Sunday, 22 August 2021 13:17

“የአገራችን የድርሰት ነገር ብልጭ ዕልም እያለ ነው!”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ስንቅነህ እሸቱ (ኦ‘ታም ፑልቶ) “40 ጠብታዎች” የግጥም መድብል፣ "የፈላሱ መንገድ”፣“የኤላን ፍለጋ” “ኬክሮስና ኬንትሮስ” ጽሐፊ፣ “ሺህ የፍቅር ዲቃላዎች” “Catch With Thunder” የተሰኙ መጻህፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡ ለብዙ ጊዜያት ግን ጠፍቷል፡፡ ለመሆኑ የት ጠፋ? ከአዲስ አድማስ ጸሃፊ ሳሙኤል በለጠ (ባማ) ጋር በሕይወቱና የድርሰት ሥራዎቹ ዙሪያ አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡

          እስቲ ስለ ልጅነትህ አጫውተን?
የተወለድኩት ኮንሶ ነው። ደብዛዛ ምሥሎች ኮንሶ ላይ ይታዩኛል። አንዳንዴ የማስታውሰውን ነገር ስናገር፣ "ይህንን ልታስታውስ አትችልም" ይሉኛል። ልጅ ሆኜ ኮንሶ ላይ አመጽ ያለ ይመስለኛል። ለአባቴ ስነግረው፤ "ከእኛ ሰምተህ ነው" ይለኝ ነበር፤ እኔ ግን አስታውሳለሁ፤ ፍዝዝ ብሎ ምሥሉ አሁንም አዕምሮዬ ላይ አለ፤ አባቴ ወታደር ነበር፤ ከቦታ ቦታ ይዘዋወራል። ኮንሶ ብዙ ሳንቆይ ወደ ጂንካ ሄድን፤ እስከ 3ኛ ክፍል ጂንካ ነው የተማርኩት። ጣፋጩን የልጅነት ጊዜዬን ያሳለፍኩት ጂንካ ነበር፤ ከተፈጥሮ ጋር ቅርበት ነበረኝ፤ አንዲት ትንሽ አበባ ነበረች፤ መሬት ተጠግታ የምትበቅል፤ አጠገቧ ሄደህ ስትዘፍንና ስታጨበጭብ አበባዋ ይዘጋል። የሆነ ዘፈን አለ እሱን ካልዘፈንክ አትሰበሰብም ይባላል። ቡልጋር ነው ዘፈኑ.. እኔ ግን በማጨብጨብ ሌላ ዘፈን እየቀየርኩ፣ በተለያየ መንገድ እሞክር ነበር፤ ትሰበሰባለች፤ ስለዚህ ሰዎች የሚሉት ነገር ልክ ላይሆን ይችላል ማለት ጀመርኩ፤ ”Catch with thunder” መጽሐፌ ላይ ሞኛሞኝ ገጸ ባህሪ አለ፤ ዝም ብሎ የከለከሉትን የሚሞክር ገጸ ባህሪ ነው። ገጸ ባህሪውን የሳልኩት ከራሴ የሕይወት ተሞክሮ ተነስቼ ነው። ለምሳሌ ወደ ሙሉ ጨረቃ ፊትህን አዙረህ ከሸናህ "መሽኒያህ ይደፈናል" ይባላል፡፡ እኔ ወደ ሙሉ ጨረቃ ፊቴን አዙሬ እሸና ነበር፤ ያው ሞኝነት ነው። ከተደፈነ ከሰርክ ማለት ነው! ግን በድፍረት እሞክረው ነበር፡፡ አንድ ኪንታሮት የነበረበት የጎረቤት ልጅ ነበር፤ "ኪንታሮት ከቆጠርክ ኪንታሮት ይወጣብሃል" ይለኛል፤ እኔ ግን እቆጥርለት ነበር፡፡ ወደ ወንዝ እንሄድ ነበር፤ "ገበሎ ዲንጋይ ላይ ቁጭ ብሎ አንገቱን ካሰገገ ሴቶችን እየመረቀ፣ ወንዶችን እየረገመ ነው" ይባላል፣ "ገበሎውን የገደለ ሠይጣን ይወጣበታል" ይባላል፤ እኔ ለመግደል እሞክር ነበር፤ እነዚህ የማረሳቸው የልጅነት ትውስታዎቼ ናቸው።
የትምህርት ቤት ቆይታህስ?
