Monday, 19 October 2020 00:00

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 2 መቶ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብል በአንበጣ ወድሟል

Written by  በጋዜጣው ሪፖርተሮች
Rate this item
(2 votes)

   • የአንበጣ መንጋ በኦሮሚያ ፣አማራና ትግራይ የከፋ ጉዳት አድርሷል
              • ተጎጂዎች የመንግስት ድጋፍ ጠይቀዋል
                     
       ከጥር 2012 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ወረራ 2መቶ ሺህ ሄክታር መሬት የሸፈነ ሰብል ሙሉ በሙሉ ማውደሙን የአለም የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ባወጣው መግለጫ አስታውቋል::
እንደ ዓለም እርሻ ድርጅት ሪፖርት፤ በዚህ የአንበጣ መንጋ ወረራ የኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ አፋርና ድሬደዋ አስተዳደር በእጅጉ ተጠቂ ሆነዋል።
“ባለፉት 25 ዓመታት  ተከስቶ የማያውቅ  የአንበጣ መንጋ ወረራ ነው ኢትዮጵያን የገጠማት’’ ያለው የፋኦ ሪፖርት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም  ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን ጠቁሟል::  
የአንበጣው  መንጋ በኦሮሚያ የከፋ ጉዳት ያደረሰባቸው አካባቢዎች ጉርሱምና አሬሮ መሆናቸውን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ ጉዳት የደረሰባቸው አርሶ አደሮችንም ከወዲሁ የመደገፍ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በኦሮሚያ ድጋፍ እየተደረገላቸው ያሉትም ከ86 በላይ አባራዎች ሲሆኑ በቀጣይ የተረጂዎች ቁጥር በእጅጉ ሊጨምር ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።  
በአማራ ክልልም የበርሃ አንበጣ የከፋ ጉዳት ያደረሰ  ሲሆን ከሰሞኑም በ4 ዞኖች በሚገኙ 125 ቀበሌዎች መከሰቱ ታውቋል። ራያ ቆቦና ሀርቡ ወረዳ፣ ጉባላፍቶ ወረዳዎች ከፍተኛ ጉዳት በማስተናገድ ተጠቃሽ ሆነዋል።
ከሰሞኑ በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የተከሠተውን የአንበጣ መንጋ ወረራ የፌደራልና  የክልል ባለስልጣናት እንዲሁም ጋዜጠኞች በስፍራው ተገኝተው ተመልክተዋል።
የአንበጣ መንጋው በሰሜን ወሎ በ3 ወረዳዎች፣ በ34 ቀበሌዎች የተከሰተ ሲሆን ጉዳቱን ለመከላከል በ305 ሺህ 705 ሄክታር መሬት ላይ አሰሳ ተደርጐ፣ በ241 ሺህ 685 ሄክታር መሬት ላይ አንበጣው መከሰቱም ተገልጿል፡፡ በደቡብ ወሎ ዞንም እንዲሁ በወረባቦ፣ በአርጐባና ተውለደሬ ወረዳ በ20 ቀበሌዎች ላይ የተከሰተ ሲሆን በ49ሺህ 054 ሄክታር መሬት ላይ ጉዳት ማድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በኦሮሞ ብሔረሰቦች አስተዳደር ዞንም እንዲሁ በ5 ወረዳና በ71 ቀበሌ የአንበጣ መንጋ የተከሰተ ሲሆን በሰሜን ሸዋ በዘጠኝ ወረዳዎችና በ26 ቀበሌዎች በ736 ሄክታር መሬት ላይ መከሰቱንና ጉዳት ማድረሱን የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ የአማራ ክልል የግብርና ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ሀላፊ ከትላንት በስቲያ፣ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በአጠቃላይ በምስራቅ አማራ የአንበጣ መንጋ በ20 ወረዳዎች፣ በ252 ቀበሌዎችና በ443 ሺህ 614 ሄክታር መሬት ላይ የተከሰተ ሲሆን 123ሺህ 056 ሄክታር