Monday, 15 March 2021 00:00

"ከአላማጣ በኋላ የሚኖረው ጉዞ አስቸጋሪ እንደሚሆን ተነግሮን ነው ያቋረጥነው"

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   https://youtu.be/6lZ9OZtGm5A?t=15

በትግራይ ያለው ሁኔታ በጥንቃቄ ካልተያዘ አድዋን ላንዘክር የምንችልበት ጊዜ ይመጣል የትግራይ ህዝብ ከደረሰበት የስነ-ልቦና ጫና መውጣት    አለበት
             125ኛውን የአድዋ ድል ምክንያት በማድረግ፣ 125 “የጉዞ አድዋ 8” ተጓዦች በየዓመቱ እንደተለመደው ጉዟቸውን በየጊዜው ነበር የጀመሩት። 600 ኪ.ሜ እንደተጓዙ ግን አላማጣ ላይ  ችግር ገጥሟቸዋል ጉዟቸውንም ለመግታት ተገድደዋል። ለምንና? እንዴት?  በዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከጉዞ አድዋ መስራች አርቲስት ያሬድ ሹመቴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

          የዘንድሮው ጉዞ አድዋ ተጓዦች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሶሎዳ ተራራ አናት ድረስ መዝለቅ አልቻሉም። ምን ገጠማቸው?
በዘንድሮው ጉዞ አድዋ በእኛ እምነት፣ በበቂ ሁኔታ በስኬት ተልዕኳችንን አጠናቀናል ብለን ነው የምናምነው፡፡ እርግጥ ነው አድዋ አልገባንም። አድዋ ያልገባንበት ምክንያትም ግልፅ ነው። አሁን በትግራይ ላይ ባለው የፀጥታ ሁኔታ ከአላማጣ በላይ ጉዟችንን መቀጠል አልቻልንም። እኛ ሁሌም ማረጋገጥ የምንፈልገው ጉዞ አድዋ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ መካሄዱን ለአገር የምናረጋግጥበት መንገድ ነው። በመሳሪያ ታጅበን መጓዙን በፍፁም አልፈለግነውም። እኛ በተለየ መንገድ በመሳሪያ ታጅበን ብቻችንን ሆነን ብናልፍ፣ ሰላም ያጣ ህዝብ በአካባቢው እያለ እኛ ሰላም እንዳለ አድርገን ተጉዘን ብንጨርስ፣ ይሄ ለሌላው የተሳሳተ መልዕክት ማስተላለፍ ስለሆነ ተገቢ አይደለም። በዚህ ምክንያት ሰላም እስካለበት ቦታ ድረስ ያለውን ተጉዘን እዛ ላይ መግታቱ በቂ ነው በሚል ጉዟችንን አላማጣ ላይ አድርገናል። ይህ ማለት ከአዲስ አበባ 600 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነው ያጠናቀቅነው።
በፀጥታ አካላት እንዳታልፉ ተደርጋችሁ ነው ወይስ ራሳችሁ ናችሁ ጉዞውን ያቆማችሁት?