ሃይስኩል የተማርኩት አርባ ምንጭ ነው። አሁን ላለኝ አመለካከት መሠረት የሆነኝ ትምህርት ቤት ገብቼ የተማርኩት ትምህርት ሳይሆን፣ ከተፈጥሮ ጋር የነበረኝ ትስስር ነው። አባቴ ከቦታ ቦታ ሲሄድ ለእኔ ትልቅ ትምህርት ነበር፤ ምክንያቱም ከተረት ወደ ተረት፣ ከአንድ ባህል ወደ ሌላ ባህል፣ ከአንድ ጊዜ ወደ ሌላ ጊዜ እየተጓዝኩ ነበር። ጊዜን እንደ ተራራ ብታየው -- የሆነ ማሕበረሰብ ግርጌ ላይ ቢሆን፣ ሌላው አናት ላይ ቢሆን፣ አንድን አመት እየኖርክ የተለያየ ጊዜ ላይ ነው የምትኖረው፤ ይህ ነገር ሳስበው ያስገርመኛል። የተረት ዓለም ከትምህርቱ ዓለም ይስበኝ ነበር፤ አያቴ አተቴ ታመልክ ነበር፤ አንድ ጊዜ ታማ ከግድግዳ ጋር ያጋጫታል። "ገበያ ላይ አውጥቼ ዛፍ ላይ ሰቅዬ አሰቃያታለሁ" እያለ ይጮኻል። ከጎረቤት ሰዎች መጥተው ምስ ጠይቀው፣ ባሩድ ስታሸት ዳነች፤ አሁን ሳስበው ይደንቀኛል። ሙጼ የሚባል ስርዓትም ነበር፤ በሽታ መጦ ያወጣል ይባላል፡፡ እናቴ በሙጼ ስርዓት ትታከም ነበር፤ አንድ ቀን ሙጼውን አየሁት፤ እንዴት ይሆናል? ብዬ ተደምሜ ነበር፤ በመንፈሳዊ ዓለም ምንም ገደብ የለም ማለት የጀመርኩት ያኔ ነው። እኒህን ነገሮች ወደ ታሪክ እቀይራቸዋለሁ፤ በትምህርት ቤት ተማርኩኝ አልልም፤ ገብስና ስንዴን ሳልለይ ነው ግብርና ተማርኩ የምል የነበረው፡፡ ትምህርቱ ብዙም ስለማይስበኝ አነብ ነበር፡፡
ድርሰት የሙሉ ጊዜ  ሥራህ ነው?
አይደለም፤ ተጨማሪ ሥራ እሰራለሁ። መቀሌን ጨምሮ በተለያዩ ክፍለ አገራት እየተዟዟርኩ ሰርቻለሁ፤ በእነዚህ ቦታዎች ላይ መስራቴ ጠቅሞኛል። ግብርናን የተፈጥሮ ሃብትን በደንብ ያወቅኩበት ጊዜ ነበር፤ የገጠሩ ሕይወት ያስደንቀኝ ነበር፤ ጽሑፎቼ ላይም ይንጸባረቃል፤ ያጠናሁት “Landscape architecture” ነው። አሁን የምሰራው በዚሁ ዘርፍ ነው።
"40 ጠብታዎች" የግጥም መድበልህ  ከታተመ በኋላ፣ ወደ ቻይና ሄድክ፤ እዚያ ምን ሰራህ?
