Saturday, 21 September 2019 12:23

“ቆመን ጠበቅናቸው፤ ጥለውን አለፉ”

Written by 
Rate this item
(10 votes)


             “ከብረው ይቆዩኝ ከብረው
ባመት ወንድ ልጅ ወልደው!
አምሣ ጥገቶች አሥረው…!”
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አሳማ፤ በጐች በብዛት ወደተሰማሩበት የግጦሽ መስክ ጐራ ይላል::  እረኛው “ምን ሊያደርግ መጣ” በሚል ጥርጣሬ ያስተውለዋል፡፡ አሳማው ወደ በጐቹ ለመቀላቀል ይሞክራል፡፡ እረኛው ያደፍጥ ያደፍጥና ፈጥኖ ተጠግቶ አሳማውን ይይዘዋል፡፡ ከዚያም፤
“ለምን መጣህ?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡
አሳማውም፤
“ከበጐች ልመሳሰል” ሲል ይመልሳል፡፡
“ተመሳስለህስ?”
“እንደ በጐች ልኖር”
“ኖረህስ?”
“እንደ በጐች እንድታኖረኝ!?”
“አንተን እንኳን ለዚህ አልፈልግህም አያ አሳማ”
“እንግዲያ እንዴት እንድኖር ትፈልጋለህ?”
“አይ፤ ኑሮው ይቅርብህና ወደ ተገቢው ቦታ ብወስድህ ነው የሚሻለው፡፡” ብሎ፤ እየጐተተ ወደ እንስሳ ማረጃው ቦታ ይዞት ሊሄድ ይጐትተዋል፡፡
አሳማው፤ መወራጨት፣ መንፈራገጥ፣ ማጓራት መጮህ ይጀምራል፡፡
ይሄኔ ከበጐቹ መካከል አንዱ ብቅ ይልና፤
“አያ አሳማ?” አለ በለጋስ ጥያቄ ቅላፄ፡፡
“አቤት” አለ አያ አሳማ፡፡
“ምንድነው እንደዚህ  የሚያስጮህህ?  እኛ  ሁላችንም ’ኮ  በጌታችን  እየተጐተትን  ወደ  ሌላ  ቦታ  እንወሰዳለን፡፡”
“ነው፡፡ ግን የእኔ ይለያል” አለ አሳማ፡፡
“እንዴት?” አለ በጉ፡፡
“አይ አያ በግ፣ የሁለታችን ለየቅል ነው!”
“እኮ እንዴት?”
“ጌታህ አንተን የሚፈልግህ ከቆዳህ ሱፍ ለመሥራት ነው፡፡ እኔን የሚፈልገኝ ግን ለሥጋዬ ነው - ጠብሶ ሊበላኝ”
አያ አሳማ፤ እንደፈራው እየተጐተተ ሄደ፡፡
***
በአዲሱ ዓመት ከእንዲህ ያለ ምርጫ ይሰውረን፡፡ ለጥብስ ይሁን ለሱፍ፣ ዞሮ ዞሮ መታረድ ላይቀር ምርጫውን በቅናት መልክ ከማሰብ ይሰውረን፡፡ አራጁንም መሆን ታራጁንም መሆን በፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ አሰቃቂ ነው፡፡
“አውራ ዶሮ ጮኾ መንጋቱን ነገረኝ
ዛሬ ማታ ላርደው ቀጠሮ ነበረኝ”
እንዳለው አንዱ የእኛ ገጣሚ፤ የታራጅና አራጅ ምፀት የምንነጋገርበት እንዳይሆን አዲሱ ዓመት ልቡን ይስጠን፡፡ አዲሱን ዓመት የእኩልነት ያድርግልን!
“ይገብር ካላችሁ ዝንጀሮም ይገብር
የንጉሥ አይደለም ወይ የሚጭረው ምድር”  የምንልበት ዘመን ይሁንልን!
“ከብረው ይቆዩኝ ከብረው
ባመት ወንድ ልጅ ወልደው
አምሣ ጥገቶች ወልደው…”
ስንባል ሞቅ የሚለን፣ ከጭንቅ የሚገላግለን የአዎንታዊነት ምርቃት እንዲሆንልን እንጽና፣ እንጽናና፡፡
