Saturday, 17 August 2019 13:10

ግዙፉ ‹‹ሜላንዥ ኮፊ ሮስተር›› የቡና ማቀነባበሪያ ሥራ ጀመረ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ጥሬውን ወደ ውጭ በሚላከው ቡናችን ላይ እሴት በመጨመር ቆልቶ፣ ፈጭቶና አሽጐ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ‹‹ግዙፉ የሚያቀርበው ሜላንዥ ኮፊ ሮስተር›› ፋብሪካ ሰሞኑን ሥራ ጀመረ ፡፡
መገናኛ አካባቢ የተተከለው ፋብሪካ ከትናንት በስቲያ የተመረቀ ሲሆን ቱርክ ሠራሽ የ2019 ሞዴልና፣ የረቀቀ ዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የተገጠመለት እጅግ ዘመናዊ ፋብሪካ መሆኑን ባለቤቱ አቶ ሰለሞን ካሳ በምረቃው ወቅት ባረጉት ንግግር ገልፀዋል፡፡
በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ሆላንዳዊ በሆኑት በአቶ ሰለሞን ካሣ ኃይሌና በወ/ሮ ሙሉ ለገሠ ባለቤትነት የተገነባው ‹‹ሜላንዥ ኮፊ ሮስተር››፤ ከፍተኛ መዕዋለ ንዋይ የፈሰሰበት ግዙፍ ፋብሪካ መሆኑ ታውቋል፡፡ ፋብሪካው በሰዓት 720 ኪ.ግ፣ በቀን 7,500 ኪ.ግ፣ በሳምንት 52,500 ኪግ በወር 210ሺህ ኪ.ግ፣ ቡና ቆልቶ፣ ፈጭቶና አሽጐ ለገበያ እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡
የቡና ማቀነባበሪያ ማሽኖቹን ልዩ የሚያደርጋቸው፣ የቡና መቁያው ማሽን ሆት ኤር የተባለ አዲስ ቴክኖሎጂ የተገጠመለትና የአየር ብክለትን ለመቆጣጠር ‹‹አፍተር በርነር›› የተሰኘ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያለው ሲሆን በማቀነባበሩ ሂደት ወቅት ምንም ዓይነት የእጅ ንክኪ ሳይኖር ከአረንጓዴ ቡና እስከሚቆላ ድረስ በተገጠሙለት የማሽኖቹ የትራንስፖርት ማመላለሻ እየተጓዘ ጥራቱን በጠበቀ ‹‹ናይትሮጂን ጋዝ›› ታሽጐ ወደሚፈለጉት ቋቶች ውስጥ እንደሚገባ አቶ ሰለሞን አብራርተዋል፡፡
የፋብሪካው የማሸጊያ ማሽን በደቂቃ 100 የተቆላና የተፈጨ ቡናን በተለያየ መጠን የሚያሽግ ሲሆን፤ ቡናን አቀነባብሮ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሂደት ውስጥ ምንም ዓይነት የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር እንደሚተጋ ኢንቨስተሩ ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው እጅግ ዘመናዊ የቡና ማሽኖችን በመትከል በዓለም አቀፍ ደረጀ ጥራቱን የጠበቀ የአገራችንን ቡና ቆልቶ፣ ፈጭቶና አሽጐ ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ገበያ ያቀርባል ያሉት ባለቤቱ፣ ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ለ35 ያህል ዜጐች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልፀዋል፡፡  
ወደ ከተማ የሚመጡ ቱሪስቶች ቡናችንን የሚቀምሱበት ላቦራቶሪ ካፌ አለን ያሉት ባለቤቱ፤ አቶ ሰለሞን ካሳ፤ ቱሪስቶች በፈለጉት ዓይነትና መጠን ቡናችንን በውጭ ምንዛሪ ገዝተው የሚሄዱበት የገበያ ሥርዓት መዘርጋታቸውንም ተናግረዋል፡፡

Read 2474 times