ይገርምሃል፤ በወቅቱ ለውጥ ፈልጌ ነበር፤ ዲቪ  ሞላሁ፤ ቻይና አገርም እስኮላርሺፕ ሞላሁ (ያኔ ወደ ቻይና መሄድ እምብዛም አይታወቅም) ዲቪውም የቻይና እስኮላሩም እኩል መጡ፤ ዲቪውን ትቼ በ1997 ዓ.ም ወደ ቻይና ሄድኩ፤ ቻይናን ማወቅ እፈልግ ነበር፤ እዚህ ሆኜም አነብ ነበር፤ "ግማሽ እስኮላርሺፕ እየከፈልክ ትማራለህ" ተብዬ ነበር፤ ነገር ግን እዛ ስሄድ እየተቸገርኩ የምበላው እያጣሁ ነው የተማርኩት፡፡ እንደዛም ሆኖ የሰውና የተፈጥሮ ትስስርን፣ ባህልንና ተፈጥሮን በቅጡ የተረዳሁት እዛ ነው። የቻይናውያን “Landscape History” ያስገርማል። ፍልስፍናቸው ይደንቃል። በአኗኗራቸው፣ በአለባበሳቸው፣ በሕክምናቸው Abstract (ሥውር አስተኔ) የሆኑ ነገሮች ሥጋ ይዞ ታያለህ፤ አጸዳቸውን ብትመለከት የብዙ ሃሳቦች ጥምር ነው። ቅኔያቸው ሰፊ ነው። ቻይናውያን “በጀበና ውስጥ ዓለምን መስራት” የሚል አመለካከት አላቸው፤ ቻይና መሄዴ እና “Landscape architecture” መማሬ ሰውና ተፈጥሮ የሚለውን ቃል ሰጠኝ። (ፊትም ሳላቀው እጠቀመው ነበር) የባህልና የተፈጥሮ ግንኙነትንም ድርሰቶቼ ላይ ታያለህ (ለምሳሌ የአርባ ምንጭን አቀማመጥ) ለምሳሌ ጉልቻ ሊኖር ይችላል፤ አንተ ምግብ ታበስልበታለህ በዛ ብቻ አይወሰን ጉልቻ ትዳር ነው። አድባርን ውሰድ መንፈስ ነው፣ የምትማማልበት፣ የምትታረቅበት ነው። ጋሞ ውስጥ አንዲት ሴት በአድባር አጠገብ ወተት ይዛ ስታልፍ ወተት ጠብ አድርጋ ነው። የምታልፈው ስለዚህ ይህ ዛፍ ውጪ ብቻ ያለ ዛፍ አይደለም ውስጣችንም ውስጥ ያለ ዛፍ ነው። ግንኙነቱ ይህ ነው።
እንዲህ ያሉ ባህሎች እየጠፉ መምጣታቸው--- ?
በጣም ጎድቶናል፤ የኔም ስራዎች ላይ ሰውና ተፈጥሮ ርዕሶቼ የሆኑት ለዛ ነው። አንዱ ወደዛ የወሰደኝ ነገር “Australian Aborigines practice" ነው። የኤላን ፍለጋ ላይም ጠቅሼዋለሁ፤ አገረ አውስትራሊያውያን አገራቸውን በተረት ቀድመው ካርታ ሰርተዋል። "Dream line Song line" የሚሉት ነገር አለ፤ አጠቃላይ ታሪኩ የሚያወራው ከሕልም ዓለም ወደ ምድር እንዴት እንደመጡ ነው። ለምሳሌ ስለ ተራራው ዘፈን ወይ ተረት አለ፤ ይህንን ካወክ የትም ብትሄድ አትጠፋም፤ በተረት አንተና ተፈጥሮ የአንድ ትልቅ ሕይወት የተለያዩ ገጽታዎች ናችሁ ማለት ነው። ይህንን ሳስብ ሰው ከተፈጥሮ ጋ ሲኖር አንዳች ትስስር መፍጠሩ አይቀርም፤ አስበው የተረትን ጉልበት፤ ይህንን ሃሳብ ወደ እኛ አገር ማምጣት እፈልጋለሁ፤ እኛም ያለውን እውነታ መመርመር አለብን፤ ከየት ተነስተን ወዴት እንደምንሄድ ማወቅ አለብን!