ከፀጥታ አካላት ጋር ምክክር ነው ያደረግነው እንጂ የከለከለን የለም። እንዳልኩሽ ከአላማጣ በኋላ የሚኖረው ጉዞ አስቸጋሪ እንደሚሆን ነው በፀጥታ አካላት የተገለጸልን። አንዱ የነበረው አማራጭ በፀጥታ ሀይል ታጅቦ መሄድ ነው። ይህም ቢሆን አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። እኛም ጉዞ አድዋ የሰላም ጉዞ መሆኑን የምናረጋግጥበት መንገድ በመሆኑ ታጅበን  የመጓዙን ነገር በጭራሽ አልፈለግነውም። የፀጥታ ችግሩ የተከሰተው  ጣሊያን አገራችን (አድዋ) ገብቶ ቢሆን ኖሮ፤ አስፈላጊወን መስዋዕትነት ከፍለን ጉዞውን እንቀጥል ነበር። አሁን አገራችን ላይ የተከሰተው ጉዳይ አንደኛው ወገን “የህግ ማስከበር” ይለዋል፤ ሌላው ወገን “ጦርነት” ይለዋል። ግራና ቀኝ መሳሳብ ስላለ ቃላት አጠቃቀም ላይ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በእኛ እምነት ወቅታዊው የአገራችን የፀጥታ ሁኔታ አስጊ ነው ብለን ነው የምንጠቅሰው። ስለዚህ አላማጣ ላይ ጉዟችንን አቁመናል።
ጉዞው ሲጀመር የወቅቱ የአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ለጉዞው አያሰጋችሁም ወይ የሚል ጥያቄ አቅርቤልህ “ጉዞ አድዋ “አገር ሰላም ስትሆን የምንተገብረው አገር ሰላም ሲደፈርስ የምንሰርዘው ጉዞ አይደለም የህዝቡን ሁኔታና ችግር ቦታው ላይ ተገኝተን እንጋራለን” የሚል ምላሽ ሰጥተኽኝ ነበር?
ትክክል ነው። ቅድም እንዳልኩሽ ጉዞውን በተመለከተ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር ምክክር አድርገን ነበር። ክልከላ አልነበረም። ምን ማለት ነው? የፀጥታ ሀይሉ ከዚህ አልፋችሁ እንድትጓዙ አንመክርም ነው ያሉት። ይህ በሆነበት ሁኔታ ሃላፊነቱን ወስደን ብንጓዝና ከተጓዦች መካከል ህይወቱን የሚያጣ ቢኖር፣ ለሀገር ሌላ ችግር መፍጠር ነው የሚለውን ነገር ነው ያየነው። አየሽ አንድ ነገር በተጓዦች ላይ ቢከሰት፣ በአገር ላይ ሌላ የመፋጫ፣ የመዋቀሻና ጎራ ለይቶ መደባደቢያ አጀንዳ ነው የምንሆነው። በነገርሽ ላይ ግልፅ ማድረግ የምፈልገው መንግስትም ሆነ የቀደመው የትግራይ ክልል ሀይል ከእኛ ጋር የተለየ ጠብ የለውም። ከዚህ ቀደም ትግራይን ከምንረግጥበት ዕለት አንስቶ እስከ ፍፃሜው ሶሎዳ ተራራ ድረስ የእነሱ ሀይል አጅቦ፣ እያበላ እያጠጣና እያስተናገደ ይወስደን ነበር- ልክ እንደ ትግራይ ህዝብ ማለቴ ነው። ምናልባት ቅሬታ ያለን የመጨረሻዋ የመድረክ ቀን ላይ እንደ ልባችን የዳግማዊ አፄ ምንሊክንና የሌሎችን ጀግኖች ስም እየጠራን ለመዘከር ገደብ የተጣለብን መሆኑን ነው። በተረፈ በደህንነት ደረጃ እኛን ችግር ውስጥ የሚያስገባ ነገር በፊት አልነበረም። ያኔ የሚጠብቁንና አጅበው የሚወስዱን አካላት እኛን ያጠቁናል ብለን አናስብም። ነገር ግን አሁን ያለው የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ግልፅ ነው። ይህንን እያወቅን “ከዚህ ማለፋችሁ አይመከርም” እየተባልን፣ ሃላፊነት ወስደን መሄድ ለአገር የሚያመጣውን ችግር በማየት ለማቆም ተገድደናል።
እንደሰማሁት ከጉዞው አስተባባሪዎች መካከል ጥቂቶቻችሁ ከመቀሌም አልፋችሁ ሁኔታዎችን ለማየትና ህዝቡን ለማነጋገር ሞክራችኋል”፡፡ እስኪ ያያችሁትን የታዘባችሁትን ጉዳይ አጋራን?
