Saturday, 24 June 2023 20:57

ኬሮድ የጎዳና ሩጫ ዓለምአቀፍ

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

እውቅና ማግኘት ጀምሯል


        3ኛው ኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ሐምሌ 8 እና 9 በወልቂጤ ከተማ በ15 ኪሎሜትር ውድድር እንደሚካሄድ ታወቀ።  የጎዳና ሩጫው ከመላው ኢትዮጵያ ከ1000 በላይ አትሌቶች እንደሚሳተፉበትና  “ለሠላማችን እንሮጣለን” በሚል መርህ እንደሚካሄድ አዘጋጆች ገልፀዋል። የኬሮድ የልማትና የስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት ተሰማ አሰልጣኝ አብሽሮ እንደተናገረው የጎዳና ሩጫው በየክልል ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር እድል የሚፈጥርና  አትሌቶችን ወደ የዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚያሸጋግር ነው። ከታዋቂ አትሌቶች ጋር የሚሰራውና ልዩ ድጋፍ የሚያገኘው የጎዳና ሩጫው ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘትም ጀምሯል።
 የጎዳና ሩጫው በጉራጌ ዞን፤ ወረዳዎችና ከተሞች የሚደረገውን የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ እያነቃቃ መጥቷል። በዞኑ ዘቢደር የአትሌቲክስ ክለብ ተቋቁሞ ከ30  በላይ አትሌቶች እየሰለጠኑበት ናቸው። የልማትና የስፖርት ማህበሩ ለአትሌቶቹ የትጥቅ ድጋፍ በማድረግና የውድድር እድል በመፍጠር ተሳክቶለታል። የወልቂጤ ዮኒቨርስቲ ደረጃውን የጠበቀ የስፖርት አካዳሚ ለመገንባት ያቀደ ሲሆን ኬሮድ የልማትና የስፖርት ማህበር ደግሞ በዞኑ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የአትሌቲክስ የስልጠና ማዕከልና ካምፕ ለመስራት መጠንሰሱን አስታውቋል።
ኬሮድ የሚለው ቃል ትርጉሙ ሰላምን ማስተጋባት እንደሆነ በጋዜጣዊ መግለጫ የተገለጸ ሲሆን የጎዳና ላይ ሩጫው ከስፖርት ባሻገር ሰላምን ለማንፀባረቅ፤ በዞኑ የሚደረገውን የስፖርት እንቅስቃሴ ለማነቃቃት፤ የስፖርትና የቱሪዝም ትስስርን ለማጠናከር ያግዛል ተብሏል።
የኬሮድ ጎዳና ሩጫን እንቅስቃሴ በመደገፍ በርካታ ዓለምአቀፍ እውቅና ያላቸው አትሌቶች በጋዜጣው መግለጫው ተገኝተዋል። የዓለም የግማሽ ማራቶን ሪከርድ ባለቤትና የለንደን ማራቶን አሸናፊ ያዓለምዘርፍ የኋላው፤ የቶኪዮ ማራቶን አሸናፊዋ ፀሐይ ገመቹ፤ የለንደን፣ የቺካጎ ኒውዮርክ ማራቶንን ጨምሮ ዘጠኝ ዓለም አቀፍ ማራቶኖችን ያሸነፈው አንጋፋው ማራቶኒስት ፀጋዬ ከበደ፤የመካከለኛ ርቀት ምርጥ አትሌት አንዱዓለም በልሁና የማራቶን አትሌት  አየለ አብሽሮ የሚጠቀሱ ናቸው። የኬሮድ ልማትና ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት የሆነው ተሰማ አብሽሮ በጋዜጣዊ መግለጫው እንደጠቀሰው የጎዳና ሩጫውን በተሻለ ሁኔታ ለማካሄድ አንዳንድ ለውጦች ተደርገዋል። ዘንድሮ በ1ኪ.ሜ የዊልቼር ውድድር የጎዳና ሩጫውን እንደሚከፈት  የገለጸ ሲሆን የመሮጫ ቲሸርቱን የጥራት ደረጃ ማሳደጋቸውንም ተናግሯል። በቀጣይ ዓመት የህፃናት ውድድር ለመጨመርም ታቅዷል ብሏል።
