Sunday, 16 October 2016 00:00

ነገሩ፣ የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን! የእያንዳንዳችን የግል ጉዳይ ነው!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

- “በየግላችን ስልጡን አስተሳሰብ በማዳበር፣ ስልጡን ባህል እንፍጠር” ብለን አፍረጥርጠን የምንነጋገረው መቼ ይሆን?
- በነባር አስተሳሰብና በነባር ባህል ውስጥ ሆነን፣ እድሜ ልክ ተመሳሳይ የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ መዘፈቅና መተራመስ ብቻ!

በአገራችን ስናየው የከረምነው ቀውስ፤... ራቅ አድርገን የመንግስትን የሚመለከት የፖለቲካ ጉዳይ ልናስመስለው እንችላለን። ለምሳሌ ለአመታት እየተጓተቱ ብዙ ቢሊዮን ብር የባከነባቸው የመንግስት ፕሮጀክቶች ከአገሪቱ ቀውስ ጋር የተያያዙ ናቸው ብለን  ብንናገር ስህተት አይሆንም። ፕሬዚዳንት ተሾመ ሙላቱ ሰኞ እለት ለፓርላማ ባቀረቡት ንግግርም፤ የመንግስት ፕሮጀክቶች ብክነትን መጓተትን ለማስተካከል እርምጃ እንደሚወሰድ ገልፀዋል፡፡ ጥሩ ነው፡፡
ግን፣ ከአመታት በፊት መደረግ አልነበረበትም ወይ ብለን መጠየቅ እንችላለን፡፡ “ፕሮጀክቶቹ በታቀደላቸው ጊዜ እየተከናወኑ ናቸው” የሚል የቲቪ ዜና በማሰራጨት እውነታውን መካድ እንደማያዛልቅ፤ ከአራትና ከአምስት አመት በፊት በዚሁ ጋዜጣ በተደጋጋሚ ተዘግቧልኮ፡፡ “ፕሮጀክቶቹ፤ በታቀደላቸው አቅጣጫ እየተከናወኑ ነው” ብሎ ማድበስበስ እንደማያዋጣም፣ ገና ድሮ መታወቅ ነበረበት።
ቢሆንም፤ ከአመታት በኋላ፣ እውነታውን መካድና ማድበስበስ እንደማያዋጣ በመገንዘብ፣... ፕሮጀክቶቹ የመጓተትና የብክነት አዙሪት ውስጥ መግባታቸውን መንግስት ማመኑ... አንድ ቁምነገር ነው።
እንዲህ... ስናወራው፣ የሩቅ ጉዳይ እንጂ፤ በቀጥታ የሚመለከተን የቅርብ ጉዳያችን አይመስልም።
እዚያው በሩቁ እንጨርሰው ካልን፤ “ለመሆኑ፣ ለፕሮጀክቶቹ ምን አይነት መፍትሄ ተበጀላቸው?” በሚል ጥያቄ መቀጠል እንችላለን።
አዎ፤ መንግስት፣ ችግሩን አምኖ መፍትሄ እንደሚያበጅላቸው ቢገልፅም፣ መፍትሄው ምን እንደሆነ አልተናገረም።
በተቻለ መጠን መንግስት ቢዝነስ ውስጥ እንዳይገባ ማድረግ፣ የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች ቀስ በቀስ ወደ ግል ኢንቨስትመንት ለማዛወር መሞከር፣ እስከዚያው ግን፤ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ፣ በጨረታ በግል ኩባንያዎች እንዲከናወን ማድረግ አንድ መፍትሄ ነው። በጨረታ በተለያዩ ኩባንያዎች የተገነቡ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችን ማየት ይቻላል - በአብዛኛው አልተጓተቱም፤ ብዙ ቢሊዮን ብሮች በከንቱ አልባከነባቸውም። መንግስት የሚገነባቸው የመስኖ ግድቦች፣ ከአስር አመታት በላይ ያለ ውጤት መጓተታቸውን ደግሞ መመልከት ይቻላል - ብዙ ቢሊዮን ብሮችን በከንቱ አባክነዋል።
ስለዚህ፣ የፕሮጀክት ግንባታዎችን በጨረታ ለኩባንያዎች መስጠት፣ ጥሩ ጊዜያዊ መፍትሄ ነው።
ለዘለቄታው ግን፣ የመንግስት ፕሮጀክቶች፣ መቼም ቢሆን፣ አነሰም በዛ፣ ከብክነትና ከመጓተት እንደማያመልጡ፣ ከታሪክ በመማር፣ እድገት የሚመጣው በግል ኢንቨስትመንት መሆኑን በመገንዘብ፣ ሁነኛ የመፍትሄ ለውጥ መፍጠር ያስፈልጋል። ይሄ ግን፣ በአንድ የአዋጅ ለውጥ ብቻ እውን ሊሆን አይችልም። ከእለት እለት፣ ከአመት አመት፣ በፅናት የሚቀጥል የረዥም ጊዜ ጥረትን ይጠይቃል - የሀሳብና የተግባር ብቻ ሳይሆን፣ ጠቅላላ የአስተሳሰብና የባህል ለውጥን የሚጠይቅ ነውና። እንዴት?
