Sunday, 30 October 2016 00:00

ኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር አልተፈጠረችም

Written by  በኃይለመለኮት አግዘው e-mail:hailethegreat@yahoo.com
Rate this item
(1 Vote)

የልማት ዕቅዶች በጃንሆይ ዘመን

   እያንዳንዱ ስርዓት የራሱ የሆነ በጎ እንዲሁም መጥፎ ገፅታዎች ይኖሩታል፡፡ በዚህ ዘመን የተሰራውን መልካም ስራ ለማወደስ ያለፈውን ማውገዝ ተገቢ አይደለም፡፡ አንድን ነገር ነጭ ነው ለማለት አጠገቡ ጥቁር መቀባት ያለበት አይመስለኝም፡፡በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በተለያየ ጊዜ ጽሁፍ በማቅረብም በመቀጠርም አገልግያለሁ። አቶ ልደቱ አያሌው በበቀደሙ ስብሰባ እንደተናገሩት፤ ሚዲያዎች በከንቱ ውዳሴ ስርዓቱን ወደ  አልተፈለገ አቅጣጫ ህዝቡንም በታሪኩና በባህሉ ላይ ጥላቻ እንዲኖረው አድርገዋል፡፡ እያንዳንዱ ስርዓት አድርባይ ባንዳ ይቀላቀለዋል።  
ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ  “የቄሳር መንግሥት መልዕክተኛ” በሚባለው ጋዜጣ ላይ ባወጡት ፅሁፍ፡- “የኢጣሊያ ሠራዊት ከዚህ ሲደርስ ጥቂቶች በጣም ጥቂቶች ብቻ ወደ ዱር ተሰማሩ። … ስለ ምን፣ እንኳንስ እነሱ ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ሲያሰኝ የነበረው ንጉሥ አንበሳነቱ ቀርቶ ጥንቸል ሆኖ ፈርጥጦ መሄዱን ያውቃሉ።
እነዚህ የዱር ትሎች መሸፈታቸው የደሃውን የአማኙን በሬ እየሰነደቡ ለመብላት ብቻ ነው፤ ሌላ ትርጉም የለውም”። (መስከረም 13/1929 ዓ.ም) በማለት ፋሺዝምን አወድሰው አርበኞችን አንቋሸው ፅፈዋል፡፡ ነጋድረስ አፈወርቅ ይህን በሚፅፉበት ወቅት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመበታተን እየሰራች ነበር፡፡
የማኀበራዊና ምጣኔ ሐብታዊ ልማትን በዕቅድ የመምራት ጅማሮ
በድህረ ፋሽስት ኢትዮጵያ ከተወሰዱ ሀገርን መልሶ የማቋቋም ዓብይት ተግባሮች ውስጥ  የልማት ዕቅዶችን በተቀመጡ የጊዜ ቀመሮች በስራ ላይ ማዋል ነው፡፡ ይህ ዛሬ ጂ ቲ ፒ ብለን የምንጠራው የዕድገትና የለውጥ መርሐ ግብር ማለትም  በተቀመጠ የጊዜ ቀመር የማኅበራዊና ምጣኔ ሀብት ልማትን በእቅድ የመምራት ጅማሮ የተጸነሰው በድኅረ ፋሽስት ኢትዮጵያ፣ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ነው፡፡  
ከ1949 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ሲሰራባቸው የቆዩት የእነዚህ የልማት ዕቅዶች ዓላማ፣ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማቆም ባለው ውስን የተማረ የሰው ኃይልና የካፒታል አቅም የህዝቡን የኑሮ ደረጃ ወደ ተሻለ ዕድገት በማድረስ በኩል የራሱ የሆነ በጎ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ይህ ዘመን  የባህር ወደቦችና ዘመናዊ ድርጅቶች መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት እንዲሁም  የአውሮፕላን ማረፊያዎች የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድቦችን ለመገንባት ኢትዮጵያ ወገቧን ታጥቃ የተነሳችበት ወቅት ነው፡፡  