የጎዳና ሩጫው ከመላው ኢትዮጵያ አትሌቶች እንደሚያሳትፍ የተናገረው ተሰማ  አብሽሮ፤ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ባደረገው ድጋፍ ሁሉም አትሌቶች ያለክፍያ መመዝገብ እንደሚችሉና የትራንስፖርትና የማረፊያ አገልግሎት እንደተዘጋጀላቸው አስታውቋል። በጎዳና ሩጫው ላይ አትሌቶችን ከኤርትራ ከኡጋንዳና ከእስራኤል ለማሳተፍም ልዩ ጥረት ተደርጓል። የኬንያ አትሌቶችን ለመጋበዝ የተሞከረ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የጅቡቲና የኤርትራ አትሌቶች እንደሚካፈሉበት ይጠበቃል ተብሏል።
ኬሮድ የልማትና የስፖርት ማህበር የጎዳና ሩጫውን ለማካሄድ ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ፣ ከጉራጌ ዞን አስተዳደር ጋር በቅንጅት እየሰራነው ከታላላቅ ኢትዮጵያ አትሌቶች  ጋር በወኪልነት የሚሰራውን ግሎባል ስፖርት ኮምዩኒኬሽንም ከጎዳና ሩጫው ጋር በማስተሳሰር የውድድሩን ዓለምአቀፍ ተደራሽነት መጎልበቱን ለማወቅ ተችሏል።
የጉራጌ ዞን አስተዳደር የስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አወል ጁማቶ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በሰጡት አስተያየት በጎዳና ሩጫው ወረዳዎችና ከተሞች ተሳታፊዎችን በጊዜ እንዲያስመዘግቡ እንሰራለን ብለዋል የከተማው አስተዳደር ሰላማዊ ውድድር ለማስተናገድና በአካባቢው የሚደረገውን የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት እንደሚፈልግም አስረድተዋል።
የወልቂጤ ዩኒቨርስቲን በመወከል በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት ዶ/ር አብዱል አዚዝ ሙሰማ በበኩላቸው በዩኒቨርስቲው የስፖርት አካዳሚ ለማቋቋም በዞኑ ከሚንቀሳቀሱ የስፖርት አካላት ጋር እየመከርን ነው ብለዋል።  
የንብ ባንክ ም/ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም ተስፋዬ ደግሞ ባንኩ በመላው ኢትዮጵያ በሚከናወኑ የተለያዩ የልማት ስራዎች በንቃት በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጸው በስፖርት ዘርፍ ትኩረት እንደምንሰጥ ከኬሮድ የጎዳና ሩጫ ጋር መስራታችን አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል። ኬሮድ የጎዳና ሩጫ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር ባህል ለማስተዋወቅ፣ የስፖርት ቱሪዝም ለማስፋፋትና ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት የጎላ ሚና እንደሚኖረው አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ ተናግሯል። በጎዳና ሩጫው ከ1ኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ለሚያገኝ ተወዳዳሪ አትሌቶች ከ75 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማትና ሜዳሊያ መዘጋጀቱንም አስታውቋል።
ተሰማ አብሽሮ ከሩጫ ዘመኑ በኋላ ወደ አሰልጣኝነት ሙያው ከገባ 9 ዓመታት ተቆጥረዋል። ከግሎባል ስፖርት ኮምኒኬሽንና ከNN የሯጮች ቡድን ጋር የሚሰራ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ 70 አትሌቶች (45 ሴቶች ናቸው) ጋር በመስራት ከፍተኛ እውቅናና ስኬት እያገኘ መጥቷል።

Read 917 times