገንዘብና ለማወቅ መነጋገራችን ለከንቱ አይደለም። ሌላ መልካም አማራጭም የለም።  ነገር ግን፣ “ምን ዋጋ አለው?” የሚል ጥያቄ ሊፈጠርብን እንደሚችል አያጠራጥርም።
“ትክክለኛው ሃሳብ” እና “ተጨባጭ ተግባር” እንደ ሰማይና ምድር ከተለያዩ፣… “ተገቢው ሥርዓት” እና “የየእለቱ አኗኗር” ወዲህና ወዲያ ማዶ በተቀራኒ አቅጣጫ ከተራራቁ፣ ማወቅና መነጋገር ምን ጥቅም አለው?
ትክክለኛ ሃሳቦችንና መፍትሔዎችን ለማጣጣል፤ በዚሁም ሰበብ የክፋትና የጥፋት ፖለቲካ ውስጥ እየተለወሱና እየተራገጡ፣ እልቂትና ስደትን እያዛመቱ ለመቀጠል ማመካኛ ዘዴ የሚፈልጉ ሰዎች ጥቂት አይደሉም።
በሌላ በኩል ግን በቅን ልቦና እያሳሰባቸው፣ ትክክለኛ ሃሳብ በተግባር ለኑሮ ይጠቅማል ወይ ብለው የሚጠይቁ ሰዎች ሞልተዋል። አዎ፣ ዛሬውኑ ለፍሬ አይደርሱም። ነገር ግን ለነገ ዛሬ መትከል የለብንም? በትክክል ካላሰብን የተግባር ስህተቶችን መለየት አንችልም። ተገቢውን ስርዓት ካላወቅን፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችን መመርመርና የቱን ያህል እንደተበላሹ መገንዘብም ሆነ ጉድለታቸውን መለካት አንችልም።
በዚያ ላይ፣ ከቀን ወደ ቀን ስህተት እየበዛና እየሰፋ፣ ብልሽት እየባሰና እየከፋ ቢሆን እንዴት ማወቅ እንችላለን? በየእለቱ ስህተቶች እየታረሙ፣ ብልሽቶች እየተቀረፉ፣ ተግባሮቻችን እየተስተካከሉ፣ አኗኗራችን እየተሻሻለ መሆኑንስ እንዴት ማገናዘብና ማመዛዘን እንችላለን?
ወደ ትክክለኛው ሃሳብና ወደ ተገቢው ስርዓት ምን ያህል እንደተራመድን ወይም የቱን ያህል የኋሊት እንደተንሸራተትን፣ ምንኛ ቁልቁል እንደወረድን በማየት ነው- መሻሻል ወይም መበላሸትን የምንለካው።
የመሻሻል መንገዶችን ለመክፈትና ጉዞ ለማቃናት እድል የሚኖረንም፣ “ትክክለኛ ሃሳብና ተገቢ ሥርዓት” ምን ዓይነት እንደሆነ የምናውቅ ከሆነ ነው። ያው ባወቅነው መጠንና ማወቅ በምንችልበት ልክ ማለት ነው።
እንዲህ ሲባል ግን፣ “ትክክለኛውና ተገቢው ሥርዓት” ወደ ተግባር ተተረጎመ ማለት… ነባር ነገሮችን ሁሉ መቀየር፣ እስከዛሬ ያልነበሩ ነገሮችን ከባዶ መፍጠር ማለት አይደለም።
በመርህ ደረጃ በግልፅ ባይቀረፁም፣ በስርዓት ደረጃ በጽኑ መሰረት ባይታነጹም፣… በተናጠልና እንደመሰንበቻ የምናከናውናቸው በርካታ የዘወትር ተግባራት፣ እንዲሁም በልማድ የምንከተላቸው በርካታ የአኗኗር ዘይቤዎች፣… እነሰም በዛ የትክክለኛ ሃሳብ፣ የተገቢ ስርዓት ገጽታዎችን በውስጣቸው ያቀፉ ናቸው።