ከ1949 እስከ 1954 ዓ.ም በነበረው የመጀመሪያው አምስት አመት የልማት እቅድ ፕሮግራም፣ የትምህርትን ሽፋን  47 ከመቶ ለማዳረስ እቅድ የተቀመጠበት፣ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን ከማስፋፋት ጎን ለጎን ቀደም ሲል የታነፁትን  መልሶ ለመገንባትና  የግል ባለሀብቶች በኢንዱስትሪው መስክ የጎላ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ የዛሬ 60 ዓመት ተቀምሮ ነበር፡፡ እነዚህን የልማት ፕሮግራሞች በተመለከተ በዘርፉ ምርምር ያደረጉ ኢኮኖሚስቶች፣  ከምጣኔ ሀብታዊ ምልከታ አንፃር አንድ ቀን ፅሁፋቸውን ጀባ እንደሚሉን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ታሪክ የመዘገበውን የዘመኑን የልማት እቅድ ፕሮግራሞች የመጀመሪያዎቹን ሁለቱን የአምስት ዓመታት ክንውኖች ዋና ዋና ወጤቶች ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡   
የልማት ዕቅዶች
ከ1949 እስከ 1954
በስራ ላይ በዋለው የመጀመሪያው የዓምስት አመት ፕላን ወጪ የሆነው ጠቅላላ ገንዘብ 848 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ምንም እንኳን በእቅዱ የተቀመጡት ዓላማዎች ሙሉ ለሙሉ የታለመላቸውን እቅድ ፈፅመዋል ባይባልም፣ ከልማት እቅዱ ጉድለቶች ትምህርት የተወሰደበትና ከተገኙት መልካም ውጤቶች በመበረታት፣ ለሁለተኛው የአምስት ዓመት የልማት ዕቅድ መሰረት ተጥሎበታል፡፡ በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመት የልማት ዕቅዶች፡-  የኢትዮጵያ ሸለቆዎችንና ተፋሰሶችን ለማልማት የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት በሙሉ አቅሙ የተንቀሳቀሰበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ዘመን የአባይ ዋቤ ሸበሌና አዋሽ ወንዞችን የማልማት ዕቅዶች መሰረት ተጥሏል በተለይም የአዋሽ ሸለቆ ልማትን በተመለከተ በወቅቱ  የኢትዮጵያ መንግስት በነበረው ውስን  አቅም፣ የመስኖ ልማትን  በማስፋፋት የስኳር ፋብሪካዎችን፣ የአትክልትና ፍራፍሬ  እርሻዎችን እንዲሁም የጥጥ እርሻ ልማቶች ውጥን የታቀደበት ነበር፡፡
በተጨማሪም ይህ የመጀመሪያው አምስት ዓመት የልማት ዕቅድ፤ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን፣ የዘይት ማጣሪያ ፋብሪካዎች የመንገድ መሰረተ ልማት በወቅቱ አጠራር አውራ ጎዳናዎችና የቴሌፎን መስመሮችን በስፋት ለመገንባት የተወጠነበት ዘመን ነው፡፡  
ከ1954-1959
ሁለተኛው የአምስት አመት የልማት እቅድ ከመጀመሪያው አምስት አመት ትምህርት በመውሰድ የልማት ፕሮግራሙ ግብርናን ጨምሮ  የማእድንና ኢንዱስትሪ  ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ ተንቀሳቅሷል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት ጥቃቅንና አነስተኛ ብለን የምንጠራቸው  በወቅቱ አጠራር ተግባረ ዕድ ስራዎችን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡   
የሁለተኛው አምስት ዓመት የልማት ዕቅድ ዋነኛ ዓላማ የኢትዮጵያን ህዝብ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ እድገት 6 በመቶ ማሳደግ ነበር። እንደ መጀመሪያው አምስት አመት እቅድ፤ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን መክፈት፣ የመምህራን ማሰልጠኛዎችን ማስፋፋት… አገሪቱ የነበረባትን የተማረ የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ ብዙ ጎዳና ተጉዟል፡፡