መሬት በባህላዊ፣ 59ሺህ 927 ሄክታር መሬት በዘመናዊ መንገድ በድምሩ 182 ሺህ 983 ሄክታር መሬት መከላከል የተቻለ መሆኑን የገለፁት አመራሮቹ፤ እስካሁን የአንበጣ መንጋው ያደረሰው አጠቃላይ ጉዳት እየተጠና መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትርና የወሎ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ኤርጐጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አባተ ጌታሁን (ዶ/ር)፣ የዩኒቨርስቲው የምርምር ክፍል ምሁራን፣ ጋዜጠኞችና የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊዎች፤ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በባቲ ወረዳ የአርሶ አደሮችን በአንበጣ የወደመ የእርሻ ቦታ ተዘዋውረው በተመለከቱበት ወቅት የወረዳው የግብርና ቢሮ ኃላፊና አርሶ አደሮቹ ሁለት ዋና ዋና አደጋዎች እንደገጠሟቸው ተናግረዋል። አንደኛው ከመስከረም 5 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በባቲ ወረዳ ከሚገኙ 26 ቀበሌዎች የ20ውን ቀበሌ ሰብልና የእንስሳት መኖ ማውደሙንና በዚህም 19ሺህ 8 አባወራዎችና በስራቸው የሚገኙ 88ሺህ ቤተሰቦቻቸው ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸው ጠቁመው፤ መንግስት ሳይረዳቸው አንድ ሳምንት ቢቆይ ልጆቻቸውን ይዘው እንደሚፈናቀሉ አሳስቧል፡፡ በዚሁ ወረዳ የጫጫቱ ቀበሌ አርሶአደሮች እንደ ሁለተኛ ሥጋት የጠቀሱት ከአፋር ጋር የሚከሰተው ግጭትና የሚሞተው የሰው ብዛት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ሲሆን፤ መንግስት ለሁለቱም  ችግሮቻቸው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
የዘንድሮው የዝናብ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ በዝናብ አጠር አካባቢዎችም እንኳን ከፍተኛ ምርት ይጠበቅ እንደነበር የገለፁት የግብርና ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ።  በዚህ የመኸር ወቅት በክልሉ 127 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቅ ነበር ብለዋል፡፡ ሆኖም ይህ የምርት መጠን በአንበጣ መንጋው ምክንያት በእጅጉ እንደሚቀንስ ነው የተናገሩት፡፡ በክልሉ በሰብል ከተሸፈነው መሬት 4.5 በመቶው፣ በክልሉ ካሉት ወረዳዎች 28 በመቶው፣ ካሉት ቀበሌዎች ደግሞ 11 በመቶው በአንበጣ መንጋው ጉዳት የደረሰበት ሲሆን እስካሁን ችግሩ ከፌደራል መንግስት አቅም በላይ እንዳልሆነና በጣም የተጐዱትን በፍጥነት ድጋፍ ለማድረግ የልየታ ስራ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በምስራቅ አማራ  ከነሀሴ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በበርሀ አንበጣ ጉዳት  የተነሳ በአጠቃላይ ከ286 ሺህ በላይ ዜጎች ለተረጂነት መዳረጋቸውም ተመልክቷል።  የበረሀ አንበጣው በአፋር ክልል ፣በትግራይና በድሬደዋ አስተዳደር አካባቢዎች በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረስ መሆኑም ነው የተገለጸው።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ኢትዮጵያ የገጠማት የአንበጣ መንጋ ወረራ እጅግ የከፋ ነው ያለው የአለም እርሻ ድርጅት ፤ጉዳቱ ሚሊዮኖችን እርዳታ ጠባቂ የሚያደርግ ነው። መንግስት ከወዲሁ የአንበጣ መንጋ ጥፋቱን ከመከላከል ባሻገር ዜጎች  የሚረዱበትን አማራጮች እንዲያፈላልግም ፋኦ አሳስቧል።


Read 11120 times