የጥረት ስኬትን የሚያደንቅና የግል ንብረትን የሚያከብር ስልጡን አስተሳሰብና ስልጡን ባህል ለመፍጠር መጣጣር ያስፈልጋላ።
አዎ፤ ይሄ ጥረትንና አለማዊ ስኬትን፤ ብልፅግናንና የግል ንብረትን የሚያስከብር ስልጡን አስተሳሰብ፣ በዛሬው ዘመን በአለም ዙሪያ ቸል እየተባለ ወይም እየተብጠለጠለ ሲደበዝዝ እናይ ይሆናል። ግን፤ ይህንን የዘመኑን የጥፋት አቅጣጫ በመከተል፣ የምናገኘው ትርፍ የለም - ከድህነትና ከትርምስ በቀር። የአለም መንግስታት ምንም ይበሉ ምን፤ ከብዙ አገራት የብዙ ዘመናት ታሪክ፣ ከራሳችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ እንዲሁም አሁን በገሃድ ከምናየው እውነታ መገንዘብ እንችላለን ስልጡን አስተሳሰብንና ስልጡን ባህል ቸል ከተባለ፤ ከጥፋት ውጪ ምንም ውጤት አይገኝም።
እናም፣ ከጊዜያዊ መፍትሄዎች ባሻገር፣ ለወደፊትም ስልጡን አስተሳሰብና፣  ስልጡን ባህል ለመፍጠር፣ … በዚህ ደልዳላ መሰረት ላይም፤ ለግል ንብረት ዋስትና የሚያረጋግጥ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን ለማስፋፋት በፅናት መጣጣር ያስፈልጋል የማያወላውል የካፒታሊዝም ስርዓትን ለማስፈን፡፡
በእርግጥ፣ ይሄ ዘላቂ መፍትሄ፣ በአንድ ውሳኔና በአንድ ወር ይቅርና በደርዘን ውሳኔዎችና አመታትም ሙሉ ለሙሉ እውን ይሆናል ማለት አይደለም። ግን ሌላ አማራጭ የለም፡፡ መጀመር አለበት፡፡ ይህንን ጉዞ … መንግስት፣ ቀሽም ስህተቶቹን በማረም መጀመር ይችላል... ባለሃብትን “ኪራይ ሰብሳቢ” እያለ ከማንቋሸሽ፣ በብር ህትመት ሳቢያ የዋጋ ንረት በተፈጠረ ቁጥር በባለሃብትና በነጋዴዎች ላይ ከማሳበብ መቆጠብ፣ “የነጋዴዎች ፍላጎት፣ ትርፍን ማግኘት ብቻ ነው” እያለ እንደ ወንጀልና እንደ ሃጥያት ከመኮነን መታቀብ አለበት። የግል ጥረትን፣ የግል ብቃትንና የግል ስኬትን ማድነቅ …. ማክበር ካልጀመረ፣ የሚያዛልቅ መፍትሄ ማግኘት አይችልም። እያየነው ነውኮ።
መንግስት የግል ጥረትንና ስኬትን ሳያከብር፣ ሌሎች ሰዎች በተለይም ወጣቶች … ህይወታቸውን በጥረት እንዲያሻሽሉና ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ቢጠብቅ፣ ከንቱ ጥበቃ ነው። መንግስት የግል ንብረትን ከመንካት ሳይቆጠብ፣ ሌሎች ሰዎች በተለይም ወጣቶች፣ የሰውን ንብረት እንዲያከብሩ ቢጠብቅ፣ ሞኝነት ነው። ይሄውና ስንት ህይወትና ንብረት ጠፋ! መንግስት፣ ከእስካሁኑ ጥፋቶች ተምሮ፣ ቀሽም ስህተቶችን በማረም ከጀመረ፣ ሌሎቻችንስ?