የአቦ - ሰጡኝ ሳይሆን የትግል ዓመት እንዲሆንልን ልብና ልቡናውን ይስጠን!
የችግር ማውሪያ ሳይሆን የመፍትሔ መፈለጊያ ዘመን እንዲሆንልን አንጐሉን ይስጠን!
የመለያያ ሳይሆን የመዋሃጃ፣ የመተሳሰቢያ ዘመን እንዲሆን በጐ አመለካከቱን አያጨልምብን!
ዕድሜ የጊዜ ሳይሆን፤ የመጠንከር  አቅም - የመገንባት፣ እርምጃችንን የማትባት ይሆንልን ዘንድ እርዳታው አይለየን፡፡
ሽቅብ እየተመነደግን እንጂ ቁልቁል እያደግን እንዳንሄድ፣ ድላችንን አስተማማኝ ያድርግልን፡፡
ፀሐፊዎቹ እንዳሉን፤
“አንድ ግዙፍ የብርቱካን ዛፍ እናስብ፡፡ በስሎ የተንዠረገገ ብዙ ብርቱካን አለው፡፡ ወደ ታች፣ በሰው ቁመት ያሉትን ብርቱካኖች በብዛት ለቀምኳቸው፡፡ ከዚያ በላይ ያሉትን ለመቅጠፍ ቁመት አጠረኝ፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ የብርቱካን እጥረት አለ ልል ነው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን አንድ አዋቂ ሰው አንድ ቴክኖሎጂ ፈጠረ፤ መሰላል የሚባል፡፡ ወደ ማይደረሱት ብርቱካኖች መድረሻዬን አበጀልኝ:: ችግሬ ተቃለለ፡፡ ቴክኖሎጂ ወደ ኃይል ምንጭ መዳረሻ/ ማግኛ ስርዓት ነው፡፡ ያኔ እጥረት ያልነው ነገር፣ አሁን በሽ - በሽ፤ ነው ያሰኘናል፡፡” (“አበንዳንስ”፤ በፒተር ዲያማንዲስ እና ስቲቨን ኮትለር)
ስለ ዕጥረትና ስለ ዕጦት የምናስብበት ዓመት እንዳይሆን መሰላሉን የሚሰጠን አዋቂ ይዘዝልን፡፡
በሁሉም ዘርፍ ለድል ያብቃን፡፡
የጀመርነው  ለውጥም ይቅናን፡፡ ኑሮም ይታደገን!
በጐ እንድንመኝ፣ በጐ እንድናገኝ፤ በጐ እጅ ይስጠን!
“አይቀጭጭ  ትልማችን፣ አይራብ ህልማችን!
አይሙት ሐሞታችን፣ አይቃዥ ርዕያችን!
አይንጠፍ ጓዳችን፣ አትምከን ላማችን!
አይክሳ ቀናችን፣ አይላም ጉልበታችን!!
ከሁሉም ከሁሉም አይጥፋ ሻማችን!”
ብለን የምንመኝበትን የህይወት ፀጋ አይንሳን!!
በአንድ ወቅት ታዋቂው የእስፖርት ሰው ይድነቃቸው ተሰማ፣ ሱዳን ከእግር ኳሱ አምባ ጠፍታ ከርማ ወደ ሜዳ ስትመለስ ያሳየችውን ድንቅ እርምጃ በተመለከተ የሰጡት አስተያየት፤ ማስገንዘቢያ፣ ማስጠንቀቂያና የእግር ኳሱን ሂደት ማሳያ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ደግሞ ዋና ማሳሰቢያ ነው!
“ቆመን ጠበቅናቸው ጥለውን አለፉ!” ነበር ያሉት፡፡ ከዚህ ይሰውረን!
እንደ አዲስ ዓመት ምላሽ “ከብረው ይቆዩን ከብረው” የምንባባልበት እንዲሆን እንመኛለን”
መልካም አዲስ ዓመት!!
(ከአዘጋጁ፡- ከላይ የቀረበው የዛሬ 6 ዓመት በአዲስ ዓመት መባቻ ላይ በአዲስ አድማስ ድረ-ገጽ የወጣ ሲሆን ለ”ትውስታ አድማስ” መርጠነዋል፡፡ ሴፕተምበር 13፣2013 )

Read 12994 times