እውነት ነው፤ አስተባባሪዎቹ ከአላማጣ ተነስተን መቀሌን አልፈን እስከ ውቅሮና አካባቢው ያለውን ሁኔታ ለመገንዘብ ሞክረናል። ያየነው ችግር በእኛ እምነት፣ በኢትዮጵያ  ለዘመናትና ለትውልድ የሚተርፍ ቁርሾ እንዳያፈራ የሚያሰጋ፣ የስነ-ልቦና ጉዳት መድረሱን አስተውለናል። እናም የትግራይ ህዝብ አሁን ባለበትና በተያዘው መንገድ የሚተውና በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ፣  ሁኔታው እስከ ዛሬ በተያዘው የብሽሽቅ መንገድ ከቀጠለ ምናልባትም ምን ሆናል መሰለሽ? ዶጋሊ የኤርትራ ክፍል በመሆኗ የዶጋሊ ድልን ማክበር እንዳ ቆምነውና ራስ አሉላንም አብረን መዘከር እንዳቆምነው ሁሉ አድዋንም ላንዘክር የምንችልበት ጊዜ ይመጣል። እንደሚታወቀው በአብዮቱ ዘመን የዶጋሊ ድል በየዓመቱ ጥር 18 ላይ ለዶጋሊ መታሰቢያ ይደረግለት ነበር። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትነጠል ይሄንንም ድል ማክበር አቆምን። ራስ አሉላም አይዘከሩም።  አሁን ባለው ሁኔታ እኛ አድዋ አልገባንም ማለት፣ በቀጣይ አድዋን ለማክበር ራሱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንደ አገር መግባታችንን ያሳያል። ምክንያቱም እኛ ከህዝቡ ውስጥ ለተጨማሪ ብሽሽቅ መግባት አንፈልግም። ለምን ካልሽኝ ህዝቡ ጥያቄ አለው። እያንዳንዱ ቦታ ላይ ያስተዋልነውና ያየነው ነገር በሁለት መንገድ የተወጠረ ነው። ከውጪ ያለውና የትግራይን ጉዳይ አንስቶ የሚሟገተው አካል የያዘበትና መንግስት ጉዳዩን የያዘበት መንገድ ከፍተኛ ውጥረት ያለበት ነው። መሀል ላይ ያለውን ህዝብ ስታይው ግን ከፍተኛ የስነ-ልቦና ጉዳት ላይ መውደቁን ትረጂያለሽ። የወደሙ ንብረቶች አሉ፣ መቀሌን ስንመለከት የከፋ የሚባል ቁሳዊ ጉዳት የለም። የሞራልና የኢኮኖሚ ውድመት ግን አለ። እንቅስቃሴው በሙሉ ዝግ ነው። ስለዚህ ኢኮኖሚው እየሞተ ሰው እንዴት በልቶ ሊያድር ይችላል? እንዴትስ ሰርቶ መግባት ይችላል? ይህ ትልቅ  ችግር ነው።
ውቅሮን ስንመለከት ከፍተኛ ውድመት የደረሰበት፣ የተዘረፉ ቤቶች፣ የተሰባበሩ እቃዎች ፣ በጥይት የተበሳሱ መስታዎቶች፣ የተዘረፉና ኦና የቀሩ ቤቶችን አይተናል። በየመንገዱ ግራና ቀኝ ላይ በርካታ የወደሙና የተቃጠሉ የጦርና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን ተመልከተናል። መንገዶችም አሁን ታድሰው ይሆናል እንጂ ያ ሁሉ ውድመት ሲደርስ አብረው  ወድመው እንደሚሆን መገመት አያዳግተም። የመታደስ ምልክትም አይተናል። በሌላ በኩል፤ ህዝቡን ለማናገር ሞክረን ነበር። እኛንም ይቀበሉን  የነበሩ ሰዎች ጋር ለመነጋገር እንደሞከርነው ኢትዮጵያዊነታቸው ላይ ጥያቄ ምልክት እንደፈጠረባቸውና የስነ-ልቦና ጉዳት እንደደረሰባቸው አስተውለናል። በምን ምክንያት ይህ ጉዳት ደረሰባቸው ብትይኝ እኔ ልተነትነው አልችልም።
መልሱ ፖለቲካዊ ሊሆን ይችላል። ግን በአጠቃላይ የትግራይ ህዝብ ሰላም አግኝቷል ብሎ ተረጋግቶ መቀመጥ እንደ ሀገር ዋጋ ያስከፍለናል። የአድዋን ድልም እንዳናከብረው የሚያደርግ የትውልድ በደል ወይም ጥላ ሊያጠላበት ይችላል የሚለው ስጋትም  አለን።
ተጓዦች ጉዞውን መጨረስ እንደማይችሉ ሲነገራቸው ምን ተሰማቸው?
