Monday, 12 December 2016 12:42

ትራምፕ፤ የ“ታይም” መጽሄት የአመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰው ተባሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 “በመመረጤ ትልቅ ኩራት ይሰማኛል”

     ላለፉት 90 አመታት በዓለማችን በየአመቱ በበጎም ይሁን በመጥፎ ተጽዕኖ የፈጠሩ ግለሰቦችን እየመረጠ ይፋ ሲያደርግ የቆየው ታዋቂው “ታይም” መጽሄት፣ ዘንድሮ ተመራጩን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን “የአመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው” በሚል መርጧል፡፡
በመጽሄቱ አዘጋጆች አቅራቢነት ለ2016 የታይም መጽሄት “የአለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው” ምርጫ ለመጨረሻው ዙር ከደረሱት 11 የአለማችን ታዋቂ ግለሰቦች መካከል፣ አነጋጋሪው ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሰኞ አሸናፊ በመሆን የተመረጡ ሲሆን በመመረጣቸው ትልቅ ኩራት እንደተሰማቸው፣ ትራምፕ ለኤንቢሲ በሰጡት ቃለምልልስ ተናግረዋል፡፡
ታይም መጽሄት ትራምፕን የዘንድሮ የአለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው አድርጎ በመረጠበት እትሙ የፊት ገጽ ላይ እንደ ወትሮው የተመራጩን ትራምፕ ፎቶግራፍ ያወጣ ቢሆንም፣ ከስማቸው ግርጌ “PRESIDENT OF THE DIVIDED STATES OF AMERICA” የሚል ሸኝቋጭ ጽሁፍ ማስፈሩ ግን ብዙዎችን እያነጋገረ ነው ተብሏል፡፡ ለ2016 የአመቱ የታይም መጽሄት፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው ምርጫ በዕጩነት ከቀረቡት የአለማችን ታዋቂ ግለሰቦች መካከል፣ ተሸናፊዋ የዲሞክራት ዕጩ ሄላሪ ክሊንተን፣ ድምጻዊቷ ቢዮንሴ ኖውልስ፣ የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግና የቱርኩ ፕሬዚዳንት ጠይብ ኤርዶጋን ይጠቀሳሉ፡፡
ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ እ.ኤ.አ በ2008 እና በ2012 ለሁለት ጊዜያት የታይም መጽሄት የአመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰው ተብለው እንደነበር ያስታወሰው ሮይተርስ፤ ባለፈው አመት የታይም መጽሄት የአመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰው በሚል የተመረጡት የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ መርኬል እንደነበሩም አክሎ ገልጧል፡፡
ታይም መጽሄት ከዚህ ቀደም የአመቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰው በሚል ከመረጣቸው ፖለቲከኞችና ታዋቂ ግለሰቦች መካከል አዶልፍ ሂትለር፣ ማህታማ ጋንዲ፣ ግርማዊ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ፣ የሮማው ሊቀጳጳስ ፍራንሲስ፣ ንግስት ኤልዛቤጥ ሁለተኛ ይጠቀሳሉ፡፡

Read 3681 times