Sunday, 30 October 2016 00:00

የዓለማችን ዝነኛ ድምጻውያን ከሄላሪ ጎን ቆመዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 አዴል እና ጄይ ዚን ጨምሮ አለማቀፍ ዝናን ያተረፉ ድምጻውያን በዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዲሞክራትን ወክለው ለሚወዳደሩት ሄላሪ ክሊንተን ያላቸውን ድጋፍ እየገለጹ ሲሆን ለአድናቂዎቻቸውም ሄላሪን እንዲመርጡ የሚያበረታቱ የሙዚቃ ዝግጅቶችን እያቀረቡ ነው፡፡
እንግሊዛዊቷ ድምጻዊት አዴል ባለፈው ማክሰኞ በሚያሚ ባቀረበቺውና የዲሞክራቷ ዕጩ ሄላሪ በታደሙበት የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ መቶ በመቶ ድጋፏን የምትሰጠው ለሄላሪ መሆኑን በመግለጽ፣ ለአድናቂዎቿ ትራምፕን እንዳይመርጡ ጥሪ ማስተላለፏን ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡
አዴል ባለፈው የካቲት ወር ላይም ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳዎቹ  የእሷን ሙዚቃዎች ማጫወቱን እንዲያቆም መጠየቋን ያስታወሰው ዘገባው፣ ሮሊንግ ስቶንስ የተባለው የሙዚቃ ቡድን አባላትም ለትራምፕ ተመሳሳይ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜናም ታዋቂው አሜሪካዊ ራፐር ጄይ ዚ፣ ሄላሪ ክሊንተንን በመደገፍ ለአድናቂዎቹ በነጻ የሚታደሙበት የቅድመ ምርጫ የሙዚቃ ኮንሰርት በአሜሪካ ክሊቭላንድ እንደሚያቀርብ ተነግሯል፡፡
ጄይ ዚ ምርጫው ሊከናወን አራት ቀናት ሲቀሩት በሚያቀርበው በዚህ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ አድናቂዎቹን ለዲሞክራቷ ዕጩ ሄላሪ ክሊንተን ድምጻቸውን እንዲሰጡ የመቀስቀስ አላማ እንዳነገበ የተዘገበ ሲሆን፣ በኮንሰርቱ ላይ የትዳር አጋሩ ቢዮንሴ ኖውልስን ጨምሮ ሌሎች ሄላሪን የሚደግፉ ድምጻውያንም ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ታውቋል፡፡
የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኟ ኬቲ ፔሪ ለሄላሪ ያላትን ድጋፍ ለመግለጽ በምርጫው ሳምንት በፊላዴልፊያ የሙዚቃ ዝግጅቷን እንደምታቀርብ የተነገረ ሲሆን፣  የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኙ ቦን ጆቪም በተመሳሳይ ለሄላሪ ድጋፍ ለመስጠት የታለመ የሙዚቃ ኮንሰርቱን በዚያው ሳምንት በፒትስበርግ ለታዳሚዎቹ እንደሚያቀርብ ተዘግቧል፡፡

Read 1044 times