Saturday, 24 June 2023 20:40

ኢትዮጵያ፡ የራዕይ ድህነት ያመጣው ጣጣ!

Written by  ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
Rate this item
(0 votes)

 የመንግስት ጆሮ ያጣው እውነት።  ብልፅግና ለራዕይነት ብቃት የለውም። ቢበዛ ብልፅግና የራዕይ ውጤት ነው። የፈጣሪ ራዕይ ለኢትዮጵያ የላቀ ነው። ያም ሰው-ነት ላይ ያተኮረ ነው።  ሰው መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ሰው ሰውን ገዥና ለሰው ተገዥ ሆኖ እንዲኖር በፈጣሪ አልተፈጠረም።  ሰው ተፈጥሮን እንዲገዛ እንጂ።  ሰው ግን ተባብሮና ተዋዶ ምድርን እየገዛ የምድርን በረከት ከመብላት ይልቅ፥ አንዱ ሌላውን ለመግዛት እየሮጠ እርስ በርስ መበላላትን መረጠ። ላባችንን የናፈቀችን ምድር፣ የደም መሬት አድርገን መርገምን አመጣን።
ሰው-ነት ላይ ከተሰራ ብልፅግናው ባለቤት አለው። ያም ሰው ነው።  ሰው እየፈረሰ የሚመጣው ብልፅግና ባለቤቱ የተጠመደ የጊዜ ቦንብ ነው።  ሰው-ነት ላይ ከተሰራ ብልፅግና መምጣት ብቻ ሳይሆን የመጣው ብልፅግና ሁለንተናዊና የሚፀና ይሆናል።  
ዓለም ብልፅግና ብርቋ አይደለም። ዓለም የተቸገረችው ሰው መኾንነትን ነው። ሱፐር ፓወር ሳይሆን የጠፋው ሱፐር ሞዴል ነው። በስንት ዝንተ ዓለም በረሀብ፥ በጦርነት ተሰቃይተን ስናበቃ፣ ትልቁ ራዕያችን ዳቦ መብላት ብቻ ሊሆን አይገባም። ኢትዮጵያን የሚመጥናት ሱፐር ሞዴልነት ነው።  ያኔ ከራዕያችን ጋር የሚሄድ የሰው-ነት ሰብዕና ይኖረናል። ያኔ ከእርስ በርስ ትግል ወጥተን፥ ከሥራ ጋር ትግል እንገጥማለን።  በሰብዕና ላይ ያተኮረ፥ ለሥራ ለመነሳት አቅም አለው።  የሚሰራ ደግሞ ይበለፅጋል።  
የኢትዮጵያ ቃል ባለፀጋ ሲል ከሀብታም በላይ ነው።  የፀጋ ባለቤት ማለት ነው። ትልቁ ፀጋ ለሰው ልጅ እራሱ ሰው መኾንነቱ ነው። ያንን ክቡር ቦታ ሰጥተን ዋና መካከለኛ ነገር ካላደረግን፥ ውጤቱ ደሙ የሚፈስ የተራበ ሕዝብንና ባለፀጋ የሆነ ሌባ ባለስልጣንን ማብዛት ነው።
የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ፤ የምድያም አገር መጋረጃዎች ተንቀጠቀጡ። ትንቢተ ዕንባቆም  3፡7
በድሀ የሚያላግጥ ፈጣሪውን ይሰድባል፤ በጥፋትም ደስ የሚለው ሳይቀጣ አይቀርም። መጽሐፈ ምሳሌ  17፡5
ድሀን የሚያስጨንቅ ፈጣሪውን ይሰድባል፤ ለድሀ ምሕረትን የሚያደርግ ግን ያከብረዋል። መጽሐፈ ምሳሌ  14፡31
ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፥ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል። መጽሐፈ ምሳሌ  19፡17
የድሀውን ጩኸት እንዳይሰማ ጆሮውን የሚደፍን ሰው፥ እርሱ ራሱ ይጮኻል አይሰማለትምም። መጽሐፈ ምሳሌ  21፡13
ድሀን በግድ አትበለው ድሀ ነውና፤ ችግረኛውንም በበር አትግፋው፤ እግዚአብሔር የእነርሱን ፍርድ ይፋረድላቸዋልና፥ የቀሙአቸውንም ሰዎች ሕይወት ይቀማልና። መጽሐፈ ምሳሌ  22፡22-23
ለድሆችና ለድሀ አደጎች ፍረዱ፤ ለችግረኛውና ለምስኪኑ ጽድቅ አድርጉ፤ ብቸኛውንና ችግረኛውን አድኑ፤ ከኃጢአተኞችም እጅ አስጥሉአቸው። መዝሙረ ዳዊት  82:3-4
እግዚአብሔር ለድሀ ዳኝነትን ለችግረኛም ፍርድን እንዲያደርግ አወቅሁ። መዝሙረ ዳዊት  140:12


Read 1560 times