Saturday, 28 January 2023 20:56

እስካሁን ያለፍነው ሁሉ ወደዚህ የሚያመጣን ነበር ይሄኛውም ነገ ወደ ሚመጣው የሚወስደን ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን፣ በአንድ ትልቅ ከተማ ውስጥ ከፍተኛ የፈረሰ ግልቢያ ውድድር ይካሄድ ነበር፡፡
የውድድሩ ዓይነት ግን ለየት ያለ ነበር፡፡ እንደተለመደው ፈጥኖ ቀድሞ በገባ ሳይሆን ተንቀርፍፎ ኋላ በመቅረት ነው፡፡ አራት ጋላቢዎች ነበሩ ለፍፃሜ የደረሱት፡፡
ጨዋታው አስደሳች ቢሆንም፣ ውጤቱ ግን እንደተለመደው አስደናቂ አልሆነም፡፡ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ሆነ!
ውድድሩ ከመቆም እኩል መስሎ ቀጭ አለ፡፡ ይሄኔ አንድ ጮሌ የአወዳዳሪው ኮሚቴ አባል አንድ ሀሳብ ሰነዘረ፡፡ ይሄውም፡-
“አራቱ ተወዳዳሪዎች ፈረሶቻቸውን ይቀያየሩ፡፡ ያኔ ሁላቸውም በሰው ፈረስ አንደኛ ለመውጣት መጭ ማለታቸው አይቀርም፤ ለየፈረሰኞቹም ቲፎዞው ህዝብ ጩኸቱን በእጅጉ ማስተጋባቱ አያጠያይቅም፡፡ ጃልሜዳ ሙሉ ህዝብ አለ! ሁሉም በሀሳቡ ተስማሙና ውድድሩ ሽምጥ ግልቢያ ሆነ፡፡ ፈረስ ከኮለኮሉት ሥራው መጋለብ ነው፡፡ መንቀርፈፍማ በምን ዕድሉ!
ቀጣዩ ስነሥርዓትም፣ የውጤትና የማዕረግ መንጋ ማወጃ ሆነ፡፡ የየፈረሱ ደጋፊ የሆኑ ሹማምንትም ጮኸው አይናገሩ እንጂ፣ ክቡር ትሪቡኑ ላይ ተሰይመዋል! የየራሳቸውን ድጋፍ በሆዳቸው ይዘዋል! ጋላቢው ሁሉ ከሰው ፈረስ ወርዶ የየራሱን ፈረስ ጋማ እያሻሸ ቆመ፡፡ ሁሉም ጋላቢ ፊት ላይ በፈረሱ የመኩራት ስሜት ይነበብ ነበር፡፡
በውድድር ዓለም እንዲህም ዓይነት ውድድር አለ! ግጥሚያው የፈረሰኞቹ ብቻ ሳይሆን የፈረሶቹም ጭምር የሆነ፡፡ ውጤቱም የዚሁ ፍሬ ነው!
የእኛ ተወዳዳሪ ፓርቲዎችስ፣ ፈረስ ቢለዋወጡ እንዴት ይሆኑ ይሆን? ብሎ ለመጠየቅ ይቻላል። በእውነት የተለያዩ ፈረሶች አሏቸውን? ፓርቲዎቹ ከአርማና ቀለም የተለየ ምን ልዩነት አላቸው? ጋላቢዎቹስ ምን ያህል የክህሎት፣ የልምድ ፣ የዕውቀት፣ የትግል ልምድ አላቸው? መንቀርፈፍን ትተው ዋናውን እሽቅድድም እንዴት ይወጡት ይሆን? የሚያቋርጥ ይኖር ይሆን? በመካከል  ከፈረሱ የሚወርድ ይኖራል? በእሽቅድምድሙ መጠላለፍስ? ዳኞችስ አያዳሉም ? …ዘርፈ ብዙ   ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ድምፅ መስጠት ቢኖር እጅግ አሳሳቢ በሆነ ነበር! ሳይደግስ አይጣላም ! በታሪክ በሀገራችን የተካሄዱ ምርጫዎች ሰርተው የሚሄዱት የድምፅ አሰጣጥን ሁኔታ ዞሮ መመልከት ይበቃል! ለየ ትውልዱ የሚበቃና የሚዳረስ መዝገብ ትተውልናል፤ አንብቦ መረዳት የየባለጉዳዩ ፋንታ ነው፡፡
ከልምዱ መማርም እንደዛው (የተቀደደና የጠፋ ሊኖር ቢችልም እንኳ!) ይሁን፤ ከታሪክ የማይማር ፈንጅ መርማሪ ብቻ ነው! ተብሏልና እንቀበለው፡፡
ተስፋ መቁረጥን ወደ ጎን በመተው፣ እረጅም እርቀት የሚጓዙ ንፁሀን ናቸው! በአጭር ጊዜ ድል የሚሹ ደግሞ ዘላቂ አይሆኑም፡፡ የትግል ውስብስብነትና ረቂቅነት፤ በአንድ በኩል ግልፅና የሚጨበጥ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ህቡዕና ግራ ገቢ መሆኑ ላይ ነው፡፡ በዚያ ላይ እንደጥንቱ አባባል “ረጅምና መራራ መሆን አለበት” በሚሉ ይብሱን ዝግጁነትና ጥንቃቄ የሚጠይቅ ያደርገዋል፡፡ ዞሮ ዞሮ የሁሉም መጠቅለያ ግን መሰዋዕትነትን መሻቱ ነው የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የንብረትና የህይወት ዋጋን ማስከፈሉ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንደኛ አገር ምዝበራና ጦርነት የማይሰማው ሲሆን ደግሞ “ከእቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” የሚባለውን ስዕል ያመጣል፡፡ የታሪካችን ድግግሞሽ ከላይ የጠቀስነውን መሰረተ ጉዳይ ሁሉ አሻራውን አሳርፎበታል፡፡ በዚህም ሳቢያ ሁሌም ጀማሪዎች ሆነን እንገኛለን። ጥናቱን ይስጠን!
“ምንግዜም ስንል እንደኖርነው ዛሬም አረፈደም!” እንላለን፤ ምነው ቢሉ፤ (all that had gone before was a preparation to this, and this , only a preparation to what is this to come.) (እስካሁን ያሳለፍነው ሁሉ ወደዚህ የሚያመጣን ነበር፡፡ ይሄኛውም ነገ ወደ ሚመጣው የሚወስደን ነው)  
ስለዚህ እኛም  መንገድ እንድንጀምር አስበን እንዘጋጅ!

Read 1930 times