በዚህ በሁለተኛው አምስት ዓመት የልማት ፕሮግራም፣ የግብርናው ዘርፍ የልማቱ ምሰሶ መሆኑ ታምኖበት፣ 463 ሚሊዮን ብር ተምድቦለታል። ኢትዮጵያን   በምግብ ሰብል እህል ምርት ራሷን ማስቻል የወቅቱ ኢትዮጵያውያን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች መሰረታዊ ፍልስፍናና እምነት ነበር። ይህ ወቅት ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኝ በሚችል ዘርፍ ታላላቅ እርሻዎችን የማስፋፋት እቅድ ውስጥ የገባችበትና ፍሬያማ የሆኑ ውጤቶችን ያስመዘገበችበት ነው፡፡ የመሬት ስሪቱን ለማሻሻል ጥረቶች የተደረጉበት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም።  
ኢንዱስትሪ
ኢንዱስትሪ በሁለተኛው አምስት አመት የልማት ፕሮግራም፣ 515 ሚለዮን የኢትዮጵያ ብር ተመድቦለታል፡፡ የኢንዱስትሪ ሽፋኑን 15 በመቶ ማድረስ የውጭ ምንዛሪ እንዲቆጥቡ ማድረግ፣ አንዱስትሪዎቹ ለግብርናው ግብዓት ለሚሆኑ ምርቶችን እንዲያመርቱ ማድረግ ዋነኛ የእቅዱ ምሰሶ ነበሩ፡፡
የማዕድን ዘርፍ ልማት
በሁለተኛው አምስት አመት የማዕድን ልማትን 25 በመቶ ለማሳደግ እቅድ ተወጥኗል፡፡ በማዕድን ልማት ዘርፍ የነበሩ ባለሙያዎች ውስን በመሆናቸው በዘርፉ ባለሙያዎችን ማሰልጠን፣ የአገሪቱን ጥቅም የሚያስጠብቁ የውል ስምምነቶችን ማፅደቅ ለዘርፉ 179 ሚሊዮን ብር ካፒታል ተመድቦለታል፡፡
መገናኛ ዘርፍ
ዘርፉ 10.3 በመቶ እንዲያድግ የመንገድ፣ የአየር መስመሮች፣ የባቡር ሐዲዶች፣ 624 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡
በእነዚህ አምስት ዓመታት ውስጥ የአውራ ጎዳና ባለስልጣን እንዲሰራቸው ከታቀዱት 5050 ኪሎ ሜትር መንገዶች፣ 1915 ኪ.ሜ በጠጠር የሚሰሩ የሁለተኛ ደረጃና መጋቢ መንገዶች፣ 2450 ኪ.ሜ ከገጠር የገበሬ መንደሮች ወደ አቅራቢያ የገበያ ስፍራዎች በበጋ ወራት የሚያገለግሉ ጥርጊያ መንገዶች፣ የመጀመሪያ ደረጃ መንገዶች፣ 695 ኪ.ሜ አይሮፕላን ማረፊያዎች መገንባት፣ አሰብና ምፅዋ ወደቦችን ማሻሻል፣ የባቡር ህዝብን የማመላለስ አቅም ማሻሻል የእቅዱ አካላት ነበሩ፡
ትምህርት
ለትምህርት ዘርፍ 600 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል፣ 12 በመቶ እንዲያድግ ዕቅድ ተይዞለታል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ማስፋፋት፣ ስርዓተ ትምህርቱን ማሻሻል፣ የትምህርት መሳሪዎች አቅርቦትን በስፋት ማዳረስ፣ የሳይንስና ቴክኒክ ትምህርት እንዲስፋፋ በማድረግ  616 ሺህ ተማሪዎች በመንግስት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት እንዲማሩ ታቅዷል፡፡ 186 ሺህ ተማሪዎች የመንግስት ባልሆኑ ትምህርት ቤቶች፣ ለ30000 ሺህ ጎልማሶች  ማንበብና መፃፍ ማስተማር፣ ለጎልማሶች 128 ሺህ ከስራ ጋር ተያያዥ ስልጠና ከ6000 በላይ አዳዲስ የትምህርት ክፍሎች እንዲሰሩ ማድረግ፣ ከ9000 በላይ አዳዲስ አስተማሪዎችን ማሰልጠን፣ 100000 በላይ ተማሪዎች በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ታቅዷል፡፡  በዚሁ የእቅድ ዘመን 5000 ተማሪዎች በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት ዘርፍ እንዲገቡ ታቅዷል፡፡