በፀጥታ አካላት ጉዞውን መጨረስ እንደማንችል ሲገለጽልን ተጓዦች ቁጭት ነበር የተሰማቸው።  ቁጭቱ አድዋ አለመግባታችን ሳይሆን እንዳንገባ ያደረገን ምክንያት ነው። የመጀመሪያ ፍላጎታችን የነበረው አድዋ መግባት ነው። አድዋ መግባት እንፈልጋለን። እንደ ምንም ብላችሁ አድዋ አድርሱን አላልንም። እንደዛ ካልናቸው አጅበው ነው የሚወስዱን። ይህንን ካደረግን ቅድም እንዳልኩሽ “እኛ ሰላም ደርሰን ተመልሰናል፤ ሁሉም ሰላም ነው” የሚል የተሳሳተ መልዕክት ከማስተላለፍ ውጪ ለአገራችንም የምናተርፈው ለህዝቡም የምንፈይደው ነገር የለም። እኛም አጅባችሁ ውሰዱን አላልንም እነሱም አልጠየቁንም። ስለዚህ ቀደም ሲል እንደገለፅኩልሽ ጉዟችን ስኬታማ ነው የምንለው እስከምንችለው ተጉዘንና ያየነውን አይተን ተመልሰናል። ይህንን ለህዝብ መናገርና ማሳወቅ ደግሞ ሌላ ስኬት ነው የምንለው። ስለዚህ ትግራይ ላይ ያለው ጉዳይ እስካሁን በተያዘው ሁኔታና መንገድ ተይዞ የሚቀጥል ከሆነ ምናልባትም የአድዋ ድልን ልናጣም እንችላለን። ይሄንን በአፅንኦት መናገር እፈልጋለሁ።
በትግራይ ያለውን ጉዳይ በምን መልኩ መፍታት ይቻላል ትላለህ? ምን ምን አማራጮችስ ይታዩሃል?
እንግዲህ ከስር መሰረቱ መፈተሽ ያስፈልጋል። አሁን በተካሄደው የፀጥታ ውትርክ በመንግስት አካባቢ ውትርኩን ከአድዋ ጦርነት ጋር የማመሳሰል አዝማሚያ ታይቷል።
አድዋ ከውጭ ወራሪ ጋ የተካሄደ የነጮችን የበላይነት መንፈስ ሰብሮ የሰው ልጆችን እኩልነት ያረጋገጠ ለአለም ነፀብራቅ የታየበት ድል ነው። አሁን ያለው የአገራችን ወቅታዊ ውትርክ በታሪክ አይን ስናየው ሰገሌን እንጂ ፈፅሞ አድዋን  አይመስልም።  
ታሪክ እንደሚነግረን፤ ሰገሌ በንጉስ ሚካኤልና በልጅ ተፈሪ (ራስ ተፈሪ) ጦር የመሀል አገሩ ጦር  የተደረገ ጦርነት ነበር። በወቅቱ በስሙ ቤተ-ክርስቲያን እስከ መሰየም ድረስ ተደርሷል። ለዛ ድል ስላበቃኸን ተብሎ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ተሰይሟል። ዘመን ካለፈ በኋላ ግን 100ኛ ዓመቱ ላይ እኛ አስታውሰነዋል። የታሪካችን አካል ነው። ስለዚህ የወቅቱ ውትርክ የአድዋን ሳይሆን የሰገሌን ነው የሚመስለው። የትግራይን ጉዳይ በአዳዲስ መንገዶችና የመፍትሄ ሀሳቦች፣ እስከዛሬ ባልተካሄደበት አዲስ  መንገድ ሰላም መፈጠር አለበት። ይሄንን ከእኛ ውጪ ያሉ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችም ሆኑ ማህበራዊ አንቂዎች ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው። በምንም ተባለ በምንም. ህዝቡ ከደረሰበት የህይወት ጫና፣ የስነ-ልቦና ስብራትና  ምስቅልቅል መውጣት አለበት። ለዚህ ደግሞ አዲስ የሰላም መንገድ መፈጠር አለበት ባይ ነኝ።
የዘንድሮው  የአድዋ ተጓዦች፣ ሁኔታዎች ሲመቻቹ ቀሪውን 400 ኪ.ሜ ለመጓዝና ሶሎዳ ተራራ ለመውጣት ያሰቡት ይኖር ይሆን?