ያው፣ ምሁራንና ዜጎችም፣ ለሰው ህይወትና ለግል ንብረት ዋጋ ሳንሰጥ፣ መንግስት ህይወታችንና ንብረታችንን እንዲያከብርልን ብንጠብቅ ሞኝነት ነው፤ አልያም ግብዝነት፤ አልያም ቅጥፈት።
በፅሁፌ መግቢያ ላይ እንደገለፅኩት፤ … ይሄውና ጉዳዩ በጣም ቅርብ የግል ጉዳያችን እንደሆነ ማሳየት እየጀመርኩ ነው፡፡ ለብዙ ሰዎች፣ ፖለቲካ ማለት፣ በቃ … ሁሉንም ነገር በመንግስት ላይ የማላከክ ጨዋታ ይመስላቸዋል፡፡ አገሪቱ ፖለቲካ፣ ከዘመን ዘመን፣ ብዙም ነገር ሳይሻሻል የሚቀጥለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ እንዴት በሉ፡፡
የእውነት... የምር... በሃሰት ያልቆሸሸ አእምሮንና ሃሳብን የምንፈልግ ከሆነ፣ ስልጡን አኗኗርን... ስኬትንና የጥረት ብልፅግናን የምንፈልግ ከሆነ... ክቡር ሰብእናን፣ በራስ የመተማመን እርካታን የምንፈልግ ከሆነ... አዎ፣ እነዚህን የምንፈልግ ከሆነ፣ … “ከመንግስት ፕሮፓጋንዳና አፈና መላቀቅ፣ ከመንግስት በደልና ዝርፊያ መዳን፣ ከመንግስት የዘፈቀደ ፍረጃ መገላገል” … በሚል ዲስኩር ነገሩን ሁሉ መንግስት ላይ ከምረን፣ ከኃላፊነት የምንሸሽት ጉዳይ ሊሆን አይችልም።
ከመንግስት ውጭ፣ ሌላ ሰው... ሌላ ቡድን... ሌላ ፓርቲ... በአሉባልታ ላይ እየተማመነ በዝምታ እንድንቀበል ለማስፈራራት ሲሞክር፣ የጥረት ስኬትን ሲያንቋሽሽና የግል ንብረት ላይ ዘመቻ ሲያውጅ፣ ሰዎችን በጅምላ እየፈረጀ በዘር ወይም በሃይማኖት ተከታይነት ለማቧደን ሲሞክርም... ‘አልቀበልም’ ማለት ያስፈልጋል። ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ፣ በየግላችን፣ በአሉባልታ ፕሮፓጋንዳ ላይ ከመተማመን በመቆጠብ፣ ሌሎችን በዛቻ ለማፈን ከመሞከር በመራቅ፣ እያንዳንዱን ሰው በዘር በተወላጅነት ሳይሆን፤ በግል ብቃቱ፣ በተግባሩና በባህርይው የምንመዝንበት የእውነትን ጉዞ መጀመር እንችላለን - በስልጣኔ ጎዳና። የሰዎችን የጥረት ስኬት ከማንቋሸሽና የግል ንብረት ላይ ጥላቻ ከመቀስቀስ በመቆጠብ... የስልጡን አኗኗር አቅጣጫን መያዝ እንችላለን።
በጣም ሩቅ ሃሳቦች ሊመስሉ ይችላል። ግን ሌላ ምን የተሻለ አማርጭ አለ? በዚያ ላይ ደግሞ፤ ብዙ ኑሯችን የተመሰረተው በዚህ ቀና አስተሳሰብ ላይ ነው። ሀሰትንና እውነትን፣ የሀብት ፈጠራንና የሀብት ዝርፊያን ወይም ውድመትን፣ ታታሪነትንና ማምታታትን ለይተን ማወቅ ያቅተናል እንዴ? ብቃት ያለውና ብቃት የሌለውን ሰው መለየትም እንችላለን። መጥፎ ተግባር የፈፀመና ድንቅ ተግባር የፈፀመ ሰውን ለይተን የማወቅ አቅምም አናጣም፡፡ ክፉ እና መልካም የሰው ባህርይን መለየት እንችላለን። ነገርዬው፣ የዘር ወይም የሃይማኖት ተከታይነት ጉዳይ እንዳልሆነኮ ግልፅ ነው፡፡ ሩቅ ሳንሄድ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እንኳ፣ የብቃትና የባህርይ ልዩነት እንዳለ እናውቃለን - አንዱ ታታሪ፣ አንዱ ሌባ... አንዱ ቀና፣ አንዱ አስመሳይ፣ አንዱ መልካም አንዱ ክፉ።