ቅንነትንና መከባበርን እንደ መርህ  እንኖርባቸው ይሆናል። ነገር ግን፣ በቅንነትና በመከባበር ለመኖር ሞክረን አናውቅም ማለት አይደለም። በየሰፈራችንና በየከተማው፣ በስራ ቦታና በየጎዳናው፣… ሁሌም ባይሆን እንኳ በአብዛኛው በሰላም ለመንቀሳቀስና በሰላም ለማደር የምንችለው አለምክንያት አይደለም። በነባሩ ባሕል ውስጥ በጥቂቱም ቢሆን የመከባበርና የጨዋነት መንፈሶች በመኖራቸው ነው በጥቂቱም ቢሆን በሰላም የምንኖረው።
እነዚህን ነባር የጨዋነትና የመከባበር ገጽታዎች ወደ መርህ የማሳደግ ጉዳይ ነው- ስልጣኔ። የሰውን ሕይወት ማክበር ማለት፣ የሰውን አእምሮ፣ ሃሳብ፣ እውቀትና ንግግር፣ የሰውን አካል፣ ስራ፣ ምርትና ግብይት፣… ቤትና ንብረት፣ የእያንዳንዱን ሰው ህልውናና ሰብዕና ማክበር ማለት ነው- ስልጣኔ-ሌላ አይደለም።
ትክክለኛና ተገቢ ሥራዓት፣… ነባር ነገሮችን ሁሉ የማፍረስ፣ ታይተው የማያውቁ ነገሮችን የመፍጠር ጉዳይ አይደለም።
“ትክክለኛና ተገቢ ሥርዓት” ምን ማለት እንደሆነ ይበልጥ ባወቅን ቁጠር፣… ከታሪክ የተማርናቸው ከህይወት ዘመንም የታዘብናቸው ትክክለኛ ተግባራትን፣ ቀና መንገዶችን አጥርተን እያገናዘብን፣ በተናጠልና በዘልማድ ብቻ ሳይሆን በመርህ ደረጃ አዋህደን ቅጥ ልናስይዛቸው፣ ቅርፅ ልናበጅላቸው እንችላለን።
በሌላ አነጋገር፣ ስህተትንና ጥፋትን ላለመድገም ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ ችግሮችን ለመከላከል ይረዳል- መርህ። ትክክለኛና ተገቢ ተግባራትን ላለመዘንጋት ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ ነገሮችን አጥርተን የምናይበት ብርሃን፣ እነዚህን የሚያበራክት የተቃና መንገድ ይሆንልናል-መርህ።
ያተሞከሩና ያልነበሩ አዳዲስ የመፍጠር ጉዳይ አይደለም-ሥልጣኔ።
ነባር ስህተቶችንና ትክክለኛ ተግባራትን፣ አጥፊና አልሚ ነባር የአኗኗር ልማዶችን በማገናዘብ፣ ጠማማና መጥፎ ገደላገደሎችን ከወዲሁ ባህርያቸውን ማወቅና መጠንቀቅ፣ የሕይወት መስመሮችንና የተቃኑ የበረከት መንገዶችንም ባሕርያቸውን እያወቁ በዚያው ልክ የማጽናትና የማስፋፋት ጉዳይ ነው- ሥልጣኔ።
ነባር ክፋቶችን እየገቱ አዳዲስ የክፋት መርዞችን እንዳንፈጥር መከላከል ስልጣኔ ነው።
ነባር ፀጋዎችን እያከበሩ፣ እያሳደጉና እያሻሻሉ፣ አዳዲስ ፍሬዎችን መጨመርም ሥልጣኔ ነው።
ሁለቱንም ነጥቦች አያይዘን መጨበጥ ይኖርብናል።
ሥልጣኔ፣ ነባር ነገሮችን የማጥፋት ጉዳይ አይደለም። ነባር ነገሮችን በዘልማድ የመደጋገም ጉዳይም አይደለም።