አንዳንዶች--- ሥራዎችህን ግራ ያጋባሉ ይላሉ፤ አንተ ምን ትላለህ ?
 እኔ በእድሜ ብዙ ከሄድኩ በኋላ ነው ወደ ሥነ ጽሑፍ ዓለም የገባሁት፤ ሥነ ጽሑፍ ባህል መፍጠር እንደሚችል ስላመንኩ ነው የምጽፈው፡፡ ጽሑፍ የግድ ትርጉም መስጠት አለበት ብዬ አስባለሁ፤ የገጠር ተረቶችን ስትሰማ ትርጓሜ ካልፈለክላቸው ስሜት ላይሰጡ ይችላሉ፤ ሥነ ጽሑፍ ለውበት ይጻፍ በሚለው አላምንም፤ የሰውንም ሕይወት መቀየር መቻል አለበት፤ ያለዛ አልጽፍም፤ ስለዚህ የምጽፈው- የሰውን አስተሳሰብ ያበለጽጋል ብዬ ስለማምን ነው። ወይም አንባቢ ካነበበ በኋላ “ውቅያኖስ ሃሳብና ራዕይ አዕምሮው ውስጥ ባይፈጥር እንኳን ጠብታ መፍጠር አለበት” ብዬ ስለማምን ነው። እንዲህ ካልሆነ መጻፍ ዋጋ አለው ብዬ አላስብም፤ ስለዚህ አንባቢ የራሱን ትርጓሜ መፈለግ አለበት!
ምን አይነት አጻጻፍና ጸሐፊ ይማርክሃል?
እኔ መጽሐፍ የሚማርከኝ በእያንዳንዱ መስመር ላይ የተጠቀመው ቃልና አገላለጽ ሃይል ሲኖረው። ቅኔ ሲኖረው፣ ውበት ሲኖረው--- እንዲህ ዐይነት ጽሑፎች ደስ ይሉኛል፡፡ አንድ ወዳጄ የጻፈውን ልንገርህ፡- ይሁዳን እንደ ቅዱስ አድርጎ ስሎታል። ከይሁዳ አንጻር የክርስቶስን ታሪክ ይተርክልናል። ጽሑፉ ላይ ይሁዳ ራሱን ልክዳ አልክዳ እያለ ሲያቅማማ ታያለህ፤ ይህ ለእኔ ከሚጮኸለት ታሪክ ባሻገር የማየት ችሎታ ነው። እንዲህ ዐይነት አጻጻፍ እወዳለሁ፤ ነገር ግን  አጻጻፉ ውበት ከሌለው ምንም ጥሩ ታሪክ ቢኖረው ለማንበብ ልቸገር እችላለሁ።
ለጥቂት ዓመታት ጠፍተሃል፤ በደህና ነው?
በድሮ ሂሳብ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የትም ቀርቶብኛል። (ብሩ የኔ አልነበረም፤ ከቤተሰብ የተበደርኩት ነው።) አሁን መጽሐፍ የማሳትምበትም ገንዘብ የለኝም! ላሳትምልህ ብሎም የመጣ የለም እንጂ ይዤው የምቀርበው ስራ አላጣሁም! ይህ ነው ያጠፋኝ፡፡
መሰናበቻ "40 ጠብታዎች” ከሚለው የግጥም መድበል ----
- ሕብረ - ነፍስ
ሕብረ - ነፍስ
ተንሰቅሳቂ ልቤን
ፈረሰኛ ደስታ
አፍነከነከልኝ፤
በዓለም አንድ ጥግ
አንዲት ነፍስ አዜመች
ዘመረች መሰለኝ።

Read 2013 times