በጤና ጥበቃ ዘርፍ
የጤና ጥበቃ ዘርፍ  380 ሚለዮን ብር ተመድቦለታል፤ 11 በመቶ ያድጋል፡፡ 1000 ያህል አልጋ የሚይዙ ተጨማሪ ክፍሎችን ለመስራት ዕቅድ ተይዟል፡፡ 56 አዳዲስ ጤና ጣቢያዎች፣ 410 አዳዲስ ክሊኒኮች፣ ወባ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች 17 ዓቢይ ጣቢያዎች፣ 110 ንዑሳን ጣቢያዎች  ለመስራት ታቅዷል፡፡
እነዚህ ከላይ ከተጠቃቀሱት አገርን በተቀመጠ የጊዜ ቀመር የማሳደግ ብሄራዊ ተልእኮ ጎን ለጎን በተለያዩ ዘርፎች የዕድገት መሰረቶች ተጥለዋል፡፡ ለመትቀስም ያህል፡-
የባቡር መስመር
በ1933 ዓ.ም ፋሺዝም ድል ከተመታ በኋላ፣ የኢትዮጵያ የባቡር መስመር በእንግሊዝ አስተዳደር ስለተያዘ፣ ኢትዮጵያም በጦርነቱ ጊዜ እንግሊዝ ላደረገችው ዕርዳታ ያለምንም ዋጋ እንድትጠቀም ፈቅዳ ነበር፡፡
በጦርነት በደቀቀ ኢኮኖሚ ላይ የባቡር መስመሩን ለእንግሊዝ ማስረከቡ ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ስለታመነበት የኢትዮጵያ መንግስት ከአንግሊዝ ጋር ያደረገውን ስምምነት በመመርመር አቋሙን፣ በመቀየር የባቡር መስመሩ ለአምስት ዓመት ያህል በእንግሊዝ እጅ ከቆየ በኋላ በ1939 ዓ.ም ለኢትዮጵያ እንዲመለስ አድርጓል። በ1948 የምድር ባቡር  ኩባንያ 38 የእንፋሎት ባቡሮች፣ 18 የኤሌክትሪክ ዲዝል ባቡሮች፣ 61 ሰው የሚያጓጉዙ ፉርጎዎች(ጋሪዎች) 2 ንጉሠ ነገስቱና የመንግስት ባለስልጣኖች የሚሄዱባቸው ጎታቾች፣ 664 የዕቃ ፉርጉዎች 10 ኮኮ ትራክተሮችና 3 ሉተሪናዎች ተገዙ፡፡
ቴሌኮሙዩኒኬሽን
ከ1939 -1947 ዓ.ም በገንዘብና በሰራተኛ እጥረት ለዓይን የጎላ ዕድገት አሳይቷል ባይባልም ስራውን እጅግ በቀለጠፈ መንገድ ማስኬድ በሚቻልበት መንገድ ከ1942 ዓ.ም ጀምሮ ስራው በአዲስ መንፈስ ለመስራት በሚቻልበት መንገድ ተቀይሷል። ከዓለም ባንክ መገናኛ መንገዶችን ለመስራት ብድር እንዲሰጥ የሚያስችል ቡድን እንዲልክ ኢትዮጵያ በጠየቀችው መሰረት፣ ከዘርፉ በተገኘው እርዳታ ብዙ ተራምዳለች፡፡
በ1945 በቦርድ ራሱን እንዲያስተዳድር በአዋጅ ተቋቋመ፡፡ በበጀት ደረጃ 6 ሚለዮን 750 ሺህ ብር ለዘርፉ ተመደበ፡፡ ከዚህ ውስጥ 3 ሚለዮን ብር ከዓለም ባንክ የተገኘ ብድር ነው ለሁለተኛው የማስፋፋት ዕቅድ 15 ሚሊዮን ብር አስፈለገ ከዚህ ውስጥ 7 ሚሊዮን 250 ሺህ ብር ከዓለም ባንክ ቀሪው 7 ሚሊዮን 750 ሺህ ብር ቦርዱ ከገቢው ላይ የሚያወጣው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት መዝግበዋል።
ለኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኬሽን ለሶስተኛው የስራ ዕቅድ በድምሩ 27 ሚሊዮን ብር አስፈለገ ከዚህ ውስጥ 12 ሚሊዮን ብር በብድር ከዓለም ባንክ ሲገኝ፣ 11 ሚሊዮን ብር ከቴሌኮሚዩኒኬሽ ቦርድ ገቢ፣ ቀሪው 4 ሚሊዮን ብር ለማስታወቂያ ሚኒስቴር የራዲዮ ማሰራጫ አገልግሎት ማስፋፊያ የተገኘ ነበር፡፡ የደንበኞች ቁጥር በ1945 - 3640 በ1955 - 1200  በ1960 - 22736 ደንበኞች ነበሩት፡፡ እንዲህ እንዲህ አየተባለ ነው ዛሬ ላይ ለተደረሰው እድገት መሰረት የተጣለው፡፡












Read 1562 times