በየጊዜው የምናስተውለው ይህንን የዘወትር እውነታ፣ ይህንን ግልፅ እውቀት... አንቅበረው። አንካደው። ሁሌም፣ መተማመኛችን እንዲሆን በክብር እንያዘው፣ እንጠብቀው፣ እናጠንክረው። ያኔ፣ የማንኛውም መንግስት ወይም የሌሎች ፖለቲከኞች መጫወቻ ላለመሆን በሙሉ ልብ መከላከል እንችላለን። ቀስ በቀስም እንደማያዋጣቸው ይገነዘባሉ። መጫወቻ የሚያደርጉን፣ መጫወቻ ለመሆን ስለምንመቻቸው ነው።
ለእውነት ክብር ከሌለን፤ በሰበብ በአስባቡ እውነትን የምንክድ ከሆነ፤... በፕሮፓጋንዳና በአሉባልታ፣ በአፈናና በስድብ እንዲያጣድፉን የልብ ልብ እንሰጣቸዋለን - እውነትን እያዋረድን፣ እውነትን አክብሩ ብለን ለመከራከር፣ ውስጣዊ ሃይል አይኖረንማ።
ለጥረትና ለስኬት፤ ለግል ንብረትና ለብልፅግና ክብር ከሌለን፣ እንዳሻቸው በኑሯችንና በንብረታችን ላይ እንዲዘምቱ ፈቃድ ሰጠናቸው ማለት ነው።
ግን ስህተታችንን የማረም እድል የለንም ማለት አይደለም። ለእውነት፣ ለጥረት፣ ለስኬት፣ ለግል ብቃትና ለግል ማንነት ትልቁን ክብር በመስጠት፣ የስልጡን ጎዳና ጉዞን መጀመር እንችላለን።
ያኔ፣ ማንኛውም መንግስትም ሆነ ሌሎች አጥፊዎች፣ እንዳሻቸው የመፈንጨት ጉልበታቸው ይቀንሳል። ለነገሩ ባይቀንስ እንኳ፣ እነሱ ይዋሻሉ ብለን፣ የላቀ ውሸታም በመሆን ልናሸንፋቸው ከሞከርን... ከጅምሩ ተሸነፍን ማለት ነው። ደግሞስ፣ ፕሮፓጋንዳና አሉባልታ መጥፎ ከሆነ፤ የላቀ ፕሮፓጋንዳና የላቀ አሉባልታ፣... በአንዳች ተአምር፣ “ጥሩ” ሊሆን አይችልም። በሰው ኑሮና ንብረት ላይ መቀለድ ወይም መዝረፍ፣.. ‘መጥፎ’ ከሆነ፤ ከዚህ የላቀ አዲስ የዝርፊያ ወይም የጥፋት ሪከርድ ማስመዝገብ፣... በአንዳች ተአምር፣... ‘ጥሩ’ ሊሆን አይችልም።
ይችላል እንዴ?
የዚያኛው ጎራ ፕሮፓጋንዳ፣ ‘ለመጥፎ አላማ’ ነው። የዚህኛው ጎራ አሉባልታ ግን፣ ‘ለበጎ አላማ’ ነው... ብለው ራሳቸውን የሚያታልሉ ሰዎች ጥቂት አይደሉም።
“ለበጎ አላማ እስከሆነ ድረስ”... እውነትን መካድና መዋሸት፣ አገሬውን በፕሮፓጋንዳ ማጥለቅለቅ፣ መንግስት በሰዎች ኑሮ ላይ አድራጊ ፈጣሪ እንዲሆን መፍቀድ፣ ተቃዋሚ ነኝ በሚል ሰበብ የሰውን ንብረት መዝረፍና ማጥፋት፣ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካን ማስፋፋት፣ ይህንን እቃወማለሁ በሚል ሰበብ ሰዎችን በጅምላ እየፈረጁ በዘር ወይም በሃይማኖት ማቧደን... እነዚህ የሃሰት፣ የጥፋትና የክፋት መንገዶች በሙሉ... “ለበጎ አላማ እስከሆነ ድረስ”...  ይፈቀዳሉ? ለዛሬ ብቻ! ለነገ ብቻ! ለዚህኛውና ለዚያኛው ጉዳይ ብቻ! እገሌን ለመደገፍና እንቶኔን ለማጥቃት ብቻ! ከዚያ በኋላ፣ ወደ እውነት፣ ወደ ቀናው መንገድ፣ ወደ መልካም ጎዳና እንመለሳለን? … እንዲህ ዓይነት ጨዋታ እንደማያዋጣ እንደገና ዘንድሮም አየነው፡፡