ሁሉም በቀጣዩ ዓመት ሰላም ከሆነ ከቆሙበት ከአላማጣ ጀምረው ቀሪውን ለመጓዝ አቅደዋል የሚወሰነው ቀጣዩ  የሀገራችን ሁኔታ ነው። እንዳልኩሽ በፀጥታ ሀይሉ ከአላማጣ በኋላ መጓዝ አስቸጋሪ እንደሆነ ሲሰሙ የቆጫቸው ጉዞውን እንዳያጠናቅቁ ያደረገው ምክንያት ነው። እኛ አላማጣ ላይ ተጓዦቹን አቁመን እስከ ውቅሮ ስንጓጓዝ ከአላማጣ እስከ ውቅሮ ባለው 200 ኪ.ሜ ውስጥ በአካባቢው ጦርነቱ የጣለውን አስከፊ ጠባሳ አይተናል። ንብረት ወድሟል፣ ሰው ከቤት ከንብረቱ ተፈናቅሏል፣ ወጣቶች በአካባቢው አያታዩም፣ እንቅስቃሴው እንደ ድሮው አይደለም። በዚህ መሃል ሰው መሞቱ አይቀሬ ነው። ይህ በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ህዝቡ በስነ-ልቦና የሚያገግምበትና የሚታደስበት አዲስ የሰላም መንገድ መፈጠር አለበት። ይህ ካልሆነ የአድዋ ድልን ማክበር ቅንጦት ነው የሚሆነው ማለት ነው። በነገርሽ ላይ በቀጣዩም ዓመት እንጓዛለን ስንጓዝ 600 ላይ ነው የምንቆመው 700 ላይ ነው? አናውቅም ። እኛ ግን እንጓዛለን።
ጉዞውን አትቀጥሉም ሲባልና አድዋ መድረስ እንደማንችል ስናረጋግጥ አምባላጌ ብናከብር ብለን ጠይቀን ነበር። አምባጌ አንዱ ጦርነቱ የተካሄደበትና ቀረብ ያለ ስለሆነ። እዛም ማክበር እንደማንችል ከፀጥታ አካላት ሲነገረን ሀዘን ብቻ ሳይሆን ለቅሶም ነበር። ሁሉም ነው የተላቀሰው። ለቅሶው ለምን አድዋ አልገባንም አይደለም የቀረንበት ምክንያት ነው ደጋግሜ እንደነገርኩሽ በተለይ አንዲት ተጓዥ እምባ እያፈሰሰች “አድዋ አለመግባቴ አይደለም አድዋ ያልገባሁበት ምክንያት ነው የሚያስለቅሰኝ ለልጆቼ የማስተላልፋት አገር እንደዚህ መሆኗ ያስለቅሰኛል” ነው ያለችው እና የሚያሳዝን ነገር ነው። ዞሮ ዞሮ በቀጣይ ከአላማጣ ተነስተው ይጓዛሉ አገር ሰላም ከሆነ። በቀጣይ ዓመት አድዋን ማክበር ከፈለግን ከላይ የጠቀስኳቸው ብዙ የቤት ስራዎች በወቅቱ መሰራት አለባቸው እላለሁ አመሰግናለሁ።


Read 5324 times Last modified on Tuesday, 16 March 2021 19:09