እንደማንኛውም አስደናቂ ፈጠራ፣… ነባር ፈጠራዎችን እንደመንደርደሪያ በመጠቀም፣ ነባር ነገሮችን በአዲስ ቅንብር ከቀድሞው የላቀ ውጤታማ ሥርዓት (System) የማበጀት ጉዳይ ነው።
ከቀድሞ አዋቂዎች ምንም አልማርም፣ ከነባሩ ተፈጥሮ አንዳችም አልነካም ብሎ፣… ቅንጣት ቁም ነገር መስራት የሚችል ሰው የለም። የተሻለ ነገር ለመፍጠር ይቅርና፣ በወጉ መቆምና መራመድም ይሳነዋል እንጂ። ነባር ጥበበኞችንና ነባር እውቀቶች ያላከበረ ሰው፣ ይባስ ብሎም ማንኛውንም ነባር ሃሳብና ቅርስ፣ ታሪክና ባሕል ለማፍረስ የመዝመት ሱስ የተፀናወተው ሰው፣ ቅንጣት  አዲስ ነገር መገንባት አይችልም። ማጥፋትና ማጨለም አዲስ ብርሃን መለኮስ አይደለምና።
በሌላ በኩል፣ ነባር ነገሮችን በዘፈቀደ በዘልማድ መደጋገምም፣ ቀደምት ጠቢባንንና ታሪክን ማክበር ሳይሆን ማዋረድ ነው፡፡
ነባር ነገሮችን ማጥላላትና በጭፍን መቃረን፣ ከዚያም አልፎ ለማፍረስ መዝመት፣ የቀድሞ ልማዶችን ብቻ ሳይሆን፣ ራስን የመጥላትና የማዋረድ በሽታ ነው፡፡
መቼም፣ በነባሩ ውስጥ እንጂ ከመጪው ዘመን ተወልዶ ወደ ዛሬ የመጣ ሰው የለም፡፡
ማንም ሰው ቢሆን በነባር ወላጆች፣ በነባር አሳዳጊዎች፣ በነባር አስተማሪዎች ነው የሚችለውን ያህል የሚያድገው፣ የሚማረው፡፡
አነሰም በዛ፣ በነባር አቅም ነው የነገን ህንፃ ዛሬ መገንባት የሚችለው፡፡ የቅርብም ይሁን የሩቅ፣ የትናንት ጥረቶችንና ነባር ግንባታዎችን፣…እንማርባቸዋለን፤ እንሰራባቸዋለን፤ አርአያነት እናገኝባቸዋለን። የእውቀት መማሪያ፣ የኑሮ መገልገያ፣ የተግባር መሳሪያ፣… የመንፈስ ሃይል ከነባሩ ውስጥ ለማግኘት ያልፈለገና ያልቻለ ሰው እንዴት ውሎ ማደር ይችላል?
ነባሮችን ዘወትር እያጥላላን ለጊዜው ግን እየተጠቀምንባቸው፣ ተጠልለንም እየኖርንበት፣ ግን ደግሞ እለት በእለት ማፍረስ፣ የት ያደርሰናል? የቀድሞ ፍሬያማ ጥረቶችን፣ የተገነቡ ቅርሶችን፣ የተዋቀሩ ሥርዓቶችን ያላከበረ፣… አዳዲስ ግንባታዎችን የማክበርም ሆነ የመስራት መንፋሳዊ ሃይል ያጣል፡፡ ውስጡ ይንጠፈጠፋል፡፡
 ማፍረስን እንደ ስራ ይቆጥረዋል፡፡ የእውቀትና የሃሳብ፣ የኑሮና የተግባር፣ የማንነትና የራዕይ፣ የስልጣኔና የብልፅግና መነሻችን፣… አነሰም በዛ፣ ሌላ ሳይሆን ነባሮቹ የትናንት ውጤቶች ናቸው፡፡ ሁለት ነጥቦችን አይተናል። የወደፊት ራዕይ እና የቀድሞ ነባር ቅርስ፡፡
የወደፊት ራዕያችን፣ ማለትም መርህ ትክክለኛውና ተገቢው ሥርዓት ምን ዓይነት ነው?