ሰዎች! ራሳችንን አናታልል። በመሰረታዊ ሃሳቦች ላይ፣ ‘ለዛሬ ብቻ’፣ ‘ለዚህኛው ጉዳይ ብቻ’፣ ‘ለእገሌ ብቻ’ የሚባል ነገር የለም። የተሳሳቱ፣ አጥፊና ክፉ ሃሳቦች፣ ‘በአላርም’ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚያገለግሉ፣ ወይም በአድራሻ የሚላኩ ወይም በፋይል የሚከደኑ ቁንፅል ቁሶች አይደሉም።... እውነትን፣ የግል ንብረትን፣ የግል ማንነትን በማንቋሸሽ... አገርን ለመምራት የሚያስብ ባለስልጣን ወይም ሰዎችን ለመቀስቀስ የሚሞክር ተቃዋሚ... የሃሰት፣ የጥፋትና የክፋት ማዕበል እንዳይፈጠር መግታት አይችልም።
ሃሳቦች፣ ሃያል ናቸው... በድንበር፣ በጊዜና በዘበኛ ታጥረው አይቀመጡም። ለዛሬ፣ ለእንትን፣ ለእገሌ... ተብሎ የሚገደብ መሰረታዊ ሃሳብ የለም። መንግስትም ሆነ ተቃዋሚ፤... በአንዳች ማመካኛ፣ ሰዎችን በዘር ለማቧደን ወይም የዘረኝነት ስሜትን ለመቀስቀስ ከሞከረ፣ ነገርዬዋ እዚያው ተገድባ አትቀርም። እዚህም እዚያም፣ በዚህና በዚያ በኩል፣ ለመሰንበቻውና ለከርሞ፣ ስፍር ቁጥር የሌለው መዘዝ ታስከትላለች። ለዚህም ነው፤ የመንግስት ባለስልጣናትም ሆኑ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ በየጊዜው የሚጀምሩት ነገር ከቁጥጥር ውጭ ሲሆንባቸው የምንመለከተው።
እሺ። ግን፣ የሃሰት፣ የጥፋትና የክፋት ጎዳና የተጀመረው፣... ለበጎ አላማ ከሆነስ? አዎ፣ እንዲህ አይነት ማመካኛ እየደረደሩ ራሳቸውን የሚያታልሉ ሰዎች ብዙ ናቸው። ደግሞም አስቡት።
በይፋ፣ “ለክፉ አላማ” በማሰብ፣ ኑሯችሁን አጠፋለሁ፣ ንብረታችሁን እዘርፋለሁ” የሚል ፖለቲከኛም ሆነ መንግስት፣ ገዢም ሆነ ተቃዋሚ የትም አይኖርም። ሁሉም አምባገነኖችና ነውጠኞች፣ ጥፋትና ዝርፊያ የሚፈፅሙት፣ “ለበጎ አላማ” በሚል ማመካኛ ነው።
“ለበጎ አላማ ራሳችሁን መስዋዕት አድርጉ” በማለት ይሰብካሉ። መስዋዕትነትን በእሺታ ተቀብለን እናጨበጭባለን። ከዚያስ? ከዚያማ … ‘ለበጎ አላማ’፤ ኑሯችሁን እንደ በግ ለእርድ፣ እንደ ቁራጭ እንጨት ለማገዶ ይወረውሩታል። ይሄ የመስዋዕትነት አምልኮ፣ በጭራሽ... ፈፅሞ... ‘በጎ አላማ’ ሊሆን አይችልም። ከበጎ አላማ ጋርም ጤናማ ግንኙነት ሊኖረው አይችልም። ‘በጎ አላማ’ን የሚያጠፋ ክፉ በሽታ ነው - የመስዋዕትነት አምልኮ።
ይልቅስ፣ ከመስዋዕት አምልኮ በተቃራኒ፤... የሰውን ኑሮ፣ የጥረት ስኬትንና የግል ንብረትን ማክበር ነው - ‘በጎ አላማ’። ይሄ፣ ያን ያህልም ውስብስብ ሃሳብ አይደለም። ነገር ግን፣ ምንም ሳይሸራረፍና ሳይበረዝ፣ በፅናት ለመተግበር ብዙም ሙከራ አይታይም። ለምን? ለዘመናት ስር በሰደደ ‘የመስዋዕት አምልኮ’ ሳቢያ!!  በሌላ አነጋገር፣ ጉዳዩ መንግስትን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ አይደለም፡፡ ለእያንዳንዳችን … የግል ጉዳያችን ነው፡፡ ለእውነትና ለግል አዕምሯችን፣ … ለጥረትና ለግል ንብረት፣ … ለግል ብቃትና ለግል ማንነት … ክብር የሚሰጥ ስልጡን አስተሳሰብ በየግላችን ለማዳበር እንጣር፡፡ በዚህም ስልጡን ባህል እንፈጥራለን፡፡

Read 1750 times