በአንዳች ተዓምር፣ በአንድ ጀምበር እውን አይሆንም፡፡ ነገር ግን፣ አቅጣጫችን ወደ ተሻለ ኑሮ ወደ ከፍታ መሆኑን ወይም ወደ ባሰ መቀመቅ የሚያሽቆለቁል መሆኑን ለይተን ለማወቅ፣ ትክክለኛ ሃሳብና ትክክለኛ ራዕይ ሊኖረን ይገባል። ያኔም ለማስተካከል እንችላለን። “እያንዳንዱ እርምጃችን የመገንባት እርምጃ መሆኑን ወይም የማፍረስ  እርግጫ መሆኑን በውል ማወቅና መለካት የምችለው፣ በመልካም የወደፊት ራዕይ አማካኝነት ነው፡፡ ከነባሩ የሚሻል ነገር ለመፍጠር መፈለጋችን ተገቢ ነው፡፡ የነባሩ ጉድለቶች ላይ ቅሬታ ቢኖረን አይገርምም፡፡ ነገር ግን፣ በቅሬታ ሰበብ በጥላቻ ስሜት ወደ ባሰ ገደል ለማሽቆልቆል ሳይሆን ለመሻሻልና ለማደግ መሆን አለበት ዋና ሃሳባችን፡፡
ሁለተኛ ነገር፣ የህልውናችን ምንጭ ሁሌም የቀድሞው ታሪክና ነባር ቅርስ ውስጥ ነው፡፡ የተሻለ የነገ ራዕይ ለመያዝና ለመጓዝም፣ መነሻችንና አቅማችን ከትናንት ውጤቶችና ከነባር ታሪኮች የሚመነጭ ነው ይብዛም ይነስ፡፡ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ የተወለዳችሁበት ዘመን፣ የጥጋብ ጊዜ፣ ወይም የድርቅ ዓመት ሊሆን ይችላል። የተማራችሁበት ቦታ፣ ያደጋችሁበት የኑሮ ደረጃ፣… ለሕይወት አመቺ ወይም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡
ነገር ግን፣ በችግርም ይሁን በምቾት፣ ከዚያው ከነባሩ ሁኔታ ነው የእርምጃ መነሻና መንደርደሪያ የምናገኘው። ከነባሩ ነው ትንፋሽ የምንወስደው።
 የህልውናችን ምንጭም ሆነ የነገ መነሻችን ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ ከመወለድ ውጭ ሌላ መነሻ፣ ከእስከዛሬው ነባር ባሕልና ከእስከዛሬው ታሪካችን ውጭ፣ ለነገ ጉዟችን የሚጠቅም ሌላ መነሻ አቅም የለንም፡፡ ሊኖረንም አይችልም፡፡ ከነባሩ ውስጥ እንጂ፡፡
የትናንት ነባር አቅሞችን ማክበር፣ ለነገ መልካም ራዕይን መያዝ፣ ዛሬ በቅጡ ለማሰብና ለመነጋገር፣ የዛሬ ተግባራችንን ለማስተካከልና ለመምረጥ ይጠቅመናል፡፡ የጉዞ መስመራችን ይቃናል፣ የእለት ተእለት እርምጃችንም ብርታት ያገኛል። የመሻሻል ግስጋሴን ይሰጠናል፡፡
እንደ ማዕቀፍ ሰብሰብ አድርገን፣ እንደ መነፅር የቅርብና የሩቁን አጥርተን አዛምደን የአገራችንን ሁኔታ ለማገናዘብ ይረዱናል የትናንት ነባር አቅሞችና የነገ ትክክለኛ ራዕዮች፡፡
እነዚህ ማዕቀፎችና መነፅሮች፣ እልፍ አእላፍ አላስፈላጊ ውዝግቦችን ለማስወገድ፣ በዚያው ልክ የመግባቢያ መንገዶችን ለመክፈት ይጠቅማሉ፡፡
ለእነዚህ ማዕቀፎችና መነፅሮች ቀዳሚ ትኩረት ካልሰጠን፣ ውይይቶች ሁሉ ከንቱ ወገኛ ወሬዎች ወይም መያዣ መጨበጫ የሌላቸው ውዝግቦችና የፀብ ማቀጣጠያ ሰበቦች ይሆናሉ፡፡ ምክክሮች ሁሉ፣የእልፍ መከራዎች ክምር፣ የቅንጥብጣቢ ሃሳቦች ግርግር፣ ወይም የጉም ሃሳቦች አሰልቺ ስብሰባ፣ ወይም በትንሽ በትልቁ የመከራከር፣ በብሽሽቅ ነጥብ የማስቆጠር ንትርክ ይሆናሉ፡፡

Read 1425 times